“አሰልጣኝ ውበቱ መርጦኝ ካላየኝ መጀመሪያውኑ ባይጠራኝ ይሻል ነበር”ደስታ ደሙ /ቅዱስ ጊዮርጊስ/

“አሰልጣኝ ውበቱ መርጦኝ ካላየኝ መጀመሪያውኑ ባይጠራኝ ይሻል ነበር”
“የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዛቻ የኢትዮጲያውያንን አንድነት የሚያጠናክር ይመስለኛል”
ደስታ ደሙ /ቅዱስ ጊዮርጊስ/


የእግር ኳስ ህይወቱ ጅማሮ ከሙገር ቢ ቡድን ይነሳል፡፡ በዚህ ክለብ ማልያ 4 አመት፣ ለደደቢት 2 አመት እንዲሁም ለወልዋሎ አዲግራት 1 አመት ከተጫወተ በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ ማሊያ 2ኛ አመቱን ይዟል፡፡ ወንጂ ሳይደርሱ መልካአዲ ቦኩ ተብላ የምትጠራው ስፍራ የእንግዳችን የትውልድ ስፍራ ነው፡፡ የእግር ኳሱ ጉዞው ለየት ይላል፤ ሙገር እያለ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን፣ ወልዋሎ አዲግራት እያለ ለኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን ተመርጧል፡፡ ተጨዋቹ ከወልዋሎ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሚያቀናበት የሽግግር ጊዜ በፈረሰኞቹ ማልያ በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱና በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የመመረጥ እድል አግኝቷል፡፡ ከሰሞኑ በአሰልጣኝ ውበቱ ከተቀነሱ 10 ተጨዋቾች መሀል የሆነው የዛሬው እንግዳችን የፈረሰኞቹ የተከላካይ መስመር ተፋላሚ ደስታ ደሙ ክፉኛ ማዘኑን ከዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል፡፡ አንድም የመሰለፍ እድል ሳላገኝ በግጥሚያ ያለኝን አቅም ሳያይ እንዴት ይቀንሰኛል ሲልም ቅሬታውን ለሀትሪክ አስረድቷል፡፡ ከብሔራዊ ቡድኑ መቀነሱን አለመቀበሉን፣ ሳይጎዱ ካልተጫወቱ 2 ተጨዋቾች መሀል አንድ መሆኑን እንደማይቀበለው፣ ዳሌ አውጥተዋል ስለተባለው ጉዳይ፣ ስለዝግጅቱና የካፍ አካዳሚ ቆይታው ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈትን መጥላትና ስለደፊጋዎቹ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ 3 አመት ዋንጫ ስላለማግኘቱ፣ አሰልጣኝ ውበቱን ተቀይረህ ግባ ሲለው ለምን እንቢ እንዳለ፣ በልምምድ ላይ ጥሩ አልነበርክም ወይ ስለተባለው፣ ስለ ኮሮና ተጠቂ ተጨዋቾችና ክርስቲያኖ ሮናልዶ የተናገረው፣ ስለ ዶናልድ ትራምፕ ድንፋታና ስለ አባይ ግድብ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት ታላላቅ በዓላትን ከቤተሰቡ ጋር ስለማሳለፉና ሌሎች ጉዳዮች ሰፋ ያለ ምላሹን የሰጠው የደስታ ደሙ ቃለ ምልልስ ከታች ያለውን ይመስላል፡፡

ሀትሪክ፡- የተወሰኑ የዋሊያዎቹ ተጨዋቾች ዳሌ አውጥተዋል ተብሏል… አንተስ ዳሌ አውጥተሃል?

ደስታ፡- /ሳቅ በሳቅ/ ኧረ በጭራሽ አይታሰብም /ሳቅ/

ሀትሪክ፡-የዳሌ አወጥተዋል ጉዳይ አወዛግቧል፤ ግን ግን ዳሌ ያወጡ እንበለው ወይም የወፈሩ እንበል ለብሔራዊ ቡድን የማይመጥኑ ተጨዋቾች አላየንም?

ደስታ፡- ለኔ እንግዲህ እስካየሁት ድረስ ዳሌ ያወጡ ተጨዋቾች አላየሁም፡፡ ዳሌኮ ለሴት ነው፤ ወንድ አያወጣም… ተጋኗል ባይ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡-7 ወር ማረፍ ውፍረት ወይም ለዳሌ ማውጣት አይዳርግም?

ደስታ፡- ተፅዕኖ አለው.. 7 ወር ሙሉ መቀመጥ በራሱ ችግር ይኖረዋል በተለይ ካልሰራህበት… ቁጭ ብሎ ለተቀመጠ ለኪሎ መጨመር ይዳርጋል፤ ይሄ እውነት ነው እዚህ ላይ ግን አማርኛው ያናድዳል ወንድ ልጅን ዳሌ አውጥቷል ማለት ይከብዳል፡፡

ሀትሪክ፡- እስቲ ወደ መነሻህ እንምጣና የቀኝ መስመር ያንተ ቦታ ነው… በኮሪደሩ ላይ በፍጥነት ስትሮጥ ያን ቦታ ስትሸፍን ነው የሚታየው… ቦታውን እንዴት መረጥከው?

ደስታ፡- መነሻው ሙገር ቢ እያለሁ የገባሁት በመሀል ተከላካይነት ነበር፡፡ በኋላ ላይ ቀስ እያሉ ወደ ቀኝ መስመርና የመሀል ተከላካይነት ሊጠቀሙብኝ ችለዋል፡፡ አሰልጣኝ ግማር ሀብተ ዮሀንስ ተመላላሽ ላይ ወደ 3 ጨዋታ ላይ አሰልፎኛል፤ ሙገር እያለሁ ነው የቀኝ ተመላላሸ ተጨዋች የሆንኩት፡፡

ሀትሪክ፡- ሁለቱንም ቦታህን ታምንበታለህ…? ተቀብለኸዋል?

ደስታ፡- ተቀብዬዋለው…. የመሀልም ሆነ የቀኝ ተመላላሽ ቦታ ብሰለፍ ደስተኛ ነኝ ደደቢትም እያለሁ ሁለቱ ቦታ ላይ ተሰላፊ ነበርኩ፡፡

ሀትሪክ፡- በዚህ ቦታ ላይ ያንተ ምርጡ ማነው?

ደስታ፡- በሀገር ደረጃ በቀኝ መስመር ስዩም ተስፋዬን አደንቃለሁ፤ በመሀል ተከለካይ… አስቻለሁ ታመነ ለኔ ምርጡ ነው፤ ከውጪ በቀኝ መስመር ብራዚላዊው ዳኒ አላቬዝ በመሀል ተከላካይ ቪዲችን አደንቃለሁ በእርግጥ ሰርጂዮ ራሞስም ልዩ ነው፤ /ስቅ/ በአሁኑ ሰዓት አሉ ከሚባሉ የመሀል ተከለካዮች መሀል አንዱ ነው፤ ጎሎችንም ያስቆጥራል አጥቂ ነው የሚመስለው /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- በትውልድ ስፍራህ የሚታወቁ ተጨዋቾች ነበሩ?

ደስታ፡- ኳሱን በሚገባ ሳንጀምርና ደጋፊ እያለን ጥሩ ጥሩ ልጆች ነበሩ እነ ራሺድ እነ ደምስ የሚባሉ ጥሩ ልጆች ነበሩ ወንጂ ከወረደ በኋላ ነው ተጨዋቾች የጠፉት፡፡

ሀትሪክ፡-ቅዱስ ጊዮርጊስን እንደተ ትገልፀዋለህ?

ደስታ፡- /ሳቅ/ ሁሉም ያውቀዋል በቃላት የምትገልፀው አይደለም ጊዮርጊስ አገራችን ካሉት ትልልቅ ክለቦች አንዱ ነው፡፡ ለብሔራዊ ቡድን በርካቶችን አስመርጧል እነ ሳላህዲን ሰይድ ሽመልስ በቀለና አዳነ ማርማ የመሰሉ ኮከቦችን አሳይቷል፡፡

ሀትሪክ፡-በጊዮርጊስ የተደነቅከው በምኑ ነው?

ደስታ፡- በጊዮርጊስ ቤት ሽንፈት ይጠላል እንኳን መሸነፍ አቻ መውጣት የሚፈጥረው ስሜት ከባድ ነው፤ የምወደው እልህ ውስጥ የሚከት ጠንክረህ እንድትሰራ የሚያደርግ ሽንፈት ጠይ ክለብ መሆኑ ነው፤ ማሸነፍ አቻና መሸነፍ ቢኖርም ሁለቱን /ሽንፈትና አቻ/ በጊዮርጊስ ቤት መቀበል ይከብዳል ሁሌ የሚገርመኝ ይሄ ስሜት ነው፡፡

ሀትሪክ፡-ደጋፊዎቹን እንዴት አገኘሃቸው?

ደስታ፡- ከውጪም ሆኜ ሳያቸው ደጋፊዎቹ የሚገርሙ ናቸው በቅርብም ሳያቸው ደጋፊው ለጊዮርጊስ ትክክለኛ 12ኛ ተጨዋች ነው ማለት ይቻላል ሁሌ ከጎናችን ናቸው በነርሱ ደስተኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡-በኮቪድ 19 ምክንያት 2012 አልተጠናቀቀም ዋንጫ የወሰደም የለም፤ ጊዮርጊስ በ2010 እና 2011 ዋንጫ አላገኘም ይሄ ነገር ካልከኝ የድል ፈላጊነት ስሜት አንፃር አይጋጭም?

ደስታ፡- በርግጥ ዋንጫ ለለመደ ክለብ 3 አመት ዋንጫ አለማየት ያበሳጫል፡፡ ኮቪዱ ባይኖር ኖሮ ዋንጫ ለመውሰድ አልመን ነበር፤ ነገር ግን አለም ላይ በመጣው ወረርሽኝ ያሰብነው አልሆነም፡፡ አቅሙ ግን ነበረን 2013 ላይ ድሉን ለማሳካት ጠንካራ ዝግጅት ማድረጋችን የግድ ነው በዚያ ላይ ሲቪውም የዳበረ ምርጥ አሰልጣኝ መጥቷል፤ ትልልቅ ክለቦችን አሰልጥኗል በዚህ ደስተኛ ነኝ የእርሱ መምጣት ለኛ እድገት ነው ብዙ ነገር ይለውጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ 2013 የሊጉን ዋንጫ ማግኘት ግድ ነው፡፡

ሀትሪክ፡-እስቲ ስለ ዋሊያዎቹ እናውራና ለዋሊያዎቹ ተጠርተሃል የየትኛው ክለብ ቆይታህ ነው ያስመርጠህ?
ደስታ፡- ከ20 አመት ታደጊ ብሔራዊ ቡድን የተመረጥኩት ሙገር እያለሁ ነው፡፡ ከዚያ ማንንም ሳያይ በበረኛ አሰልጣኙ ፀጋዘአብ አስግዶም ድጋፍ ወደ ደደቢት አቀናሁ በዚህ አጋጣሚ ፀጋ ዘአብን አመሰግናለሁ፤ ተማምኖብኝ ኃላፊነቱን በመውሰዱ ደስተኛ ነኝ፡፡ ከዚያ ወልዋሎ ስገባ ለኦሎምፒክ ቡድኑ ተጠራሁ፡፡ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስፈርም በአሰልጣኝ አብርሃምም ሆነ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እንድጠራ አድርጎኛል፤ በነበረኝም ቆይታ ደስተኛ ነኝ ጥሩ ጊዜ ነበረኝ፡፡

ሀትሪክ፡-ከብሔራዊ ቡድን ከተቀነሱት ይልቅ ቀሪዎቹ ተናደዋል አሉኝ… ይሄን ያህል መጥፎ ስሜት ነበር እንዴ?

ደስታ፡- እኔ ደግሞ በተቃራኒው ነው ያየሁት… የሌሎቹን እይታ አላውቅም፤ ነገር ግን በኔ ትዝብት ይሄን መሰል ችግር አላየሁም፤ ይሄኮ የአገር ጉዳይ ነው ከ110 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ወክለን ነው የምንጫወተው የማንኛውም ተጨዋች ትልቁ እድገት የመጨረሻው ግብ አገሩን መወከል ነው ይሄ ነው ህልማችን፤… በራሴ ምልከታ ይሄ ችግር አለ ብዬ አላምንም፡፡

ሀትሪክ፡ ከዋሊያዎቹ ከተቀነሱ 10 ተጨዋቾች መሀል አንዱ አንተ ነህ…ተቀበልከው?

ደስታ፡-ተቀብዬዋለው.. አሰልጣኙ ለኔ አትመቸኝም ለአጨዋወቴ አትሆንም ካለ ከመቀበል ውጪ ምንም አይነት አማራጭ የለም፡፡

ሀትሪክ፡-ኢትዮጵያ ከዛምቢያ ጋር ባለፈው እሁድ ሲጫወቱ ተቀይረህ ግባ ስትባል እንቢ አልክ.. ለምን? የ110 ሚሊየን ህዝብ ውክልና ነው ካልክ ለምን አላከብርከውም?

ደስታ፡- በጣም ቅር ብሎኛል ጥሩ ስሜት አልፈጠርብኝም ከ35ቱ ተጨዋቾች መሀል በጉዳ0ት ካልተጫወቱት ውጪ ጤነኛ ሆኜ ያልተሰለፈኩት እኔ ብቻ ነኝ… ይሄ አያበሳጭም ምናልባት አንድ በረኛ ነው ከኔ ጋር ያልተጫወተ ይሄን እውነት ሁሉም ያውቃል… ተናደድኩ… አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ በመሀልም ሆነ በቀኝ መስመር ተመላላሽነት አጫውቶኛል በዚህ ቦታ ጥሩ ነበርኩ… ሁሉም ተጨዋቾች ታይተዋል ለኔ ግን እድሉ አልተሰጠኝም፤ ቦታው የኔ ነው እድሉን አግኝቼ ባልችል ቅነሳው ምክንያታዊ በመሆኑ እቀበል ነበር… አሰልጣኝ ውበቱ መርጦኝ ካላየኝ መጀመሪያውኑ ባይጠራኝ ይሻል ነበር ሁለቱ የወዳጅነት ጨዋታዎች ተጨዋቾች የሚለዩበት ነው ከተባለ መታየት አለብኝ ማለት ነው በልምምድ ነው የቀነሰኝ? በጣም ቅር ብሎኛል፡፡

ሀትሪክ፡-አልመለሰክልኝም..?በዚህ ተከፍተህ ነው ተቀይሬ አልጫወትም ያልከው…?

ደስታ፡- ሌላ ምክንያትማ የለኝም ይሄ ነው ቅሬታዬ ውስጤ ያለው ቅሬታ አልበረደም.. ሀገሬን ለማገልገል ተጠርቼ ከዚያ ሁሉ ተጨዋች ተለይቼ የማልታየው ለምንድነው የሚለው አናዶኛል በርግጥ ስሜታዊ ሆኜ አልቀየርም ማለቴ ስህተት ነው ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-ድክመት ካልብህ ለማረም አሰልጣኙን አላናገርከውም?

ደስታ፡- በተፈጥሮዬ ሰው ላይ መድረስ አልወድም እንዲደርሱብኝም አልሻም የሆነ ነገር ሲፈጠር መጠየቁ ጥሩ ሊሆን ይችላል እኔ ግን ተፈጥሮዬ አይደለም በቃ መቼም መጠየቅ አልችልም አላረገውም፤ አሰልጣኙ ግን ችግርህ ይሄ ነው አርም ብሎ ሊነግረኝ ይገባል ባይ ነኝ በተረፈ ከእርሱ ጋር የተለየ ቅራኔ የለኝም፡፡

ሀትሪክ፡-ተጨዋቾች ተጎድተዋል.. ሜዳው ጥሩ አልነበረም የሚሉም አሉ… አንተስ እንዴት አየኸው?

ደስታ፡-በጣም አሪፍ ሜዳ አይደለም.፤. የተወሰነ ድንጋይ አለበት ከተጨዋቾቹ ጋር እንነጋገር ነበር ሜዳ ቢቀየር ጥሩ ነበር ግን ብዙ መጋነን የለበትም፡፡

ሀትሪክ፡- በልምምድ ጊዜ ጥሩ አልነበርክም እንደዚህ አይነት መረጃም ደርሶኛለ ልክ ነው…?

ደስታ፡- /ሳቅ/ ይገርማልኮ.. ሰው የራሱ እይታ ይኖረዋል የአሰልጣኙም አስተያየት እንዲሁ ነው… ወርጃለሁ መጥፎ አቋም አሳይቻለሁ ብዬ ግን አላምንም፤ ሰው የፈለገውን ሊል ይችላል፡፡

ሀትሪክ፡-ጥሩ ሁን መጥፎ ማወቅህ የግድ ነው?

ደስታ፡- በጥሩ ሁኔታ ልምምዱን ሰርቻለሁ መጀመሪያ አካባቢ ትንሽ ጉዳት ነበረብኝ ግን ጉዳቴን ሳላይ ጠንክሬ ሰርቻለሁ፤ በኔ እምነት በኳሱ ጥሩም ሆነ ደካማ አቋም የምናሳይበት ጊዜ ሊኖር ይችላል፤ ይሄ የትም አለም አለ፤ ነገር ግን እንዳያጫውተኝ የሚያደርግ ደካማ አቋም አሳይቻለሁ ብዬ አላምንም፡፡

ሀትሪክ፡-ለተጨዋቾቹ የነበረው ክትትልና ድጋፍ ጥሩ ነበር ማለት ይቻላል ምስር ነበር ስንበላ የነበርነው የሚል ቅሬታም አለ?

ደስታ፡- /ሳቅ/ በምግብ በኩል ጥሩ ነበር፡፡ የሚጠቅሙ የተለያዩ ምግቦችም ነበሩ ምስር ብቻ ነው የሚለው ልክ አይደለም ለጨዋታ ስንወጣም ስንገባም የነበረው ደጋፍ ጥሩ ነው የሚባል ነው በግሌ ምስሩ ቀይ ወጥ ከሆነ አልበላም አልበላሁምም /ሳቅ/ የሚጠቅመንን የሚነግረን አንድ ሰው አለ ስሙን አላውኩትም በርሱ ምክር ነው የምንበላው፡፡

ሀትሪክ፡-ከዋሊያዎቹ ብትሰናበትም ለቀጣዩ ጉዟቸው ምን ትመኛለህ?

ደስታ፡- የጓደኞቼ ጉዞ ቀጥሏል፤ ለብሔራዊ ቡድናችን ከኒጀር ጋር ያለው የደርሶ መልስ ጨዋታን በማሸነፍ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚደረገውን ጉዞ እንደሚያጠናክሩ አምናለው መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ቡድኑን እደግፋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-ከውጨ ኳስ የማን ደጋፊ ነህ?

ደስታ፡- የማን.ዩናይትድ ደጋፊ ነኝ፡፡ በግሌ ተከላካይ ብሆንም የፖርቹጋላዊው ኮከብ የክርስቲያኖ ሮናልዶ ደጋፊና አድናቂ ነኝ፤ ያኔ ለማን.ዩናይትድ ሲጫወት ነበር ማንቼዎችን መደገፍ የጀመርኩት… እርሱ ያለበት ቡድን ደጋፊ በመሆኔ የሪያል ማድሪድ ደጋፊ ነበርኩ አሁን ደግሞ የጁቬንቱስ ደጋፊ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡-የኮሮና ቫይረስ ያዘው ስትባል ምን ተሰማህ?
ደስታ፡- ከባድ ነው ያስደነግጣል.. መላው አለምን ያሸበረ ወረርሽኝ ቢሆንም ግን ጠንካራ ሰራተኛ በመሆኑ ቶሎ አገግሞ እንደሚመለስና በጁቬንቱስ ማሊያ ድጋሚ እንደማየው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

 

ሀትሪክ፡-ብሔራዊ ቡድን ተመርጣችሁ ስትገቡና የኮቪድ 19 ምርመራ ስታደርግ አልሰጋህም?

ደስታ፡-/ሳቅ በሳቅ/ በጣም እንጂ… እኔ ብቻ ሳልሆን ማንም ሰው ይጠራጠራል ራሴን አውቀዋለው አይዘኝም የምትለው አይደለም አለምን ያሸበረ አለም ላይ ያለ በሽታ በመሆኑ የተወሰነ ጥርጣሬ ይኖራል /ሳቅ/ ?

ሀትሪክ፡ ነፃ ነህ ስትባል.. እፎይ አልክ አሉኝ

ደስታ፡-/ረጅም ሳቅ/ አያስብልም? ያስብላልኮ ትልቅ እረፍት ነው የተሰማኝ በጣምም ደስ ብሎኛል፡፡

ሀትሪክ፡-አምስቱ የዋሊያዎቹ ተጨዋቾችንስ ከኮቪድ ነፃ ሆነው ሲቀላቀሏችሁ ምን ተሰማችሁ?

ደስታ፡- ትልቅ እረፍት ደስታ ነው የተሰማን.. እንደ ሰው በሽታ ነውና አዝነን ነበር ነፃ ሲወጡ በጣም ተደስተናል ማታ ላይ ሲቀላቀሉን አጨብጭበን ነው የተቀበልናቸው ሲመጡ ያለው ሁኔታ ደስ ይል ነበር…

ሀትሪክ፡-ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ግብፅ የአባይን ግድብ ልታፈነዳው ትችላለች ማለታቸው ተከትሎ በሀገር ቤት ቁጣ ቀስቅሷል….. ምን ተሰማህ?

ደስታ፡- /ሳቅ/ ይሄ የሚያሰጋ አይደለም ሰውየው ስለተናገረ ያለው ይሆናል ማለት አይደለም ይሄ መታወቅ አለበት፡፡ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዛቻ የኢትዮጵያዊያን አንድነትን የሚያጠናክር ይመስለኛል ከዚያ ውጪ አያሰጋኝም በፕሬዚዳንቱ ንግግር የተደናገጡ ሰዎች አሉ ይሄ ልክ አይደለም፤ አንድነታችንን የሚያመጣ ይመስለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- እንደ እግር ኳስ ተጨዋችነትህ ህብረተሰቡ ተግባብቶ ተማምኖና ተከባብሮ እንዲኖር ከማድረግ አንፃር ምን ትመኛለህ?

ደስታ፡- የዘርና የጎሳ ነገር ፈፅሞ መቅረት አለበት ለኛና ለሀገራችን የሚጠቅም አይደለም፡፡ ሁላችንም አንድ ነን ከእግዚአብሔር ነው የተፈጠርነው በቃ ዘር ባንለይ ባንጣላ ሚና ለይተን በጎሳ ባንናቆር ደስ ይለኛል፡፡ አገሬ ትቅደም … ዘረኝነቱና ልዩነቱ ቀርቶ ኢትዮጵያ ብትቀድም ደስ ይለኛል ለህዝቡም የምለው ይህን ነው፡፡

ሀትሪክ፡-7 ወር የኮቪድ 19 ፍርሃት አንተንስ እንዴት አድርጎህ ነበር?

ደስታ፡- በጣም ለምፈልገው ነገር ካልወጣው በቀር ቤት ውስጥ ነበር የማሳልፈው ጓደኛዬም አለ .. ልምምድ እየሰራን ቆይተናል ጊዜዬን ባልተለመደ መልኩ ቤቴ ውስጥ ነው ያሳለፍኩት፡፡

ሀትሪክ፡-ቤት ውስጥ ከማሳለፍህ የተነሣ ቀላህና ልጃችን እንዲህ ቀይ ነው እንዴ አላሉህም?

ደስታ፡- /ሳቅ በሳቅ/ ከቤት ካልተወጣ መቅላትህ አይቀር እንዴትስ አይባል?.. ፀኃይ ካላገኘህኮ ቅላትህ ይጨምራል፡፡

ሀትሪክ፡-በዚህ ደረጃ ቀን በቀን ሲያገኙህ ቤተሰቦችህ ምን አሉ?

ደስታ፡- በጣም ደስ ብሏቸዋል ከእናታችን ጋር አንድ ወንድምና እህት ነው ያለኝ.. ተሰብስብን ስንጫወት ደስ ይላል በርግጥ በሽታ ቢኖርም መልካም ጎኑ ደግሞ እንዲህ አሰባስቦናል በፊት በአመት ውስጥ አንዴ ወይም ሁለቴ ነው ቤት የምሄደውና በነበረው ጊዜ ደስም ብሏቸዋል፡፡

ሀትሪክ፡-ለመጀመሪያ ጊዜ ፋሲካና እንቁጣጣሽ ከቤተሰቦችህ ጋር አከበርክ?

ደስታ፡- አዎ በጣም የሚገርም ገጠመኝ ነበር… በተለይ ፋሲካና እንቁጣጣሽን ከቤተሰቤ ጋር አክብሬ አላውቅም በዚህ ገጠመኝ ደስ ብሎኛል፡፡

ሀትሪክ፡-የመጨረሻ ቃል ካለህ…?

ደስታ፡- ለዚህ ደረጃ ያደረሰኝን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ ከርሱ በመቀጠል ከጎኔ ያሉትን እናቴን እህትና ወንድሜን አመሰግናለሁ፤ ከታዳጊነቴ ጀምሮ አይቶ እምነቱን ለጣለብኝ ፀጋ ዘአብ አስግዶምን ከልብ አመሰግናለሁ መካሪዬ ነው እንድለወጥ ይፈለጋልና ላመሰግንው ይገባል፤ ትልቅ ፍቅር እንዳለኝም መናገር እፈለጋለሁ… ጓደኛዬ ኤሊያስ ተሻለንም አመሰግናለሁ… በነበርኩባቸው ክለቦች ላሰለጠኑኝና ለደገፉኝ ላመኑብኝ በሙሉ ምስጋና አቀርባለሁ የሀትሪክም ስፖርት ጋዜጣ እንግዳ ስላደረጋችሁኝ እናንተንም አመሰግናለሁ፡፡

ስለ ኮቪድ 19
ከካቪድ 19 ፍርሃት ነፃ የወጣንና ጥንቃቄውን የተውን ይመስለኛል እንደኔ ግን ብንጠነቀቅ ይሻላል ችግሩ አሁንም አለና ጥንቃቄው ሊጨምር ይገባል ማለት እፈልጋለሁ…በተለይ የህክምና ሰዎች የሚሉንን የጥንቃቄ መንገዶችን ማክበር አለብን የግድ ነው ነገን ካለምን ዛሬን በጥንቃቄ ልናልፈው ይገባል አለበለዚያ ትልቅ አደጋ ነው የሚፈጠረው እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን እንዲጠብቅ እፀልያለሁ…

ስለ አባይ ግድብ
የኢትዮጵያ ህዝብ ለሀገሩ ሟች ነው፤ በሀገሩ ደረጃ ቀልድ አያውቅም.. ህዝቡ ከመንግሥት ጋር ተረባርቦ በመሥራቱ የጋራ አንድነት የነበረበት በመሆኑ በጣም ተደስቻለሁ… ትልቅ ትርጉም ያለው ስራ በመሆኑ ከጎኑ ልንቆም ይገባል… በኔ በኩል ከሙገር ጀምሬ ቦንድ ገዝቻለሁ በ8100A አለሁበት በዚህም የበኩሌን ማድረጌ ይሰማኛል… እንደ ሀገር ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ሲጀምር ማየት እመኛለሁ.. መላው ህብረተሰብ ሁልጊዜም ሊደግፈው ይገባል በዚህ አጋጣሚ ግድቡ የኛ ምልክት አድርጎ ማየትም ይገባል እላለሁ፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport