ምንጊዜም ካፒታል ሰርቪስ አክሲዮን ማኅበር

ከኩራዝ ንብረት እስከ 240 ሚሊዮን ብር ሀብት ባለቤት ለመሆን የሚደረግ አዲስ ታሪክ የማፃፍ ሩጫ
በጣሊያን ወረራ ወቅት የተመሠረተው ክለብ በወቅቱ ያስመዘገበው ንብረት በኩራዝ ጭስ የምትሠራ አንዲት ማህተም ብቻ ነበረች፡፡ ዛሬ ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ በተለያዩ ውጣ ውረዶች፣ መሰናክሎችና ፈተናዎች ውስጥ አልፎ የፈረጠመ አስተማማኝ የፋይናንስ ጡንቻ ያለው በደጋፊዎቹ ባለቤትነት የሚተዳደር ክለብ ለመሆን የስኬት ጉዞውን አንድ ብሎ ጀምሯል፡፡

የክለቡን የፋይናንስ አቅም ይበልጥ ለማጠናከርና ክለቡን በሁለት እግሩ ለማቆም ይረዳል ያለውን የምንጊዜውም ካፒታል ሰርቪስ አክስዮን ማህበርን በሀገራችን እግር ኳስ ታሪክ በመመስረት የመጀመሪያ የሚያደርገውን ሥራውን ባለፈው ቅዳሜ በሸራተን አዲስ በይፋ አስጀምሯል፡፡

የአክሲዮን ማህበሩ ካፒታል 244 ሚሊዮን የሚደርስ እንደሆነ በተገለፀበት የሸራተን አዲሱ የአክሲዮን ማህበሩ ሽያጭ ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ ይፋ እንደተደረገው የዚህ አክሲዮን ማህበር አባል ለመሆን መስፈርት መቀመጡ የተገለፀ ሲሆን የአክሲዮን ማህበሩ አባል የሚሆኑት የስፖርት ማህበሩ የፀና አባልነት ላላቸው ሰዎችና ድርጅቶች ብቻ በጥሬ ገንዘብ የሚሸጡ እንደሆነ የስፖርት ማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አብነት ገ/መስቀልና የሥራ አመራር ቦርዱ ዋና ፀሐፊ የሆኑት አቶ ነዋይ በየነ በየተራ በሰጡት መግለጫ ላይ አሳውቀዋል፡፡

የዕለቱን ቅዱስ ጊዮርጊስን ወደ ዘመነ የክለብ አወቃቀርና የፈረጠመ የፋይናንስ አቅም ያሸጋግረዋል የተባለውን የአክሲዮን ማህበር ሽያጭ በይፋ መጀመሩን ያበሰሩት የስፖርት ማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አብነት ገ/መስቀል “የቅዱስ ጊዮርጊስን ራዕይና ተልዕኮ ለማሳካት በጠንካራ የፋይናንስ መሠረት ላይ ለማቆም የሚያስፈልገውን አማራጭ የገቢ ምንጭ ለመፍጠርና አሁን ያለውን የደጋፊውን ባለቤትነት የሚመራበትን ስርዓት አጠንክሮ ራሱን ለረዥም ጊዜ በፋይናንስ ብቁ ለማድረግ ያለውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል የንግድ ተቋም ለማቋቋም” ያለመ እንደሆነ የእንኳን ደህ መጣችሁ ንግግራቸውን በማስቀደም ይፋ አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ በምስረታ፣ በስኬታማ ጉዞ፣ በውጤታማነት የሀገሪቱ መኩሪያ ብቻ ሣይሆን ፈር ቀዳጅ በመሆንም ተለይቶ የሚታወቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁንም በመሪነትና በፈር ቀዳጅነት የሚያስቀምጠውን የአክስዮን ማህበር “ምንጊዜም ካፒታል ሰርቪስ አ.ማ በሚል ስያሜውን ሰኔ 11 ቀን 2012 ዓ.ም በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስመዝግቦ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብቷል፡፡

የአክሲዮን ማህበሩ መመስረትን በጉጉት ሲጠበቅ እንደነበር በመክፈቻ ንግግራቸው ያካተቱት የቦርድ ሰብሳቢው አቶ አብነት ገ/መስቀል “ያለፍንባቸው መንገዶች ያጋጠሙን ፈተናዎች መሰናክሎች እጅ ሲያሰጡን በፀና ቤተሰባዊ አቋም መንፈሳችን በአሸናፊነት መዳረሻችንን ድል አድርጊነት አድርገን የመጣንበት ጎዳና ታላቅነታችን ፈክቶበት 85ኛው አመት ላይ በአዲስ እምርታ ወደ ሌላ የስኬት ምዕራፍ ተሸጋግረናል” በማለት የአክስዮን ማህበሩ የተመሠረተበትንና የክለቡን ሂደት ባሳዩበት ንግግራቸው “በአክስዮን ሽያጩ ታሪክ እንደምትሠሩ በመተማመን አባላቶችና አጋር ድርጅታችንን በሙሉ አክሲዮን በመግዛት የታሪክ ባለቤት እንድትሆኑ በማለት ለክለቡ ደጋፊዎችና አጋር ድርጅቶች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የምንጊዜውም ካፒታል ሰርቪስ አክሲዮን ማህበር በይፋ መመስረትን አስመልክቶ በማስቀጠል ስለ አክሲዮን ማህበሩ አላማ ዘርዘር ያለና ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት የስራ አመራር ቦርዱ አባልና ዋና ፀሐፊ የሆኑት አቶ ነዋይ በየነ “ቅዱስ ጊዮርጊስ በተለያዩ ደረጃዎች በተለያየው አርበኞች በተወሰነ ደረጃም ተዓምራዊ በሆነ መልኩ እስከ አሁን ዘልቋል፤ ከአሁን በኋላ ደግሞ ማስቀጠልም የእኛ ድርሻ ነው፤ በሰለጠነና ዘመናዊ በሆነ መንገድ ክለባችንን ተፎካካሪ፣ ኢንተርናሽናል ክለብ አድርጎ ለማቆየት ስንል ዛሬ ይፋ እያደረግን ያለውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበርን በፋይናንስ ለመደገፍ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለን ያስብነውን የአክሲዮን ማህበር ይፋ አድርገናል ብለዋል፡፡

“ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ ክለባችን የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የፋይናንስ ጥያቄዎች እየበረቱና እየከበዱ ስለመጡ አማራጭ የገቢ ምንጭ ለመፍጠር፣ አሁን ያለውን የደጋፊዎች ባለቤትነት ቅርፁን ሳንቀይር እንዳለ ለማስኬድ በሚል የተዋቀረ የአክሲዮን ማህበር ነው” በማለት ስለ አላማው ማስረዳታቸውን የቀጠሉት አቶ ነዋይ በየነ “ሊቀመንበራችን እንደተናገሩት የሚቋቋመው አዲሱ አክሲዮን ማህበር የሚሸጠው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የፀና አባልነት ላላቸው ብቻ ነው” ብለዋል፡፡

“የምናቋቁመው የአክሲዮን ማህበር በሀገሪቱ ባሉ በተቋቋመ የንግድና ተያያዥ ህጎች መሠረት የሚከናወን ሲሆን የጠቅላላ ካፒታሉን 244 ሚሊዮን ብር አድርጎ የሚነሣ ይሆናል፤ ከዚህ ውስጥ የስፖርት ማህበሩ አሁን ያለው ንብረት በውጪ በገለልተኛ ኦዲተር በተረጋገጠው መሠረት 94 ሚሊየን ብር በአይነት የሚያዋጣ ይሆናል፤ አንድ ሰው ወይም አንድ ድርጅት መግዛት የሚችለው የአክሲዮን መጠን 120 ሚሊዮን ይሆናል ይህ ማለት 49% ፐርሰንት ማለት ነው” በማለት በንግግራቸው የቀጠሉት ዋና ፀሐፊው 51% ለደጋፊው ይሆናል” ብለዋል፡፡
“የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበርና ምንጊዜም ካፒታል ሰርቪስ አክሲዮን ማኅበር ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው” በማለት ያስመሩበት አቶ ነዋይ ዝቅተኛው የአክሲዮን ዋጋ አንድ ሺ ብር ሆኖ የፀና አባልነት ያላቸው ደጋፊዎች በግልም በቡድን ተደራጅተው በውልና ማስረጃ በፀደቀ ውክልና በጋራ መግዛት እንደሚችልም ገልፀዋል፡፡

የአክሲዮን ማህበሩ ሽያጭ ከሐምሌ 25/2012 ከጠዋቱ 3፡00 አንስቶ እስከ ታህሳስ 22/2013 ዓ.ም ከቀኑ 11፡30 ድረስ ለሽያጭ የሚቀርብ ሲሆን በምስረታ ላይ ያለው የማህበሩ አድራሻ በቅሎ ቤት ጋራድ ህንፃ በሚገኘው ኖክ የነዳጅ ማደያ አንደኛ ፎቅ ላይ መሆኑን ይፋ ያደረጉት ከፍተኛ አመራሮቹ የአክሲዮን ማህበሩ የትርፍ ድርሻ በሚከፋፈልበት ዙሪያም በጋራ አስረድተዋል፡፡
የሚመሰረተው የአክሲዮን ማህበር ዋና አላማ በተለያዩ የንግድ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ከስራው በሚገኘው ትርፍ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበርን ለመደገፍና ለማጠናከር በመሆኑ የአክሲዮን ማህበሩ ሥራ ከሚጀመርበት በጀት አመት ጀምሮ ቢያንስ ለ10 አመታት ለባለ አክሲዮኖች የትርፍ ድርሻ ክፍፍል እንደማያደርግ በእለቱ ይፋ ያደረጉት አመራሮቹ ወደ አክሲዮን ማህበሩ የሚመጡ ይሄንን አምነውበትና ተስማምተውበት በንግድ ሕጉ አንቀፅ 389 መሠረት ትርፍ እንደ ማይጠይቁ ተስማምተው በፊርማቸው ማረጋገጥ እንዳለባቸውም አስረግጠው ገልፀዋል፡፡
የአክሲዮን ማህበሩ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ የመሳተፍ የንግድ እንቅስቃሴ የማድረግ ሃሳብም እንዳለው በመድረኩ የተናገሩት የሥራ አመራር ቦርዱ አባልና ዋና ፀሐፊው አቶ ነዋይ በየነ ምንጊዜም ካፒታል ሰርቪስ አክሲዮን ማህበር እንደ አስፈላጊነቱ በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር የኢትዮጵያ የታክስ፣ የኢንቨስትመንቶችና የንግድ ሕጎችን ተከትሎ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት አክሲዮን ማህበሩ ሕንፃዎችን በመግዛት፣ በማከራየት እንዲሁም እንደ አስፈላጊነታቸው በትርፍ በመሸጥ የተለያዩ ኩባንያዎችንና አክሲዮኖችን መግዛት የገዙትንም አክሲዮኖች የትርፍ ድርሻዎችን ማስተዳደርና ለተገቢው ጥቅም ማዋልና በተለያዩ የአገልግሎት የማምረቻ፣ የማከፋፈያ፣ የትራንስፖርትና የሎጀስቲክስ እንዲሁም በኢንዱስትሪ ዘርፎች ለብቻቸውም ሆነ ከሌሎች ጋር በሽርክና የመስራት ሃሣብ እንዳለም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ስፖርት አንጋፋውን ክለብ አሁንም ከፊት የሚያስቀምጠውን ይሄንን ታሪካዊ አክሲዮን ማህበር የማደራጀት ሥራን በበላይነት የሚመሩት የክለቡ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብነት ገ/መስቀል፣ የሥራ አመራር ቦርድ አባልና ዋና ፀሐፊ አቶ ነዋይ በየነ፣ የክለቡ የልብ ምት የሆኑት አቶ ጀማል አህመድ፣ የቦርድ አባሉ አቶ ዳዊት ውብሸት፣ አቶ ወንዱ ለገሠና የህግ ባለሙያው አቶ ሚሊዮን አለሙ መሆናቸውን በዕለቱ ተገልጿል፡፡

ቁጥሮች ስለ ምንጊዜውም ካፒታል አክሲዮን ማህበር
240,000 ለሽያጭ የቀረበው የአክሲዮን አጠቃላይ ብዛት
120,000 ሊገዛ የሚችለው ከፍተኛው የአክሲዮን ብዛት 120,000 አክሲዮኖች
1 ሊገዛ የሚችለው አነስተኛው የአክሲዮን መጠን 1 አክሲዮን
150,000 በጥሬ ገንዘብ የሚሸጠው የአክሲዮን ብዛት 150,000
94,000 በአይነት የሚሸጠው የአክሲዮን ብዛት 94,000

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.