“ለሁለት ዓመት ዋንጫ ያጣንበት ሳይሆን የተነጠቅንበትና የተቀማንበት ጊዜ ነው” አቶ አብነት ገ/መስቀል (የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የቦርድ ፕሬዝዳንት)

“ለሁለት ዓመት ዋንጫ ያጣንበት ሳይሆን የተነጠቅንበትና የተቀማንበት ጊዜ ነው”
አቶ አብነት ገ/መስቀል (የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የቦርድ ፕሬዝዳንት)

ዘንድሮ 85ኛ አመት የምስረታ በአሉን የሚያከብረው ቅዱስ ጊዮርጊስ የ2ዐ13 የኢትዮጰያ ፕሪሚየር ሊግ የዋንጫ አሸናፊ የመሆን ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ፡፡
ፈረሰኞቹ ጀርመናዊውን ልምደ ብዙ አሰልጣኝ ኤርነስት ሚዲንድሮፕን ለቀጣዮቹ 3 አመታት አሰልጣኝ አድርገው መሾማቸውን በተመለከተ በሸራተን አዲስ በተካሄደ ስነ ሥርዓት ላይ የስፖርት ማኅበሩ የቦርድ ፕሬዚዳንት አቶ አብነት ገ/መስቀል እንደተናገሩት “ዘንድሮ 85ኛ አመታችንን የምናከብረው ከሊጉ ድል ጋር ነው አሰልጣኙ ካለው ልምድ አንፃር ከእስከዛሬዎቹ ነው የውጪ አሰልጣኞች የተሻለ ነው፤ በውል ስምምነታችን መሰረት የ2ዐ13 ፕሪሚየር ሊግ ማግኘት፣ በ2ዐ14 በሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ የመጨረሻዎቹ ስምንት ውስጥ መግባት ወይም የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ማሳካት ይጠበቅበታል” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የቦርድ ሰብሳቢው ሲናገሩ “የሊጉ ፉክክር ጠንካራ ይሆናል ብለን እናስባለን፤ ሊግ ካምፓኒው የሊጉን ደረጃ ከፍ በማድረግ በዲ ኤስ ቲቪ ለማስተላለፍ እየሰራ መሆኑ ጥሩ ነው ያለፉትን 3 አመታት ማስታወስ አንሻም ከእግር ኳሳዊ ህጎች ውጪ ብዙ ነገሮች ታይቷል፡ የእግር ኳስ ጨዋታም አልነበረም፤ ለውድድር ክልል ስንጓዝ ተጨዋቾቻችን ለነፍሳቸው የሚሳሱበት አስቸጋሪ ጊዜ አሳልፈናል፤ ሁለት አመታት ዋንጫ ያጣንበት ሳይሆን የተነጠቅንበትና የተቀማንበት ጊዜ ነው” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ አቶ አብነት ስለ አሰልጣኙ ሲናገሩ “ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ የውጪ አሰልጣኝ አያስፈልገንም፤ ጀርመናዊውን አሰልጣኝ የቀጠርነው በአፍሪካ ደረጃ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሰን አካዳሚው ላይ ትልቅ እገዛ እንዲያደርግልን ነው አካዳሚው ላይ እገዛ ለማድረስ ትልቅ ተስፋ ሰጥተውናል” ሲሉ የውል ሂደቱ ምን ያህል እንደተጓዘ አብራርተዋል፡፡ አቶ አብነት አፅንኦት በሰጡት አስተያየታቸው “የውጪ ሀገር አሰልጣኝ ሆነው መጥተው የደላላነት ስራ የሰሩ አሰልጣኞች ገጥመውናል፤ ይህን በፍፁም አንታገስም ፀሐይ ሳይወጣ እናባርራለን፤ ጊዮርጊስን በፍፁም ማዳከም አይቻልም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ማኅበር የቦርድ ዋና ፀሓፊ አቶ ንዋይ በየነ በበኩላቸው “ከውጪ ሀገር አሰልጣኞች ዋንጫ ብቻ ሣይሆን መዋቅራዊ ለውጥና እድገት እንድናስመዘግብ እንዲረዱን ነው የምንፈልገው፤ የኛ ሀገር ስልጠና በቀን 2 ሰዓት ብቻ ነበር እነ ሚቾ ግን በቀን 24ሰዓት እየሰሩ አዲስ ባህል አምጥተው የአሁኑ የዋሊያ አሠልጣኝ ላይ ሳይቀር ተፅዕኗቸውን አሳርፈዋል፡፡ እነኚህ ጀርመናዊ አሰልጣኝ የስራ ፍሬያቸውና ልምዳቸውን ይሰጡናል እዚህ መገኘታቸውም ለሊጉ እድገት ነው፤ ድብድብ የሌለበት ሕጋዊነት የተንሰራፋበት ክለቦች እርስ በርስ መላቀቃቸውን የሚያቆሙበት የውድድር አመት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ከአሰልጣኙ ጋር ስላላቸው ውል የተናገሩት አቶ ንዋይ “ውጤት ከጠፋ ሙሉ ቡድን አይቀየርም አሰልጣኙ ግን ይሰናበታል ካመንበት በ24 ሰዓት ውስጥ አሰልጣኙን የመቀየር መብቱ አለን፤ በኛ በኩል በአሰልጣኙ ስራ ጣልቃ አንገባም የአጨዋወትንና የአሰላለፍ መብቱ ሙሉ በሙሉ የአሰልጣኙ ይሆናል፤ ጣልቃ አለመግባት በታሪካችን ውስጥ መገለጫ ሆኖ ቆይቷል፤ የምንፈልገውን ካጣን ግን ማባረራችን የግድ ነው ይሄ ጣልቃ ገብነት አይደለም” በማለት ተናግረዋል፡፡

ዋና ፀሐፊው ሲናገሩ “በአፍሪካ አገርን የሚወክል ክለብ አባላት የዲፕሎማቲክ ቪዛ ያገኛሉ እኛ ሀገር ግን በተቃራኒው በግድ ነው ቪዛ የምናገኘው፤ የአፍሪካን ተሞክሮ ስንነግራቸው ተስቆብናል፤ ይሄ መቀጠል የለበትም እንደእኛ እምነት አሰልጣኙ ከነበረብን ክፍተቶች መሀል አንዱ ነው፤ ይሄ ክፍተት በደንብ ደፍነናል ብለን እናስባለን ያለን ቀሪ 8 ሳምንት ለአሰልጣኙ በቂ የመዘጋጃ ጊዜ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ አስተያየታቸው ሰጥተዋል፡፡

ፈረሰኞቹ የራሣቸውን የህክምና ቡድን ያቋቋሙ ሲሆን ከአንድ የህክምና ማዕከል ጋር ኮንትራት በመግባት የተጨዋቾቻንን በየጊዜው ወደ ተለያዩ ህክምና ቦታዎች የመጓዝ ታሪክን እንቀርፈዋለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የቡድኑ አባላትም የፊታችን ማክሰኞ ደብረዘይት በሚገኘው የክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ በመሰባሰብ ከአዲሱ ጀርመናዊ አሰልጣኝ ኤርነስት ሚደንድሮፕ ጋር በመሆን ልምምዳቸውን በይፋ እንደሚጀምሩ ታውቋል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport