ሲዳማ ቡና በእኛ ዘመን አይወርድም፤ ማሊያውን ለብሶ እንደተጫወተ ኢት.ቡና ስኬታማ በመሆኑ እደሰታለሁ እንጂ አልከፋም” ፈቱዲን ጀማል (ሲዳማ ቡና)

ታላቁ የረመዳን የጾም ወር በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የተለየ ወር ነው፤ ሰዎች ስጋቸውን ጎድተው በጾም በፀሎት ወደ ፈጣሪያቸው “አላህ” የሚቀርቡበት የተቀደሰ ወር ነው፤ በጾም በፀሎት ፈጣሪን ከማሰብ ባለፈ ያለው እንደአቅሙ ምስኪኖችን የሚረዳበት ለሌሎች የሚያስብበት ቅዱስ ወርም ነው፤ የዛሬው እንግዳችን የሲዳማ ቡናው ፈቱዲን ጀማልም ይህንን የእስልምና አስተምህሮት በመከተል ድፍን አንድ ወሩን ስራውን በአግባቡ እየሰራ በመጾም ኃይማኖታዊ ግዴታውን ሲወጣ ቆይቷል፡፡

“ኢድ ሙባረክ” የሚለውን የመልካም ምኞት መግለጫ ያስቀደመው የሀትሪክ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ በፕሪሚየር ሊጉ እየተጫወተ የአንድ ወር ጾሙን በአግባቡ የተወጣውን ፈቱዲን ጀማልን እየጾሙ መጫወት አይፈትንም? የሚለውን ወቅታዊ ጥያቄ አስቀድሞ ሲዳማ ቡና ይወርዳል ወይስ አይወርድም? የሚለውን ፍርጥም ያለ ጥያቄ ጠይቆ የቀድሞ ክለብህ ኢትዮጵያ ቡና ስኬታማ ሆኗል በተቃራኒው ደግሞ አዲሱ ክለብህ ላለመድውረድ እየተጫወተ ነው ይህ ሁኔታ ምነው ከቡና ባለቀክኩ ያሰኘሃል? የኢትዮጵያ ቡና ውጤት ያስደስተሃል ወይስ ያስከፋሀል? የሚሉና ሌሎች ፈታኝ ጥያቄዎችን ጠይቆት ምላሹን ከዚህ በታች ባለው መልኩ አቀናብሮታል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለእስልምና እምነት ተከታዮች “ኢድ ሙባረክ” እያልን ቆይታችሁን እንድታውሱን በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

ሀትሪክ፡- …የረመዳን የጾም ወር የሚፈታው ነገ ነው…ከዚህ አንፃር ቀድሜ አንተንም የሙስሊሙን ማህበረሰብ ረመዳን ከሪም ማለት እወዳለሁ…?…

ፈቱዲን፡- … በጣም አመሰግናለሁ…አሌና አሌኩም ብያለሁ እኔም…

ሀትሪክ፡- …ብዙዎች የዘንድሮው ረመዳን ቶሎ አለቀብን ብለው በጣም ሲቆጩ እሰማለሁ…ለፈቱዲንስ…?…

ፈቱዲን፡- …እውነት ነው…በእኔ ውስጥም ያለው ተመሳሳይ የቁጭት ስሜት ነው… የዘንድሮው ምንም ሳናውቀው ነው ወሩ ያለቀብን…የታላቁ የረመዳን የጾም ወር እንደምታውቀው በአመት አንዴ ብቻ ስለሚመጣ በጉጉት፣በጣም በስስት ነው የምንጠብቀው…ወሩ ከመቼው እንደሚበር ሳስበው ይገርመኛል…የታላቁ የረመዳን የጾም ወር ብዙ ምንዳ የምናገኝበት በመሆኑ እንዲህ ፈጥኖ በማለቁ በጣም ያስቆጫል…

ሀትሪክ፡- …የአሁኑን የረመዳን የጾም ወር ትዳር ከያዝክ በኋላ የመጀመሪያው ረመዳን ነው…?…ምን የተለየ ስሜት አለው…?…

ፈቱዲን፡- …በእርግጥ ሁሉም በጣም ደስ የሚል ነገር አለው…፤…ነገር ግን የራሴን አዲስ ህይወት ጀምሬ የማከብረው የመጀመሪያ በዓል በመሆኑ የራሱ የሆነ የተለየ ስሜት አለው…ትዳር ይዘህ ለወግ ለማዕረግ በቅተህ ስትጾም በራሱ የሆነ የተለየ የደስታ ስሜት አለው…እቤት ስግባ ከበፊቱ የተለየ ድባብ ነው የሚጠብቀኝ…ያ ደግሞ የሚጨምረው ነገር አለ…15 ቀን ያህል ድሬደዳዋ ስለነበርን ይሄን ምርጥ አጋጣሚ ሳላገኝ ነበር የቆየሁት…አሁን ግን ከትዳር አጋሬ ጋር ታላቁን የረመዳንን የጾም ወር ለነፍሳችን በሚሆን መልኩ አሳልፈናል…በረመዳን ስትጾም ለራስህ ብቻ አይደለም… ከባለቤቴ ጋር በአቅማችን ምስኪኖችን ለማስፈጠር ሞክረናል…ይሄንን ስታደርግ ከአላህ ብዙ በረከቶችን ታገኛለህ….

ሀትሪክ፡- …ረመዳን ማለት ለአንተ…?…

ፈቱዲን፡- …ረመዳን በአመት አንዴ ብቻ የምታገኘው…ስጋህን ጎድተህ አላህን የምታመሰግንበት፣ ለምስኪኖች የምታስበበት፣ ከፈጣሪ ጋር በፀሎት በተደጋጋሚ የምትገናኝበት ቅዱስ ወር ነው…ማንኛውም ሰው ስጋ ለባሽ ሰው በመሆኑ ብቻ በህይወት እያለ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሚሠራቸው ብዙ ኃጢአቶች ይኖራሉ… እነዚህን ሀጢአቶች ጾም ፀሎትህን ተጠቅመህበት በምላሹ ከፈጣሪ ምህረትን የምታገኝበት የተቀደሰ ወር ነው የረመዳን የጾም ወር… በተለይ ያሳለፍነው የመጨረሻው 10 ቀናት ትልቁን ሀጅር (ምንዳ) የምታገኝበት ስለሆነ… እየፀለይክ እየሰገድክ የምታሳልፈው ልዩ የጾም ወር ነው… ለሰራኸው መልካም ስራ አላህ ምንዳውን ይቀበልህ ማለት ነው… በዚህ አጋጣሚ ለሙስሊም ወገኖቼ አላህ መልካም ኢድ ያድርግልህ እለለው፡፡

ሀትሪክ፡- …በየቀኑ ትሬይኒንግ እየሠሩና እየተጫወቱ ሙሉ ቀን መጾም አይፈትንም…?…

ፈቱዲን፡- …እኔ እስከአሁን መፈተኔ አይታወቀኝም…እንደውም በረመዳን የጾም ወር የሆነ የተለየ ጉልበትና ኃይል እያገኘሁ እንደምጫወት ነው የማውቀው…እየጾምኩ መጫወት ለብዙ አመታት ያደረኩት በመሆኑ ተላምጄዋለሁ(Adapt)አድርጌዋለሁ ማለት ነው የሚቀለኝ…ከአላህ ብርታቱንና ጥንካሬውን ስለማገኝ አንድም ጊዜ ተፈትኜ አላውቅም…

ሀትሪክ፡- …ድሬዳዋ ላይ ስትጫወቱ የማታ የ1፡00 ጨዋታ ሲሆን ለማፍጠር አትቸገሩም…?…

ፈቱዲን፡- …ከማታው ጨዋታ ይልቅ ትንሽ ፈተን ለማድረግ የሚሞክረው የ10:00 ሰዓቱ ጨዋታ ነው…ምክንያቱም ለ10:00 ሰዓቱ ጨዋታ በጣም ከባድ ፀሐይ ባለበት በዘጠኝ ሰዓት ስለምናሟሙቅ ጾሙ ከፀሐዩ ጋር ተደምሮ ለማስቸገር ይሞክራል… የማታው ጨዋታ ግን ለእኛ እንደውም በጣም የተመቸ ነው…ድሬዳዋ ላይ 12፡30 አካባቢ ስለነበር የአፍጥር ሰዓት…እያሟሟቅን የተወሰነች ደቂቃ ውሃ የሆነች ትንሽ ነገር ለመቅመስ እድሉን ስለምናገኝ የማታው ጨዋታ ይሻለናል…

ሀትሪክ፡- …ፈቱዲን ኢትዮጵያ ቡናን ከለቀቀ በኋላ ጠፍቷል…ኧረ እንደውም እየተረሳ መጥቷል የሚሉ አሉ…ትቀበለዋለህ…?…

ፈቱዲን፡- …(ሣቅ)… ኧረ አልጠፋሁም…ተረስቻለሁ ብዬም አላስብም…እንደዚህ የሚሉ ሰዎች ለምን እንዳሉ ምክንያቱን የሚያውቁት እነሱ ናቸው…አንድ ያለው እውነታ ግን ምንአልባት የቡድናችን ውጤትም ሆነ ደረጃው ዝቅ ስላለ ይሄ ሁሉን ነገር አስረስቶት ትኩረቱን ቀንሶት የተረሣሁ ወይም የጠፋሁ አስመስሎት ይሆናል…የውጤታችን መቀዝቀዝ ለእኛ ያለውን ትኩረት አቀዝቅዞት ይሆናል የሚል ግምቱ ነው ያለኝ… የቡድኑ ውጤት ወርዶ አንተ ለብቻህ ከፍ ብለህ የምትታይበት እድል አለመኖሩም ነው ብዬ አስባለሁ…ሌላው እንደ አንድ ተጨዋች የሆነ ቡድን ስትግባ ሁሉም ነገር እንደ አዲስ ነው የሚሆነው…በፊት በነበርክበት ክለብ ያለህን እዚህ የሌለህን እስክትላመድ ትንሽ ጊዜን የሚወስድ ነገር ተጨምሮ ካልሆነ በስተቀር…ጠፋህ ወይም ተረሳህ የሚለውን አልቀበለውም…

ሀትሪክ፡- …አንተ በግልህስ ፈቱዲን ኢትዮጵያ ቡና የነበረውን ያህል ገዝፎ እየታየ ነው ትላለህ…?…

ፈቱዲን፡- …በፍፁም አልቀበለውም…!…ምክንያቱም የሚታይና የሚታወቅ ስለሆነ… አሁንም መልሴ ከላይ እንዳልኩህ ነው…ቡድናችን በውጤትም በደረጃም በጣም ስለቀዘቀዘ ለብቻዬ ተለይቼ የምታይበት እድል የለም…ደግሞም እኔ ብቻዬን በጣም ጎልቼ መታየት ሳይሆን ቡድኔ በውጤትም በደረጃም ጎልቶ ከፍ ብሎ እንዲታይልኝ ነው የምፈልገው…አሁን እንደ ቡድን በተወሰነ ደረጃ እየተለወጥን እየተሻሻል የመጣንበት ሁኔታ አለ ብዬ ነው የማስበው…

ሀትሪክ፡- …ከዚህ አንፃር ፈቱዲን ሲዳማ ቡናን እንደፈለገው አግኝቶታል ተመችቶታል…?…ብዬ ጥያቄዬን ቀየር አድርጌ ብጠይቅህ መልስህ ምንድነው…?…

ፈቱዲን፡- …እንዳልኩህ የውጤቱና የደረጃችን ነገር የጠበኩትን ያህል ባያረካኝም…እንደ ክለብ በግሌ ሲዳማ ቡና በጣም ተመችቶኛል ነዋ መልሴ…

ሀትሪክ፡- …በፊት ስትጫወትበት የነበረው ኢትዮጵያ ቡና ለዋንጫና ሁለተኛ በመውጣት የሚገኘውን ሀገርን የመወከል እድል ለማግኘት እየተጫወተ ነው…የአንተ አዲሱ ክለብ ሲዳማ ቡና ደግሞ በተቃራኒው ውጤት ርቆት ላለመውረድ እየተጫወተ ነው…እነዚህ እውነታዎች ወደ ሲዳማ ቡና ምነው ባላመራው የሚል ፀፀት በውስጥህ እንዲፈጠር ያደርጋሉ…?…

ፈቱዲን፡- …(በጣም ሳቅ)…በፍፁም…!…እንደዚህ አይነት ስሜት በውስጤ የለም… ምክንያቱም ይሄ እግር ኳስ በመሆኑ የውጤት መውረድና መውጣት የሚጠበቅ ነው… አላህ ያላለውን ነገር ብፀፀት፣ብፈርጥ ብነሳ የማመጣው ነገር ስለሌለ እሱ ይሁን ያለውን መቀበል ነው…ደግሞም እኔ ደስታዬንም፣ፀፀቴንም የምለካው በራሴ በቡድኔ ውጤትና ስኬት እንጂ ከሌላ ጋር በማነፃፀር አይደለም…አንተ በጥያቄህ ያነሳኸውን አይነት ነገር እያሰብኩ አዕምሮዬን አላስጨንቅም…ማሰብ ያለብኝ ስለምጫወትበትና ማልያውን ስለለበስኩት ክለብ ብቻ ነው…አሁን ውጤታችን በተለያየ ምክንያት ደካማ ሊሆን ይችላል…ግን ማን ያውቃል…?…ነገ ደግሞ ነገሮች በሌላ አዲስ መልክና ታሪክ ሊቀየርና ጥያቄህም አብሮ ሊቀየር ይችላል…(ሣቅ)…

ሀትሪክ፡- …የኢትዮጵያ ቡናን የዘንድሮ ግስጋሴ እንዴት አየኸው…?…

ፈቱዲን፡- …ኢትዮጵያ ቡና ዘንድሮ በጣም የተሻለ ሆኖ ነው የቀረበው…በጣም አሪፍ የሚባል የውጤትና የጨዋታም ጊዜ እያሳለፉ ነው…በተለይ ደግሞ ባህር ዳር ላይ በጣም ጥሩ ነበሩ…ምናአልባት ድሬዳዋ ላይ ጥሩ ጊዜን አላሳለፉም ብለን ካላነሳን በስተቀር ኢት.ቡና ዘንድሮ በጣም ጥሩ የሚባል ጊዜን እያሳለፈ ነው…ድሬዳዋ ላይ ቀዝቀዝ ያለውን ነገር ሀዋሳ ላይ አሻሽለው ከቀረቡ…ሀገር የመወከል ህልማቸውን ሊያሳኩ ይችላሉ የሚል እምነቱ ነው ያለኝ…

ሀትሪክ፡- …ኢት.ቡና በውጤትም በደረጃም ዘንድሮ የተሻለ ነው ከማለትህ አንፃር…ምነው ዘንድሮ እዚህ ቡድን ውስጥ ብኖር ኖሮ ብሎ ውስጥህ የተመኘበት አጋጣሚስ ነበር…?…

ፈቱዲን፡- …(አሁንም ሳቅ)…እውነት ለመናገር እንደዚህ አይነት ምኞት መመኘቴን አላስታውስም…ራሴንም በእንደዚህ አይነት የምኞት ሃሣቦች መጥመድም አልፈልግም… ምክንያቱም እኔ አሁን የሌላ ክለብ ተጨዋች ነኝ…የሚያስጨንቀኝም የምመኘውም ማልያውን የለበስኩለትን ክለቤን እንዴት ውጤታማ አድርገዋለሁ፣ከተደቀነበት አደጋስ እንዴት አድነዋለሁ…?…የሚለው ነው…

ሀትሪክ፡- …አሁን የሌላ ክለብ ተጨዋች መሆንህን ገልፀህልኛል…የሌላ ክለብ ተጨዋች ብትሆንም የቀድሞ ክለብህ ኢት.ቡና ውጤታማ በመሆኑ ይከፋሀል ብዬ አላስብም…?…

ፈቱዲን፡- …(በጣም ከት ብሎ እየሳቀ)…አንተ ምን አይነት ጠማማ ጥያቄ ነው የምትጠይቀኝ…(አሁንም ሳቅ)…ቡና ውጤታማ በመሆኑ ለምን ይከፋኛል..?… እንደውም ልንገርህ ማልያውን ለብሶ እንደተጫወተ፣ከክለቡ ጋር ትልቅ ታሪክ እንዳለው ተጨዋች የቡና ስኬታማ መሆን ያስደስተኛል እንጂ አያስከፋኝም…ደግሞም ተጨዋቾቹም አሰልጣኞቹም ስኬታማ የሆኑት ለፍተው ነው…ልፋቱን ደግሞ እኔም በተግባር ስለማውቀው አይከፋኝም…ተጨዋቾቹ አብዛኛዎቹ አብሬያቸው ያሳለፍኳቸው የምወዳቸው ጓደኞቼ በመሆናቸው በጣም ደስተኛ ነኝ…ኢት.ቡና እኮ ማልያውን ለብሼ የተጫወትኩበት፣ብዙ ፍቅር ያገኘሁበት፣ይበልጥ ከፍ ያልኩበት ከመሆኑ አንፃር ከመከፋት ይልቅ በጣም ነው የምደሰተው…

ሀትሪክ፡- …በተለይ ከኢት.ቡና ምን አስገረመህ…?

ፈቱዲን፡- …ሁሌም እንደ ቡድን ጥሩ ናቸው…በተለይ የአቡበከር ናስር ይበልጥ ከፍ ብሎ መታየት ግን የምጠብቀው ቢሆንም በእሱ የዘንድሮ አቋም የበለጠ አስገርሞኛል… አቡኪ ላይ ዘንድሮ በጣም ደስ የሚል ለውጥ ነው የታየው…ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴው በተጨማሪ ከአንድም ሶስቴም ሶስት ሀ (ሀትሪክ) ሠርቷል…ሜዳ ላይ ልዩነት ፈጣሪ ተጨዋች ሆኖ ከመታየቱ ውጪ የኢት.ቡና የአሸናፊነት ምስጢርም ነው…በዚህ የጾም ወር ወቅት ድሬዳዋ እያለን ከአቡኪና ከሌሎች ተጨዋች ጋር አብረን የምናፈጥርበት አጋጣሚ ስለነበር ከእሱ ጋርም በጣም እናወራ ነበር…ያመከናቸው እድሎች ስለነበሩ እንጂ…ከዚህ የበለጠ ሪከርዶች ይኖሩት ነበር…ከአቡኪ ጋር አብሬው የተጫወትኩበት ጊዜ አጭር ነው…በአብዛኛው ስገጥመው የነበረው በተቃራኒ ስለነበር አቅሙን አውቀዋለሁ…ከዚህ አንፃር የበለጠ ነገር ነው ከእሱ የምጠብቀው…አቡኪ ቡድኑ ውስጥ ሲኖርና ሳይኖር ልዩነት ይገባሃል…ብቻውን ቡድን ይዞ መውጣት የሚችል ተጨዋች ነው…በቀጣይም የተሻለ ነገር እንደሚያደርግም እጠብቃለሁ…

ሀትሪክ፡- …ከሁለት የሊጉ ጨዋታ በኋላ…ኢትዮጵያ ቡናን ከለቀክ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀድሞ ክለብህን በተቃራኒ ትገጥማለህ…የታወክበትን፣በአጭር ጊዜ ትልቅ ስኬትን ያገኘህበትን ክለብ በተቃራኒ ስለመግጠም ስታስብ ውስጥህ ምን ይልሃል…?…

ፈቱዲን፡- …ከኢት.ቡና ጋር እንዳልከው በአንደኛው ዙር በጉዳት ምክንያት የመጫወት እድል አላገኘሁም…በ24ተኛው ሳምንት የምናደርገው ጨዋታ ቡናን ከለቀክኩ በኋላ የማደረገው የመጀመሪያ ጨዋታዬ ነው…የሁለታችን ጨዋታ ሁለት የተለያየ ስሜት ይዞ የሚደረግ ጨዋታ ነው…ኢት.ቡና ሁለተኛነቱን አስጠብቆ የሀገር ውክልናን ለማግኘት …እኛ ደግሞ ላለመውረድ፣ራሳችን ለማትረፍ የምናደርገው ወሳኝ ጨዋታ ነው… ይሄንን ጨዋታ አስመልክቶ ብዙ ትኩረት የማደርገው በግል ጉዳዬ ሣይሆን ስለ ክለቤ ብቻ ነው…ክለቤን የማትረፍ ነገር ነው በዋናነት የሚያስጨንቀኝ…ከዚህ ውጪ ግን እንደ ቡና አይነት…ማልያውን የለበስኩት፣የታወኩበት፣የሀገሪቱ ትልቁን ክለብ በተቃራኒ ስትገጥም የተለየ የደስታ ስሜት ነው የሚሰማህ…በጣም ነው ደስ የሚለኝ…ማንነትህን ለማሳየትም የምትጫወትበት ጨዋታ ስለሚሆን በዚህ ደረጃ በመገናኘታችን ከፍተኛ የደስታ ስሜት ነው የሚሰማኝ…

ሀትሪክ፡- …ግብ የማግባት እድል ብታገኝ ደስታህን እንዴት እንደምትገልፅ ከወዲሁ ከራስህ ጋር ያወራህበት…ያስብክበት አጋጣሚስ አለ…?…

ፈቱዲን፡- …(የግርምት ሳቅ እየሳቀ)…ወይ አንተ ሰውዬ…!…እውነት ለመናገር በዚህ ዙሪያ አላሰብኩም…ግን ውስጤ የሚያውቀውን አንድ ነገር ልንገርህ…ቡና ትልቅ ክለብ ነው…ለክለቡም ትልቅ ክብር አለኝ…ብዙ ታሪክ ትልቅ ክብርም ያገኘሁበት ክለብ በመሆኑ የተለየ ነገር ስለማሳየት አላስብም…እንዳልኩህ ግብ የማግባት እድሉን ባገኝ ያልሆነ ባህሪ በማሳየት ሳይሆን ጨዋነት በተሞላበት ክለቡን በሚያከብር መልኩ ነው ደስታዬን መግለፅ የምፈልገው…

ሀትሪክ፡- …ከኢት.ቡና ከወጣህ ወደ አንድ አመት አካባቢ እየተጠጋህ ነው…ከቡና የሚናፍቀህ ወይም ፊትህ እየመጣ ድቅን የሚልብህ ነገር ምንድነው…?…

ፈቱዲን፡- …እንደ ኢትዮጵያ ቡና አይነት ትልቅ ክለብ ውስጥ ስትጫወት ሁሌም ከውስጥህ የማይጠፋ ውስጥህ ታትመው የሚቀሩ ብዙ ነገሮች አሉ…አንደኛውና የመጀመሪያው ልዩ የሆነው የደጋፊው ነገር ነው…የኢት.ቡና ደጋፊ ለእኔ ደጋፊ ብቻ አይደለም…የቤተሰቤ አንድ አካል ያህልም የምቆጥረው ደጋፊ በመሆኑ ሁሌም ፊቴ ላይ ቀድሞ የሚመጣ ሁሌም የሚናፍቅህ ደጋፊ ነው…የካሳዬ አራጌ ስልጠናና የተለየ ባህሪው፣የቡድኑ ተጨዋቾች…ብቻ ብዙ ነገር ይመጣብሃል…

ሀትሪክ፡- …ከዚህ በኋላ ምናልባት አንድ ቀን የቡናን ማልያ ትለብሳለህ ብሎ ውስጥ ሹክ ብሎህ ያውቃል…?…

ፈቱዲን፡- …(በጣም ሳቅ)…ወላሂ…ይሄን የሚያውቀው አላህ ብቻ ነው…(አሁንም ሳቅ)…

ሀትሪክ፡- …ሲዳማ አሁን የሚገኘው በወራጅ ቀጠና ውስጥ ነው…ከዚህ አንፃር ሲዳማ ይወርዳል…?…አይወርድም የሚል ፍርጥ ያለ ጥያቄ ብጠይቅህ መልስህ ምንድነው…

ፈቱዲን፡- …ሲዳማ ቡና…?…በፍፁም አይወርድም ነዋ መልሴ…(ሣቅ)…

ሀትሪክ፡- …እርግጠኛ ነህ ወይስ ፉከራ ነው…?…

ፈቱዲን፡- …(አሁንም ሳቅ)…የምን ፉከራ አመጣህ…?…

ሀትሪክ፡- …በዚህ ደረጃ ለመናገር የሚያበቃ ምክንያት አለህ…?…ምናልባት ከረሳኸው ሲዳማ ቡና እኮ ደረጃው ከሶስቱ ወራጅ ክለቦች አንዱ ነው…?…ይሄንን ልብ ብለሃል…?…

ፈቱዲን፡- …እሱ አልጠፋኝም…!…ሲዳማ ቡና አይወርድም ስልህ ያለ ምክንያት አይደለም…ደግሞም ሲዳማ ቡና መውረድ የሚገባው ክለብም አይደለም…ድሬደዋ ላይ ቡድናችንን በደንብ አይተኸው ከሆነ እየተሻሻለ እየተለወጠ እየመጣ ነው…አይወርድም ለማለት ያበቃኝ ሌላኛው ምክንያቴ ከእኛ በደረጃ ከፍ ያሉት ቡድኖች የሚበልጡን በአንድ ነጥብ ነው…ይሄ ደግሞ አንድ ጨዋታን ማሸነፍ ብዙ ነገሮችን ይለውጣል… ከዚህ ውጪ እኛ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ አለን…ያንን ስናሸንፍ የደረጃ መለዋወጥ ይመጣል…እኛ በቀጣይ የምናደርገው አምስት ጨዋታ ነው…ከእኛ የሚበልጡን ቡድኖች የሚያደርጉት አራት ጨዋታ ብቻ ነው…ከዚህ በመነሣት በሂሣብ ስሌት በወረቀት ላይ እንኳን ስታየው የመውረድ እድላችን በጣም ጠባብ ነው…

ሀትሪክ፡- …ሲዳማ ቡና ጥሩ ተፎካካሪ ቡድን ነው…ዘንድሮ ከሌላው ጊዜ በተለየ የመውረድ አጣብቂኝ ውስጥ የገባበትን ምክንያት ምንድነው ማለት እንችላለን…?…

ፈቱዲን፡- …አሁን እንደዚህ ነው እየተባለ የሚወራበት ሰዓት አይደለም…እንደዚህ አይነት ነገር አንዳንዴ እንድ ክለብ ያጋጥማል ብዬ ባልፍ ነው የምመርጠው…..

ሀትሪክ፡- …አንተ መናገር ከከበደህ ምናልባት የችግሩ አንደኛው ምክንያት ቡድኑ ውስጥ ከአንድነት ይልቅ መከፋፈል መኖሩ ይሆን…?…

ፈቱዲን፡- …ነገርኩህ እኮ አሁን እንደዚህ አይነት ነገሮችን በማንሣት ቡድኑ ላይ ለውጥ አናመጣም…እንደዚህ አይነት ጥያቄ የሚነሳበት መልስ የሚሰጥበትም ሰዓት ነው ብዬ አላስብም…

ሀትሪክ፡- …አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ሄዶ አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ መጣ ምን አንድነትና ልዩነት አየህባቸው…?…

ፈቱዲን፡- …(በጣም ያላባራ ሳቅ)…ይሄ ከባድ ጥያቄ ነው…(አሁንም ሳቅ)…ለጊዜው ይለፈኝ…

ሀትሪክ፡- …እስቲ አሁን ደግሞ ወደ ሊጉ መሪ ፋሲል እንሂድ…የፋሲልን የዘንድሮ ግስጋሴ እንዴት አየኸው…?…

ፈቱዲን፡- …ፋሲል ከቅርብ አመታት ወዲህ የሊጉ ጠንካራው ክለብ መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል…ዘንድሮ ደግሞ እንደ ክለብ በጣም ጥሩ ናቸው…አሪፍ ግስጋሴ እያደረጉ ነው…እንደ ቡድን ወጥ አቋማቸውን በማሳየት የአሸናፊነትን መንገድ ከሌሎች በበለጠ አግኝተው በመጓዝ ላይ ናቸው….

ሀትሪክ፡- …ከዚህ አንፃር የሊጉ ዋንጫ ይገባቸዋል…?…

ፈቱዲን፡- …በጣም ይገባቸዋል…!…ባለፉት ሁለት አመታትም ዋንጫው ጋ እየደረሱ በተለያየ ምክንያት ሳያሳኩ የቀሩበት ሁኔታ ነው የነበረው…ዘንድሮ ግን ያንን የዋንጫ ቁጭታቸውን ለመወጣት መቁረጣቸውን ውጤታቸው ራሱ ያሳብቃል…በአጠቃላይ ግን የሊጉ ሻምፒዮን መሆናቸው የሚገባቸው ነው…በዚህ አጋጣሚ ፋሲሎችን “እንኳን ደስ አላችሁ” ልላቸው እፈልጋለሁ…
ሀትሪክ፡- …የዘንድሮ የሊጉ ክስተት የሆነ ተጨዋች ጥራ ብልህ ማንን ትጠራለህ…?…

ፈቱዲን፡- …ይሄንን ጥያቄ ለሁሉም ብታቀርብ ተመሳሳይ መልስ የምታገኝ ይመስለኛል…የዘንድሮ ልዩ ክስተት የኢት.ቡናው አቡበከር ናስር ነው ለእኔ…

ሀትሪክ፡- …እንደ ቡድንስ ያስገረመህ (ሰርፕራይዝ) ያደረገህ አለ…?…

ፈቱዲን፡- …እንደ ቡድን ፋሲልን ነው የማስቀድመው…ሀዲያ ሆሳዕናም መጀመሪያ ላይ የተሻለ ነበር…ሀድያ ስልህ የኳስ ፍሰቱን እያልኩህ ግን አይደለም…ግን መጀመሪያ ላይ የነበረው ሀዲያ ሆሳዕና አሸናፊ በቀለ ጠንካራ ቡድን ገንብቶ መምጣቱን ነበር የሚጠቁመው…አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን ከቀጠረ በኋላ ድቻም በተለይ በሁለተኛው ዙር ልዩ ክስተት ሆኖ የቀረበ ቡድን ነው ለእኔ…

ሀትሪክ፡- …የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች በDSTV የቀጥታ ስርጭት ማግኘታቸውን እንዴት ታዘብከው…?…

ፈቱዲን፡- …የዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ በሱፐር ስፖርት በቀጥታ የመተላለፍ እድል ማግኘቱ ለእግር ኳሱም በተለይ ለእኛ ተጨዋቾች ብዙ ጠቀሜታ አለው…በፊት የተጨዋቾች አቅም በአለም የመታየት እድሉ አልነበረም…አሁን ግን ተጫዋቹ ራሱን የማሳየት ብሎም ለተሻለ እድል የመብቃት አጋጣሚን ይፈጥርለታል…ውድድሩ በመላ ሀገሪቱም የመታየት እድል ስላለው…“እኔም በርትቼ ከሰራሁ በDSTV አለም ሊያየኝ ሊያደንቀኝ ይችላል”…የሚል ተነሳሽነትንም ይፈጥራል…ይሄ መልካም ጎኑ ሲሆን የዚያን ያህል ደግሞ የስታዲየሞች የብቃት ደረጃዎች ገፅታን የሚያበላሹ በመሆናቸው ይሄም ሊታሰብበት ይገባል…ቶሎ አባራ እንጂ ድሬደዋ ላይ ስንጫወት በቦካ ጭቃ ውስጥ ነበር ማለት ይችላል…በተለይ ትንሽ ሲዘንብ እንኳን ለመጫወት ለማየትም የሚከብድ ነበር…በዚህ ደረጃ ያለ ስታዲየም ላይ ስንጫወት ጨዋታው በመላው አለም ሲተላለፍ ገፅታችን በማበላሸቱ በኩል አሉታዊ ሚና ይጫወታልና ሊታሰብበት ይገባል… ድሬዳዋ ላይ ጨዋታው ቶሎ ማለቁ በጀ እንጂ በነበረበት ሁኔታ ቢቀጥል ኖሮ ነገሮች ከባድ ይሆኑ ነበር…

ሀትሪክ፡- …ለሊጉ አሸናፊ የሚሰጠው የ150 ሺ ብር ሽልማት ማደጉንስ እንዴት ነው የምትገልፀው…?…

ፈቱዲን፡- …ይሄም ራሱ የሊጉ ክስተት ነው ለእኔ…(ሣቅ)…ምክንያቱም አመት ሙሉ ተጫውተህ ብዙ ሚሊዮን ብር አውጥተህ የ150 ሺ ብር ሽልማት ማግኘት በዚህ ዘመን የማይመጥን ነው፤ለፊርማ በሚሊዮን ብር እየወጣ አመት ሙሉ ተጫውተህ የ150 ሺ ብር ሽልማት ካለው ሁኔታ ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም…አሁን ይሄን ታሪክ አርጎ የሚያስቀር ስራ መስራቱ ለእኔ የብቃት ጥግ ነው…የቡድኖችን ፉክክር ይጨምራል… የበለጠም ያነሳሳል…ምናልባትም በአዲሱ አመት የተለየ…ከዚህ የበለጠ አዲስ ነገርም ሊታይ ይችላል…እንደ መጀመሪያ ግን እግር ኳሱ ከፍ እያለ መምጣቱን ከሀገር አልፎ አለም አቀፋዊ ሽፋን እያገኘ ገፅታው እየተቀየረ እየመጣ መሆኑን ያሳያልና በጣም አሪፍ ነው…

ሀትሪክ፡- …ፈቱዲን ባልበላ አንጀትህ ከዚህ በላይ እንዳደከምህ አልፈልግምና ለተለመደው ትብብርህ ከልብ አመሰግኜህ ብንለያይስ…?…

ፈቱዲን፡- …ኧረ ምንም ችግር የለም…እኔም እንግዳ ስላረከኝ ከልብ አመሰግናለሁ…

ሀትሪክ፡- …ግን …ግን…ቆይ…ቆይ…ፈቱዲን…ከመለያየታችን በፊት…ውስጤን ሲበላኝ የነበረ አንድ የመጨረሻ ጥያቄ ልጠይቅህ…?…

ፈቱዲን፡- …ምንድነው እሱ ደግሞ…?…

ሀትሪክ፡- …ትዳር መስርተህ ከባለቤትህ ጋር በአንድ ጣሪያ ስር አብራችሁ መኖር ከጀመራችሁ አመት እያለፋችሁ ነው…ደፈርከኝ ካላልከኝ…ወይም በውስጥ ጉዳዬ ገብተህ ዘባረክ ካላልከኝ በስተቀር…ቤታችሁን የሚያሞቅ ሳሎን ውስጥ ድክ ድክ የሚል ህፃንስ ወደዚህች አለም ለማምጣትስ አልተንቀሳቀሳችሁም…?የሚለውን የስንብት ጥያቄዬ ላድርገው…

ፈቱዲን፡- …(በጣም ያላባራ ሣቅ)… ወይ አንተ…!…በጣም ትገርማለህ…(ሣቅ)…ልጅ የአላህ ስጦታ ነው…እንደ አላህ ፍቃድ ምንአልባትም ከሁለት ወር በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የልጅ አባት እሆናለሁ…(አሁንም ሳቅ)…አይበቃህም…?…በል ቻው አንተን ቶሎ መገላገል ነው…

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.