ዋሊያዎቹ ላይ የታየው ስጋትና የአሰልጣኙ ተስፋ

ከ18 ቀናት በኋላ ከኒጀር አቻቸው ጋር ላለባቸው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች እየተዘጋጁ ያሉት የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ዋሊያዎቹ ከዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ 3ለ2 ተረተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ስታዲየም በ8 ወር ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የእግር ኳስ ውድድር ማራኪ ባልነበረ ጨዋታ በርካታ ክፍተቶች የታዩባቸው ዋሊያዎቹ በገዛ ሜዳቸውና በለመዱት አየር ምንም አይነት ብልጫ ሳያሳዩ፤ በታዩባቸው ግዙፍ ስህተቶች ለሽንፈት መዳረጋቸው ዛሬን ጨምሮ ለኒጀሩ ጨዋታ 19 ቀን መቅረቱና ስህተትን የማረሚያ ጊዜ መገኘቱ እንደማፅናኛ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ አጥቂና ተከላካይ የዋሊያዎቹ ዋናና ም/ል አምበል የሆኑት የጌታነህ ከበደና የአስቻለሁ ታመነ የጨዋታና የፍፁም ቅጣት ምት ግቦች ዋሊያዎቹን ከሽንፈት ሳይታደጉ ቀርተዋል፡፡

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ አሰልጣኝ ከጨዋታው በኋላ ቡድኑ የነበረበትን ጠንካራና ደካማ ጎን እንዲህ ሲሉ ለሀትሪክ ገልፀዋል፡፡ እንደ አሰልጣኙ የቡድኑ ጠንካራ ጎን “ዋሊያዎቹ መጫወት የፈለጉት ኳስን ተቆጣጥሮ ኳስን መሰረት አድርጎ መጫወት ነው ከዚህ አንፃር ኳሱን ለመቆጣጠር ሞክረዋል ይሄ መልካም ነው፤ የመጀመሪያው 45 ደቂቃ ላይ በኳስ ቁጥጥርም የተሻሉ ነበሩ፤ የመጨረሻ የማጥቃት የተቃራኒ ቡድን ሜዳ ላይ ያለው የተጨዋቾች ቁጥር ብዛቱና በመከላከል ሽግግሩ ውስጥም ጥሩ ነገር አሳይተውናል፤ ግብ ሲያስቆጥሩ የሄዱበት ሂደትና ተጋጣሚ ተጨዋቾችን የቀነሱበት መንገድ አስደሳች ነበር፤ በ45 ደቂቃ ውስጥ 2 ግብ ማስቆጠራቸውና 7 ወራት ያህል ከውድድር የራቁ ቢሆንም በመጀመሪያ ጨዋታቸው የነበረው አቋም ጥሩ እንደነበሩ ያሳየ በተናጠል የተወሰኑ ተጨዋቾች የነበራቸው አቋም የተሻለ መሆኑን የታዘብንበት ዋሊያዎቹ ላይ የታየው ጠንካራ ጎናቸው ነው” ሲሉ ገልፀዋል፡፡

እንደ እነኚሁ አሰልጣኝ እምነት የቡድኑ ደካማ ጎን የሚባሉት “የቡድኑ ስብስብ ላይ ክፍተት መታየቱ፣ በረኞች ላይ የታየው የተፈራው ክፍተትና የማይለወጥ ደካማ አቋም እንደበፊቱ ጎል ጠሪ መሆናቸው፣ አራቱ ተከላካዮች መሀል የማች ፊትነስ ክፍተት መታየቱና በተለይ እንደ ቡድን ሲንቀሳቀሱ ታክቲካል ክፍተት መኖሩ የታዩባቸው ችግሮች ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ “እንደ አጠቃላይ ሁለት አይነት ፊትነስ አለ፡፡ የመጀመሪያ በልምምድ የሚመጣ ፊትነስ ሲሆን ሁለተኛው ጨዋታ ላይ ያሳየኸው ብቁነት ማች ፊትነስ ይባላል፡፡ ዋሊያዎቹ በ90 ደቂቃው የማች ፊትነስ ችግር ነበረባቸው፤ የማይጠበቁና አላስፈላጊ ሪስኮች ወስዶ ስህተት መፍጠር፣ ከተከላካይ ወደ አማካይ ኳስ ሲሄድ የመደጋገፍ አቅም አናሳ መሆኑ፣ ግብ ለማስቆጠር አምስት ተጨዋች የተጋጣሚ ግብ ክልል ላይ ደርሰው ምንም ሳይሞክሩ መመለሳቸው በአጠቃላይ የታዩ ደካማ ጎኖች በመሆናቸው መስተካከል አለባቸው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

“ዛምቢያዎች ተጭነውን አልተጫወቱም ተጭነው ሳይጫወቱ ይህን መሰል ስህተት ከሰራን ተጭኖ የሚጫወት ቡድን ቢገጥመን በርካታ ስህተት ሊሰራ እንደሚችል ተገንዝበው ባሉት የዝግጅት ቀናቶች ጠንካራ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ ጨዋታ ለቡድኑ ብቁ ያልሆኑ ጥቂት ተጨዋቾች ቆይታ ላይ አሰልጣኙ በአስቸኳይ መወሰን አለበትም” በማለት አሰልጣኙ በዋሊያዎቹና በቺፖሎፖሎ መሀል የታየውን ሂደት ለሀትሪክ አስረድተዋል፡፡ በዚህ ጨዋታ ላይ አቋማቸው ለጨዋታ ዝግጁ ያልሆኑና የወፈሩ እንደ አሰልጣኝ ሰለሞን አባተ አባባል ዳሌ አውጥተዋል የተባሉ ተጨዋቾች የታዩ መሆናቸው የአሰልጣኙ፣ የተጨዋቾቹና የፌዴሬሽኑ ቅሬታን ተገቢ አለመሆንን ያሳየ ሆኗል፡፡ አሰልጣኙ ባለፈው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ “ተጨዋቾቹ ዳሌ አውጥተዋል የሚለውን ሰምቻለሁ ነገር ግን ዳሌ ያወጣ ተጨዋች አልገጠመኝም” ቢሉም በሀሙሱ ጨዋታ የታየው እውነት ግን የወፈሩና ለጨዋታ ዝግጁ ያልነበሩ ተጨዋቾች መገኘታቸው የአደባባይ ምስጢር ሆኗል፡፡

የአማርኛ ምልልስና የቃላት ስንጠቃን ትቶ ሁሉም ወገን የሚጠበቅበትን ያደርጋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ በጣም የወፈሩ ተጨዋቾች ዳሌ አውጥተዋል መባሉን እንደ ትልቅ ስህተት ከመቁጠርና የባለሙያዎችን የመናገር ነፃነት ከማፈን ይልቅ ለኒጀሩ ጨዋታ የሚጠበቀውን እልህ አስጨራሽ ዝግጅት ማድረጉ ይበጃል በማለት የስፖርት ቤተሰቡ ተናግሯል፡፡ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚሰለጥኑት ዋሉያዎቹ ነገ 10 ሰዓት ላይ ከዛሚቢያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ሁለተኛውን የወዳጅነት ጨዋታ ካደረጉ በኋላ የተወሰኑ ተጨዋቾችን በመቀነስ በቀሪ 18 ቀናት ጠንካራ ዝግጅቱን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport