By using this site, you agree to the Privacy Policy and Terms of Use.
Accept
ሀትሪክ ስፖርት ኢትዮጵያሀትሪክ ስፖርት ኢትዮጵያ
  • መነሻ ገፅ
  • ዜናዎች
  • ፕሪሚየር ሊግ
    • ባህርዳር ከተማ
    • ወላይታ ዲቻ
    • ድሬዳዋ ከተማ
    • ፋሲል ከነማ
    • ሲዳማ ቡና
    • አዳማ ከተማ
    • ሀዋሳ ከተማ
    • ቅዱስ ጊዮርጊስ
    • ኢትዮጵያ ቡና
    • ጅማ አባጅፋር
    • ወልቂጤ ከተማ
    • ሰበታ ከተማ
    • ሀዲያ ሆሳዕና
  • ዋልያዎቹ
  • ውድድሮች
  • English Article
  • French Articles
  • ስለ እኛ
Reading: “የታሪክና የውጤት ሀብታም የሆነውን ቅ/ጊዮርጊስን ማሰልጠን ትልቅ ዕድል ነው”አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን (የቅ/ጊዮርጊስ ዋና አሰልጣኝ)
Share
Notification Show More
Latest News
በጨምበላላ ዋዜማ የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ጣፋጭ ድል ቀምሷል
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዜናዎች የጨዋታ ዘገባ
ዩጋንዳዊው የሲዳማ ቡና ግብ ጠባቂ በዛሬው ጨዋታ አይሰለፍም
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዜናዎች ሲዳማ ቡና
የቅዱስ ጊዮርጊስ የቦርድ አመራሮች ከሀላፊነት ለመነሳት ፍቃደኛ ሆኑ
ዜናዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ
የሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂ ታገደ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዜናዎች ሲዳማ ቡና
መቐለ 70 እንደርታ ናይጄሪያዊ አጥቂ አስፈረመ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዝውውር ዜናዎች ዜናዎች መቐለ 70 እንደርታ
Aa
ሀትሪክ ስፖርት ኢትዮጵያሀትሪክ ስፖርት ኢትዮጵያ
Aa
  • መነሻ ገፅ
  • ዜናዎች
  • ፕሪሚየር ሊግ
  • ዋልያዎቹ
  • ውድድሮች
  • English Article
  • French Articles
  • ስለ እኛ
  • መነሻ ገፅ
  • ዜናዎች
  • ፕሪሚየር ሊግ
    • ባህርዳር ከተማ
    • ወላይታ ዲቻ
    • ድሬዳዋ ከተማ
    • ፋሲል ከነማ
    • ሲዳማ ቡና
    • አዳማ ከተማ
    • ሀዋሳ ከተማ
    • ቅዱስ ጊዮርጊስ
    • ኢትዮጵያ ቡና
    • ጅማ አባጅፋር
    • ወልቂጤ ከተማ
    • ሰበታ ከተማ
    • ሀዲያ ሆሳዕና
  • ዋልያዎቹ
  • ውድድሮች
  • English Article
  • French Articles
  • ስለ እኛ
Have an existing account? Sign In
Follow US
  • Advertise
© 2023 Hatrick Spoert. Design by Tech-ethiopia.com All Rights Reserved.
Uncategorizedሀትሪክ ስፖርትጋዜጣቅዱስ ጊዮርጊስብቸኛዋ ባለቀለም የስፖርት ጋዜጣThe BiG Interview

“የታሪክና የውጤት ሀብታም የሆነውን ቅ/ጊዮርጊስን ማሰልጠን ትልቅ ዕድል ነው”አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን (የቅ/ጊዮርጊስ ዋና አሰልጣኝ)

Teshome Fantahun
Teshome Fantahun 7 years ago
Share
SHARE

በተሾመ ፋንታሁን (የሀትሪክ ጋዜጣ ተባባሪ አዘጋጅ)


“ኢትዮጵያ አፍሪካም አረብም አይደለችም፤ የራሷ ቀለም የራሷ ለዛ ያላት ምርጥ ሃገር ናት”

“እግር ኳስ ኤሌክትሪክ አይደለም በማብሪያና ማጥፊያ መቆጣጠር አይቻልም”


- ማሰታውቂያ -


ሀትሪክ ፦ ለጋዜጣችንና ለአንባቢዎቻችን ክብር ሰጥተው የዚህ ሳምንት እንግዳችን ስለሆኑ በአንባቢዎቻችን ስም ከልብ እናመሰግናለን፡፡

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ ለኔም ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያ ቃለ-ምልልሴ ነው፤ እስካሁን የድህረ-ጨዋታ(Post Match Interview) ቃለ-ምልልስ ብቻ ነበር ያደረኩትና ለመጀመሪያ ጊዜ በሀትሪክ የስፖርት ጋዜጣ ቃለ-ምልልስ በማድረግ ከደጋፊዎቻችንና ከስፖርት ቤተሰቡ ጋር የምገናኝበትን መድረክ ስለፈጠራችሁልኝ በጣም አመሰግናለሁ፡፡

ሀትሪክ ፦ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራትን እንዴት አገኙት?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ ከመጣሁ ገና አንድ ወሬ ነው፤ ባህሉንና ህዝቡን ለመልመድ እየሞከርኩ ነው፡፡ በራሴ መንገድ ህዝቡን ለመረዳት እየጣርኩ ነው፤ እኔ ብዙ አፍሪካ ሀገራት ውስጥ ሰርቻለሁ፤ ባለኝ ልምድ የተረዳሁት ነገር እያንዳንዱ ሀገር የራሱ የሆነ የተለየ ባህልና አኗኗር አለው፤ ስለዚህም ለመማርና ለማወቅ ጊዜ ያስፈልግሃል፤ከአንድ ወር በኋላ እኔም ቀስ በቀስ ለመለማመድ እየሞከርኩ ነው፡፡ እውነት ለመናገር የኢትዮጵያ ህዝብ እኔ ከሰራሁባቸው የአፍሪካ ህዝብ ትንሽ ኮስተር ያለ (Serious) ህዝብ ነው፤ የተሻለ ፕሮፌሽናል ህዝብ ነው፡፡ እዚ ያለው ፕሮፌሽናሊዝም ከሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት የተሻለ ነው፡፡ በደምብ ሳስተውለው ኢትዮጵያ በአፍሪካና በአረቢያ መካከል ያለች ሀገር ትመስለኛለች (Ethiopia is where Africa meets Arabia):: በባህል፣ በአስተሳሰብ፣ በአመለካከት ሁሉ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትንሽ ለየት ያለ ህዝብ ያለባት ሀገር ናት፡፡ የሰውን እምነት ለማግኘት ትንሽ ከሌላው ሕዝብ የረዘመ ጊዜ ሳያስፈልገኝ አይቀርም፡፡

ሀትሪክ ፦ከዚህ በፊት እንግሊዛዊ አሰልጣኝ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጥኖ ያውቃል፤ በክለብ ግን እርስዎ መሰሉኝ የመጀመሪያ…?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ አዎ…! ኤፌ ኦኑራን በደንብ አውቀዋለው፤ በጣም ወዳጄ ነው፡፡ ኦኑራ እዚ የናንተን ብሔራዊ ቡድን ሲያሰለጥን እኔ ደግሞ የዛንዚባርን ቡድን ይዤ በሴካፋ እወዳደር ነበር፡፡

ሀትሪክ ፦የሀገሪቱን እግር ኳስ ደረጃ እንዴት አገኙት?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ በጣም ጥሩ ነው፤የእግር ኳስን አራቱን መልኮች (The four aspects) ከተመለከትክ በጣም ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያለው፡፡ እንግሊዝ ውስጥ ባለአራት ገጽ ሞዴል (The four corner model) የሚባል ቲዎሪ አለ፡፡ አራቱን የእግር ኳስ መልኮች (The four aspects of football) ይመለከታል፤ የቴክኒካዊ ብቃት (The technical aspect)፣ የታክቲከ ብቃት (The tactical aspect)፣ የአካል ብቃት (The physical aspect) እና የአእምሮ ብቃት (The mental aspect) ናቸው፡፡ እነዚህን አራቱን ገጾች ለየብቻ ስትመለከት ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም በቴክኒክ የላቁ ተጫዋቾች አሉ፡፡ ኳስ አያያዛቸው፣ ኳስ ሲቀበሉ፣ ኳስ ሲገፉ፣ ኳስ ሲያቀብሉ በአጠቃላይ ከኳስ ጋር ምቾት የሚሰማቸው በጣም ብዙ ተጫዋቾች አሉ፡፡ ስለዚህ በቴክኒክ ረገድ በጣም ጥሩ ነው ማለት ነው፡፡ በአካል ብቃትም ቢሆን ኢትዮጵያ ዓለምን ያስደነቁ አትሌቶች መገኛ ሃገር ናት፤ በኣካል ብቃትም ብዙ ችግር አላየሁም የተጫዋቾችን አቋምና ቅርጽ (Shapes of players) ስትመለከት በተለይ አንዳንድ ተጫዋቾች በጣም ጥሩ አቋም ነው ያላቸው፡፡ ለምሳሌ እኔ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጣሁት ከባንግላዴሽ ነው፡፡ ባንግላዴሽ ተጫዋቾቹ ከልክ በላይ ወፍራም (Over weight) ናቸው፤ እሱ ደግሞ ለአሰልጣኝ (Disrespectful) ደስ አይልም፡፡ እንደደረስኩ መጀመሪያ እያንዳንዱ ተጫዋች አምስትና ስድስት ኪሎ ማስቀነስ ነበረብኝ፡፡ ተጫዋቾቹ አላስፈላጊ የስብ ክምችት ስለነበራቸው እሱ መጀመሪያ ወደ ጤናማ የአካል ብቃት መውረድ ነበረበት፡፡ ይሄን ሁሉ የምነግርህን ችግር እዚህ አላየሁም፡፡ ነገር ግን እንደማንኛውም የአፍሪካ ሃገር የታክቲክና የአእምሮ ስራ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ እንደ ጊዮርጊስ አይነት የደጋፊ ጫና ባለበት ክለብ ውስጥ ብዙ የአእምሮ ሥራ መስራት ያስፈልጋል፤ ተጫዋቾቹ ላይ የደጋፊ ጫና እንዳለ ይታያል፤ አእምሮ ላይ ብዙ መሥራት እንዳለብን ይሰማኛል፡፡ በአጠቃላይ ግን ጥሩ እግር ኳስ ደረጃ እንዳለ ነው የተረዳሁት፡፡


ሀትሪክ ፦ጊዮርጊስ በ2015 የካጋሜ ዋንጫ ላይ ተሳትፎ ነበር፤ በተቃራኒ የመጫወት ወይም የማየት ዕድል ነበርዎት?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ በፍጹም እኔ ሁለት ጊዜ ነው በካጋሜ ዋንጫ የተሳተፍኩት መጀመሪያ በ2011 የዋንጫ ተፋላሚ ሆነን የተሸነፍንበት ሁለተኛው ደግሞ በ2016 የዋንጫ ባለቤት የሆንኩበት፡፡ እኔ አሰልጣኝ ሆኜ የገጠምኩት ብቸኛ የኢትዮጵያ ክለብ ደደቢት ነው፤ በ2016 የካጋሜ የክለቦች ዋንጫ ላይ የምድብ ጨዋታ ላይ ተገናኝተናል፡፡

ሀትሪክ ፦ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከመምጣትዎ በፊት ስለ ክለቡ ያውቁ ነበር?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ በኬንያ፣ በታንዛኒያ ሁሉም ሰው ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ በጣም ያውቃል፤ ጊዮርጊስን ደጋፊዎቹን ማንም ነው የሚያውቀው፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በጣም ትልቅ ታሪክ ያለው ክለብ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሁን አይደለም ለረጅም ዓመታት ነው የማውቀው፡፡ ከራባት ካዛብላንካ ጋር ተጫውቻለሁ፣ ከኤስፔራንስ፣ ከቢድቬዝት፣ ከማሜሎዲ ሰንዳውንስ፣ ኦርላንዶ ፓይሬትስ፣ ዜስኮ ሁሉ ጋር ተጋጥሜያለሁ፡፡ ለምሳሌ ያንጋ በታንዛኒያ ከመቶ ዓመት በላይ እድሜ ያለው በጣም ትልቅ ክለብ ነው፤ በጣም ትልቅ ደጋፊ ያለው ክለብ ነው፤ ቅዱስ ጊዮርጊስም በጣም ታላቅ የታሪክ ሀብታምም የሆነ ክለብ ነው፡፡

ሀትሪክ ፦ ጊዮርጊስ እንደሚፈልግዎት ሲሰሙ ምን ነበር የተሰማዎት?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ በጣም ከፍተኛ ደስታ ነው የተሰማኝ፤ምክንያቱም ይሄንን የውጤትና የታሪክ ሀብታም የሆነ ክለብ ማሰልጠን ዕድልም ነው፤ ለዚህም ነው ወደ ጊዮርጊስ ስመጣ ገንዘብ ቀንሼ ነው የመጣሁት፤ ወደ ጊዮርጊስ በፍጹም ለገንዘብ አልመጣሁም፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በፊት በነበረኝ ኮንትራት አሁን ከማገኘው የተሻለ ገንዘብ አገኝ ነበር፤ ገንዘብ እንጨምርልህና ኮንትራትህን አራዝም የሚል ጥያቄም ቀርቦልኝ ረግጬ የመጣሁትም ለዚህ ነው፤አፍሪካ ውስጥ ያሉ ትላልቅ ሀገራትን ሁሉ አውቃቸዋለሁ፤እውነቱን ለመናገር ቅዱስ ጊዮርጊስ ስቦኝ ነው የመጣሁት (St. George Interests me)፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በጣም ትልቅ ክለብ እንደሆነ አውቃለሁ፤ ከዚህም በላይ ማደግ እንደሚችልም ጭምር አውቃለሁ፡፡ የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግና የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተጫውቻለሁ፤ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ተጫውቻለሁ፤ ጊዮርጊስ በዚህ ታላቅነቱ በነዚህ መድረኮች ፍጻሜ ላይ አለመታየቱ ሁሌም ይገርመኛል፡፡ አቅሙ እንዳለው አውቃለሁ፤ ለዛም ነው የመጣሁት፡፡

ሀትሪክ፡ የቋንቋ ችግርስ አልገጠምዎትም?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ እውነት ለመናገር በቋንቋ በኩል እስካሁን ከሰራሁባቸው ሀገራት የበለጠ ኢትዮጵያ ውስጥ ትንሽ ከብዶኛል፡፡

ሀትሪክ ፦ኬንያ ሁለት ጊዜ የመሥራት እድል ገጥሞዎት ነበር፤ በ2011 ሶፋፓካ በ2016 ደግሞ ሌዎፓርድስ ፤ ነገር ግን አንዱንም ጊዜ ሙሉ የውድድር ዓመት አልጨረሱም ምክንያቱ ምን ነበር?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ ሁለቱም ጊዜያት የገንዘብ ችግር ነው ያስለቀቀኝ፤ ሁለቱንም ጊዜያት ምክንያቴ ገንዘብ ነው፤ ሁለቱንም ጊዜያት የገቡልኝን ቃል አጥፈውብኛል፡፡ ምሳሌ ላንሳልህ ከዛሬ አስራ ስምንት ወራት በፊት ነበር ወደ ሌዎፓርድስ የሄድኩት፤ ስደርስ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አላቸው ይህ ኮሚቴ ዋንጫ ማንሳት እንደሚፈልጉ፣ ሻምፒዮናውን ካሸነፉ አስራ ሶስት ዓመታት እንደሆናቸው አሁን ግን ሻምፒዮናውን ለማሸነፍ ተጨማሪ ገንዘብ፣ ጊዜና ጥረት ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ሁሉ በግልጽ አስረዱኝ፡፡ በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ አንድም የሌዎፓርድስ ተጫዋች እንደሌለ ይህ ደግሞ በጣም እንደሚያበሳጫቸው ነገሩኝና ቡድኑን እንደ አዲስ እንዳደራጅ ኃላፊነቱን እንደሚሰጡኝና በሶስት ዓመት ውስጥ አሸናፊና ወጣት ቡድን ለመገንባት በቂ ጊዜና ገንዘብ እንደሚመድቡልኝ ነግረውኝ በቂ ደሞዝና ማበረታቻ እንደሚሰጡኝ ቃል ገቡልኝ፡፡ እኔ ሥራ ስጀምር የውድድር ዓመቱ ሊጠናቀቅ አንድ ወር ብቻ ነበር የቀረው፡፡ በቀሪው ጊዜ በክለቡ ያሉትን ተጫዋቾች በሚገባ ገመገምኩ፣ ከ20 ዓመትና ከ17 ዓመት በታች ቡድኖቹን በሚገባ ተመለከትኩ፣ የአንደኛ ዲቪዚዮን ውድድሮችንም እንደዚሁ እያየሁ ዝግጅቴን ጀመርኩ፡፡ ክለቡ በርካታ ዲቪዲ ሰጠኝ ስለዚህም የመጪውን ዓመት ዝግጅት በሚገባ ጀመርኩ፤ ጠዋት ዋናውን ቡድን ልምምድ አያለሁ ከልምምድ መልስ ዲቪዲዎችን አያለሁ፣ ወደ አስር ሰዓት ደግሞ የአንደኛ ዲቪዚዮንና የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን እመለከታለሁ፡፡ ከዚ ሁሉ ሥራና ድካም በኋላ የምፈልጋቸውን 20 ተጫዋቾችን ስም ዝርዝር፤ ከዝርዝሩ ውስጥ ደግሞ ቢያንስ 13 ወይም 14 ተጫዋቾችን እንዲያስፈርሙልኝ ከማስጠንቀቂያ ጋር ለኮሚቴው ሰጠሁ፡፡ እንደ አጋጣሚ ከበጀት በታች ስለነበር 12 ተጫዋቾችን አስፈረሙልኝ፤ ከዚህ ዝርዝር ውስጥ አሁን በስዊድን ሃገር እየተጫወተ የሚገኘው የብሔራዊ ቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ኤሪክ ዮሃና ይገኝበታል፡፡ ከአስራ ሁለቱ አዳዲስ ተጫዋቾች በተጨማሪ ሁለት ልጆችን ከወጣት ቡድን በማሳደግ 14 አዳዲስ ተጫዋቾችን ይዘን የአዲሱን ዓመት ዝግጅት ጀመርን፤ በጣም ጥሩ የዝግጅት ጊዜ አሳለፍን፤ ከስድስት ጨዋታ በኋላ የሰኝጠረዡ አናት ላይ ተቀመጥን፤ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከወራጆቹ ክለቦች በጥቂት ነጥብ በልጦ መጨራሻ ላይ የተረፈ ቡድን መሆኑን ልብ በል፡፡ ከዚህ ሁሉ ስኬት በኋላ ቃላቸውን አጥፈው ደሞዝ የለ፣ ማበረታቻ የለ፣ ስናሸንፍ ቃል የተገባልን ሁሉ ገደል ገባ፡፡ ይባስ ብሎ በልምምድ ወቅት እንኳ ውሃ ቅንጦት ሆነብን፣ የመለማመጃ ኳስ እጥረት ገጠመን፡፡ ኳስ እንኳን የሚገዙልን ደጋፊዎች ነበሩ፡፡ አንዱ ኳስ ሲገዛ ሌላው ውሃ ያመጣል፤ በዚ ሁኔታ ነው እንግዲህ ከሌዎፓርድስ ጋር የተለያየነው፡፡ በዚህ ዓመት እንኳን በዚሁ ምክንያት ብቻ ክለቡ ውስጥ አምስት አሰልጣኞች ናቸው የተፈራረቁት፡፡ ከደጋፊው፣ ከነዋሪውና ከተጫዋቾች ጋር ያለምንም የቋንቋ ችግር ነበር የምሰራው፣ በዛ ላይ ናይሮቢ ምርጥ ከተማ ነበረች፤ ምክንያቴ ቃላቸውን አለማክበራቸውና ገንዘቤን አለመክፈላቸው ብቻ ነው፡፡


ሀትሪክ ፦አዛም ደግሞ ሁለት ጊዜ ተመላልሰው አሰልጥነዋል፤ ብዙ ስኬትም አግኝተዋል፤ ሁለተኛ ቤትዎ ስለሆነው የታንዛንያ የአዛም ቆይታዎ ደግሞ እስቲ አጫውቱን…?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ አዛም ደግሞ ስደርስ ቡድኑ አንድም ዋንጫ አሸንፎ አያውቅም፤ በርግጥ ከኔ በፊት ሁለት ብራዚላውያን አሰልጣኞች አሰልጥነውታል፤ በወቅቱ የክለቡ ታላቅ ስኬት ለቮዳፎን ፕሪሚየር ሊግ ማለፉ ብቻ ነበር፡፡ ስለዚህ በነጭ ወረቀት ላይ (On a blanc paper) ነው ሥራ የጀመርኩት፤ ከኔ በፊት ክለቡ የሚኮራበት ታሪክ አልነበረውም፤ ግልጽ የሆነ መመሪያ ከክለቡ ተቀበልኩ፡፡ በሀገሪቱ ሁለት ታላቅ ክለቦች አሉ፤ ያንጋ አፍሪካና ሲምባ ስለዚህ የመጀመሪያው ሥራህ ሊሆን የሚገባው እነዚህን ሁለት ክለቦች መርታት ነው ተባልኩ፤ በሁለቱ ክለቦች መካከል መሆንና በሰንጠረዥ ሁለተኛ ሆኖ ለአፍሪካ ውድድሮች ማለፍ፡፡ ክለቡ የሚፈልገው ነገር ሁለቱን ክለቦች ማሸነፍ ብቻ ነበር ግልጽ ዓላማ ነበር የተሰጠኝ፤ የገንዘብ ችግር አልነበረብኝም ምክንያቱም የአዛም ባለቤት በአፍሪካ ውስጥ ካሉ ባለረብጣ ዶላር ቱጃሮች አንዱ ቤተሰብ ነው፡፡ ክለቡ ባለ አምስት ሚሊዮን ዶላር የመለማመጃ ሜዳ አለው፡፡ ወደ ሜዳ ስንመጣ በደስታ ነው፤ በክለቡ የጠየቅነው ሁሉ ይሟላልናል፤ የምፈልጋቸውን ልጆች አስፈረምኩ፡፡ የውድድሩን ግማሽ ሶሥተኛ ሆነን ጨረስን፤ ሙሉ ዓመቱን ደግሞ ሁለተኛ ሆነን ለአህጉራዊ ውድድርና ለካጋሜ ዋንጫ አለፍን፤ በካጋሜ ዋንጫ ኤኤስ ቪታን፤ ተስከርን የመሳሰሉ ታላላቅ ክለቦችን ረትተን በመጨረሻ ከሲምባ ጋር ለፍጻሜ ደረስን፤ ሲምባን 3-0 ረትተን ዋንጫውን አነሳን፡፡

ሀትሪክ ፦ከታዳጊዎችና ከወጣቶች ጋር በመስራት በቂ ልምድ አልዎት፤ የአዋቂዎች ቡድንንም ውጤታማ በማድረግ እንዲሁ፤ የጊዮርጊስን አመራሮች ልብና አእምሮ አሸንፎ መንበሩን ያስፈቀደልዎ ፕሮጅክት ምን ይሆን?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ የቅዱስ ጊዮርጊስ አመራሮች አጽንኦት ሰጥተው የነገሩኝ አንድ ነገር ቢኖር ክለቡ አምስት የውጭ ተጫዋች ብቻ የማስፈርም ዕድል አለው በየዓመቱ ተጫዋች ሲያስፈርም ከአምስቱ ውስጥ ሶሥቱ ወይም ሁለቱ የክለቡን ደረጃ የማይመጥኑ እየሆኑበት በጣም እንደተቸገረና አፍሪካዊ ተጫዋቾችን በሚገባ የሚያውቅ አሰልጣኝ እንደሚፈልግ ነገሩኝ፡፡ እኔ ደግሞ በዚህ ረገድ በቂ እውቀት አለኝ በታንዛኒያ፣ በኬንያ ሰርቻለሁ በቻምፒዮንስ ሊግ፣ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተጫውቻለሁ፤ የደቡብ አፍሪካ፣ የአይቮሪኮስት፣ የናይጀሪያ፣ የቱኒዚያ ክለቦችን በተቃራኒ ገጥሜ አሸንፌያለሁ፣ ዓለም ዓቀፋዊ ውድድሮች ላይ ብዙ ተሳትፌያለሁ፤ ስለዚህ መውፈርቱን በሚገባ አሟላለሁ፡፡ ጊዮርጊስ ከአፍሪካውያን ተጫዋቾች ጋር የሰራ አሰልጣኝ ነበር የሚፈልገው፤ እኔ ደግሞ ኤስፔራንስን፣ ቢድቬዝትን፣ ማሜሎዲ ሰንዳውንስን፣ ኤኤስ ቪታን፣ ዜስኮነ ዛናኮን የመሳሰሉ ታላቅ ክለቦችን ገጥሜ አሸንፌያለሁ፡፡ ይሄንን ሁሉ ስለሚያውቁ ነው እኔን የመረጡኝ፤ ከዛ በተጨማሪ ግን ጊዮርጊስ በጣም ጥሩ አካዳሚ አለው፤ ስለዚህ በሃገሪቱና በክለቡ እድገት ላይ አብረን መሥራት መፈለጋችን ነው ያገናኘን፡፡

ሀትሪክ ፦አካዳሚውንም የማሳደግና ታዳጊዎችን የማብቃት ኃላፊነትም አብሮ ተሰጥዎታል ማለት ነው?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ ለጊዜው ኃላፊነቴ ዋናውን ቡድን ማሰልጠን ነው፤ ምክንያቱም ዋናው ቡድን በባለፈው የውድድር ዓመት ምንም ዋንጫ አላሸነፈም። ይህ ደግሞ በጊዮርጊስ ቤት የተለመደ አይደለም፤ ስለዚህ ለጊዜው ኃላፊነቴ ዋናውን ቡድን ወደቀደመ አሸናፊነቱ መመለስ ነው፡፡ ከዛ በኋላ ደግሞ አካዳሚውን ማየትና በእግር ኳስ ልማት ላይ መሥራት እንጀምራለን ማለት ነው፡፡ እኔ የተረከብኩት ቅዱስ ጊዮርጊስ የተወሰኑ ችግሮች ነበሩበት፤ የቴክኒክ ዳይሬክተር አልነበረውም፤ ሁለት ታላላቅ ባለልምድ አጥቂዎቹ ጉዳት ላይ ናቸው፤ ምናልባትም ከዚህ በኋላም ለጥቂት ሳምንታት አይኖሩም፤ ከአምስቱ የውጭ ተጫዋቾች ውስጥ ሁለት ወይም ሶስቱ ከሳምንት ሳምንት የመጀመሪያ አስራ አንድ ውስጥ የማይገኙበት ክለብ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን በአጥቂ ክፍላችን ውስጥ የተወሰነ ክፍተት አለብን፡፡ የተጫዋቾቼ መነሳሳት በባለፈው የውድድር ዓመት ዋንጫ ካለማግኘታቸው ጋር ተያይዞ መጠነኛ የሞራል መውረድ አስተውያለሁ፡፡ እንደ ጊዮርጊስ ዓይነት ታላቅ ክለብ ውስጥ ስትጫወት ሁሌም የደጋፊ ጫና አለብህ፤ አሁን በፍጥነት ወደ አህጉራዊ ውድድሮች መመለስ አለብን፡፡ ፕሪሚዬር ሊጉን አሸንፈን ወደ ቻምፒዮንስ ሊግ መመለስ አለብን የኢትዮጵያ ዋንጫን የግድ ማሸነፍ አለብን፡፡

ሀትሪክ ፦፡ በህንድና ባንግላዴሽ የነበርዎት ቆይታ ምን ይመስል ነበር?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ እኔ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ኢንስትራክተር ነኝ፤ እናም በኤዥያ የአሰልጣኞች ስልጠናን እሰጣለሁ፡፡ በኮርያ፣ ቻይናና ሆንግ ኮንግ እንዲሁም በደቡብ ምስራቅ ኤዥያ የአሰልጣኞች ስልጠናን እሰጣለሁ፡፡ ስለዚህም በህንድና ባንግላዴሽ ከሚገኙ አሰልጣኞች ጋር መልካም የሚባል ግንኙነት ነበረኝ፡፡ በነዚሁ ሀገራት ለአውሮፓ ደረጃ ያበቃዋቸው አሰልጣኞች ነበሩና በነዚሁ አሰልጣኞች ጥቆማ ነው ወደ ኤዥያ የሄድኩት፡፡ ህንድም ባንግላዴሽም ስሄድ እኔ አንድም ጊዜ ማመልከቻ አላስገባሁም፤ ለውድድርም አልቀረብኩም፤ እጩም ሆኜ በአሰልጣኝ ዝርዝር (Short list) ፉክክር ውስጥም አልገባሁም፤ ነገር ግን የክለቦቹ አመራሮች ስልኬ ላይ ደውለው ወደ ህንድ ወይም ወደ ባንግላዴሽ እንድትመጣ እንፈልጋለን ምን ያህል እንክፈልህ ነው ያሉኝ፡፡

ሀትሪክ ፦፡ ባንግላዴሽ ውስጥ ግን እግር ኳስ አለ?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ አዎ ከክሪኬት ቀጥሎ፡፡

ሀትሪክ ፦ ከህንድ ቀጥሎ በትሪንዳድና ቶቤጎ እንዲሁም በቅዱስ ቨንሰንት ብሔራዊ ቡድኖችን አሰልጥነዋል፤ የካሪቢያን ቆይተዎ ምን ይመስል ነበር?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ ከዩዜይን ቦልት በኋላ ከአትሌቲክስ ቀጥሎ ተወዳጅ ስፖርት ሆኗል፤ ቦልትን ማንም ያውቀዋል፤ ስለዚህ ኳሱም በሚገባ ተዋውቋል፡፡ ወደ ካሪቢያንም ሳቀና እንዲሁ በወዳጄ በድዋይት ዮርክ ጥቆማ ነበር፤ በበርሚንግሃም አካዳሚ ከዮርክ ጋር በሚገባ እንተዋወቃለን፡፡ እንደምታውቀው ዮርክ የካሪቢያን ምልክት ነው፤ በሱ ጥቆማ የትሪንዳድና ቶቤጎ ወጣት ቡድን የቴክኒክ አማካሪ ሆኜ ጀመርኩ፤ ከዛም የ20 ዓመት በታች ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆኜ ሰራሁ፡፡ ከዛ በመቀጠል ወደ ቅዱስ ቨንሰንት ብሔራዊ ቡድን አመራሁ፤ ይልቅ በቅዱስ ቨንሰንት ምርጥ ቆይታ ነበረኝ፤ ከቬኑዝዌላ፣ ከጃማይካ፣ ጓዳሉፕ፣ ካናዳና ኩባን ከመሳሰሉ ቡድኖች ጋር በሜዳና ከሜዳ ውጭ በተቃራኒ ተጫውተናል፤ ለኮንካካፍ ማለፍም ችለናል፣ እውነት ለመናገር በጣም ጣፋጭ ጊዜ ነበረኝ፡፡


ሀትሪክ ፦ከፑን ኤፍ ሲ ጋር ሲለያዩ ምክንያትዎ ከተጫዋቾች ፊርማ ጋር የተያያዘ ነበር …እርስዎ ባላስፈርሟቸው ልጆች መጫወትን በሚመለከት ነበር መሰለኝ…?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ የልጆቹን አለማስፈረም ብቻ አይደለም ፊርማውም ፕሮፌሽናል አይደለም ፤ፑን ኤፍ ሲ በዲታ ሃብታም ባለቤትነት የተያዘ አዲስ (Brand new) ክለብ ነበር፡፡ በወቅቱ በህንድ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ነበር የሚወዳደረው የኔ ኃላፊነት ክለቡን ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማሳደግ ነበር፤ክለቡን በአዲስ መልክ የማዋቀርና ፕሮፌሽናል ክለብ የማድረግ ኃላፊነት ነው የተሰጠኝ፡፡ ሃያ ስድስት ተጫዋቾችን ሲያስፈርሙ አንዱንም እንኳን እኔ አላስፈረምኩም፤ ክለቡን ቀርቤ ሳስተውለው በፍጹም ሚዛን የለውም፡፡ እውነቴን ነው የምልህ ስብስቡ በፍጹም እግር ኳሳዊ አይደለም፤ ከሃያ ስድስቱ ውስጥ ስምንቱ የክንፍ ተጫዋቾች ነበሩ፤ ስምንቱ ደግሞ Wide players ነበሩ፤ አንድ ወይም ሁለት የክንፍ ተጫዋች ነው ልታጫውት የምትችለው፤ ስምንት የክንፍ ተጫዋች ምን ያረግልኛል? ለባለሃብቶቹ አስረዳዋቸሁ፤ ነገር ግን ተጫዋች ለማስፈረም በቅድሚያ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማለፍ እንደሚጠበቅብኝ ተስማማን፡፡ ባሉን ልጆች የተቻለንን ሁሉ ሞከርን ዓላማችንንም አሳካን፡፡ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ከባለቤቶቹ ጋር ስብሰባ ተቀመጥኩ ነገር ግን አሁንም እኛ ነን የምናስፈርመው ሲሉኝ በፍጹም ልቀበል አልችልም፤ እኔም ተሰሚነት ሊኖረኝ ይገባል በሚል ነው አለመግባባቱ የተፈጠረው፡፡

ሀትሪክ ፦በአንድ የርስዎ ቃለ-ምልልስ ላይ “ክለቡን አውሮፓዊ ቀለም European style ያለው ክለብ ለማድረግ እየሰራሁ ነው የቆየሁት ብለው ነበር ለመሆኑ European style ምን ማለት ነው?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ ፡ ለምሳሌ የክለቡ ባለቤቶች አውሮፓ ክለቦች ያላቸውን ዓይነት መለማመጃ ሜዳ መገንባት እንፈልጋለን አሉኝ፤ የመለማመጃ ሜዳ ብቻ ሳይሆን የአውሮፓ ደረጃ ያለው አመጋገብ፣ የአውሮፓ ደረጃ ያለው ስልጠና፣ የአውሮፓ ደረጃ ያለው አሰልጣኞች ስታፍ ሁሉ ያስፈልጋችኋል፤ የኮሪያ ሩዝ ብቻ አይደለም ምግብ፡፡ በዛን ወቅት ክለባችን ከሌሎች የህንድ ክለቦች ሁሉ የቀደመ ነበር፤ አሁን የህንድን ሊግ ስታይ በጣም ደረጃው አድጓል ያኔ ግን የኛ ክለብ ከሌሎቹም የህንድ ክለቦች የቀደመ ነበር፡፡ የህንድ ክለቦች የአውሮፓ አሰልጣኞችን እንዲሁም ኒኮላ አኔልካና ዴቪድ ጀምስን የመሳሰሉ አውሮፓውያን ተጫዋቾች መሳብ ችለዋል፡፡ የህንድ ክለቦች ዛሬ ላይ የህንድ ክለቦች ሳይሆኑ የህንድ ለዛ ያላቸው የአውሮፓ ክለቦች ናቸው (European clubs with Indian flavor)፡፡

ሀትሪክ ፦ አሁንም ጊዮርጊስ ውስጥ ያሉትን ልጆች እርስዎ አላስፈረሟቸውም፤ ይህ ተመሳሳይ ችግር አይፈጥርቦትም?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ ከጊዮርጊስ ጋር በፍጹም የተለያየ ነው፡፡ ጊዮርጊስ ውሰጥ ያሉትን ልጆች እኔ እንዳላስፈረምኳቸው በሚገባ አውቃለሁ፤ ነገር ግን እኔም ባስፈርም ምንም ልዩነት የለውም ስብስቡን ስመለከተው በርግጥ ጥቃቅን ችግሮች አሉብን፤ ይሁን እንጂ ባብዛኛው በጣም ጥሩ ስብስብ ነው ያለን።

ሀትሪክ ፦እስቲ ደግሞ ስለ ባንግላዴሽ ክለብ ሳይፍ ኤፍ ሲ ቆይታዎ ያጫውቱን….

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ ሳይፍ ስፈርምም ልክ እንደ አዛም ሁሉ አዲስ (Brand New) ክለብ ነበር፤ ባለቤቱም የበጣም ብዙ ቢሊዮን ዶላር ድርጅቶች ባለቤት ነው፤ ምንም የገንዘብ ችግር የለበትም። እንደ ሌዎፓርድስ አይደለም ተጫዋቾችን አስፈርመው ነበር እኔ ያስፈረምኩት የውጭ ተጫዋቾችን ብቻ ነው፡፡ የሀገር ውስጥ ተጫዋቾችን በሙሉ አስፈርመው ጨርሰው ነበር፡፡ በጣም ወጣት ቡድን ነበር የክለቡ ዓላማ ለኤዥያ ቻምፒዮንስ ሊግ ወይም ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ማለፍ ነበር፤ በክለቡ በጣም ደስተኛ ነበርኩ ይሁን እንጂ በሃገሪቱ የስፖርት መሰረተ ልማት ደረጃና በውድድሩ ደረጃ ግን ደስተኛ አልነበርኩም፡፡ አስራ ስምንት ጨዋታ አድርገን በአንዱ እንኳን አልተሸነፍንም፤ አራቱን አቻ ስንወጣ አስራ አራቱን አሸነፍን፡፡ ሁለት ውድድር አሸነፍን ሌላ ሶስተኛውን ውድድር ደግሞ ሩብ ፍጻሜ ገብተን ነው የለቀቅኩት፤ እኔ ከወጣሁ ከሁለት ቀናት በኋላ በሩብ ፍጻሜው ተሸንፈው ከውድድር ወጡ፡፡ ባንግላዴሽ የክሪኬት ሀገር ነች፤ በሄድክበት ሁሉ የክሪኬት አካዳሚዎችን ነው የምታየው፤ ለማመን የሚከብዱህ ትላልቅ የክሪኬት አካዳሚዎችን ታያለህ፤ ሃገሪቱ ውስጥ በጣም ገንዘብ አለ አብዛኛው ብር ግን ወደ ክሪኬት ነው የሚሄደው፡፡ ታዋቂ አሰልጣኞች፣ ውብ የመለማመጃ ሜዳዎች፣ ትላልቅ አካዳሚዎች ሁሉ የክሪኬት ናቸው፡፡ ስለዚህ ለኔ ባንግላዴሽ ትክክለኛ ቦታ አይደለም ብዬ ወሰንኩ፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን ፕሮፌሽናል አካባቢ መሆን እመርጣለሁ፡፡ የክለቡ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እጅግ በጣም ወዳጄ ነው፤ሥራዬን ከመውደዴ ውጭ ሌላ ምክንያት የለኝም፡፡

ሀትሪክ ፦ወደሳይፍ ሲሄዱ በታንዛኒያ ረዳትዎ የነበረውን ዴኒስ ኪታምቢን ይዘው ነበር የሄዱት ነገር ግን እርስዎ ሲወጡ እዛው ትተውት ነው የወጡት ምክንያቱ ምን ይሆን?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ ዴኒስ ኪታምቢ አሁንም እዛው ነው፤ ምክንያቱም ዴኒስ የስምምነቱ ከፊል አካል ነው፡፡ በውላችን መሰረት እኔ እንኳ ብለቅ ዴኒስ በዛው ቆይቶ ከቀጣዩ አሰልጣኝ ጋር እንደሚሰራ ተስማምተናል፡፡ እንደነገርኩህ ከዋና ሥራ አስፈጻሚው ከአቶ ናስር ጋር በጣም መልካም ግንኙነት ነበረን፤ እንዲለቁኝ ስጠይቃቸው ተተኪ አሰልጣኝ እንድፈልግና ዴኒስ ደግሞ አብሮ እንደሚቀጥል ተስማምተን ተተኪ አሰልጣኝ ሰጥቼአቸው ነው የለቀቁኝ፡፡


ሀትሪክ ፦እርስዎ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣትዎ በፊት ፓትሪክ ማታሲን ቡድኑ እንዲያስፈርመው ሃሳብ መስጠትዎን የኬንያ ጋዜጦች እየዘገቡ ነበር፤ ፓትሪክ ከርስዎ ጋር አብሮ አልሰራም እንዴት እንዲህ ሊያምኑበት ቻሉ?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ ሁለቱንም ጊዜያት ኬንያ ስሄድ እሱ ፕሪሚየር ሊግ ይጫወት ነበር፤ መጀመሪያ በ2012 ስሄድ እርሱ የብሔራዊ ቡድን አባል ነበር ነገር ግን ዋና ግብ ጠባቂ አልነበረም፤ በ2016 ተመልሼ ስሄድ ግን የክለቡ ዋና ግብ ጠባቂ ነበር፡፡ ፓትሪክን በደንብ አውቀዋለሁ፤ በተደጋጋሚ በተቃራኒ ገጥሜው ሲጫወት ብዙ ጊዜ አይቼዋለሁ፤ በጣም ጥሩ ግብ ጠባቂ ነው፡፡

ሀትሪክ ፦ የቀድሞው የጎርማህያ አጥቂም አሁን እርስዎ ቡድን ውስጥ ይገኛል፤ ስለእሱስ ምን አስተያየት አልዎት?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ አሌክስን አላውቀውም፤ እኔ ኬንያ እያለሁ እሱ ሩዋንዳ ነበር፤ ወደ ኬንያ የሄደው እኔ ከኬንያ ከወጣሁ በኋላ ነው፤ ስለዚህ አሌክስን አላውቀውም፡፡

ሀትሪክ ፦ የክለቡን የቴክኒክ ስታፍ እንዴት አገኙት?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ ጥሩ ነው ነገር ግን በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ትንሽ አስቸግሮኝ ነበር፤ የተጫዋቾችን ስም አላውቅም ማን? የት ቦታ? እንደሚጫወትም አላውቅም፤ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ሁለት ቦታ ላይ ይጫወታሉ፤ ስለዚህ ይህን በሚገባ የሚያውቅ ሰው ያስፈልግሃል፡፡ ለምሳሌ ደግሞ ወደ ሃዋሳ ጉዞ ማድረግ ሊኖርብህ ይችላል፤ ጉዞው ምን ያህል ሰዓት ይወስዳል? ሆቴል የትና? እንዴት ነው የሚያዘው? ምን ማድረግ አለብህ? ወይም ማድረግ የለብህም? የሚለውን ሁሉ የሚያውቅ ሰው ያስፈልግሃል፡፡

ሀትሪክ ፦በቡድኑ ስብስብ (Squad) ደስተኛ ኖት?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ አዎን በጣም በቴክኒክ ብቃታቸው የላቁ ባለተሰጥኦ ተጫዋቾች እንዲሁም ጥሩ የአካል ብቃት ያላቸው ልጆች በቡድናችን ውስጥ አሉን፤ በእርግጥ በአእምሮና ታክቲክ ረገድ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል፡፡

ሀትሪክ ፦የክለቡ የተሻለ ጠንካራው ክፍል የቱ ነው?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ በጣም ጥሩ የተከላካይ ክፍል አለን፤ ጥሩ የመሃል ሜዳ ተጫዋቾችም አሉን፤ ምናልባት ችግር አለብን ካልን በጉዳት የሳሳው የአጥቂ ክፍላችን ነው፡፡ እንደምታውቀው ሁለት ልምድ ያላቸው አጥቂዎች ጉዳት ላይ ናቸው፤ ሁለት ኳስ መጨረስ የሚችሉ የሳጥን ውስጥ አጥቂዎች፣ ሁለት ጥሩ ኳስ መያዝና ዕድል መፍጠር የሚችሉ እንዲሁም ሁለት በጣም ፈጣን የሆኑ የላቀ የቴክኒክ ችሎታ ያላቸው ወጣት አጥቂዎች አሉን፤ የሚጠበቅብን እነዚህን ልጆች እንዴት አመጣጥኖ መጠቀም እንዳለብን ማወቅ ነው፡፡ አንዱን ባለ ልምድ አጥቂ ከአንዱ ወጣት ጋር ማቀናጀት ከቻልን የተሻለ የአጥቂ ክፍል ይኖረናል ማለት ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ግን የተጎዱት ልጆች እስከሚመለሱ መጠበቅ ግድ ይሆንብናል፡፡ ከሳላና ከጌታነህ የአንዱ በጥሩ ብቃት ላይ መሆን የግድ ያስፈልገናል፡፡


ሀትሪክ ፦ስለ ሳላሃዲን ከመምጣትዎት በፊት ያውቁ ነበር?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ ስለሱ ብዙ አውቃለሁ፤ ስለ ሪከርዶቹ፣ ግብጽ እንደተጫወተ አውቃለሁ፣ ለብሔራዊ ቡድን የሠራውንም አውቃለሁ፣ ጥሩ አጥቂ እንደሆነም እንደዛው፡፡ ከመጣሁ በኃላም ብዙ አውርቼዋለሁ፤ ስለ ልምዶቹ፣ ስለ ክለቡ አውርቼዋለሁ፤ አሁን ልምምድ ጀምሯል፤ በቅርቡ በጥሩ ብቃት ወደ ጨዋታ እንደሚመለስ አስባለሁ፡፡

ሀትሪክ ፦ከአሰልጣኞች የማን አድናቂ ኖት?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ ጋርዲዮላ ነው፤ አዎ የመጀመሪያ ምርጫዬ ጋርዲዮላ ነው። ነገር ግን የርገን ክሎፕና አንቼሎቲም ይመቹኛል።

ሀትሪክ ፦ጋርዲዮላ፣ አንቼሎቲ፣ ክሎፕ ሶስቱም ኳስን በመያዝና ተጭኖ በመጫወት የሚታወቁ አሰልጣኞች ናቸው፤ ምናልባት የርስዎም ፍልስፍና ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ይሆን?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ አዎን እኔም በጣም ፈጣን ጨዋታ መጫወት ነው የምፈልገው፤ ፈጣን፣ በተጋጣሚ ላይ የበለጠ ጫና ያለው (Pressng)፣ አስጨናቂ ወራሪ ( More aggressive)፣ የአውሮፓዊ ክለብ ባህሪ ያለው ጨዋታ ( having a European style) ነው መጫወት የምፈልገው፡፡ ይህን ለማድረግ ግን የአካል ብቃታችንን ማሻሻል ይጠበቅብናል፡፡ ተጫኖ ለመጫወት ጥሩ ትንፋሽና የአካል ብቃት ያስፈልግሃል፤ ልጆቹን እንዳየሃቸው ይህን ለማድረግ ብቃት አላቸው፤ በመጀመሪያ ጨዋታዬ ከሽሬ ጋር ስንጫወት ያየሁት ነገር ሁሉ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡

ሀትሪክ ፦ብዙ ባለሙያዎች ኢትዮጵያውያን ኳስ ይይዛሉ ነገር ግን ወደ ውጤት መቀየር ላይ ግን ደካማ ናቸው ይላሉና እርስዎም ይህን ታዝበው ይሆን?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ አዎ እውነት ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ እኔ እንደሚመስለኝ ዋናው ምክንያት የቦታ አያያዙ በጣም ቀርፋፋ ነው፡፡ የተወሰነው የኳሱ አመሰራረት ጥሩ ነው ነገር ግን ለተቃራኒ ቡድን ብዙ ጊዜ የምትሰጥ ከሆነ ግን ዋጋ የለውም፤ በፍጥነት ወደ ውጤት መቀየር አለበት፡፡ እኔ እንዳየሁት ለተቃራኒ ቡድን በቂ ጊዜ ትሰጣላችሁ፤እግር ኳሳችሁ ለመልሶ ማጥቃት የበለጠ ትኩረት መስጠት አለበት፡፡ ከመልሶ ማጥቃት ባሻገር በፍጥነት ማጥቃት ያስፈልጋል፤ እሱን ነው እንግዲህ በተደጋጋሚ በልምምድ ሜዳ ላይ እየሰራን የቆየነው፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ ከሽሬ ጋር በመልሶ ማጥቃት በጣም ጥሩ ነበርን፤ ነገር ግን ሲዳማ ላይ ያንኑ እንኳን መድገም አልቻልንም፤ኳስ ምስረታ ላይ በጣም ቀርፋፋ ነበርን፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን አዲስ ነገር ስትማር አእምሮህ ወደለመደውና ቀድሞ ወደሚያውቀው ነገር ያዘነብላል፡፡ አዲሱን ነገር ለመለማመድ ትሞክራለህ፤ አእምሮህ ግን ወደቀደመው ነገር ማዘንበሉ አይቀርም፡፡ አዲሱን ነገር ባህሪህ ለማድረግ ጊዜ ይፈልጋል፤ እኛም በዚህ ሂደት ላይ ነን ምናልባትም ግማሽ መንገድ ሄደናል ግማሽ ደግሞ ይቀረናል፡፡ በየቀኑ የተወሰነ ሰዓት ወስደን በሚገባ እንለማመዳለን፤ ባህሪ ያደረግነው ዕለት ግን የፈለግነውን ያህል ጎል ምምረት እንችላለን፡፡ መንገዱ አንድና አንድ ብቻ ነው ምንም አቋራጭ መንገድ የለውም፡፡

ሀትሪክ ፦ካነሱት አይቀር በሁለት ጨዋታ ሶስት ግብ ስላስቆጠረው አቤል እስቲ እናውራ አቤልን እንዴት አገኙት?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ አቤልን በሚመለከት ግልጽ ያልሆነ ነገር አለ፤ አንዳንዶች የክንፍ ተጫዋች ነው ይሉኛል፤ ሌሎቹ ደግሞ የፊት አጥቂ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ እኔ በፊት አጥቂነት ነው ያስጀመርኩት ነገር ግን በተሰጠው ነጻነት ወደ ክንፍ እየወጣ ይጫወታል፡፡ መጫወት የጀመርነው በሁለት ፈጣን የፊት አጥቂዎች ነው፤ ሁለቱም ወጣቶች ናቸው፣ ፈጣኖች ናቸው፤ አቤል ደግሞ የበለጠ ፈጣን ነው፤ ከአቤል ጋር በጊዜና ቦታ አጠቃቀም ላይ የበለጠ ጊዜ ወስደን እየሰራን ነው፡፡ በርግጥ አሁንም ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ በፊት መስመር ላይ ብዙ መሥራት አለብን ምክያቱም አቤል አሁን ከክንፍ እየተነሳ ሲጫወት ነው የተሻለ የሚሆነው ስለዚህ ከግብ ፊት ለፊት ብዙ ሥራ አለበት፡፡ አቀባበሉ፣ አመለካከቱ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ፍጥነቱና እንቅስቃሴው ለተጋጣሚ በጣም አስቸጋሪ ነው፤ በፍጹም የማይገመት እንቅስቃሴ ያለው አጥቂ ነው፤ በፍጹም ከሰው በፊት ኳስ ማየት አይፈልግም ከተጋጣሚ ኋላ እንጂ፤ አቤል በጣም ተስፋ ያለው ተጫዋች ነው፡፡

ሀትሪክ ፦በተከላካይ ክፍልም ሳላህዲን ባርጌቾ (ሳላ) ጉዳት ላይ መሆኑስ?….

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ ሳላ አሁንም በድጋሚ ተጎድቶብናል፤ ልምምድ ጀምሮ ተስፋችን መልሶት ነበር ከሃያ ዓመት በታች ቡድኑ ጋርም 70 ደቂቃ ተጫውቶ ነበር አሁንም ተመልሶ ተጎድቷል ለጨዋታው ግን ይደርሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ (ውድ አንባቢያን ቃለምልልሱ ከእሁዱ ጨዋታ ቀደም ብሎ የተሰራ ቃለ-ምልልስ መሆኑን እንድትገነዘቡልን እንፈልጋለን) የአምና ጨዋታዎችን ቪዲዮዎች እያየሁ ነበር፤ ሳላህዲን አብዛኛውን ጨዋታዎች ተጫውቷል፤ ይሄ ደግሞ ለመሃል ተከላካይ በጣም ከባድ ነው፡፡ ሳላ አገግሞ በቅርቡ ወደ ቡድኑ እንደሚመለስ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሀትሪክ ፦ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የመጀመሪያዎት ነው?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ አዎ የመጀመሪያዬ ነው ከትራንዚት ውጭ፤ ከኬንያና ከታንዛኒያ ወደ እንግሊዝ ስሄድ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ አበባ ላይ ትራንዚት አደርግ ነበር፡፡ አዲስ አበባ በጣም ምርጥ ከተማ ነች፤ እኔ እንዳየሃት ከሆነ አዲስ አበባ የአፍሪካ መናገሻ ከተማ ነች፤ ኢትዮጵያ አፍሪካም አረብም አይደለችም፤ የራሷ ቀለም ያላት የራሷ ለዛ ያላት ምርጥ ሃገር፣ ሙዚቃ፣ ምግብ፣ ባህል፣ አለባበስ ወዘተ የራሷ የሆነ የተለየ ውበት ያላት ሃገር ናት ኢትዮጵያ፡፡ ይህን የተለየ ውበት ለባለቤቴ መንገር ፈልጌ ምን ብዬ ልግለጽላት ኢትዮጵያ አራቢያም አይደለችም አፍሪካም አይደለችም (Ethiopia is not Africa, it is not Arabia either) የአፍሪካና የአራቢያ መገናኛ ናት ( It is where Africa meets Arabia)፡፡

ሀትሪክ ፦ከኢትዮጵያ ምግብ የትኛውን ይበልጥ ወደዱት?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ የሸክላ ጥብስ

ሀትሪክ ፦ትርፍ ጊዜዎን በምን ያሳልፋሉ?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ ጂምናዚየም ውስጥ፤ በሳምንት አምስት ስድስት ቀናት ጂምናዚየም ውስጥ አሳልፋለሁ፤ከዚህ ውጪ ምግብ ማብሰል በጣም ደስ ይለኛል፤ የራሴን እራት ማዘጋጀት በጣም ያዝናናኛል። ከዛ ውጭ ኳስ ማየት እወዳለሁ፤ የእንግሊዝ ፕሪምዬርሊግ አያለሁ፤ ባለፈው ሳምንት ሳውዛሃምፕተን ሲጫወት ናታን ሬድሞንድ ሲጫወት እያየሁት ነበር፤ ሬድሞንድን እኔ ነኝ ለበርሚንግሃም በዘጠኝ ዓመቱ ያስፈረመኩት፤ ከዘጠኝ ዓመቱ እሰከ አስራ ዘጠኝ ዓመቱ ተጫውቶ በብዙ ብር ተሸጠ፡፡ ከሳውዝጌት ጋር አንድ ላይ የአሰልጣኝነት ኮርስ ወስደናል፤ ስቶክ ሲቲ ውስጥ ጃክ በትላንድ የኛ አካዳሚ ልጅ ነው፤ ሌስተር ሲቲ ውስጥም የበርሚንገሃም አካዳሚ ውጤት አለ፡፡ ስለዚህ እግር ኳስ ብዙ አያለሁ፡፡

ሀትሪክ ፦ እግር ኳስ ተመልካች ከሆኑ የትኛው ክለብ አድናቂ ኖት?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ ሊቨርፑልን ማየት በጣም ነው ደስ የሚለኝ፤ ፈርሚኖ፣ ሳላህና ማኔን ማየት በጣም ደስ ይለኛል፤ ፍጥነታቸው፣ እንቅስቃሴያቸው አንድ ላይ ሶሥቱን ማየት በጣም ነው ደስ የሚለኝ፡፡

ሀትሪክ ፦ስለ ቤተሰብዎ…ያጫውቱኝ እስቲ…?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት ነኝ፤ ከመጀመሪያው ትዳሬ ሁለት ሴት ልጆች አሉኝ አሁን ሰላሳዎች ውስጥ ናቸው፡፡ የመጨረሻው ወንድ ነው፤ ካሁኗ ባለቤቴ የተወለደ ነው፤ እሱ ደግሞ አሁን የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነው፡፡ ኳስ በፍጹም አይወድም የኮምፒዩውተር ፍቅር ነው ያለው፡፡

ሀትሪክ ፦በቅዱስ ጊዮርጊስ በአጭርና በረዥም ጊዜ ምን ለማሳካት ያስባሉ?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ ያጭር ጊዜ ግባችን ወደ አህጉራዊ ውድድር መመለስ ነው፤ ጊዮርጊስ የካጋሜ ዋንጫን የሚወዳደር አይመስለኝም ስለዚህ የካጋሜ ዋንጫ ግብዣን ማግኘት፣ ካጋሜ ዋንጫን ማሸነፍ፣ ከተሳካ ለቻምፒዮንስ ሊግ ካልሆነ ግን ለኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ማለፍ ይጠቀሳል፡፡ የረዥም ጊዜ ደግሞ የአካዳሚውን ደረጃ ማሳደግና ሁልግዜም ቡድኑን የሚረከቡ ታዳጊዎችን እያፈሩ ለዋናው ቡድን መመገብ፡፡ የአሰልጣኞችን ብቃት እያሻሻሉ የተሻለ ብቃት ያላቸውን ታዳጊዎችን ማፍራት፡፡ በተጨማሪ አጠቃላይ የክለቡን እድገት በማሻሻል የዋናውን ቡድን ውጤት አስተማማኝ ደረጃ ላይ ማድረስ ነው፡፡

ሀትሪክ ፦ለውጭ አሰልጣኞች ኢትዮጵያ ውስጥ አንደኛው መሰረታዊ ችግር ካላንደር ነው ፤ከሀገሪቱ ሻምፒዮና ውጭ ሌላ የወዳጅነት ጨዋታም ሆነ ውድድር እምብዛም አልተለመደም በዚህስ ረገድ ምን አስበዋል?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ የካጋሜ ዋንጫ በጣም ይጠቅመናል፤ በተለይ ዘንድሮ ምንም አህጉራዊ ውድድር እንዳለመጫወታችን ውድድሩ በጣም ይጠቅመናል፡፡ ችግሩ ግን የካጋሜ ዋንጫ አንድ ዓመት አለ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ የለም፡፡ የወዳጅነት ጨዋታ የግድ ያስፈልገናል፡፡ ለምሳሌ በአዛም በነበርኩበት ጊዜ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄጄ ከቢድቬዝት ጋር ከመጫወታችን በፊት ወደ ዛምቢያ ሄደን ከዜስኮና ዛናኮ ጋር ተጫወትን፡፡ በጣም ነው የጠቀመን ምክንያቱም ሁለቱም ክለቦች በየዓመቱ የካፍ ውድድሮች ላይ የማይጠፉ ክለቦች ናቸው፡፡ አንድ ዓመት ቀድሞ ደግሞ ወደ ኬንያ ሄደን ተስከርና ጎርማህያን ገጠምን፡፡ ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ጨዋታዎችማ በጣም ነው የሚጠቅሙት፡፡

ሀትሪክ ፦ዘንድሮ የወዳጅነት ጨዋታ ይኖራል ማለት ነው?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ መኖር አለበት፤ ተጫዋቾችህ ኢንተርናሽናል ጨዋታ የተለየ ነገር እንዳለው ማወቅ አለባቸው

ሀትሪክ ፦ከሽሬ ጋር የተጫወቱ እለት ቡድኑ ሲያሟሙቅ በደጋፊው ተደምመው እጆትን በአፍዎ አድርገው በአግራሞት ሲመለከቱ ነበር፡፡ ደጋፊውን እንዴት አገኙት?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ በርግጥ እጄን አፌ ላይ ሳደርግ የሆነ የማስበው ነገር አለ ማለት ነው፤ ደጋፊው በጣም ድንቅ ነው፤ የማይታመን፣ እጅግ በጣም ልዩ ነው፡፡ ከተጫዋቾቹ ጋር ስለደጋፊው እያወራሁ ነበር፤ አንዳንዶቹ ይፈሩታል አንዳንዶቹ ደግሞ ይወዱታል፡፡ እርግጥ ነው ደጋፊ ጫና ነው፡፡ ነገር ግን ደግሞ እንደ ጊዮርጊስ አይነት ደጋፊ ሲኖርህ 12ኛ ተጫዋች ማለት ናቸው፤ በአግባቡ ካልያዝከውም እንዲያው ለተቃራኒ 12ኛ ተጫዋች ማለት ነው፡፡ ለተጫዋቾቼ ምን አልኳቸው መሰለህ እነዚህ ሁሉ ሰዎች እናንተን ብለው ነው የመጡት ለናንተ እንደ 12ኛ ሰው ናቸው፡፡ ልታስደስቷቸው ልታከብሯቸው ይገባል፡፡ ስለዚህ ምላሹ ጨዋታውን በፍጥነት ጀምራችሁ በኃይል ማጥቃት ይበልጥ ጎል መራባችሁን በተደጋጋሚ ማሳየት፤ “ዛሬ በጣም ርቦኛል” “ዛሬ በጣም ርቦኛል” “Today I am hungry” የሚለውን ምልክት ካሳያችኋቸው ለናንተ 12ኛ ናቸው ማለት ነው፡፡ ነገር ጨዋታውን ቀዝቅዛችሁ ጀምራችሁ ቀርፋፋ ጨዋታ የምትጫወቱ ከሆነ ደጋፊው እናንተ ላይ ይነሳል፤ እሱ ደግሞ የባሰ አደጋ ነው ያልኳቸው፡፡


ሀትሪክ ፦በቅርቡ የሸገር ደርቢ በቅዱስ ጊርጊስና በቡና መካከል ይደረጋል፤ ለመሆኑ ስለዚ ደርቢ ሰምተው ያውቃሉ?

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ አዎን ዲቪዲዎችን አይቻለሁ፤ ከሰውም ሰምቻለሁ። ነገር ግን እኔ ያደግኩበት ከተማ በጣም ትልቅ ደርቢ አለ፤ ሁለቱም ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ በነበሩበት ወቅት የበርሚንግሃም ሲቲና የአስቶንቪላ ደርቢ፤ ኬንያ ስትመጣ የናይሮቢ ደርቢ ጎርማህያና ከሌዎፓርድስ እንዲሁም የዳሬሰላም ደርቢ ያንጋና አዛም ሲጫወቱ ሃምሳ ሚሊዮን ሕዝብ የሚይዝ ስታዲየም ጠጠር መጣያ የለውም፡፡ ደርቢውን ለማጣጣል ሳይሆን እዚ ብቻ አለመሆኑን ለመናገር ፈልጌ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ደርቢ በጣም ትልቅ ደርቢ እንደሆነ ሰምቻለሁ፤ ነገር ግን ደርቢ የትም ቦታ ደርቢ ነው፡፡

ሀትሪክ ፦በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ ለርስዎ ዕድሉን ልስጥና እናብቃ

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ በኔ የአመራር ፍልስፋና አሁንም ሂደት ላይ ነን፤ በትክክለኛ መንገድ ላይ እንደሆንን ግን መናገር እፈልጋለው። በጉዞ ላይ ነን ከ A ተነስተን ወደ B እየተጓዝን ነው፡፡ ይህ ጉዞ ጊዜ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ የምንችለውን ሁሉ እያረግን ነው፡፡ በየጨዋታው ሶሥት ነጥቦችን ማግኘት እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን ወዲያው ማድረግ አንችልም እግር ኳስ ኤሌክትሪክ አይደለም በማብሪያና ማጥፊያ መቆጣጠር አይቻልም፡፡ ጠንካራ ሥራ ይጠይቃል ጠንክረን እየሰራን ነው፡፡ እርግጠኛ ነኝ ውጤታማ እንሆናለን፡፡

ሀትሪክ ፦በድጋሚ በአንባቢዎቻችን ስም ግብዣችንን ተቀብለው እንግዳ ለመሆን ስለፈቀዱ ጊዜ ሰጥተው ጥያቄዎቻችንን ስለመለሱልን ከልብ እናመሰግናለን

አሠልጣኝ ስቱዋርት ጆን፦ እኔም አመሰግናለሁ፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ሠፊ ቃለ-ምልልስ ከእናንተ ጋር በማድረጌ።

Photo source:- Hatricksport archives 

                      -capitalfm kenya website

                      -Google 

You Might Also Like

የቅዱስ ጊዮርጊስ የቦርድ አመራሮች ከሀላፊነት ለመነሳት ፍቃደኛ ሆኑ

ወላይታ ድቻ የሊጉን መሪ አሸንፏል

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአማካዩ ጋር ተለያየ

መቻል እና ወልዋል ሲያሸንፉ የሀዋሳ ጨዋታዎች በአቻ ተጠናቀዋል

አቤል ያለው እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊለያዩ ነው

Share this Article
Facebook Twitter Email Print
By Teshome Fantahun
Follow:
Editor at Hatricksport
Previous Article የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የመከላከያ ና ወላይታ ድቻ ጨዋታ ላይ የቀን ለውጥ እደረገ
Next Article የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተስተካካይ ጨዋታዎችን ፕሮግራም ይፋ አደረገ

Follow US

Find US on Social Medias
127k Like
2.9k Follow
1.6k Follow
19.7k Follow

Weekly Newsletter

Subscribe to our newsletter to get our newest articles instantly!

ተነባቢ ዜናዎች
ዜናዎችመከላከያየጨዋታ ዘገባቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግኢትዮጵያ ቡና

የጨዋታ ዘገባ | መከላከያ ኢትዮጵያ ቡናን በሰፊ ውጤት አሸንፏል

Habtamu Mitku By Habtamu Mitku 4 years ago
11ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ኘሪሜየር ሊግ 6 ጨዋታዎችን /LIVESCORE/
ቢንያም በላይ የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል እግርኳስ ተጫዋቾች ማህበር የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ዘርፍ አሸናፊ ሆነ
ለካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት ፍክክር ኢትዮጵያ አቶ ጁነዲን ባሻህ በመጨረሻው ሠዓት ራሳቸውን ከፉክክሩ ዉጪ(ሪዛይን) አርገዋል
ኢትዮጵያ መድን ከአሰልጣኙ ጋር በስምምነት ተለያይቷል
- Advertisement -
Ad imageAd image
Global Coronavirus Cases

Confirmed

0

Death

0

More Information:Covid-19 Statistics
about us

Phone: 0993808668 Email: [email protected] .

Find Us on Socials

© Hatrick Sport 2023 All Rights Reserved.

Removed from reading list

Undo
 

Loading Comments...
 

    Welcome Back!

    Sign in to your account

    Lost your password?