መነሻ ገጽ Uncategorized ሀትሪክ ኤዲቶሪያል| “ይልቀቁ ይሸለሙ?” አዲሱ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ፋሽን
Uncategorized

ሀትሪክ ኤዲቶሪያል| “ይልቀቁ ይሸለሙ?” አዲሱ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ፋሽን

አጋራ
አጋራ

እየተካሄደ ያለው የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር እጅግ ወሳኝ
ወደ ሆነ ምዕራፍ በመሸጋገር ልብ ሰቃይ ለመሆን በበቃበት በዚህ ወቅት የዋንጫው
አሸናፊን ለመለየት የሚደረገው ፉክክር የተጋጋለ ደረጃ ላይ ለመድረስ ከመቻሉ ባሻገር
ላለመውረድ የሚደረገው ትንቅንቅ ወደ ላቀ ጡዘት ለመሸጋገር መቻሉ በልዩ ልዩ
ከተሞች የሚደረጉትን ቀሪ ጨዋታዎችን በከፍተኛ የተመልካች ቁጥር እንዲታጀቡ
ለማድረግ የቻለበት ዕውነታ ላይ መድረሱ በተጨባጭ እየታየ መሆኑን የምትረዳው
ሀትሪክ… ለዋንጫው አሸናፊነት ለመብቃት ከሚደረገው ጠንካራ ፉክክር በላቀ መልኩ
ላለመውረድ የሚደረገው ትንቅንቅ በልዩ ልዩ ስውር ሴራዎችና ተንኮሎች ሊጠላለፉ
ይችላል የሚል ጠንካራ ስጋት ያደረባት መሆኗን ለመግለፅ መሻቷን በአክብሮት
ታስረዳለች፡፡
የፕሪሚየር ሊጉ የዋንጫ አሸናፊ ለመሆን የሚደረገው ፉክክር እጅግ እየተጋጋለ
በመጓዙ ከዚህ ቀደም በተደረጉትና በርካታ ጨዋታዎች እየቀሩ የዋንጫ አሸናፊውን
ቀድሞ ለማወቅ ከተቻለባቸው ውድድሮች የተለየ ለመሆን እንደበቃ በፉክክሩ እየታየ
መሆኑን በመልካም መልኩ ለመጥቀስ የምትሻው እንደሆነ የምትጠቁመው ሀትሪክ…
የዋንጫው አሸናፊ ለመሆን የሚደረገው ፉክክር እንዲህ በጠበበ መልኩ ለመጓዝ
መብቃቱ በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የሚገኙ ደጋፊዎች ቁጥር ከማንኛውም ጊዜ
በላይ ከፍ እንዲል ማድረጉ የዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ ተጨማሪ ቱሩፋት ለመሆን
መብቃቱን ለመታዘብ መቻሏን በአክብሮት ትገልፃለች፡፡
የዋንጫው አሸናፊ ለመሆን ከሚደረገው ትንቅንቅ ውጪ የመውረድ ሥጋት
ያንዣበባቸውን ክለቦች ቁጥር በርካታ መሆናቸው የመላው ስፖርት አፍቃሪያንን ቀልብ
ለመሳብ አይነተኛ ምክንያት መሆኑን የተረዳችው ሀትሪክ… በዚህ የስጋት ቀጠና ወስጥ
ስድስት ክለቦች ማለትም ወላይታ ዲቻ፤ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፤ ጅማ አባቡና፤ ድሬደዋ
ከተማ እና ኢትዮ.ንግድ ባንክ በቀሪ ጨዋታዎች የሚያደርጓቸው ፍልሚያና በወረቀት
ስሌት መሠረት ወደ ታችኛው ሊግ እንዲወርድ ሊታሰብ የሚቻለው የአዲስ አበባ
ከነማ ቡድን የሚያካሂዷቸው ፍልሚያዎች በፅኑ ክትትል ሊታዩ የሚገባቸው መሆኗን
ለመግለፅ ትወዳለች፡፡
እንደ ስድስቱ ክለቦች ሁሉ ይህ አቋሟን ይፋ እስካደረገችበት ሰዓት ድረስ
በደረጃ ሰንጠረዡ ከሰባተኛ እስከ አስረኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ማለትም ወልዲያ
ከተማ፣ መከላከያ፣ ሃዋሳ ከተማ እና አርባ ምንጭ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ሆነው
እየተፎካከሩ መሆኑ ውጥረቱን የበለጠ እንዲከር እንዳደረገው የምትረዳው ሀትሪክ…
እስትንፋሳቸውን በፕሪሚየር ሊጉ ለማቆየት ብርቱ ጥረት የሚያደርጉ ክለቦች እንዲህ
በዝተው መታየታቸው የሊጉን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም የሚደረገውን ጥረት በሜዳ
ላይ የበላይነት ብቻ ሣይሆን ከሜዳ ውጪ በሚደረጉ የመሞዳሞድ ሴራ ለማግኘት
የሚደረጉ ተግባራት ለመታየት የሚችሉበት ፍንጭ መፈጠሩ እግር ኳሳችን ውጤትን
ለማጭበርበር ለሚደረጉ ተግባራት የመጠቃት ዕድሉ ሰፊ እንዲሆን በማስቻሉ ረገድ
የራሱ ድርሻ እንደሚኖረው ትረዳለች፡፡
በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ክለቦች ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ በሆነ
የመሞዳሞድ ተግባራት ውጤትን አስመዝግበው በፕሪሚየር ሊጉ ለመቆየት በከፍተኛ
ውጣ ውረድ ላይ መጠመዳቸውን በማስመልከት የሚናፈሱ ወሬዎች መብዛታቸውን
በማስመልከት የራሷን አቋም የምትይዝ መሆኗን የምታስረዳው ሀትሪክ… እነዚህ
በማስረጃ ያልተደገፉ የአደባባይ ላይ ወሬዎች ተራ አሉባልታ ናቸው ብላ ልታልፋቸው
የምትሻ አለመሆናቸውን አስረግጣ በመግለፅ ያደረባትን ብርቱ ስጋት ጠቁማ ከማለፍ
ወደ ኋላ የማትል መሆኗን ለመጠቆም ትወዳለች፡፡
የሊጉ ውድድር ሊጠናቀቅ እየተቃረበ በመጣበት በዚህ ወቅት የጨዋታ ውጤትን
ለማጭበርበር ከሚደረገው እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ጨዋታዎች ቅሬታ
እየቀረበባቸው ከመሆናቸው ባሻገር ተመልካቹ ድርጊቱን አውቆ በይፋ እስከ መቃወም
የደረሰበት ሁኔታ በግልፅ መታየቱ ከስፖርት ቤተሰቡ የተሰወረ እንዳልሆነ የምታምነው
ሀትሪክ… ሊጉ “ይልቀቁ ይሸለሙ” በሚመስል መልኩ የጨዋታ ነጥብን አጭበርብሮ
ከጥቁር ገበያ ለመግዛት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ለማየት መቻሏ ዳዴ እያለ
ለሚገኘው እግር ኳሳችን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መሆን ወደሚቻልበት ደረጃ
ለመሸጋገር መብቃቱ ለከፋ ስጋት አጋልጦ የሰጣት መሆኑን ልታረጋግጥ ትሻለች፡፡
በሊጉ የማጠቃለያ ጨዋታ ወቅት ወደ ታችኛው ሊግ ለመውረድ በስጋት ውስጥ
ያሉ ክለቦች የመጨረሻውን ወሳኝ ውጤት ለመገብየት ዳኞችን፣ ተጨዋቾችን እና
የክለብ አሠራሮችን ሳይቀር የብላክ ማርኬቱ ወጥመድ ውስጥ ለማስገባት ድርድር
እያደረጉ ስፖርታዊ ጨዋነትን በይፋ ሲፃረሩ መመልከቱ በእግር ኳሱ ላይ የሞት
ፍርድ እንደማስተላለፍ ሊቆጠር የሚገባው መሆኑን የምታምነው ሀትሪክ… ዳኞች
ቃለ መሀላ ፈፅመው ለገቡበት ሙያቸው ሊገዙና የክለብ አመራሮች፣ ተጨዋቾች እና
አሠልጣኞችም ከዚህን መሰሉ መናኛ አስተሳሰብ ነፃ ወጥተው የዘሩትን ሰብል በማጨድ
ተግባር ላይ ብቻ ትኩረት ሊሰጡ የሚገባቸው መሆኑን ልታሳስብ ትወዳለች፡፡
በዚህን መሰሉ የውንብድና ተግባር ላይ ተሰማርተው ውጤት በመሰብሰብ
በፕሪሚየር ሊጉ ለመሰንበት የሚሞከሩ ክለቦች በገንዘብ የተገዛ ውጤት መሠረት
የሌለው በመሆኑ ነገ ከነገ ወዲያ ከውድቀት ሊያመልጡ የሚችሉበት አቅም ሊኖራቸው
እንደማይችል የምታሳስበው ሀትሪክ… ይህ አይነቱ መጥፎ ድርጊት ከፌዴሬሽኑ
አመራሮች በተለይም ከዳኞች ኮሚቴ የሚሰወር ባለመሆኑ ከዚህ ቀደም በዳኞች
አመዳደብ ላይ ሲደረግ ከነበረው ጥንቃቄ በላቀ መልኩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው
መሆኑን አበክራ ትጠቁማለች፡፡
የሚመለከታቸው አካላት ውጤትን በገንዘብ የመገብየት ጣጣ ውስጥ ለመግባት
እንቅስቃሴ እያደረጉ የሚገኙ ስለመሆናቸው የሚነገርላቸው ክለቦችን መጥፎ ሴራ
ለማምከን ይቻል ዘንድ ሥውር ክትትል ከማድረግ በዘለለ ውድድሮች በተመሳሳይ
ሰዓት እንዲካሄዱ፤ በምስል ተቀርፀው ለማጣራት የሚቻልበት መንገድን መዞርነት
ይጠበቅባቸዋል ብላ የምታምነው ሀትሪክ… ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ በመጓዝ
በተጠቀሰው አይነት ከንቱ ተግባር ውስጥ ተሰማርተው የሚገኙ አካላትን ሊያስተምር
በሚችል መልኩ ለመቀልበስ ጠንከር ያለ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ ትገልፃለች፡፡
በውድድሩ ሂደት ላይ ያልሰበሰቡትን ምርት ወደ ጎተራቸው ለመክተት አስበው
ከፍተኛ ብር በመመደብ ውጤትን ከጥቁር ገበያ ለመግዛት የሚንቀሳቀሱ ክለቦች
በሃቃቸው ያላገኙትን ውጤት ከመነጠቅ በዘለለ ወደ ታችኛው ዲቪዚዮን ወርደው
ለመጫወት የሚገደዱበት ቅጣት ውስጥ መውደቅ የሚጠበቅባቸው መሆኑን
የምታምነው ሀትሪክ…. ፌዴሬሽኑ ክለቦች በዚህን መሰሉ ተግባር ተሰማርተው ወደ
ቅጣት የሚሄድበትን አማራጭ ለመጠቀም ከመገደዱ በፊት በጨዋታ ሰዓት አደላደል
እና በዳኞች አመዳደብ እንዲሁም በጨዋታ ሂደት የምስል ቀረፃዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ
የተጠናከረ ስራ ሊሰራ የሚገባው መሆኑን ለማሳሰብ ትወዳለች፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ይህ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል የኢትዮጵያ እግር ኳስ
ፌዴሬሽን ፍንጭ ማግኘቱን ከታማኝ ምንጮቿ የተረዳቸው ሀትሪክ… በመሞዳሞድ
የሚላቀቁ ክለቦች ላይ ከበድ ያለ ቅጣት ለመጣል እና አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ጨዋታዎችን
እስከ መሰረዝ የሚያደርስ እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጀ መሆኑን ለማወቅ ችላለች፡፡
ፌዴሬሽኑ በእርግጥም ይህንን የሚያደርግ ከሆነ ከላይ በርዕሱ ለመግለፅ የተሞከረውን
“ይልቀቁ ይሸለሙ?” እየተባለ ላለው የፕሪሚየር ሊጉ አንዳንድ ክለቦች አዲሱ ፋሽን
ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሀትሪክ ታምናለች፡፡

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
Uncategorized

ቅዱስ ጊዮርጊስ የመቶ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደረገለት

ዛሬ አንጋፋውን የቅዱስ ጊዮርጊስ የስፓርት ማህበር ከገጠመው የመፍረስ አደጋ ለመታደግ የተለያዩ አካላትን...

Uncategorized

ለዋልያዎቹ መጫወትን የሚመኘው የሴሪ ኣው ክለብ ተጫዋች ማነው ?

የጣሊያን ሴሪ ኣው ክለብ ቶሪኖ ንብረት ስለሆነው አስደናቂው የአጥቂ አማካይ ተጫዋች እንንገራችሁ።...

Uncategorized

ቡናማዎቹ ተጫዋች ለማስፈረም ተስማሙ !

  በዛሬው ዕለት ግብ ጠባቂ በማስፈረም ወደ ዝውውሩ የገቡት ኢትዮጵያ ቡናማዎች ዘካሪያስ...