ሰበታ ከተማ የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቀሪ የአንድ ዓመት ክፍያ እንዲከፈለው እግር ኳስ ፌዴሬሽኑን ጠየቀ

የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሰበታ ከተማን የአንድ አመት ክፍያ ተመላሽ አለማድረጉ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ በ2012 የሁለት አመት ኮንትራት ፈርሞ ሰበታ ከተማን የተቀላቀለው አሰልጣኙ የ2012 ፕሪሚየር ሊግ በተለይ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተቋረጠበት 17ኛው ሳምንት ድረስ በተደረጉ 17 ጨዋታዎች 6 ጊዜ ረትቶ 4 ጊዜ ብቻ ወጥቶ 7 ጊዜ ተሸንፎ በ22 ነጥብና 1 የግብ እዳ 11ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡

የሰበታ ከተማ አመራሮች ለ2013 መርሃ ግብር ከአሰልጣኙ ጋር ዝግጅት ለመጀመር የሚያስችል የአዳዲስ ተጨዋቾች ዝውውርና የተሰናበቱትን የመሸኘት ስራ እየሰሩ ባሉበት ሰዓት የኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱን ውል አናድስም ያለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ2 አመት ስምምነት በመስጠት አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ከሰበታ ከተማ ላይ ሀገራዊ ጥሪ ቅድሚያ እንደሚሰጥ በመተማመን መውሰዱን የቅርብ ጊዜ እውነታ ነው፡፡

በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቦታ ሁነኛ ተተኪ ሲያፈላልግ የሰነበተው ሰበታ ከተማ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱን የክለቡን ያለመውረድ የቤት ስራ በመስጠት ካስፈረመና ወደ ዝግጅት ከገባ ቀናት በኋላ ይፋ የሆነው መረጃ ክለቡ የቀድሞ አሰልጣኙ ቀሪ የአንድ አመት ደመወዝ ክፍያ እንዲመለስለት መጠየቁ ተሰምቷል፡፡ ከታማኝ ምንጭ መረጃውን ያገኘችው ሀትሪክ ከክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ ጋር በነበራት ቆይታ የመረጃውን እውነተኝነት ማረጋገጥ ችላለች፡፡

ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ አለማየሁ ምንዳ ለሀትሪክ እንደተናገሩት “ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር ያለን ግንኙነት በህጋዊ መንገድ አልተቋጨም ቀሪ የአንድ አመት ክፍያ እንዲመለስልን ፌዴሬሽኑን ጠይቀናል ለብሔራዊ ቡድን በመመረጡ አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ልቀቁልን ብለው ደብዳቤ ፃፉልን እኛም ለሀገራዊ ጥሪ ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል ብለን ጥያቄውን ተቀብለናል ነገር ግን ቀሪ የአንድ አመት ክፍያ ሊመልስልን ይገባል ይህንንም ለፌዴሬሽኑ ጠይቀን ምላሽ እየጠበቅን ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዋና ስራ አስኪያጁ እንደሚሉት “ፌዴሬሽኑ ላቀረበው ጥያቄ ተገቢ ምላሽ መስጠታችንን እንኮራበታለን ነገር ግን አሰልጣኙ የአንድ አመት ውል እያላቸው ስለለቁ የወሰዱትን የአንድ አመት ክፍያ እንዲመልሱልን ወይም ፌዴሬሽኑ እንደሚልስልን ጠይቀናል በቀጣይ ፌዴሬሽኑ የሚሰጠውን ምላሽ እየጠበቅን ነው” ሲሉ ያለውን ሁኔታ ለሀትሪክ ገልፀዋል፡፡

ከአሰልጣኙ ጋር ያላቸው ግንኙነት እስካሁን አልተቋረጠም ወይ? አሰልጣኙ አናግራችሁት ከሆነ ምን ምላሽ አገኛችሁ የተባሉት አቶ አለማየሁ “አሰልጣኝ ውበቱን ስለ ገንዘቡ የምንጠይቀው ወደ ክለባችን መጥቶ ክሊራንስ ሲጠየቀን ነው ብለን ብንጠብቅም ክሊራንሱን እስካሁን ከኛ ጋር አልወሰደም በአጠቃላይ ግን ፌዴሬሽኑ ትብብር ጠይቃችሁን እሺ ካልን ገንዘባችንን እንዲያስመልሱልን ወይም በነርሱ በኩል እንዲከፈለን ጠይቀናል በቀጣይ የሚሆነውን አብረን አናያለን” በማለት ለሀትሪክ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ከሀትሪክ ጥያቄ የቀረበላቸው የፌዴሬሽኑ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በበኩላቸው” በአሰልጣኙና በክለቡ መሀል ያለው ስምምነት ጋር ተያይዞ እኛን የሚመለከተን ነገር በውላችን ውስጥ የለም፡፡ ነገር ግን ሰበታ ከተማ ያቀረበውን ጥያቄ ለስራ አስፈፀሚ ኮሚቴ ቀርቦ ምላሽ የሚሰጥበት ይሆናል” በማለት የፌዴሬሽኑን አቋም ገልፀዋል፡፡ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ሹመታቸው ይፋ በተደረገበት እለት ከሰበታ ከተማ ጋር የነበርዎት ውል በስምምነት ተጠናቀቀ ወይ ሲባሉ አዎ ሕጋዊ በሆነ ሂደት እያለቀ ነው ብለው የነበረ ቢሆንም ከክለቡ የተሰማው መረጃ ግን ቀሪ የአንድ አመት ክፍያ እንዳልመለሱ ነው፡፡ ሀትሪክ በጉዳዩ ዙሪያ ለአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጥያቄ አቅርባላቸው በሰጡት ምላሽ “ክለቡ ላከ የተባለው ደብዳቤ አልደረሰኝም አላየሁትምም በቀጣይ የደብዳቤውን ይዘት ካየሁ በኋላ ምላሽ የምሰጥበት ይሆናል” በማለት መልሰዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አዲሱ የሰበታ ከተማ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ክለቡ ከሰጣቸው ኃላፊነት አንዱ የሆነውን የታዳጊ ምልመላ ላይ ቃላቸውን ጠብቀው እየሰሩ መሆናቸውን ክለቡ አሳውቋል፡፡ አሰልጣኙ በእርሣቸው ስር የመጀመሪያ ፈራሚ የሆነውን ቢያድግልኝ ኤሊያስን ጨምሮ ሙሉ ቡድናቸውን በመያዝ ጠንካራ ዝግጅት እያደረጉ ሲሆን ሊጀመር 15 ቀን በቀረው የፕሪሚየር ሊጉ መርሃ ግብር ላይ ጥሩ ተፎካካሪ ለመሆን እየተዘጋጁ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡ ከዚህ ጎን ወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ለክለቡ ታዳጊ ፕሮጀክት ተተኪዎችን ለመፍጠር ተግባራዊ ስራ እየሰሩ መሆናቸው ታውቋል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport