መከላከያዎች በ2 ተጨዋቾቻቸው ተከሰዋል

የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ከቡድኑ አባል ዊልያም ሰለሞን ጋር በተያያዘ የቀረበበት ቅሬታ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ሀትሪክ
ባገኘችው መረጃ መሠረት ደግሞ ተጨዋቹ ከክለቡ ጋር የገባው የውል ስምምነት ቅሬታ መቀስቀሱ ታውቋል፡፡ ሁለቱ
ወገኖች ፌዴሬሽን ድረስ ሄደው ያፀደቁት ውል ላይ ያለው ስህተት ከ2 አመት በኋላ ሌላ ውዝግብ መፍጠሩ ታውቋል፡፡

በውል ስምምነቱ ላይ እንደተገለፀው ከጥቅምት 1/2011 እስከ ሰኔ 30/2013 የገቡት ውል ለሁለት አመት ብቻ
ፀንቶ ይቆያል ቢልም ዘመኑ ሲለካ 2 አመት ከ8 ወር መሆኑ ከፌዴሬሽንም ይህን ውል ያዋዋለው ባለሙያ ትክክለኛ
መሆኑን በደንብ ያለማረጋገጥ ክፍተት መፍጠሩ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ክለቡ ለ3 አመት ነው ቢልም ተጨዋቹ ግን እኔ
የማውቀው ለ2 አመት ነው አብረውኝ የፈረሙት ተጨዋቾች ውሉን ጨርሰው ሲወጡ እኔ ግን 3 አመት ያለፍላጎቴ
በተፈጠረ የውል ስህተት ለመቆየት አልገደድም ማለቱ ታውቋል፡፡ ጉዳዩ ፌዴሬሽን የደረሰ ሲሆን ሁለቱን ወገኖች
የማግባባት ስራ የመስራት ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ውሉን ያዋዋለው ሠራተኛ ላይ ርምጃ እንደሚወስድ ለሀትሪክ ገልጿል፡፡

የክለቡ አመራሮች ውሉ አለቀ አላለቀም በአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ እንደማትፈለግ ሣናውቅ አንለቅህም በማለታቸው
ተጨዋቹ ቡድኑ ለዝግጅት ወደሚገኝበት ደብረዘይት በማቅናት አሰልጣኙን ዮሀንስ ሳህሌን ማነጋገሩ ታውቋል፡፡ መረጃዎች
አሰልጣኙ ለዋና ቡድንም ይሁን ለተስፋ ቡድን እንደማይፈልጉት መልቀቅም እንደሚችል እንደነገሩት ለክለቡ ኃላፊዎች
ቢገልፅም አሁን ድረስ ሊለቁት አልፈለጉም፤ በተለይ የክለቡ ስራ አስኪያጅ ኮ/ል ደሱ ታደሰ ተጨዋቹን ላለመልቀቅ
እየታገሉ መሆኑ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ውሉን ካጠናቀቀ በሠላም አመሰግነው ሊሸኙት ሲገባ እየተፈጠረ ያለው ማንገላታት
ምክንያቱ ምን ይሆን ያለው የውስጥ አዋቂ ፌዴሬሽኑ በፍጥነት መልቀቂያውን ሊሰጠው እንደሚገባ አስረድቷል፡፡
ሀትሪክ ባገኘችው መረጃ መከላከያዎች ተጨዋቹ አንድ የፕሪሚየር ሊግ ክለብ ሊወስደው እንደሚፈልግ በመስማታቸው
በክፍያ እንዲለቅ ፈልገው ያደረጉት መላ ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡ ተጨዋቹ እንደጓደኞቼ ለቀውኝ ቤተሰቤን ልረዳበት
ወደ ምችልበት ክለብ የመግባት መብቴን ሊያከብሩልኝ ይገባል ማለቱም ተሰምቷል፡፡ በተጨዋቹና በክለቡ መሀል
በተነሳው ውዝግብ ዙሪያ የመከላከያው ስራ አስኪያጅ ኮ/ል ደሱ ታደሰ ለሀትሪክ እንደገለፁት “ተጨዋቹ አምናም
ቡድናችን ውስጥ የነበረ ነው፡፡ አሰልጣኝ ዮሐንስ አልፈልግህም አለኝ የሚለው ልክ አይደም፡፡ አቋምህ ወርዷል፣ ታችኛው
ቡድን ወርደህ ጥሩ ስትሆን እመልስሃለሁ ነው ያለው፡፡ ተጨዋቹ ሌሎች ክለቦች ፈልገውኛልና ልቀቁኝ እያለ ነው፡፡ ነገር
ግን በኤም.አር.አዩ ከ2ዐ ዓመት በታች ቡድናችን ወርዶ መጫወት ስለሚችል እዚያ እንዲጫወት እንፈልጋለን፡፡ ሕጉም
እኛም እናስገድደዋለን፡፡ ውሉ ላይ ያለው ስህተት በእርግጥም ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ከታች ያደገ ተጨዋች ቡድኑን ለ3
ዓመት ማገልገል አለበት የሚለው ሕግ የግድ መከበር አለበት” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ መከላከያዎች የአንድ አመት ውል እያለው በአሰልጣኙ ዮሀንስ ሳህሌ እቅድ ውስጥ የለም
የተባለውን ግብ ጠባቂ ሰሚር ነስሮ ብሔራዊ ሊግ ለሚገኝ ክለብ በውሰት እንዲጫወት ለአሰልጣኙም ኮ/ል በለጠ
ገ/ኪዳን ሪፖርት እንዲያቀርብ የሰጡት ትዕዛዝ ደግሞ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ ግብ ጠባቂው ሰኔ 30/2013 ድረስ ውል
ያለው ሲሆን የውል ስምምነቱ እንዲከበር ጠይቆ የማይሆን ከሆነ ደግሞ በውሉ መሰረት ሰኔ 30/2013 ድረስ ያለው
ደመወዙ እንዲከፈለው በመጠየቅ የክለቡን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል፡፡ ተጨዋቹ ውሳኔው ከውል ስምምነቱ ውጪ
እንደሆነ በመግለፅ ደብዳቤ ያስገባ ሲሆን በግልባጩ ለፌዴሬሽኑ ያለበትን ሁኔታ ማሳወቁ ታውቋል፡፡ ፌዴሬሽኑ በበኩሉ
ለሀትሪክ እንደገለፀው ከከፍተኛ ሊግ ወደ ብሔራዊ ሊግ አስገድዶ ሳይሆን በፈቃዱም መላክ አይቻልም የሁለቱ ሊጎች
ክፍያ በጣም ይለያያል፤ በከፍተኛ ሊግ በመከላከያ የሚከፈለው ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም እንደማይነካበት መገለፁ
ደግሞ የብሔራዊ ሊጉን ሕግ እንደማያከብር ማሳያ ነው፤ በፍፁም የሚፈቀድ ሕጋዊ አካሄድ አይደለም” በማለት
በቀጣይ የሚሆነውን አስረድቷል፡፡

የመከላከያ ኃላፊዎች የሰሚር ነስሮን አቅምና ብቃት እንደሚያምኑበት ነገር ግን ወሳኝ ግብ ጠባቂ የሚሆነው ከ2
አመት ልምድ በኋላ መሆኑና ክለቡ ግን ለአሁኑ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የመመለስ ጠንካራ እቅድ በመያዙ ልምድ ያላቸውን
ለማስፈረም እንደወሰነ ለተጨዋቹ ወኪል መናገራቸው ታውቋል፡፡ የአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ መከላከያ ወደ ፕሪሚየር
ሊግ ለማዳግ በያዘው እቅድ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ባቀናው አቤል ማሞና አንፈልግህም ባሉት ሰሚር ነስሮ ቦታ ከቡድኑ ጋር
ካለው ታሪኩ አረዳ ውጪ ከመቐለ 7ዐ እንደርታ ሶስተኛ በረኛውን ምህረተአብ ገ/ሕይወትን እንዲሁም ከአዳማ ከተማ
ሁለተኛ በረኛውን ጃፈር ደሊልን አስፈርመዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ አስተያየታቸውን የሰጡት የመከላከያው ስራ አስኪያጅ ኮ/ል
ደሱ ታደሰ በበኩላቸው “በእኛ በኩል የያዝነው አቋም ናና እንደራደር የሚል ነው፡፡ የተለየ ማስገደድ የለውም፡፡ ታችኛው
የወታደር ቡድን ሄደህ ሪፖርት አድርግ ማለት አቋምህ ወርዷል ሲስተካከል ትመለሳለህ ማለት ነው፡፡ ከዚያ ውጭ
የምንዳኘው በሕግ ስለሆነ አናስገድደውም” በማለት ምላሻቸውን ለሀትሪክ ሰጥተዋል፡፡

 

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport