የሩብ ፍፃሜውን ለመቀላቀል ዛሬም በቀጣይ ጨዋታዎችም ጠንካራ ፍልሚያ እናደርጋለን
አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ
የቅዱስ ጊዮርጊስና የኤ ኤስ ቪታ የቻምፒየንስ ሊጉ ተጠባቂ ጨዋታ ዛሬ በ12 ሰዓት በዲሞክራቲክ ኮንጎ ይካሄዳል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ለእዚህም ጨዋታ እሁድ ዕለት 18 ተጨዋቾችን ይዞ የተጓዘ ሲሆን ወደ ስፍራው ከማምራታቸውም በፊት ቅዳሜ በነበረው የቡድኑ ልምምድ ላይ ደጋፊዎች
ያዘጋጁትን ኬክ በማስቆረስና ሻምፓኝ በማስከፈት የአሸኛኘት ፕሮግራም ሊያደርጉላቸውም ችለዋል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎው የእስካሁኑ ፍልሚያ ከደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውንስና ከቱኒዚያው ኤስፔራንስ ጋር 0-0 ከተለያየ በኃላ የዲሞክራቲክ ኮንጎውን ኤ ኤስ ቪታን በሳላህዲን ሰይድ ብቸኛ ግብ 1-0 በማሸነፍ ከምድቡ ኤስፔራንስን ተከትሎ የሁለተኛ ስፍራ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ወደ ተከታዮ ዙር የሚያልፍበትን ዕድል ለማመቻቸትም ዛሬ የሚያደርገው ጨዋታ ላይ እንደዚሁም ለቀጣይ ግጥሚያዎቹ በሚገባ መዘጋጀታቸውን የቡድኑ አሰልጣኝ ከሆኑት ውስጥ አንዱ ዘሪሁን ሸንገታ ለሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ ድህረ-ገጽ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን በማሰልጠን የሚገኘው ዘሪሁን ስለ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎአቸው ዛሬ ስላለባቸው ጨዋታ ወደ ሩብ ፍፃሜው ለማለፍ ስላላቸው ዕድልና ስለደጋፊዎቻቸው አጠር ባለ መልኩ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
ስለ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎአቸው
የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የእዚህ ዓመት የምድብ ድልድል ጨዋታችንን ምንም እንኳን ከጠንካራ እና ከባድ ቡድኖች ጋር ተመድበን ብናደርግም እያሳየን ያለው እንቅስቃሴ እና ውጤታችን ጥሩ የሚባል ነው፡፡ በተሳትፎአችን የራሳችንን ጠንካራ እና ክፍተት ጎንም አይተናል
ጥሩ ጎናችን ግን ያመዝናል ስለዚህም በእዚያ ጉዞ ውስጥ መቆም ሳይሆን ወደፊት ተጉዘን ጥሩ ውጤት ለማምጣት ተዘጋጅተናል፡፡
ከኤ ኤስ ቪታ ጋር ዛሬ ስለሚያደርጉት ጨዋታ
የውድድሩ ተሳትፎአችን ላይ እኛ ለዛሬው ጨዋታ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ግጥሚያ ነው እየተዘጋጀን ያለነው ዛሬ የምንፋለመው ቪታም ምንም እንኳን ሶስቱን ግጥሚያዎች የተሸነፈ ቢሆንም ጠንካራ እና ጥሩ ቡድን ነው ለእዚህ ጨዋታም ስለ እነሱ አቋም ከተመለከትነው እና ከእኛም ጋር ሲጫወቱ ካየነው ነገር በመነሳት ለጨዋታው በአህምሮም በአካልም በሚገባ ተዘጋጅተናል የጨዋታው አሸናፊ ለመሆንም ነው እያሰብንም ያለነው፡፡
ወደ ተከታዩ ዙር ስለማለፍ
የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ላይ የእኛ የሁልጊዜ ተሳትፎ ወደ ተከታዩ ዙር ማለትም ወደ ሩብ ፍፃሜው የምናልፍበትን እድል ማሳካት መቻል ነው ዘንድሮ ካለን አካሄድና ጥንካሬ አንፃርም ያንን እልም የምናሳካው ይመስለኛል፡፡
ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች
የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ለእኛ ሁሌም ልዩ ናቸው ዘንድሮ ደግሞ ለየት ባለና አስደናቂ በሆነ ሁኔታ እየደገፉን ይገኛል በእዚህ ሁኔታም ክለባችን ውስጥ ያለው ስሜትም ደስ ይላል ደጋፊዎቻችን እንደ 12ኛ ተጨዋች ሆነውም ጫካ ሜዳዎች ላይም ሆነ የትም ሄድን ጥሩ ድጋፍን ሲሰጡንም ነበሩ ደጋፊዎቻችን ቀኝ እጆቻችን ናቸው ያም ስለሆነ በእኛ የኮቺንግ ስታፍ በቦርዱ እና በተጨዋቾቹም የሚከበሩና የሚደነቁም ስለሆነ ላመሰግናቸው እፈልጋለው፡፡እኛም በምላሹ በውጤት ልናስደስታቸውም ዝግጁ ሆነናል፡፡

አስተያየት ይስጡ