የኢትዮጵያ ወንድ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን የማበረታቻ ሽልማት እና እውቅና ሊበረከትለት ነው ፡፡

የኢትዮጵያ ወንድ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን የማበረታቻ ሽልማት እና እውቅና ሊበረከትለት ነው ፡፡

ግንቦት 4/2013 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ወንድ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ከ8 አመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን ተከትሎ በመንግስት እና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አማካኝነት የእውቅና እና ሽልማት ሊበረከትለት መሆኑን የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮምሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በጋራ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታወቁ ፡፡

ብሄራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን ተከትሎ በወቅቱ በተለያዩ ምክንያቶች የሽልማት እና የማበረታቻ ፕሮግራም ባይካሄድም የሀገራችን ህዝቦች በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች አደባባይ በመውጣት በከፍተኛ ድምቀት የጀግና አቀባበል በማድረግ ደስታቸውን እንደገለፁ ኮምሽነሩ በመግለጫቸው አንስተዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ወንዶች እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን ለ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በማለፉ ሀገርንና ህዝብን በማኩራታቸው እና በቀጣይ ባለው አፍሪካ ዋንጫም ሆነ በሌሎች ውድድሮች ላይ ተፎካካሪ ሆኖ እንዲቀርብ የዝግጅት ስራ ለመስራት ዓላማ ተደርጎ የተዘጋጀ ፕሮግራም እንደሆነ ታውቋል ፡፡

ብሄራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ ለስፖርቱ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ፣ መነቃቃትን የፈጠረ ቢሆንም ቀጣይነት እንድኖረው ታዳጊ ወጣቶች ላይ መስራት እና ኤሊት ስፖርተኞችን በጥራትና በስፋት ማዘጋጀት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የገለፁት ኮምሽነሩ ብሄራዊ ቡድኑ ቀጣይ ባሉት ውድድሮች ላይ ጠንካራ እና ተፎካካሪ እንዲሆን የወዳጅነት ጨዋታዎችን ጨምሮ ሀብት ተመድቦ በቂ የዝግጅት ጊዜ ማግኘት እንዳለበት አሳስበዋል ፡፡

መንግስት ለስፖርቱ እድገት ከፍተኛ ስራ እየሰራ እንደሆነ ያነሱት አቶ ኤሊያስ ሽኩር ከጥረጊያ ጀምሮ ትላልቅ ስታዲየሞችን ፣ ከስልጠና ጣቢያ እስከ ስልጠና ማዕከላት እንዲሁም ከ26 በላይ ለሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ 3ኛ ዲግሪ በስፖርት ሳይንስ ሙያተኞችን ለማፍራት ሀብት መድቦ እየሰራ እንደሆነ ገልፀዋል ፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው እንዳሉት የአፍሪካ ዋንጫ የተካሄደበትን ጊዜ እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተሳተፈበትን ጊዜ በማነፃፀር ሀገራችን በቀጣይ በዚህ እና በሰል ተሳትፎዎች ውጤታማ ለማድረግ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ጥረት እንደሚጠይቅ በመግለጫቸው አስገንዝበዋል ፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በኩል 6 ሚሊየን ብር ለሽልማት የተወሰነለት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን የሀገርን አርማ ይዞ የሚሳተፍ እንደመሆኑ መጠን ሽልማት ሰጥተን የምንለያይበት ሳይሆን የወደፊት ስራ ምን መሆን አለበት የሚለውን እቅድ መነሻ ተደርጎ እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል ፡፡

የእውቅና እና የማበረታቻ ፕሮግራሙ ቅዳሜ ግንቦት 7/2013 ዓ.ም በአዋሳ ከተማ ሌዊ ሪዞርት ከ10 ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ በመግለጫው ተነግሯል ።

በሽልማት ፕሮግራም ላይ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችን ጨምሮ ታዋቂ አርቲስቶች ፣ የስፖርት ኮሚሽን አመራሮች ፣የክልልና ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮምሽነሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ታውቋል ፡፡

Hatricksport website Editor

Twitter

kidus Yoftahe

Hatricksport website Editor