ካደረጋቸው አራት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ሁሉንም በሽንፈት የጨረሱት የጦና ንቦቹ አሰልጣኙን እና ስራ አስኪያጁን ከሀላፊነት አንስቷል።
በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እስከ አሁን ያደረጓቸውን አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ የተሳናቸው የወላይታ ድቻዎች የቦርድ አመራሩ በዛሬው ዕለት ማምሻውን ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል። በዚህም መሠረት ሀትሪክ ስፖርት በደረሳት መረጃ መሠረት ክለቡን ለሁለተኛ ጊዜ የማሰልጠን ዕድልን ያገኙት የቀድሞው የደቡብ ፓሊስ ፣ ወልቂጤ ከተማ እና መቻል አሰልጣኝ የነበሩት የክለቡ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ከሀላፊነት ሲነሱ የክለቡ ስራ አስኪያጅ በመሆን በመሐል ለቀው በድጋሚ ከዓመታት በፊት የተመለሱት እና ለረጅም ጊዜያት በሀላፊነት ያገለገሉት አቶ አሰፋ ሆሲሶ በተመሳሳይ ከመንበራቸው ተነስተዋል።
አሰልጣኙ እና ስራ አስኪያጁን ማምሻውን ያነሳው ወላይታ ድቻ በጊዜያዊነት ረዳት አሰልጣኙ ቴዎድሮስ ቀነኒን ሲሾም አቶ ምትኩ ሐይሌ ደግሞ በጊዜያዊነት ከዚህ ቀደም የመሩትን የስራ አስኪያጅነት ቦታ ተረክበዋል።



