“ተጨዋቾቼ ለውጥ ቢኖራቸውም ከ7 ወራት በፊት ወደነበሩበት አቋም አሁንም አልተመለሱም” አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

ዋልያዎቹ ለወሳኙ ጨዋታ የፊታችን ሰኞ ወደ ኒጀር ያቀናሉ

“ተጨዋቾቼ ለውጥ ቢኖራቸውም ከ7 ወራት በፊት ወደነበሩበት አቋም አሁንም አልተመለሱም”
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

“ከምንተስኖት አሎ ውጪ አብዛኛዎቹ ግብ ጠባቂዎች ኪሎ ጨምረው ነው የመጡት”
የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ደሳለኝ ገ/ጊዮርጊስ

የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስብስብ ከኒጀር አቻው የፊታችን አርብ ላለበት ጨዋታ ከነገ በስቲያ ወደ ኒየሚ እንደሚያቀና ተገለፀ፡፡
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱን ተክተው የልባቸው ፍላጎት የሆነውን የሀገራቸውን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ ከዚህ በፊት ባልታየ መልኩ 3 የወዳጅነት ጨዋታ የማግኘት እድል አግኝተዋል፡፡ ከዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ጋር 2 ጊዜ ትላንት ደሞ ከሱዳን አቻቸው ጋር 1 የወዳጅነት ጨዋታ ካደረጉ በኋላ የፊታችን አርብና ከ4 ቀናት በኋላ ማክሰኞ ለሚደረገው የደርሶ መልስ ጨዋታ የፊታችን ሰኞ ወደ ስፍራው ያቀናሉ፡፡

ባልተለመደ መልኩ ፌዴሬሽኑ ተደጋጋሚ ጊዜ ሲተችበት የነበረው የወዳጅነት ጨወታ እጥረት በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጊዜ የተለወጠ ሲሆን ሶስት የወዳጅነት ጨዋታዎችን የማድረግ እድል አግኝቷል፡፡ የዛምቢያ ሁለት ጨዋታ በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የኃላፊነት ጊዜ ከተሰናባቹ የቡድኑ ማናጀር እንዳለየሱስ አባተ ከተሞከረ በኋላ በኮቪድ 19 መከሰት ቢቋረጥም በቅርብ ጊዜ ውስጥ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራና የዛምቢያው አሰልጣኝ ሚቾ ተነጋግረው ከተስማሙ በኋላ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ ከሁለቱ ጨዋታዎች በላይ ወሳኝ የነበረውና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በትክክለኛ ግጥሚያ 70 እና 80 በመቶ ዋናውን ቡድን የሚለዩበትን የወዳጅነት ጨዋታ እድል የተገኘው በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ አማካይነት ነው፡፡ አሰልጣኝ ውበቱ ለአሰልጣኝ አብርሃም ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት አሰልጣኝ አብርሃም ከካሜሩን፣ ከደቡብ ሱዳንና ከሱዳን መሀል ምርጫ አቅርበው አሰልጣኝ ውበቱ ሱዳንን መምረጣቸው ታውቋል፡፡ ይህም የሁለቱ ባለሙያዎችን መቀባበልና የአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ተባባሪነትን የሚያሳይ ተደርጎ ተወስዷል፡፡

አሰልጣኙ ከጨዋታው አንድ ሳምንት አስቀድሞ ከአሰልጣኞች ቡድን አባላት ጋር በፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት በሰጡት መግለጫ “ማጣሪያው ላይ ተፎካካሪ ለመሆንና በቀጣዩ የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመካፈል ካሰብን ኒጀር ላይ ነጥብ ይዘን መመለስ የግድ አለብን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አሰልጣኙ ስለ ስብስባቸው እንደተናገሩት “የኛ ሀገር እግር ኳስ እንደነ ፈረንሣይ እንግሊዝ ስፔን መነሻ የምናደርግበት መሠረት የለውም በቆየታዬ ግን ይህን ለመለወጥ የሚያስችል ጭላንጭል ማሳየት እፈልጋሁ” በማለት ህልማቸውን አስረድተዋል፡፡ ከዛምቢያ ጋር ከተደረገው 2 የወዳጅነት ጨዋታዎች በኋላ ስለታየው የእርምት እርምጃ የተጠየቁት አሰልጣኝ ውበቱ “ከሁለት የወዳጅነት ጨዋታ አንፃር ያየነውን ክፍተት ሙሉ በሙሉ መቅረፍ አይቻልም፤ ወሳኝ የሆነውን ስህተት ለማረም ግን ሞክረናል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በተጨዋቾቻቸው ላይ ስላዩት ለውጥ የተጠየቁት አሰልጣኙ “ተጨዋቾቼ ለውጥ ቢኖራቸውም ከ7 ወራት በፊት ወደነበረበት አቋም አሁንም አልተመለሱም” ሲሉ ፍርሃት አዘል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ዋሊያዎቹ ከትላንቱ የወዳጅነት ጨዋታ በኋላ ከያዟቸው 26 ተጨዋቾች ሶስቱን በመቀነስና ሆቴል እንዲቀመጡ በማድረግ 23 ተጨዋቾችን በመያዝ ወደ ግጥሚያው ስፍራ ያቀናሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ ከተለመደው 18 ተጨዋቾች ምናልባት በኮቪድ 19 ምርመራ ተጨወቾች ቢቀነሱ መተካካት እንዲቻል ወደ ስፈራው የሚጓዘው ቡድን አባላት 23 ተጨዋቾች እንዲሆኑ ማድረጉን ያመሰገኑት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በአስገዳጅ ችግር ምክንያት ወደ ኒጀር የሚደረገው በረራ በመቀየሩ ፌዴሬሽኑ ወደ 400 ሺ ብር ተጨማሪ ውጪ እንደሚያወጣ ተናግረዋል፡፡

የብሔራዊ ቡድኑ አባላት አዳዲስ ህጎችን ለማወቅና ከዳኝነት አንፃር ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ተሞክሯቸውን እንዲያጋሩ ኢንተርናሽናል አርቢትር በአምላክ ተሰማና ኢንተርናሽናል አርቢትር ሊዲያ ታፈሰን በመጋበዝ ስልጠና እንዲሰጥ አድርገዋል፡፡
አሰልጣኙ ውበቱ አባተ “በዝግጅታችን ጥሩ ለውጦችን እያየን ነው ሱራፌል ዳኛቸው የጉልበት፣ሙጅብ ቃሲም የታፋ ጡንቻ፣ አቡበከር ናስር የጡንቻ መሳሳብ እንዲሁም አማኑኤል ዮሀንስ የብሽሽት ጉዳት ደርሶባቸው ነበር አማኑኤልና አቡበከር አገግመው ቡድኑን ሲቀላቀሉ የሱራፌል ቀላል ጉዳት ቢሆንም እሱና ሙጅብ ግን እስካሁን ቡድኑን ተቀላቅለው ልምምድ አልሰሩም” በማለት ተናግረዋል፡፡ አሰልጣኙ 7 ወር የት እንደነበሩ የማይታወቁ ተጨዋቾችን ይህን ማድረግ አለባችሁ ማለት ይከብዳል ያም ሆኖ ከተጋጣሚያችን የዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች አንፃር ገና መሆናቸውን ተረድተናል” በማለት አስረድተዋል፡፡

የብሔራዊ ቡድኑ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ደሳለኝ ገ/ጊዮርጊስ በበኩላቸው “ወደ 6 የሚጠጉ ግብ ጠባቂዎች ከምንተስኖት አሎ ውጪ ሁሉም ኪሎ ጨምረው ነው የመጡት፤ ጉዳት ሳያስተግዱ ወደ አቋማቸው እንዲመለሱ ቀለል ያለ ልምምዶችን ስናሰራቸው ነበር፤ ከዛምቢያ ጨዋታ በኋላ ጠንከር ያለ ልምምድ አሠርተናቸዋል፤ ግብ ጠባቂዎቹ እለት እለት እየተሻሻሉ ነው የታዩ ክፍተቶች ላይ በርትተን አሰርተናቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ከሁሉም ግብ ጠባቂዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበርዎት ወይ? የተጋጩት ግብ ጠባቂስ የለም ወይ? የተባሉት አሰልጣኝ ደሳለኝ “ምንም አይነት ችግር አልነበረም መረጃው ልክ አይደለም ወደ ብሔራዊ ቡድኑ የመጣሁት ያለኝን እውቀትና ልምድ ለማጋራት ነው፤ በረኞቹም ስልጠናው ተመኝቷቸው በደንብ ሰርተዋል የማውቀው ይህን ነው” ሲሉ ማስተባበያ ሰጥተዋል፡፡

ከአርቡ ወሳኝ ጨዋታ በፊት ፊት ባወጣው የጥቅምት ወር የሀገሪት ብሔራዊ ቡድኖች የደረጃ ሰንጠረዥ ኒጀር ኢትዮጵያን በ34 ደረጃ ትበልጣታለች፡፡ ኒጀሮች በደረጃው 112ኛ ደረጃን ሲይዙ ኢትዮጵያ 146ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ፈረንሣይኛ ኦፊሺያል ቋንቋዋ የሆነው ኒጀር 22 ሚሊዮን 442.31 ህዝብ ሲኖራት የፊፋ አባል የሆነችው 1964 ዓ.ም ነው፡፡ የወቅቱ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጂን ሚሼል ካቫሊ ለዚህ ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከእስካሁኑ የምድብ 11 ጨዋታ ማዳጋስካር በ6 ነጥብ ስትመራ ኢትዮጵያ አይቬሪኮስትና ኒጀር በእኩል 3 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከ2-4 ያለውን ስፍራ ይዘዋል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport