
በተሾመ ፋንታሁን
ፈረንሣዊው አሰልጣኝ ዲዲዮ ጎሜዝ ዳ ሮሳ የቡናዎቹ አሰልጣኝ ከሆኑ ሁለተኛ አመታቸውን አስቆጥረዋል፡
፡ በሁለት አመት የቡና ቆይታቸው የነገውን ኢትዮጵያ ቡናን ለመገንባት ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ
በተጨማሪተማውን ዋንጫ ከፍ አድርገው በማንሣት አዲሱን የውድደር አመት በድል ጀምረዋል፡፡ የሀትሪክ
ጋዜጣና የሀትሪክ ድረ ገፅ ተባባሪ አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ተሾመ ፋንታሁን የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በሆነው
ፈረንሣይኛ በማነጋገር የውስጣቸውን ምስጢር አዘክዝኳቸዋል፡፡ ከሶስትና አራት አሰልጣኝ ስንብት በኋላ
በአሰልጣኝነት ወንበሩ ላይ ተደላድለው የተቀመጡት አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜዝ ዳ ሮሳ በክለቡ ወቅታዊ ጉዳዮች
ዙሪያ ከዚህ በታች ያለውን ቃለ ምልልስ በተለይ ለሀትሪክ ጋዜጣ (Exclusive) ለመጀመሪያ ጊዜ ሰጥተዋል፡
፡ አብራችሁን ሁኑ
ሀትሪክ፡-በቅድሚያ የሀትሪክ ጋዜጣ
አንባቢያንና የዝግጅት ክፍላችንን በማክበር
ለቃለ-ምልልሱ ፍቃደኛ ስለሆኑልን ከልብ
እናመሰግናለን….?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- … እኔም በጣም
አመሰግናለሁ፤ እንግዳ ስላደረጋችሁኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ….ስለ ግልህ ህይወትዎ…
ስለቤተሰብዎ ያውሩኝ እስቲ… ?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- ባለትዳርና የአንዲት
ሴት ልጅ አባት ነኝ፤ ቤተሰቦቼ የሚኖሩት
ፈረንሣይ ውስጥ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-ስለ እግር ኳስ ተጨዋችነት
ህይወትዎስ ምን ይመስላል…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- …በጣም ደስ
ይለኛል…! እግር ኳስን ከሰፈር፣ ከአካባቢ ባለፈ
በፕሮፌሽናልነት ደረጃ መጫወት የጀመርኩት
ፈረንሣይ ውስጥ ትልቅ ስምና ታሪክ ካላቸው
ክለቦች አንዱ በሆነው ኒስ (Nice) እግር
ኳስ ክለብ ውስጥ ነው፤ በዚህ ክለብ ውስጥ
ረዥም አመት የመጫወት ከፍ ወደአለ ደረጃ
የመሸጋገር ትልቅ ህልም ቢኖረኝም ወደ
ሃያ አመቴ አካባቢ የገጠመኝ ከፍተኛ ጉዳት
በዚህ ደረጃ ብዙ ርቀት እንዳልጓዝ እንቅፋት
ፈጥሮብኛል፡፡ የገጠመኝ ጉዳት ከፍተኛ የባት
መሰንጠቅ መሆኑ እንዳልኩህ ረዥሙ ህልሜ
በአጭር እንዲቀር ምክንያት ሆኖኛል፡፡
ሀትሪክ፡-…ማለት በዚህ ጉዳት ምክንያት
ከእግር ኳስ ጋር ተቆራረጡ፤አቆሙ ማለት
ነው፤.. ?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡-…አይ…!…በፍፁም
አላቆምኩም…፤ግን ጉዳቱ በጣም ብዙ
ተፈታትኖኝ ነበር፡፡ በፕሮፌሽናልነትም ብቁ
ርቀት እንዳልጓዝ ቀላል የማይባል ተፅዕኖ
አድርሶብኛል፤ ምክንያቱም የባት መሰንጠቅ
ጉዳት በትንሹ 10 ወይም 14 ወራትን
ከእግር ኳስ አንድትርቅ የሚያደርግ የጉዳት
አይነት በመሆኑ እግር ኳስን በፕሮፌሽናልነት
እንዳልጫወት አድርጎኛል፡፡ ያም ቢሆን ግን
ከእግር ኳስ ጨክኜ አልራኩም፤የፕሮፌሻልነት
ህልሜ በዚህ ምክንያት ሣንካ ስለገጠመው
ፊቴን ወደ Semi proffessionsal (መካከለኛ
ፕሮፌሽናልነት) አዞርኩ፡፡
ሀትሪክ፡- …ማለት ወደ… ሌላ ክለብ …
ተዛወሩ…ማለት…ነው…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡-…ከሙሉ ሰዓት (Full
time) ተጨዋችነት ወደ ሰሚ ፕሮፌሽናልነት
ፊቴን አዞርኩ፤ ማለት ጠዋት ጠዋት ኳስ
እየተጫወትኩ ከሰዓት ከሰዓት ደግሞ ሌላ
ገቢ የማገኝበት ሥራን እየሠራሁ። ይሄን
ሁሉ የማደርገው ከህመሜ ጋር እየታገልኩ
ነበር፤ ነገር ግን ጉዳቱ ጨክኖብኝ ብዙ ርቀት
እንዳልጓዝ ከመንገድ አስቀርቶኛል፡፡
ሀትሪክ፡- …ግን…አሰልጣኝ ዲዲዬ.. ምን
አይነት ተጨዋች ነበር…? አማካይ…? ወይስ
አጥቂ ተጨዋች …?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡-…አንተ በጥያቄ
ካነሣሃቸው ከሁለቱም ውጪ ግብ ጠባቂ
ነበርኩ፤ግብ ጠባቂ ሆነህ ከባት ጉዳት ጋር
እየታገልክ በብቃት ማገልገል ከባድ መሆኑ
ነው ህልሜን እንዳላሳካ ያደረገኝ፤ ጉዳት በዚህ
ደረጃ ባይፈታተነኝ ኖሮ በፕሮፌሽናልነት ብዙ
ርቀት እጓዝ ነበር ብዬ አስባለሁ፤ነገር ግን
አልሆነም፡፡
ሀትሪክ፡- …ጉዳቱ…ከእግር ኳስ ጋር
ካቆራረጥዎት በኋላ ወዴት አመሩ..?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- …እንዳልኩህ…
የገጠመኝ ጉዳት የጠነከረ በመሆኑ ሌላ
አማራጭ ማየት ነበረብኝ፤ አጋጣሚው
የእግዚአብሔር ትዕዛዝ በመሆኑም መቀበልና
በፍጥነት ፊቴን ወደ ሌላ ነገር ማዞር ነበረብኝ፡
፡ አንደኛው በር ሲዘጋብህ ሌላኛው በር
ይከፈትልሃል፤ ከምወደው እግር ኳስ ጨክኜ
መራቅ ባለመቻሌ በጊዜ የአልጣኝነት ዓለምን
ተቀላቀልኩ፤ ይሄው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ
ሙያዬ አገር አቋርጦ ኢትዮጵያ አድርሶኛል፡፡
ሀትሪክ፡-…ወዲያው የአሰልጣኝ ሙያ
ኮርስ ገቡ…ማለት ነው…?…የአሰልጣኝነት
ትምህርትዎስ ምን ይመስላል?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- የሚገርምህ ራሴን
በትምህርት ለማስታጠቅ ሞክሬያለሁ፤ሁሉንም
የአውሮፓ የአሰልጣኝነት ኮርሶችን ጠራርጌ
ወስጅያለሁ፡፡ በፈረንሣይ በቀጥታ አሰልጣኝ
መሆን አይቻልም፤ ብዙ ፕሮሰሶችን ማለፍ
ይጠይቃል፡፡ እኔም ቀስ በቀስ ከU-18 ከአስራ
ስምንት አመት በታች ጀምሬ ወደ U-20
ከሃያ አመት በታች ከዚያ ወደ 6ኛ ዲቪዚዮን
ከብዙ ጥረት በኋላ ደግሞ እስከ ሁለተኛ
ዲቪዚዮን በመድረስ የተጫወትኩበትን የኒስ
(Nice) ሁለተኛ ክለብን እስከማሰልጠን ደረስኩ
፡፡ በመጨረሻም ራሴን በተለየ ፈተና ውስጥ
ለመሞከር ወሰንኩና ፊቴን ወደ አፍሪካ
አዞርኩ፤ ከፈረንሣይ ውጪ ወደ ምስራቅ
አፍሪካዊቷ ሀገር ሩዋንዳ በመጓዝ ከሀገር
ውጪ የስልጠና ሀሁን አንድ ብዬ ጀመርኩ፡፡
ሀትሪክ፡- ወደ አፍሪካ ያውም በእግር ኳስ
በጣም ደካማ ነው በሚል በሚወቀሰው ምስራቅ
አፍሪካ መጥቶ ማሰልጠን የሚለው ውሳኔ
እንዴት ወደ አዕምሮዎት መጣ?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- የሚገርምህ ነገር
ማሰልጠን በራሱ ረዥም ሂደት ነው፤ ይህ
የገባኝ በጣም በልጅነቴ ነው። አሠልጣኝነት
እለት በእለት የምትማርበት ረዥም ሂደት
ነው፤ ፈረንሣይ ውስጥ ያሉትን የአልጣኝነት
ዲፕሎማዎች መጨረስ ብቻውን 7 ወይም
8 ዓመታትን ይፈጃል፡፡ ወደ አፍሪካ ከመጓዜ
በፊት ሁሉንም ነገር የመጨረስ የውዴታ
ግዴታ ነበረብኝ፤ ያንን እስካሁን ምናልባት
ወደ አፍሪካ የመጣሁት በጣም በልጅነቴም
ሊሆን ይችላል፤ግን አፍሪካ ውስጥ መስራት
የተለየ ስሜት እንደሚፈጥር ይሰማኝም ነበር፤
መጥቼ ያየሁትም ያንን ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ
ከፍተኛ ፍላጎት (Passion) አለ፤ በአሰልጣኝና
በተጨዋች መካከል ያለውን ግንኙነት በጣም
ነው የምወደው፤ አፍሪካ ውስጥ ስታሰለጥን
ለልጆቹ ከአሰልጣኝም በላይ ነህ፡፡ ተጨዋቾቹ
ተገቢውን ክብር ይሰጡሃል፤የተሻለ ቦታም
እንደምታደርሳቸው እምነት ይጥሉብሃል፡
፡ አሁን ትናንት (ያነጋገርናቸው ዓርብ
ዕለት ነው) ለምሣሌ ከወጣት ተጨዋቾች
ጋር እያወራሁ ነበር፡፡ እዚህ ክለብ ውስጥ
ያለሁት ዋንጫ ለመሰብሰብ ብቻ አይደለም፤
የእናንተንም ወደፊት የተሻለ ለማድረግ ነው፤
አሰልጣኝነት ሙያዬ ነው ልጆቹን የተሻሉ
ተጨዋቾች ሆነው ከሀገር ውሰጥ አልፈው ወደ
ውጭ ሄደው በፕሮፌሽናልነት የተሻለ ህይወት
እንዲመሩ የበለጠ ትልቅ ተጨዋች እንዲሆኑ
ለማስቻልም ነው እዚሁ የመጣሁበት ምስጢር::
ሀትሪክ፡-… አሁን በሚሉት ደረጃ ላይ ያሉ
ተጨዋቾችን በቡድኑ ውስጥ አይተዋል…?
ማለት የዓለም እግር ኳስ የሚፈልገው ደረጃ
ያላቸው ተጨዋቾች አሉ?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- …በጣም ብዙ…
አሉ…!…ግን ይሄንን… ማሳካት…
የሚቻለው… ጠንክረው ከሰሩ ብቻ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-…አፍሪካ ውስጥ የት የት ሀገር
ሰርተዋል?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- …ከላይ ለመለፅ
ሞክሬያለሁ… መጀመሪያ ወደ አፍሪካ ስመጣ
ያመራሁት ወደ ርዋንዳ ነበር፤በርዋንዳም
የራዮን ስፖርት ክለብ ውስጥ የማይረሣ
ጣፋጭ፣ በውጤትና በስኬት የታጀበ ጊዜን
አሣልፌያለሁ፡፡ ከርዋንዳ ራዮን ስፖርት ክለብ
ጋር ከተለያየሁ በኋላ ወደ ምዕራብ አፍሪካ
በማቅናት ካሜሮን ውስጥ የካሜሮኑን Cotton
sport ን፣ ወደ ሰሜን የአህጉሪቱ ክፍል
በመሄድ ደግሞ የአልጄሪያውን ኮንስታንቲንን
አሁን ደግሞ ወደ ምስራቅ አፍሪካ በመመለስ
ታላቁን ኢትዮጵያ ቡናንን በማሰልጠን
እያሳለፈኩ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በሩዋንዳ ከራዮን ስፖርት ጋር
ስለነበርዎት አስደሳች ቆይታ አውርተው
እንደማይጠግቡ ሰምቻለሁኝ፤ እስቲ ስለ ራዮን
ስፖርት አጫውቱኝ… ?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- …እውነቱን ንገረኝ
ካልከኝ… ለኢትዮጵያ ቡናና ለርዋንዳው
ራዮን ስፖርት ልዩ ፍቅር አለኝ፤ በርዋንዳ
የመጀመሪያ ሃገሬን ሁሉ ያገኘሁበት፣
ተዓምር ያየሁበት ክለብ ነው፡፡ ተዓምር
ያየሁበት ያልኩህ እኔ ወደ ርዋንዳ ስመጣ
ራዮን ስፖርት በዝቅተኛ ደረጃና ውጤት ላይ
የነበረ ነገር ግን እጅግ ተሻሽሎ ከፍተኛ ለውጥ
በማምጣት የሀገሪቱ ክለቦች ሻምፒዮናና የጥሎ
ማለፍ ባለቤትነት ክብር የበቃ ብቻ ሁሉንም
ስኬቶችን ያጣጣምኩበት ክለቤ ነው፡፡ በርዋንዳ
በአጠቃላይ የአንድ አመት ተኩል ጊዜን
አሣልፌያለሁ፤ግን ደግሞ ከቆይታም የገዘፈ
ትዝታና ታሪክን አትርፌበታለሁኝ፤ ራዮን
ስፖርትና ርዋንዳ ሁሌም በልቤ ውስጥ አሉ፤
አንድ ቀን እመለስና ሌላ ጣፋጭ ጊዜያትን
በጋራ እናሳልፍ ይሆናል፡፡
ሀትሪክ፡- …አፍሪካን ለበርካታ ዓመታት
ያገለገሉ… እንደ ክሎድ ለሩዋ አይነት
ፈረንሣዊያን አሰልጣኞች በፍፁም አፍሪካን
መልቀቅ አይፈልጉም፤ እርስዎስስ ቀጣይ
ሃሳብዎ ምንድ ነው…? …አንድ ቀን… ወደ
ፈረንሣይ… ተመልሶ የማሰልጠን… ፍላጎት
ውስጥዎ… አለ…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- …በፍፁም…! …
ወደ ፈረንሣይ የመመለስ ፍላጎት የለኝም…
፤እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ በፈረንሣይ
በተጨዋቾችና በአሰልጣኝ መካከል ያለውን
ግንኙነት በፍፁም አልወደውም፡፡ ከዚህ
በተጨማሪ አፍሪካ ውስጥ ስትሰራ አሰልጣኝ
ብቻ አይደለህም የተጫዋቾችን ህይወት
ለመለወጥ የምትሠራ (Life constructor)ም
ነህ፤ ነገ የተሻለ ህይወት ለመኖር የተሻለ ሀገር
ሄዶ ለመጫወት የሚፈልጉ ከፍተኛ ጉጉት
ያላቸው ተጨዋቾች ጋር ነው የምትሰራው፤
ይሄ ብቻውን በራሱ በጣም የሚያስደስት ነገር
ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …በዚህ ዙሪያ ከመደሰት…
ከሃሳብ… በዘለለ ተጫዋቾቹን ምን
ይሏቸዋል…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- …የሚገርምህ…በዚህ ዙሪያ… ለተጨዋቾቼ ከመንገር ቦዝኜ
አላውቅም፤ ለተጨዋቾቼ ስልጠና ላይና
ባገኘሁት አጋጣሚ እነግራቸዋለሁ፡፡
በደንብ ጠንክራችሁ ሥራ ነገ ከሀገር
ውስጥ ክለቦች አልፋችሁ
በአውሮፓ፣ በደቡብ አፍሪካ፣
በአልጄሪያ፣ በሞሮኮና በግብፅ
ልትጫወቱ የምትችሉበት
እድል አላችሁ ብዬ ሁሌም
እመክራቸዋለሁ፤አስጠነቅቃቸዋለሁም፡
፡ እኔን ከምንም ነገር በላይ
የሚያስደስተኝም
ይሄው ነው፤
ለዚህም ነው
አፍሪካ
ውስጥ
መስራት
ይበልጥ
የሚያስደስተኝ፡፡
እንዳልኩህ ነው ሁሌም ከአፍሪካዊያን
ተጨዋቾች ጋር መስራት የእነሱንም ህይወት
ከፍ ወደአለ ደረጃ እንዲሸጋገር ማገዝ
ያስደስተኛል፡፡ እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ ሁሌም
ቢሆን አፍሪካ ውስጥ ማሰልጠን አውሮፓ
ውስጥ ከማሰልጠን የበለጠ አስደሳች ነው፡፡

ሀትሪክ፡- …በዚህ ዙርያ ከተነሣ አይቀር…
ፈረንሣዊያን በአፍሪካ በተለይ በምስራቅ አፍሪካ
ላይ እያሳደሩ የመጡትን እምነትና የመስራት
ፍላጎት እንዴት ያዩታል? እርስዎ ኢትዮጵያ
ሌሎቹ ኬንያና ኡጋንዳ ከመሆናቸው አንፃር?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡-…ሳቅ…እንዳልከው
ፈረንሣዊያን ወደ አፍሪካ ቀንድ በዛ እያልን
የመጣን ይመስለኛል፤ ሰባስቲያን ሜኜ (ኬንያ)፣
ሰባስቲያን ደሳብር (ኡጋንዳ) እኔ ደግሞ እዚህ
ኢትዮጵያ፤ ከዚህ አንፃር ቁጥራችን ጨመር
ያለ ይመስላል፡፡ የሚገርምህ ብዙ ፈረንሣዊያን
ወደዚህ ቀጠና የመምጣት ከፍተኛ ፍላጎት
እንዳላቸው ስለማውቅ ቁጥራቸው ከዚህም
ሊጨመር ይችላል፡፡
ሀትሪክ፡-…እኮ…የዚህ ምክንያቱ…
ምንድነው ማለት ይቻላል… ?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- …ዋናውና ትልቁ
ነገር የምስራቅ አፍሪካ እግር
ኳስ በጣም ስርዓት ያለው
(Disciplined) መሆኑ
ነው፤ ሌላኛው ምክንያት
ደግሞ የወደፊት የእግር
ኳስ ከፍተኛ አቋም
ያለበት ቀጠናም በመሆኑ
ነው፡፡ እውነቴን ነው
የምልህ በዚህ ቀጠና
የሚገርም ብቃት
ያላቸው ተጨዋቾች
አሉ፤ ይሄ ነገር
የብዙ ፈረንሣዊያንን
ጉጉት የጨመረው
ይመስለኛል፡፡
አሁን ራሱ በርካታ
ፈረንሣዊያን “ምስራቅ
አፍሪካ ላይ መስራት
ምን ይመስላል?”
እያሉ ይጠይቁኛል፤
ፈረንሣይ ውስጥ
እንደለመዳችሁት
ሁሉም ነገር
ቀላል አይደለም
እላቸዋለሁ፤
ደግሞም እውነቴን
ነው ነገሮች ሁሉ
ቀላል ወይም አልጋ
በአልጋ አይደለም፤
ነገር ግን በጣም
አስደሳች ነው፡፡
ሀትሪክ፡
– …ከምስራቅ
አፍሪካ… በተለይ…
ኢትዮጵያ ውስጥ…
መስራትስ…?
አሰልጣኝ
ዲዲዬ፡
-የሚገርምህ
ነገር ኢትዮጵያ
ውስጥ
መስራትን
ስመኝ
የነበረው አሁን
አልነበረም፤ ከረዥም ጊዜ
ጀምሮ ወደዚህች የአሀጉሪቱ እግር
ኳስ መስራችና የአፍሪካ ዋና
ከተማ መጥቶ የመስራት ምኞቱ
ነበረኝ፡፡ በምስራቅ አፍሪካ በተለይ
በኢትዮጵያ በጣም አስደሳች የሥራ
ጊዜን እያሳለፍኩ ነው፤በበኩሌ
በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ
ከመጣሁ በኋላ ብዙ የአሰልጥንልን
ጥያቄዎች ቀርበውልኛል፤ ነገር ግን
በቡና በጣም ደስተኛ ነኝ፤ በቡናም
የጀመርኩት ሥራ አለኝ፤ ገና
ብዙም መስራት እፈልጋለሁኝ፡፡
ሀትሪክ፡- …እስቲ ወደ
ኢትዮጵያ ቡና እንዴት
መጡ?…፤…ስለ ክለቡ ቀደም
ሲል መረጃውስ ነበርዎት…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- …
ኢትዮጵያ ቡናን… የማውቀው
በፊትም ነው…፤ …ቡና የሀገሪቱ
ትልቅ ክለብ፣ የበርካታ ደጋፊዎች
ባለቤት እንደሆነም መረጃው
ነበረኝ፡፡ በተለይ ስለደጋፊው
ብዙ መልካም ነገሮችን ብሰማም
በዚህ ደረጃ ስታዲየሙን ሞልቶ
ክለቡን የሚደግፍ የተለየ ድምቀት
ያለው ደጋፊ መሆኑን ስመጣ
አይቼ ይበልጥ ተገርሜያለሁ፡፡
አሰልጣኝ ስትሆን የት ሀገር ምን
እንዳለ? ማን ምን አይነት ክለብና
ደጋፊ እንዳለው ትሰማለህ፤ ስለ
ኢትዮጵያ እግር ኳስ ስሰማ ስለ
ቡና፣ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ደደቢት
የምሰማቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ በዚህ
ሁኔታ ውስጥ እያለሁ ቡና ጥያቄ ሲያቀርብልኝ
ሁለቴ ማሰብን አልፈለኩም፤ወዲያውኑ ነው
እሺታዬን የገለፅኩት፤ምክያቱም ይሄን ታላቅ
ክለብ ማሰልጠን የማይፈልግ የለም፤ በአጭሩ
ምርጫዬ ልክ ነው፤ በጣምም ተመችቶኛል፡፡
ሀትሪክ፡- …ኢትዮጵያ ቡናዎችም… አንተ
የተመቸሃቸው ይመስላል…፤ ቀሪ የአንድ
አመት ኮንትራት እያልዎት የሁለት አመት
ኮንትራት በመፈረም ውልዎን አራዝመዋልና
ይሄስ ምን ስሜት ፈጠረብዎ…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- …ይህ መሆኑ…
ከፍተኛ የራስ መተማመን በውስጤ
እንዲፈጠር አድርጓል፤ በራስ የመተማመን
ስሜትን ከፍ ማድረግ አንደ አሰልጣኝ
የተሻለ ነገር እንድሰራ ያደርገዋል፡፡ ቡናዎች
ለጣሉብኝ ኃለፊነትና ላስደሩብኝ እምነት
በጣም ነው የማመሰግናቸው፤ የክለቡን
የቦርድ ፕሬዚዳንት፣ የቦርዱን አባላት፣
የደጋፊውን ማህበርና በአጠቃላይ በቡናማው
ማልያ ሥር ያሉትን ደጋፊዎች በሙሉ ከልቤ
አመሰግናቸዋለሁ፡፡ አንድ ተጨዋች ወደ ሜዳ
ሲገባ በራስ የመተማመን ስሜቱን ከፍ ማድረግ
እንደሚያስፈልገው ሁሉ አሰልጣኝም ይሄንን
ይፈልጋል፤ ቡናዎች ይሄንን ተረድተው
ስለጣለብኝ እምነት ባለእድል ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ከላይ አንስተውት ነበር ወደ
ቡና ከመጡ በኋላ የበርካታ ሀገሮች ጥያቄ
ቀርቦሎት ነበር የሚባለው እውነትነት
አለው…? …ከሆነስ… ለምን ጥያቄውን…
ሣይቀበሉ ቀሩ…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- …እውነት ለመናገር…
ብዙ የሥራ እድሎችን ገፍቻለሁ፤ የተለየ
ስሜት ለመፍጠር አይደለም… ከኬንያ፣
ከታንዛኒያ፣ ከአልጄሪያ፣ ከሊቢያ፣ ከሞሮኮና
ከደቡብ አፍሪካ ደግሞ የቴክኒክ ዳይሬክተርነት
ሥራ እድል ሁሉ ቀርቦልኝ ነበር፤ ነገር ግን
ለቃሌና ለሥራዬ ታማኝ በመሆኔ ለጥያቄዎቹ
ጀርባዬን ሰጥቻለሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ
በቡና መሥራት የምፈልጋቸው ብዙ ሥራዎች
አሉ፤ በቡና ይሄን ለማድረግ አሁን በጣም
በቂ ጊዜ አለኝ 3 የሥራ አመታት፤ የቦርዱ
ፕሬዚዳንት ፍላጎቴን ማሟላት የምችልበት
ተጨማሪ አመታት ከፊቴ እንዳለ ሲነግሩኝ
በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ምክንያቱም ብዙ
መስራት ስለምፈልግ፡፡
ሀትሪክ፡- …የኢትዮጵያ እግር ኳስ…
አየር… ከውጪ መጥቶ…ለሚያሰለጥን
አሰልጣኝ…ተስማሚ ነው…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- …በሌላ ሀገር
በነበርኩባቸው በርዋንዳ፣ በአልጄሪያ ያላየሁት
ፍላጎት (Passion) ኢትዮጵያ ውስጥ አለ፤
ኢትዮጵያ ውስጥ ፀጥ ያለ የሥራ መንፈስ
(Serenity) አለ፡፡ ስለዚህ በዚህ ዝምታ ውሰጥ
ብዙ የምንሰራው ሥራ አለ፡፡ ቡና ውስጥ በግል
ብቃት ከፍተኛ አቅም ያላቸው ልጆች አሉ፤
እነዚህን ልጆች እንዳግዝ ቡና ለሰጠኝ እድል
ደግሜ ማመስገን እወዳለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …አምና ኢትዮጵያ ቡናን…
በይፋ ሲቀላቀሉ… ከእርስዎ በፊት… ሶስትና
አራት አሰልጣኞችን ቀያይሮ ነበር፤ …
የያዙት ቡድንም የእርስዎ ስብስብ የሚባልም
አልነበረም፤ዘንድሮስ ከእርስዎ አጨዋወትና
ፍልስፍና ጋር የሚሄድ ቡድን ነው የገነቡት…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- …በእርግጥ… ሁለትና
ሶስት… የሚሆኑ ወጣት ተጨዋቾችን…
ከማጣቴ ውጪ የምፈልጋቸውን ተጨዋቾች
አግኝቼያለሁ…፤ …የቦርዱ ሰብሳቢም የቻሉትን
ድጋፍ ሁሉ አድርገውልኝ የምፈልጋቸውን
ተጨዋቾች አምጥቻለሁኛል፡፡ ከዚህ አንፃር
የዘንድሮው የቡና ስብስብ ከአምናው የተሻለ
ነው፤ የክለባችን ስብስብ በወጣት ተጨዋቾች
የተሞላ ነው ማለትም እችላለሁ፡፡ ምክንያቱም
የክለባችን ተጨዋቾት አማካይ እድሜ 21.5
ዓመት ነው፤ በዚህ ደረጃ መዋቀሩ ቀጣይና
የማይቆም ህልም ላለው ክለብ በጣም አስፈላጊ
ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ተስፋ ያለው፣ እግር ኳሱን
በበላይነት የሚቆጣጠር ክለብ እንሆናለን፡፡
ሀትሪክ፡- …እግር ኳስን… በበላይነት
የሚቆጣጠር… ክለብ ሲሉ…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- …አማካይ እድሜ
21.5… የዛሬ ሣይሆን የነገ ክለብ ነው…፤…
በእርግጠኘነት አሸናፊ ክለብ እንሰራለን፤ እንደ
አማኑኤል አይነት ተጨዋችን አቆይተህ፣
ልምድ ያላቸውን እንደ ካሉሻ አይነቶችን
ጨምረህ፣ ወንድይፍራውን ቶማስ፣ ካስትሮ
አይነት ልምድ ያላቸውን እንደሚኪ፣ አቡበከር
አይነት ወጣቶችን ይዘህ ምርጥ ውጤታማ
ቡድን ትገነባለህ፡፡
ሀትሪክ፡- …የዘንድሮው ስብስብ…
ከአምናው… በምን ይለያል…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- …ብዙ ልዩነት
አለው…፤ …የዘንድሮው ቡድን ከአምናው
በፍጥነት፣ በቅልጥፍና፣ እንዲሁም
በአግሬሲቭነት ከአምናው በጣም የተሻለ ነው፤
እንደ ዳንኤል፣ ካስትሮ፣ አህመድ (ሽሪላ)
ተካልኝ አይነት ታጋዮች፤ ሽንፈትን የማይወድ
ባህሪ ያላቸው ተጨዋቾች በጣም አስፈላጊዎች
ናቸው፡፡ ቡና ሁልጊዜም መሸነፍ የማይፈልግ
ደጋፊ ባለቤት ነው፡፡ ይሄ የደጋፊው ሽንፈትን
ያለመፈለግ ባህሪ ተጨዋቾቻችንም ላይ
ካልተጋባ ዋጋ አይኖረውም፤ የዚህ አይነት
ባህሪ ያላቸው ተጨዋቾች ካሉህ ዋንጫ አንስቶ
መሣም ብዙም ከባድ አይሆንም የሚል እምነት
ነው ያለኝ፡፡
ሀትሪክ፡- …በአዲስ መልክ የተገነባ…
በሚመስለው ቡድን… የሲቲ ካፑን ድል
አጣጥማችኋል፤ ድሉን እንዴት አገኙት…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- በተለይ ለዚህ ታላቅ
ደጋፊ ድሉ በጣም ጥሩ ነው፤ ይህ ደጋፊ
በዓለም ላይ ያለ ድል ሁሉ ያንሰዋል፡፡ ድሉ
ደስታን የሚፈጥር ቢሆንም ተጨዋቾቹ
ግን ይሄንን ድል እንደመጨረሻ ድልና
ግብ ቆጥረው መዘናጋት የለባቸው፤ የሲቲ
ካፑ ድል ከክብሩ በላይ ራሳችንን በደንብ
እንድናይ ጥሩ እድል ሰጥቶናል፤ ከጥሩ
ጎናችን ባልተናነሰ ብዙ ታክቲካል ሥህተቶችን
አይተንበታል፤ ብዙ ኳሶችን ስናባክን ነበር፤
ሁሌም ኳስ ይዘን እንድንጫወት እፈልጋለሁ፡
፡ ከጅማ አባቡና ጋር በነበረው ጨዋታ
በተለይ በሁለተኛው 45 የጨዋታ ክፍለ ጊዜ
ፍፁም ጥሩ አልነበርንም፤ የወጥነት ችግርም
አስተውዬበታለሁ፡፡ ይህ በውድድሩ ከድሉ
ባልተናነሰ ሌላው የተማርንበት ነገር ነው፤
ስለዚህ ውደድሩን በአግባቡ ተጠቅመንበታል
ተምረንበታል፤ ለእኛ አስፈላጊውም ይሄ ነበር፡፡
ድሉ ግን ለደጋፊው፣ ለክለቡ ክብር ብቻ ነው፡፡
ለወጣት ተጨዋቾቻችንም በራስ የመተማመን
ስሜታቸውን ከፍ በማድረጉ በኩል ይጠቅም
ይሆናል፤ ከዚህ በዘለለ ግን እንደ ድል ቆጥረን
መዘናጋት የለብንም፤ ምክንያቱም ድሉ
ለደጋፊው ብቻ ነውና፡፡

ሀትሪክ፡- … የከተማውን ዋንጫ…
አሸንፋችኋል…፤… ይሄ ለፕርምዬር ሊጉ
ማረጋገጫ ወይም ዋስትና ይሰጣል?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- …ድሉ…
ለደጋፊዎቻችን በተለይ በጣም ነው ደስ
ያለኝ…፤ ለኔና ለተጫዋቾቹ ግን ግባችን
ይሄ አይደለም… ለተጫዋቾቹም ይህን
እንደ ድል ቆጥራችሁ እንዳትዘናጉ ብዬ
ነግሬአቸዋለሁ…፤ …ገና ብዙ ይቀረናል… የኛ
አልተጀመረም ብዬም አስረድቻቸዋለሁ፡፡ ድሉ
ግን ለደጋፊዎችችን፣ ለወጣት ተጫዋቾቻችን
በጣም ጥሩ ነው ሆኖም ግን ለቡና ይሄ
አይደለም የሚጠበቅብን፡፡ አሁን ሻምፒዮናው
እየተጀመረ ነው፤ ጠንክረን መስራት አለብን
በጋራ ማጥቃት፣ በጋራ መከላከል ፣በጋራ
መሮጥ፣ በጋራ መዝጋት መቻል ፤ ጥሩ
አጥቂ ቡድን ጥሩ ተከላካይም መሆን አለበት፤
ስትከላከል ስምንት ሆነህ ነው የምትከላከለው፤
ሁለቱ የሉም ስለዚህ በጋራ መከላከል ካልቻልክ
ችግር ውስጥ ትገባለህ፡፡ ይበልጥ መጠንከር
ይጠበቅብናል፣ ይበልጥ አግሬሲቭ ይበልጥ
አውሬ መሆን አለብን ሁሌም እንደምለው
“Nice boy never wins” እንደዛ ካልሆንክ
ማሸነፍ አትችልም፡፡
ሀትሪክ፡- በሲቲ ካፑ የግማሽ ፍጻሜ ሌላው
የታየው ነገር ለመስዑድ መሀመድ የተደረገለት
ታላቅ አሸኛኘት ነው ፤ አጋጣሚውን እንዴት
አዩት…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- እጅግ በጣም ደስ ነው
ያለኝ፤ በጣምም ነው የገረመኝ፤ በጣምም ነው
የወደድኩት። ለመስዑድ ግን ይሄም ያንሰዋል፤
መስዑድ ዓለም ላይ ያለ ክብር ሁሉ
የሚገባው ተጫዋች ነው፡፡ እንደተጫዋችም
እንደሰውም መስዑድ አለማድነቅ አይቻልም፤
ስለ መስዑድ ለመናገር ተጨማሪ እድል
ካገኘሁ “መስዑድን አንተ ሁሌም የቡና
ምልክት ነህ፤ ከኔ ጋር ብትሰራ ሁሌም ደስ
ነው የሚለኝ፤ አሁን ብቻ አይደለም አንተ
በፈቀድክ ጊዜ ሁሉ መምጣት ትችላለህን ላንተ
ሁሌም የቡና ቤት ክፍት ነው፤በሄድክበት
ሁሉ መልካሙን እመኝልሃለሁ የጨዋታ
ዘመንህን ማቆም ስትፈልግ ግን መደወል ብቻ
ነው፤የመጀመሪያው የረዳትነት ቦታው ሁሌም
ላንተ የተዘጋጀ ነው፤ አንተ ግሩም ሰው ነህ
በሄድክበት ሁሉ ቸር ይግጠምህ ልለው ነው
የምፈልገው።”
ሀትሪክ፡- …ለተጫዋቾች… በዚህ
ደረጃና ቦታና… ክብር አልዎት… ማለት
ነው…?ለተጫዋቾችና ለሰው ልጆች ያልዎት
ክብር ላይ ጥያቄና ቅሬታ የሚያቀርቡቦት አሉ
ይሄንን ይቀበሉታል?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- …ይሄንን…ጥያቄ…
እንኳን አነሳኸው …በተለይ የቀድሞው
ረዳት አሰልጣኜና አንድ አንድ ተጫዋቾች
በዚሁ ጋዜጣ ላይ የሰጡት መግለጫ በፍጹም
ፕሮፌሽናል ያልሆነና እኔን የማይገልፅ
መግለጫ ነው፤ እኔ በህይወቴ ለሰው ልጅ
ትልቅ ክብር አለኝ፤ ገደብ ድንበር የሌለው
ክብር። ለምሳሌ መስዑድ መሀመድን ውሰድ
ክለቡን ለቋል ከሱ ጋር ግን ሁሌም እንደ
ወንድም፣ ጓደኛ፣ ተጫዋች ወደፊት ደግሞ
የሥራ ባልደረባ አድርጌ የማስብ ሰው ነኝ፤
መስዑድ ለቡና ለሰራው ሥራ ከማክበር
ውጭ ምንም ምርጫ የለህም፡፡ የመስዑድን
አነሳውልህ እንጂ ከእሱ ጋ ብቻ አይደለም እኔ
ከተጫዋቾቼ ጋር ችግር ኖሮብኝ አያውቅም፤
ልጀቹንም ልትጠይቃቸው ትችላለህ፤
በጋዜጣችሁ ላይ አፍሪካዊ አይወድም
ተብያለሁ፤ የት እየኖርኩ ነው አፍሪካዊ
አይወድም የምባለው? ከርዋንዳና ከካሜሩን
አሁን ድረስ “ኮች እናመሰግናለን” የሚሉ
የሚደውሉልኝ ተጫዋቾች አሉ፤ካሜሩን
ለዓለም ዋንጫ ብራዚል የላኳቸው ሁለት
ልጆች አሉ እስካሁን ድረስ በየትኛውም ቃለ-
ምልልሳቸው እኔን የሚያመሰግኑ፡፡ እዚህም
እያሱ ልጄ የሚመስላቸው ብዙ ልጆች አሉ፤
ለአማኑኤል እዚህ ድረስ የማይባል ክብር
አለኝ፣ አቡበከር ከዚህ በኋላ ለብዙ ዓመታት
ኢትዮጵያ ውስጥ እግር ኳሱን በፊታውራሪነት
የሚመራ ታታሪ ወጣት ነው፤ ሚኪ፣
ሳሚ፣ ወንድይፍራው፣ ቶማስ ወዘተ… ማንን
ጠርቼ ማንን ልተውልህ? እኔ እዚህ ስመጣ
ማንንም አላውቅም… መስፈርቴ ሥራ ነው፤
አማኑኤልን በማንነቱ ሳይሆን በሥራው ነው
የምወደው፤ እንደአማኑኤል ከሰራህ ልጠላህ
አልችልም። የራስህን ስንፍና ማንም ላይ
ማላከክ አትችልም፡፡ እያሱ አፍሪካዊ አይደለም?
መስዑድ አፍሪካዊ አይደለም?ይሄ ተራ ስም
ማጥፋት ነው፤የቀድሞው ምክትል አሰልጣኝም
“አሰልጣኙ ውሸታም ነው አለኝ” እኔ ውሸታም
አይደለሁም፤እስከ ዓመቱ ክለቡ ሲያሰናብተው
እኔን መሳደብ ተገቢ አይደለም፤እውነት ነው
እኔ ከእሱ ጋር መቀጠል አልፈልግም ያልኩት
እኔ ነኝ፤ምክንያቱም ታዳጊዎችን በሚገባ
እየረዳቸው አይደለም።አሰልጣኝነት የትርፍ ጊዜ
ስራ አይደለም፤ሁሌም ከልጆችህ ጋር መሆን
ይጠበቅብሃል።አሰልጣኙ ውሸታም ስለሆኑ
ከሳቸው ጋር መሥራት አልፈልግም ብሎ
ለመልቀቅ መልቀቂያ የጠቀየው? እኔ ጥቃቅን
ነገር ውስጥ መግባት አልፈልግም፤ ነገር
ግን አንድን አሰልጣኝ በታክቲኩ፣ በስልጠና
ዘይቤው ልትቃወመው ትችላለህ፤ በማንነቱ፣
በስብዕናው ሲሆን ግን ደስ አይልም፡፡ ቡና
እኔን ያመጣኝ ለማሸነፍ ነው፤ ለማሸነፍ
ደግሞ ታታሪና ጠንካራ ተጫዋች ያስፈልጋል
ምክንያቱ እሱ ብቻ ነው፡፡ በምንሰራው ሥራ
ደስተኛ ያልሆኑ ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች
ሊኖሩ ይችላሉ፤ ይህ በእግር ኳስ ውስጥ ያለ
ነገር ነው፡፡ የእግር ኳስ ተጫዋች ሕይወት
የትም ቢሆን እንደዚህ ነው፤ በክለቡ የሚቆይ
አለ፤ የሚወጣም አለ፡፡ አስቻለውንና ኤልያስን
በተቃራኒ ቡድን ሆነው ሳያቸው በጣም ነው
ደስ ያለኝ፡፡ ለሁሉም ቢሆን እኔ መልካሙን
ሁሉ ነው የምመኝላቸው፡፡ ኢት.ቡና ውስጥ
የሰራችሁት ታሪክ ሁሌም ይኖራል፤
በሄዳችሁበት ሁሉ ቸር ይግጠማችሁ፡
፡ እኔ ሁሌም የይቅርታ ልብ ነው ያለኝ፤
ቂም አልይዝም ስለዚህ ለሁላችንም መልካም
የውድድር ዓመት፡፡

ሀትሪክ፡- ሁለት ሦስት ረዳት አሰልጣኞችን
ሞክረዋል፤ይሄ የሆነው የልብ የሚያደርስ
ረዳት አጥተው ነው? አሁንስ …?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- አውነት ነው ጠንካራ
ሰራተኛ፣ ትጉህና ታታሪ፣ ታማኝ ረዳት
እየፈለግኩ ነበር፤ ሕብረት ያለው ስታፍ ባለቤት
መሆን ለአንድ ክለብ ዋንጫ ለማንሳት ዋናው
ነገር ነው። ርዋንዳ፣ ካሜሩን ዋንጫ ያነሳነው
ህብረት ያለው ጠንካራ ስታፍ ስለነበረን ነው፡
፡ ርዋንዳ ረዳቴ የነበረው አሁንም ድረስ
ጓደኛዬ ነው፤ ዕለት በዕለት እንደዋወላለን፣
እንጠያየቃለን ።በካሜሩንም በተመሳሳይ
ረዳቶቼ የነበሩት ሁሉ አሁንም ወንድሞቼ
ናቸው፤ እውነት ነው ይህን ገጸ-ባህሪ የተላበሰ
ረዳት እየፈለግኩ ነበር፡፡ ገብረኪዳን (ጋምብሬ)
በስልጠናው ትንሽ ልምድ ያንስው ይሆናል ነገር
ግን እምነት የምትጥልበት፣ የመማር ፍላጎት
ያለው፣ የቡና ታላቅ ተጫዋች የነበረ፣ የቡናን
ማሊያ መልበስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ
የሚያውቅ፣ ሁሌም ለተጫዋቾች ቅርብ የሆነ፣
ቅን፣ ልጆቹን ማገዝና መርዳት የሚወድ ሰው
ነው ፤ አሁን ከዚህ አንፃር የተሻለ ሰው ነው
ያገኘነው ፡፡ ቴክኒክ ስታፋችንን በተመለከተ
አሁንም ቢሆን ይበልጥ ማጠናከር ይበልጥ
ፕሮፌሽናል ማድረግ ይጠበቅብናል፤ ነገር
ግን አሁን ለጊዜው በጣም ተስማምተናል፣
እንግባባለን፣ ጥሩ ላይ ነው ያለነው፡፡
ሀትሪክ፡-አማኑኤል ባለፈው ዓመት
በእርስዎ ስር ከፍተኛ ለውጥ አድርጓል የሚሉ
አሉ ፤እርስዎስ ስለ አማኑኤል ምን ይላሉ?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- ለአማኑኤል ምን
እንዳልኩት ታውቃለህ? አማኑኤል የጠንካራ
ሥራህን ውጤት እያየህ ነው፤ አሁን ሰው
ሁሉ ስለአማኑኤል ነው የሚያወራው ብሔራዊ
ቡድን ተጫውተሀ መጣህ፤ አማኑኤል የተለየ
ተሰጥኦ ያለው ልጅ ነው፤ የራሱ የሆነ
አጨዋወት ስታይል ያለው የተለየ ተጫዋች፡
፡ ወደፊት ይጫወታል፤ ሙሉ የቡናን ጨዋታ
የሚመራ የቡና ልብ ነው፡፡ ወደፊት እየሄደ
እንድናጠቃ ይረዳናል፤ ወደኋላ ተመልሶ
ጥቃትን ይከላከላል፤ እኛ ስንጫወት መሃል
ሆኖ ጨዋታውን የሚመራው እሱ ነው፡፡
አማኑኤል የሳጥን ለሳጥን ተጫዋች አይደለም፤
ነገር ግን የቡና የመሃል ሜዳ ሞተራችን
ነው፤ የተሰጠው ሚና በደንብ ገብቶታል፡፡
ከኳስ ጋር እና ያለ ኳስ ወደተቃራኒ የግብ
ክልል መግባትን በሚመለከት የሚያሻሽላቸው
ነገሮች እንዳሉ አሁንም ይሰማኛል፤ ከዛ ውጭ
አማኑኤል ሙሉ ተጫዋች ነው፡፡ አማኑኤል
ገና ልጅ ነው፤ ከሳጥን ሳጥን የመጫወት
አቅምም አለው፤ ምክንያቱም የሚገርም
ትንፋሽ ነው ያለው ስለሆነ። እርግጠኛ ነኝ
አማኑኤል ገና ብዙ ርቀት መጓዝ ይችላል፤
ከዚህ ሃገር ወጥተው መጫወት ይችላሉ ብዬ
ከማስባቸው ልጆች አንዱ አማኑኤል ነው፡፡
ሀትሪክ፡-ሳምሶን ጥላሁን በሲቲ ካፑ
ላይ አምና በሁለተኛው ዙር በጣም ተሻሽሎ
ታይቷል ይሄንንስ ታዝበዋል?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- ሳሚ ብዙ ማውራት
የማይወድ አይናፋር ነው፤ ነገር ግን በዝምታ
ውስጥ ሆኖ ግን የሚገርም ተጫዋች ነው፡፡
በተለይ ከአማኑኤል ጋር ይበልጥ ይግባባሉ፤
ሁለቱም የሚያደርጉትን ያውቃሉ፡፡ አማኑኤል
ከጀርባው ሲሆን ይበልጥ በነጻነት መጫወት
ይችላል፤ በዚህ ሁለት ሶስት ሳምንታት ደግሞ
ይበልጥ ጥሩ ሆኗል፤ እናንተም ሲቲ ካፑ
ላይ አይታቸሁታል፡፡ ስለዚህ ዘንድሮ ሳሚን፣
አስራትንና አማኑኤልን የያዘ መሃል ሜዳ ምን
እንደሚሰራ ታዩታላችሁ ማለት ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ስለአስራት ካነሱ የአስራት
አጨዋወት ብዙዎች አይገባንም ይላሉ፤
እርስዎ አስራት ላይ ያዩት ምንድን ነው ?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- የአስራትን እምቅ
ኃይል ማንም የለውም፤ ትንሽ መነሳሳት
ይጎለዋል፣ ንቃት ይጎለዋል እንጂ አቅሙማ
ይገርማል፡፡ በጣም ጠንካራ ነው፤ ፊትነሱ፣
ፍጥነቱ በተጨማሪ ደግሞ የቴክኒክ ችሎታው
ለተቃራኒ ቡድን በፍጹም ተገማች ያልሆነ
ተጫዋች እኮ ነው፡፡ አስራት ትንሽ አዕምሮው
ላይ መስራት ብቻ ነው የሚጠበቅብህ፡
፡ ያለውን አቅም እራሱም አልተረዳውም፤
አስራት ያለውን አቅም የተረዳውና ምን
መስራት እንደሚችል የገባው ዕለት በተጨማሪ
አጨዋወቱ ላይ ትንሽ አግሬሲቭነት የጨመረ
ጊዜ አስራት ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ በጣም
ምርጥ ተጨዋቾች አንዱ ይሆናል፡፡ ነገር
ግን መስራት ይጠበቅበታል፤ቡናን አምና
ነው የተቀላቀለው በዛ ላይ ገና ልጅ ነው፡፡
የተቃራኒ ቡድን ተከላካዮችን ሄደህ የአስራት
ሚና ምንድን ነው? በላቸው፤ አስራት ሁሌም
የተቃራኒ ቡድን ፈተና ነው፡፡ በመስመር
መሮጥ ይችላል፤በተቃራኒ የግብ ክልል ውስጥ
እንዴት መንቀሳቀስ እንዳለበት ያውቃል፣
ከኳስ ጋር ተመችቶት ነው የሚጫወተው፤
የቴክኒክ ችሎታው በጣም ጥሩ ነው፡፡ አስራት
ከጥቃቅን ነገሮች በቀር ምርጥ የቡና ተጫዋች
ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ዘንድሮ… ጎልቶ የሚታይ
…የቡና ምርጥ ተጫዋች… ማን ይሆናል…
ብለው…ይጠብቃሉ…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡– …አላውቅም…!…
ምንአልባት ሁሉም…!…ባለፈው ሳምንት ምን
ሆነ መሰለህ በምንሰራው ሥራ ምንም ደስተኛ
አልነበርኩም ደከሙ እና እንደገና የፊዚካል
ሥራ አሰርቻቸው ተበሳጭቼ ሄድኩ፤ ረቡዕ
ዕለትም ያንኑ ያህል ለመስራት ተገደድን፡፡
ሃሙስ ዕለት ሁሉንም ሰበሰብኩዋቸውና ይሄን
ጥያቄ ጠየቅኳቸው በመጀመሪያ በባለፈው
ዓመት ምርጥ የነበሩትን ጠየቅኳቸው ከዛ
ደግሞ አዲሶቹንና የቀሩትን፤ ከባድ ጥያቄ ነው
ነገር ግን ከጋና ጋር ለሚደረገው የኢትዮጵያ
ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ስምንት ተጫዋቾች
በቡድኑ ውስጥ መኖር አለባቸው ተባብለናል
ከነዚህ ከስምንቱ አብዛኛው ይጠራሉ ብዬ
እጠብቃለሁ፤ አማኑኤል፣ አህመድ(ሽሪላው)፣
ካስትሮ፣ ተካልኝ፣ ሳሚ፣ ዳንኤል፣ አቡበከር፣
ቶማስ፡፡ እዚህ ያለሁት ልጆቹን ለመርዳት
ለማብቃት ነው የመጣሁት፤ ፍላጎቴ ሁሉም
ምርጥ እንዲሆኑ ነው፤ ማን ነው ምርጥ
ለሚለው ጥያቄ ሁሉም የራሱ ሚና አለው፤
ዓመቱ መጨረሻ ላይ እናያለን፤ ነገር ግን ብዙ
ምርጥ ልጆች አሉን፡፡ እንኳን የዘንድሮውን
የአምናውን አላውቅም፤ የቡና ምርጥ ተጫዋች
ማን ነበረ…? አማኑኤል፣ ኢያሱ፣ ሚኪ፣
አቡበካር…? …ከባድ ጥያቄ… ነው…

ሀትሪክ፡-…ይሄን ያህል… ለመምረጥ…
ተቸግረዋል…ማለት…ነው…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- እ…!…አንድ ሰው
ነጥሎ ማውጣት ከባድ ነው?…አማኑኤል ድንቅ
ዓመት ነው ያሳለፈው፣ ሚኪም ሁለተኛው
ዙር ላይ ጀግና ነበር፣ ኢያሱም እንደዛዉ፤
ታዲያ ማን ነበር ምርጥ…? ዘንድሮስ ማን
ይሆናል…?መልሱ አሻሚ ነው…፤ ብዙ ልጆች
አሉ… የአቡበከር ገና የአቅሙን ግማሽ እንኳን
አላየንም፤ ከጉዳት ነው የተመለሰው ገና ሙሉ
ለሙሉ ኣላገገመም ። ነገር ግን በባለፉት
ሳምንታት ያሳየን ነገር ነገ የት ሊደርስ
ይችል ይሆን ብለን እንድንጓጓ ያስገድደናል፡፡
ከኢትዮጵያ ውጭ ሄዶ በእርግጠኝነት በከፍተኛ
ደረጃ መጫወት የሚችል ምርጥ ኢትዮጵያዊ
አጥቂ እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ ዳንኤል ሌላ
ተዓምረኛ ተጫዋች ነው፤ ሜዳ ላይ ሁሉንም
ነገር ማድረግ የሚችል በተለይ አግሬሲቭነቱ
ሲያምር በዚህ የሲቲ ካፕ ያሳየን ነገር እጅግ
ይገርማል፡፡ በርግጥ ትንሽ ፍጥነት ይቀረዋል
በተጨማሪም ኮንትሮል ፓስ ኮንትሮል ፓስ
መጫወት አለበት፡፡ ገና ልጅ ነው ነገር ግን
አንድ ተጫዋች ሊኖረው የሚገባው ነገሮች
ሁሉ ያሉት ምርጥ አማካይ ነው፡፡ ቶማስ
ከጉዳት ጋር እየታገለ ቢሆንም ሃገሪቱ ላይ ካሉ
ምርጥ ተከላካዮች አንዱ ነው፤ ቶማስ ከጉዳት
ነጻ ሆኖ ካገኘነው ምን እንደሚሰራ ማሰብ
ይከብዳል፡፡ ሱሌይማን ያሳየን ነገር በጉጉት
የሚጠበቅ ነው፤ አሁን ደግሞ በመጨረሻ
አንድ በጣም ወጣት አጥቂ አስፈርመናል፤
ፍጥነቱና ቅልጥፍናው ይገርማል፡፡ ኢያሱ
ከጉዳት አላገገመም አሁንም ገና ሁለት፣ ሶስት
ወራት ገና ሊወስድበት ይችላል፤በአጭሩ አንድ
ሳይሆን እነዚህ ሁሉ ምርጦቻችን ናቸው።
ሀትሪክ፡- አዲስ ስለገቡት ልጆችስ ምን
ይሉናል…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- ተካልኝና ዳንኤል
የሚገርም አቅም፣ ችሎታ ያላቸው ናቸው፤
የካስትሮ አግሬሲቭ ባህሪ የአህመድ(ሽሪላው)
ችሎታና የቡና ካራክተር ለዛ ነው እኮ ቅድም
ዘንድሮ የተለየ ቡድን አለን ያልኩህ፤ የተሻለ
ቡድን አለን። በተለይ አምና ብዙ ስንቸገርበት
የነበረው ከሜዳ ውጭ ጨዋታዎች ላይ ለውጥ
ማምጣት አለብን፡፡ አህመድ(ሽሪላው)፣ ካስትሮ፣
ሱሌይማን ለዚህ በጣም ይጠቅሙናል፡፡
ሀትሪክ ፡-ስለ አዲሱ ፈራሚ ስለ ዳንኤልስ
ምን የሚሉን ነገር አለ…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- ዳንኤል በጣም ምርጥ
ተጫዋች ነው፤ ዘንድሮ በጣም ምርጡ
ፈራሚያችን ዳነኤል ይመስለኛል። አግሬሲቭ
ነው፣ ጉልበት አለው፣ ቴክኒክ የታደለ ልጅ
ነው፤ሜዳ ላይ ምን ማድረግ እንዳለበት
በደንብ ያውቃል፤ ትንሽ የዳንኤል ችግር ኳስን
ተቆጣጥሮ በቶሎ ማቀበል ላይ ትንሽ ይዘገያል
ያንን ደግሞ ተነጋግረናል፡፡ ከዛ ውጭ ዳንኤል
ምርጥ ልጅ ነው የቡና ካራክተር አለው፡፡
በፍጹም መሸነፍን መቀበል የማይፈልግ ልጅ
ነው፤ አምና ያጣነው አይነት ገጸባህሪ ስላለው
በጣም ይጠቅመናል፡፡ በግልም የሲቲ ካፕ ኮከብ
ነበር ለብሔራዊ ቡድኑም የተሻለ ይሰራሉ
ብዬ ከማስባቸው ልጆች አንዱ ነው፡፡ታዳጊ
የማብቃት ሥራ ያሰልጣኙን ብቻ ሣይሆን
የታዳጊውን ጥረት የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡
አምና አቡበከር፣ ሚኪ፣ ኃይሌ በትጋታቸው
ምን እንዳስመለከቱን እናስታውሳለን፡፡ ዘንድሮ
ሚኪና አቡበከር ሲነየር ተጫዋቾች ሆነዋል፡
፡ ዘንድሮም ፍጹም ጠንክሮ ከሰራ የሚወጣ
ይመስለኛል በጣም ፈጣን ተጫዋች ነው ብዙ
አቅሞች አሉት፡፡ አቅሙን ከተጠቀመበት
እሱ እራሱ አቅሙን ከተረዳው ፍጹም ጥሩ
ተጫዋች ይመስለኛል፡፡ ቢኒያም የመሃል
ሜዳ ተጫዋች ነው የሚገርም አቅም አለው፡
፡ ተመስገን ቃልኪዳንና ፍቃዱ የፊት
መስመራችንን ያግዘዙናል ብዬ አስባለው፡፡
ሀትሪክ፡- እያሱን በተመለከተ በሲቲ ካፑ
ላይ በበቂ ሁኔታ አለመጫወቱን ተከትሎ ብዙ
ሰው እያሱ የዚ ቡድን የመጀመሪያ ተመራጭ
አይሆን እንዴ የሚል ስጋት የተፈጠረባቸው
አሉ፤እያሱ የመጪው ዓመት እቅድዎ ውስጥ
አለ…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- ኦው! ኢያሱ እንዴት
ሊሆን ይችላል እንደምታውቀው እያሱ ጉዳት
ላይ ነበረ ከጉዳት ከተመለሰም በኋላ ብዙ እድል
ያላገኘበት ምክንያት ገና አላገገመም ካሁን
በኋላ ሁለት ወይም ሦሰት ወራት ይፈልጋል፡፡
በጉዳት ካልሆነ በቀር እያሱ ወሳኝ ተጫዋቻችን
ነው፡፡ ኢጥዮጵያ ውስጥ እግር ኳስን
በጭንቅላት የሚጫወት ተጫዋች እንደ ኢያሱ
አላየሁም፡፡ እያሱ ሁሉ ነገር የተሰጠው ምርጥ
ልጅ ነው ፍጥነቱ፣ ጉልበቱ፣ ቅልጥፍናው፣
ቴክኒኩ ኢያሱን ትተን የማይሆን ነገር ነው፡
፡ ቅድም ነግሬሃለው ኢያሱ ልጄ ነው፡፡ ያለ
እያሱ የማይታሰብ ነገር ነው፡፡
ሀትሪክ፡-በሲቲ ካፕ ከኤሌክትሪክ ጋር
የተደረገውን ጨዋታ 5-0 ስታሸንፉ አራቱ
ጎሎች የተቆጠሩት በታዳጊዎች ነው፤ ነገር
ግን አራቱም ማሊያቸውን በማውለቃቸው
ምክንያት ካርድ አይተዋል የዲሲፕሊን ነገር
እንዴት ነው…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- በትክክል ታዳጊዎቹ
በማግባታቸው ተደስቻለሁ፤ ምክንያቱም
ተጫዋቹ አይደለም ጎል ያገባው ቡና ነው፡
፡ የቡናን ማሊያ አውልቀህ እንዴት ሊሆን
ይችላል? በነጋታው ልምምድ ሜዳ ስንገናኝ
አራቱንም ከላይ ማሊያቸውን አውልቀው
እንዲሰሩ ነው ያደረኩት፤ ጓደኞቻቸው ሁሉ
ለብሰው ሲሰሩ አራቱም ያለ ልብስ ነው
ልምምድ ሲያደርጉ የነበረው፤ ቅጣት ነው።
ሌላ ጊዜ ሲደግም ደግሞ ቁምጣቸውን
አውልቀው እንዲሰሩ ይደረጋል፤ ስነ-ስርዓት
መልመድ አለባቸው፡፡
ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያን የመጎብኘት ዕድልስ
አግኝተዋል…? የትኛው አካባቢ ቀልብዎን
ሣበ…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- ለዝግጅት ባህርዳር
ነበርኩ፤ አጋጣሚ የጣና ገዳማትን
እንድመለከት ሠፊ እድል ፈጥሮልኛል፤ ዕድሜ
ለሲቲ ካፑ የሲቲ ካፑን ደስታ ያጣጣምኩት
ላሊበላ ሄጄ ነው፡፡ አስራአንዱንም አብያተ
ክርስቲያናት አይቼ የማያልቅ ደስታንና ሀሴት
አድርጌያለሁ፤ ከባለቤቴ ጋር ማየቴ ደግሞ
ደስታዬን እጥፍ አድርጎታል፤ ሀገራችሁ
የሚገርም ታሪክ ባለቤት ሀገር መሆንዋን አይቼ
አረጋግጫለሁ፡፡ እኔ ደግሞ በተለይ ማሪያምን
በጣም ነው የምወዳት፤ ከማርያም ጋር ብዙ
የሚያስተሳሰረን ነገር አለ፤ የሲቲ ካፑን
ደስታን ለማጣጣም ብቻ ሣይሆን ምስጋናም
ለማቅረብ ነው ወደ ላሊበላ የሄድኩት፡፡ ከዚህ
ውጪ በቂ የጥሞና ጊዜ ለማግኘት ወደብላ
ማርያም ተጉዣለሁ፤ዕውነት በዚህ ታሪካዊ
ቦታ ጥሩ የሚባል ጊዜ ነው የነበረኝ፡፡ የላሊበላ
አወቃቀር ለቤተክርስቲያኑ ውበት የሆኑት
እነዛ ልዩ ምስሎች የተለየ ስሜትን በውስጥ
የመፍጠር አንዳች ኃይል አላቸው፡፡
ሀትሪክ፡- በነጋራችን ላይ ብቸኛዋና
የመጀመሪያ ባለቀለም የሆነችው ጋዜጣችን
የእርስዎን ቃለ-ምልልስ ለንባብ የምታበቃው
በ21 የማሪያም ዕለት ነው፤…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡-…. ኧረ ባክህ… (ሣቅ)
…ብዬሃለሁ… እኮ… (ሣቅ) አሁን እዚህ
ከመጣሁ በኋላ ካየኋቸው ነገሮች አንዱ እሱን
ነው፤ እውነቴን ነው የምልህ ማርያምን በጣም
ነው የምወዳት፡፡

ሀትሪክ፡- ትርፍ ጊዜዎትን በምን
ያሳልፋሉ…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- ሥነጽሁፍ በጣም
እወዳለሁ፤ በጣም አነባለሁ። የሁለት
መጽሀፍት አድናቂ ነኝ ፤ሁለቱን መጽሀፍት
ዕለት በዕለት ባነባቸው አልረካም፤ L’Amour
tendu እና Un Volant de Kaboul።
እያንዳንዱን ገጽ ባነበብክ ቁጥር ታለቅሳለህ፤
ታሪክ ማንበብም ደስ ይለኛል፤ ሲኒማም
አልጠላም፡፡ ያለኝን ጊዜ ሁሉ በንባብ ነው
የማሳልፈው፤ አሰልጣኝ ባልሆን ኑሮ የታሪክ
አስተማሪ ነበር የምሆነው፡፡የቢየልሳን መጽሀፍ
በአንድ ቀን፣ የአንቼሎቲን መጽሃፍ በአንድ ቀን
ነው ያነበብኩት፡፡ ቢየልሳ የተለየ ሰው ነው፤
የሚያረገው ነገር ሁሉ የሚያስደስተኝ ሰው
ቢኖር ቢየልሳ ነው፡፡ ኳስን የምንመለከትበትን
መነጽር የቀየረ ሠው ነው፤የብዙ አሰልጣኞችን
መጽሀፍ አንብቤአለሁ፤ አሁንም አነባለሁ
ምክንያቱም አንድ ነገርን በተለያዩ መንገዶች
ለመስራት አቅም ይሰጥሃል፡፡ እኔም አንድ
ቀን አዚ ሆኜ ወይም ከሄድኩ በኋላ መጻፌ
አይቀርም ስለዚህ አነባለው፡፡
ሀትሪክ፡- ወጣት አሰልጣኞች ወደ
ስልጠናው ዓለም እየመጡ ነው፤ የቴዬሪ ሆንሪ
ሞናኮን መረከብስ እንዴት አዩት?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- ኦዎ… እኔ ትንሽ ስጋት
አለኝ…፤ ምክንያቱም ሆንሪ ታላቅ ተጨዋች
ነው ብዙ ነገር የሠራ፤ በተጨዋችነቱ ምድር
ላይ ያለው ክብር ሁሉ ይገባዋል፤ አሰልጣኝ
ለመሆን ግን ገና ነው። ሞናኮን ለመምራት
አቅሙ አለው ለማለት ይቸግረኛል፡፡ አስራ
አምስትና ሃያ አመት ላሰለጠነ ሰው እንኳን
ከባድ ነው፤ ቢሳካለት ደስ ይለኛል መልካም
ምኞት አለኝ፤ ምክንያቱም ቴሪ ለፈረንሣይ
ምልክት ነው፡፡ ነገር ግን ሞናኮ ትልቅ ክለብ
ነው፤ ብዙ ወጣት ተጨዋች ያሉት፤ ስለዚህ
ብዙ ይጠበቅበታል። ታላላቅ ተጨዋቾችና
ታላላቅ አሰልጣኞች ይለያያሉ፡፡
ሀትሪክ፡- የሚያደንቁት አሰልጣኝ ማን
ነው…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- ቢየልሳ…፤ ቢየልሳ
እግር ኳስን የምናይበትን መነጽር ነው
የቀየረው።ሁሉ ነገሩ ይመቸኛል፤ እንደሱ
በመከላከል አላምንም ነገር ግን አጨዋወቱ
የአዕምሮ ዝግጅቱ ሁሉ አድናቂ ነኝ፤ ከዛ
ጋርዲዮላ… እግር ኳስን ድጋሚ ነው
የፈጠረው፤እኔ እንደዛ ነው የማስበው፤
ድጋሚ ኳስን እንደፈጠረ ነው የምረዳው፡፡
የዘመናችንም ምርጥ አሰልጣኝ በእርግጠኝነት
ጋርዲዮላ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የምን ክለብ ደጋፊ ነዎት…?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡- ያደኩት ማርሴይን
እየደገፍኩ ነው፤ ለማርሴይ አሁንም
ልዩ ፍቅር አለኝ። ድጋፍ ከጠየከኝ ግን
የማንችስተር ሲቲ ደጋፊ ነኝ፤ ጨዋታቸው
በጣም ነው የሚመቸኝ። ኳስ የምትወድ ከሆነ
ትወዳቸዋለህ፤ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡
ሀትሪክ፡- ለስንብት ኢትዮጵያን በአጭር
ቃል ግለፁልኝ ብል እንዴት ይገልፃታል?
አሰልጣኝ ዲዲዬ፡ ታላቅ ሀገርን በአጭር
ቃል መግለፅ ይቸግራል፤ ከባድ ነገርም ነው፡
፡ ያም ቢሆን ግን ኢትዮጵያን ከረዥም ጊዜ
በፊት ነው የማውቃት የምወዳትም፤ በታሪክ
ብዙ ነገር አንብቤያለሁ። ታላቅ አገርነትዋንም
ተረድቻለሁ፤ እኔ እዚህ የመጣሁት ለኢት.ቡና
ነው፡፡ ኢት.ቡና ትልቅ ክለብ ነው፡፡ ታላቅ ሀገር
ውስጥ የኢትዮጵያ ምልክትም ነው፡፡
አስተያየት ይስጡ