“ይሄ ቡድን አስቀድሞ ቢኖር ለአፍሪካ ዋንጫ የምናልፍበት ዕድላችን ሙሉ ለሙሉ ይሆን ነበር፤ አሁንም ተስፋ አንቆርጥም” ጌታነህ ከበደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን /ዋልያዎቹ/ ካፒቴን ጌታነህ ከበደ በአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ላይ ቡድናችን ከማዳጋስካር ጋር ስለሚያደርገው ጨዋታ እና ስለ ቡድናቸው አቋም እንደዚሁም ደግሞ ከማላዊ ጋር ስላደረጉት ጨዋታ እና ሌሎችን ጥያቄዎች ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አንስቶለት ምላሽን ሰጥቶታል፡፡

የማላዊ ብሔራዊ ቡድንን በአቋም መለኪያ ስለተፋለሙበት እና ድል ስላደረጉበት ጨዋታ

“ከማላዊ አቻችን ጋር ያደረግነው የወዳጅነት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ እነሱ እስከ 10 እና 15 ደቂቃዎች ውስጥ ጥሩ ነበሩ፤ ቡድናቸው ቅርፅ ኖሮትም ኳስን በደንብ ይጫወትም ነበር፤ እንደዛም ሆኖ ግን በዕለቱ የነበረው ሞቃት የአየር ሁኔታ አይደለም ለእነሱ ለእኛም በጣም ከባድ ስለነበር በእንቅስቃሴው በኩል እነሱን በፈለጉት መልኩ ብዙም እንዳይጓዙ አድርጓቸዋል፤ የአየር ሁኔታውን በተመለከተ ለእኛ ጠቅሞናል ብለን የምናስበው ብዙዎቻችን የዋልያ ተጨዋቾች በባህርዳር ለአንድ ወር ያህል ለሚደርስ ጊዜ እዚሁ ተቀምጠን ስለነበር ነው፤ ወደ አጠቃላይ ጨዋታው ስናመራ እኛ በመጀመሪያው አጋማሽም ሆነ በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ተንቀሳቅሰን ነበር፤ ከማላዊ በተሻለ መልኩ ስለተጫወትንም ነው ግጥሚያውን ልናሸንፍ የቻልነው”፡፡

በወዳጅነት ያሸነፋችሁት ማላዊ ደካማ ነው ስለመባሉ

“ማላዊ ደካማ ሳይሆን ጥሩ ቡድን ነው፤ ምንአልባት አራት ግብ ስላስቆጠርንበት ደካማ ቡድን ሊመስለን ይችላል፤ በዕለቱ ጨዋታ እነሱ የተለያዩ ተጨዋቾችን እየቀያየሩ በማጫወት የቡድናቸውን አቋም ለመለካት ጥረትን አድርገዋል፤ እኛም የተወሰኑ ልጆችን በመቀየር ተጫውተናል፤ ማላዊ ደካማ ቡድን አይደለም ከዚህ ቡድን ጋር ከዚህ ቀደምም ተጫውተናል፤ በሜዳችን 0-0 ተለያይተን እዚያ 3-2 ልንሸነፍ ችለናል፤ ከዛ ውጪ ቡድኑ በፊፋ የሀገሮች ደረጃም ከእኛ የሚሻል ሀገር ስለሆነም ስለ እነሱ ጠንካራነትና ጥሩነትም ነው የማውቀው”፡፡

በረቡዕ ጨዋታ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከተቆጠሩት ግቦች ውስጥ አንዱን ስለማስቆጠሩ እና ግቡን ስላስቆጠረበት መንገድ

“ዋልያዎቹ በወዳጅነት ጨዋታው ላይ ለድል ከበቁበት ጎሎች መካከል አንዷን ላስቆጥር የቻልኩት በትሬሊንግ ሜዳው ላይ ከምንሰራቸው የታክቲክ ልምምዶች መካከል የምትጠቀሰውን ነው፤ የእኛ ቡድን ጎሎች የልምምድ ውጤቶች ናቸው፤ ቡድናችን ጎሎችን ለማስቆጠር የኮርናና የቅጣት ምቶችን ሲያገኝ በእነዚያ ላይም የተለያዩ ስራዎችንም ይሰራል፤ ለምሳሌ እኔ ጎሉን ያስቆጠርኩበት መንገድ ለየት ይላል፤ ቅጣት ምቱ ሲገኝ ኳሱ ጋር መስሑድ እና ረመዳን ነበሩ፤ መስሑድ እንደመምታትም እንደማሻማትም ብሎ ኳስን የሰጠው ከዛ ቦታ ላይ ሮጦና በፍጥነት አምልጦ ለሄደው ረመዳን ነበር፤ ማላዊዎች በእዛ እንቅስቃሴ ውስጥ ግራ ተጋብተውና ያወቁትም ነገር ብዙ ስለሌለ ረመዳን ለእኔ በግንባሩ በመግጨት ኳሱን አቀበለኝ እኔም አቋቋሜ ጥሩ ስለነበርና ታይሚንጌንም ስለጠበቅኩኝ ፈጥናብኝ የነበረችውን ኳስ ደርሼባት እንደመንሸራተት ብዬም ከመረብ ላይ ላሳርፋት ቻልኩኝ”፡፡

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ዋልያዎቹን በኃላፊነት ከተረከበ በኋላ ተከታታይ ጎሎችን ስለማስቆጠሩ እና ግቦቹን ለማስቆጠር ስለቻለበት መንገድ

“የእውነት ነው፤ በእሱ የአሰልጣኝነት ዘመን ለሀገሬ ካደረግኳቸው ስድስት የወዳጅነት ጨዋታዎች ውስጥ በአምስቱ ላይ ጎሎችን አስቆጥሬያለው፤ ግቦቹን ለማስቆጠር ከረዱኝ ነገሮች ውስጥ ልጠቅሰው የምፈልገውም ቡድኑ የያዘው የአጨዋወት ታክቲክ ኳስን መሰረት ያደረገ ይሄም ማለት ኳስ ሳይባክን ተቆጣጥሮ በመጫወት የያዘው አጨዋወት ስላለና በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱም ጊዜ የነበረው ቡድን በአብዛኛው ሳይበተን አብሮም ስላለ ይሄ ለእኔ ግብ ማስቆጠርም ሆነ አሁን ላይ ጥሩ ቡድንም እንዲኖረን እያደረገ ያለም ነገር ነው፤ በዚህ ቡድን አጨዋወት በቀጣይነትም ሌሎች ግቦችን አስቆጥራለው”፡፡

ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ ሁለቱ ተከታታይ ጨዋታዎቻችን ለእኛ በጣም ወሳኞች ናቸው፤ ከእነዚህ በፊት ካደረጋችኋቸው ጨዋታዎች ውስጥ ግን ለአንተ በጣም ያስቆጨህ ግጥሚያ የቱ ነው….?

“በአሁን ሰዓት ካለን ጥሩ ቡድን አንፃር ቀደም ሲል ኒጀር ላይ ያደረግነውና በጠባብ ውጤት የተሸነፍንበት ጨዋታ በጣም ሊያስቆጨኝ ይችል ይሆናል እንጂ በእዚያን ጊዜ ላይ ከእነሱ ጋር ባደረግነው ጨዋታ እኔ ብዙም የምቆጭበት ነገር አይኖረኝም፤ ምክንያቱም እኛ ዋልያዎች በጊዜው ኒጀርን የገጠምነው የኮቪድ ወረርሽኝ ወደ ሀገራችን ገብቶ እና ብዙዎቻችን ተጨዋቾችም በእዚህ በሽታ የተነሳ ምንም አይነት ልምምድን አይደለም በቡድን በግል ጭምር እንዳይሰሩ ክልከላ በመደረጉና በቤታቸው ተወስነው እንዲቀመጡ በመደረጉና በአጠቃላይ ከማንኛውም እንቅስቃሴዎችም የራቁበት አጋጣሚ በመፈጠሩ በዛ ደረጃ ላይ ነው ለብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሀገሪቱ የሊግ ውድድር በወረርሽኙ ምክንያት ከመቋረጡ በፊት ቀደም ሲል በነበራቸው ብቃት የሚያውቃቸውን ተጨዋቾች በመጥራት እንዲጫወቱ ያደረገውና ከዚህ መነሻነት ነው ቡድኑ ባስመዘገበው ውጤት ልቆጭ አልችልም ያልኩት፤ ኒጀርን ያኔ የገጠምነው እኛ በኮቪድ ከራቅንበት ውድድር ዳግም በመመለስ ነው፤ እነሱ ደግሞ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችንም የያዙ ስለነበሩ ውድድር ላይ ሆነው ነው፤ እንደ አሁኑ ቡድን ቢሆን ግን ያኔ እነሱን በእርግጠኝነት በቀላሉ የምናሸንፍበት እድሉ ይኖረን ነበር፤ ከዛ ውጪም ይሄ የአሁኑ ቡድን ያኔ ኖሮ ቢሆን ኖሮም ለአፍሪካ ዋንጫ የምናልፍበት እድላችንም ለሙሉ ለሙሉ ይሆንልንም ነበር፤ ይህን ልል የቻልኩት በጊዜው የነበረውን ጨዋታ በደንብ ስለማውቀውም ነበር፤ ያኔ ቡድናችን ጥሩ ቢሆንም፤ የተሸነፍነው በጥንቃቄ ጉድለት የፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቶብን ነው”፡፡

በአፍሪካ ዋንጫው የማጣሪያ ጨዋታ ማዳጋስካርን ስለሚፋለሙበት የረቡዕ ጨዋታ

“የሁለታችን ጨዋታ በጣም ወሳኝ ነው፤ በተለይ ደግሞ ወሳኝነቱ ለእኛ ነው፤ ከእነሱ ጋር የምናደርገውን ይህን ጨዋታ ከሁለት ግብ በላይ አስቆጥረን ማሸነፍ ይኖርብናል፤ ምክንያቱም በመጀመሪያው ጨዋታ እነሱ ያሸነፉን 1-0 ስለሆነና ምንአልባትም ደግሞ እኩል ነጥብ ላይ ተቀምጠን እኛ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የምናልፍበትን ዕድል የምናገኝ ከሆነ በእርስ በርስ ግንኙነት የቱ ቡድን የተሻለ ግብ አስቆጠረህ የሚለው ስለሚታይ ያ ሊጠቅመን የሚችል ነውና ማዳጋስካሮችን የግድ ማሸነፍ እና ቀጣዩን የኮትዲቯርንም ግጥሚያ ማሸነፍ ይኖርብናል”፡፡

ለአፍሪካ ዋንጫ ያልፉ እንደሆነ

“ተስፋን አንቆርጥም፤ በሁለቱ ጨዋታዎች ላይ ግጥሚያዎቹን በማሸነፍ እድላችንን እንሞክራለን”፡፡

ከአፍሪካ ዋንጫው በኋላ በዓለም ዋንጫው ላይ ስለሚያደርጉት የማጣሪያ ጨዋታ

“የእኛ የዓለም ዋንጫ ምድብ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዙምቧብዌ የሚገኙበት ነው፤ የሞት ምድብም ነው፤ ከእነሱ ጋር የሚኖረንም ጨዋታ በከባድነቱ አቻ የማይገኝለትም ነው፤ ጋናንና ደቡብ አፍሪካን ትተህ እንኳን ዙምቧቡዌን ብትወስድ እነሱም በአውሮፓ ደረጃ የሚጫወቱ በርካታ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ያሏቸው እና ጠንካሮችም ናቸው፤ ከእነሱ ጋር መደልደላችንን በጣም ነው የወደድኩት ምክንያቱም አቋማችንን በደንብ አድርገን እንድናውቅ የሚያደርጉን ስለሆነ ነው፤ ቡድናችን ለእዛም ጭምር እየተሰራም ያለ ነው”፡፡

የዋልያዎቹ የአሁኑ ስብስብ

“በጣም ጥሩ ቡድን ነው ያለን፤ ይሄ ቡድን በአሁን ሰዓት ጥሩ ልምድን እያገኘም ነው፤ ከዚህ በፊት በነበሩት ጨዋታዎች ላይ የልምድ እጦት ቡድኑን ጎድቶት ነበር፤ እኔ በጉዳት ባልነበርኩበት የመጀመሪያው የማዳጋስካር ጨዋታ ላይ እንኳን እነ አቡኪና የሐዋሳ ከነማው መስፍን ልምዱ በጊዜው ስላልነበራቸው ጎል ማስቆጠር በሚችሉበት ጨዋታ ላይ ያን ማሳካት አልቻሉም ነበር፤ አሁን ግን ልምዱን እነ አቡኪ ስላገኙ ጎልን ማንም ላይ ማስቆጠር ይችላሉና፤ በዚህ ሰዓት በየቦታው የሚጫወቱት የተጨዋቾች ስብስብም ኳስን ይዞም የሚጫወት ነውና በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ከዛ ውጪ ይሄ ቡድን ጥሩ ከመጫወቱ በተጨማሪ ጎል ጋር በተደጋጋሚ ጊዜም የሚደርስ ነውና ይሄ ቡድን ወደፊት ለጥሩ ደረጃ እንደሚበቃም እምነቴ ነው”፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁሌም ጠንካራ እንዲሆን ከተፈለገ

“ለእዛ መፍትሄው ሁሌም አንድ ላይ የተሰባሰበ ቡድን መበተን እንደሌለበት ነው፤ ከዚህ ቀደም የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውን ቡድን ባሬቶ ሲመጣ በትኖት ቡድኑ ውጤትን ሊያጣ ችሏል፤ ከእሱ በኋላም የነበረውን ቡድን አሰልጣኝ ዩሃንስ ከያዘው በኋላ ተቀይሮ ሌላ ቡድን ተሰርቷል፤ ገብረመድህን በያዘው ጊዜ ግን ያሉትን ተጨዋቾች አሳባስቦ በመቀጠል ሁለት ጨዋታን ሊያሸንፍ ቢችልም እሱ ከቡድኑ ጋር በመለያየቱ ቡድኑ ብዙም ላይጓዝ ችሏል፤ የአሁኑ ቡድን ደግሞ በኢንስትራክተር አብርሃም ጊዜ የነበረውን ቡድን ውበቱ አባተ ሊያስቀጥለው በመቻሉ ጥሩ ነገርን እየተመለከትን ይገኛል፤ ውበቱ ዋልያዎቹን አሁን ወደ ጠንካራ ቡድንነት ለመውሰድ የሚቻለውን ነገር እያደረገም ይገኛልና ይሄ ቡድን ሳይበተን ሊቀጥልም ይገባል”፡፡

የኢትዮጵያ ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ በዲ ኤስ ቲ ቪ በመተላለፉ ለሀገሪቱ ብሔራዊ ቡድንና ለተጨዋቾች ስለሚጠቅመው ነገር

“ጨዋታዎቹ መተላለፋቸው በጣም ጥሩ ነው፤ ከዚህ በፊት 40 ተጨዋቾችን ነበር ለብሔራዊ ቡድን በስምና በዝና እንደዚሁም ደግሞ ባላቸው ችሎታም ከመረጥክ በኋላ እየቀነስክ የመጨረሻዎቹን ልጆች የምታስቀረው፤ አሁን ግን በአንዴ ጨዋታዎቹን በቀጥታ በመመልከት እና በአካል በመገኘትም ተከታትለህ የምትፈልጋቸውን ተጨዋቾች በወቅታዊ ብቃታቸው ትመርጣለህና ይሄ አሰራር ጥሩ ነው፤ ከዛ ውጪም ደግሞ በተለይ ለታዳጊ ወጣት ተጨዋቾች የእዚህ ውድድር መተላለፍ ራሳቸውን ለውጪ ገበያ የሚያቀርቡበት እድሉም ስላለ እና ኤጀንቶችም ስለሚመለከቷቸው በዛ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉና በዚህ አጋጣሚ እነሱ ጠንክረው በመስራት የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በጣሙን ነው የምመክራቸው”፡፡ እኔ ነኝ እመክራቸዋለው”፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website