“ወልቂጤ ከተማ የተጎናፀፈው ድል 3 ነጥብን ከመፈለጋችን አኳያ በጣም ጣፋጭ ነው” ያሬድ ታደሰ

 

ወላይታ ድቻን 2-1 በረታበት የዛሬው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮና ክለቡን ዘንድሮ ከድሬዳዋ ከተማ በመምጣት የተቀላቀለው ያሬድ ታደሰ ሁለቱን የድል ግቦች ሊያስቆጥር ችሏል።

ለወልቂጤ ከተማ መልካም የሚባል እንቅስቃሴ ከማድረግ ባሻገር እነዚህን ግቦች በጥሩ ሁኔታ ያስቆጠረው በክለብ ደረጃም ከድሬዳዋ ከተማ ውጪ ለናሽናል ሲሚንትም መጫወት የቻለው ያሬድ በተለይ አንዷን ግብ ከርቀት በመምታት ከመረብ ላይ ያሳረፋት ሲሆን ይህን ተጨዋች በጨዋታው ዙሪያና ስለቡድናቸው እንዲሁም ግብ ስለማስቆጠሩና ምን ውጤትን ዘንድሮ ለማስመዝገብ እንደሚጫወቱ አናግረነዋል።

ወላይታ ድቻን ድል አድርጋችኋል፤ ጨዋታው ምን መልክ ነበረው?

“ባለፉት ሁለት ግጥሚያዎቻችን ነጥብ ከመጣላችን አንፃር የዛሬው ጨዋታ ለእኛ ትንሽ ከበድ ብሎብን ነበር። ምክንያቱም ከእዚህ ግጥሚያ 3 ነጥብን እንፈልግ ስለነበር ነው፤ በመጨረሻም የአሰልጣኛችንን ምክር በደንብ አድርገን ስለሰማን ከፈጣሪ እርዳታ ጋር የጨዋታው ባለ ድል ሆነናል”

ያገኛችሁት ውጤት ጣፋጭ ነው?

“በጣም እንጂ! ምክንያቱም ድሉን በጣም እንፈልገው እና ለቡድናችንም የቀጣይ ጊዜ ጨዋታዎች መንፈስ መነቃቃት የሚፈጥርልን ነገር አለና ለዛም ነው ውጤቱን በአስደሳችነቱ የምገልፀው”።

የድል ግቦችን ለቡድኑ ስለማስቆጠሩ እና አንዷ ደግሞ ከርቀት ተመታ የተገኘች ስለመሆኗ

“ለወልቂጤ ያስቆጠርኳት የመጀመሪያዋ የርቀት ግብ በጣም ማራኪና ቡድናችንንም ወደ ጨዋታው ሪትም እንዲገባ ያደረገች እና በጣም የተደሰትኩባት ነበረች። ከእሷ ውጪም ሌላኛዋ የድል ግቤንም በጥሩ ሁኔታ ስላስቆጠርኩ ደስታዬ እጥፍ ድርብም ሊሆንልኝ ችሏል”።

በሌሎች ጨዋታዎች ግብ ያስቆጥር እንደሆነ

“በአሁኑ ግቦቼ ብቻ ተወስኜ መቅረትን ስለማልፈልግ እንደ አንድ ተጨዋችማ ይሄማ የማይቀር ነው፤ ወደፊት የምናየው ቢሆንም ግቦች ግን ይኖሩኛል”።

ስለ ተጋጣሚያቸው

“ወላይታ ድቻ ጥሩ ቡድን ነው። ኳስ ይዞም ይጫወታል። በእዛም እኛን በልጠውናል። እኛ ደግሞ ግብ በመሞከር ከእነሱ ተሽለናል። ስለ አጨዋወታቸው ግን ተነግሮን ስለነበር ነው እኛ ደግሞ በመልሶ ማጥቃቱ ላይ ጥሩ ስለነበርንና ከጨዋታ የሚፈለገው ደግሞ 3 ነጥብ ስለሆነ ልናሸንፋቸው የቻልነው”።

በቀጣይነት ስለሚኖራቸው ጨዋታዎች

“እነዚህ ጨዋታዎች ለእኛ ከባድ እየሆኑብን የሚሄዱ ናቸው። ስለዚህም ከአሰልጣኛችን ጋር ተነጋግረንና ጠንክረን ሰርተን ለግጥሚያዎቹ ለመዘጋጀት ከወዲሁ እናስባለን፤ የግጥሚያዎቹ አሸናፊ ለመሆንም ከፍተኛ ጥረትን እናደርጋለን”።

ስለ ስብስባቸው

“ብዙ አዳዲስ ተጨዋቾችን ነው ክለቡ እኔን ጨምሮ ሊያስፈርምና በቡድኑ የተጨዋቾች ስብስብ ውስጥም ሊይዝ የቻለው። አሁን ላይም ከነባሮቹ ጋር ወደ መግባባቱ ላይ እያመራን ስለሆነም በቀጣይ ጊዜ ምርጥ ቡድንን ይዘን ለመቅረብ እንጥራለን”።

በመጨረሻ

“የእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኔን በክለብ ተጨዋችነት ብቻ ሳይሆን እስከ ብሄራዊ ቡድን ደረጃ እና ወደ ውጪም በመውጣት እስከመጫወት ደረጃ አስጉዤ ሀገሬን ማገልገል እና መጥቀም እፈልጋለሁ። ያን እድል ለማግኘትም ጠንክሬ እሰራለው”።

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website