ከኮትዲቫዋር ድላችን በኋላ ከኛ ብሔራዊ ቡድን ጋር ለመጫወት የማይፈልግ ሀገር የለም” አቶ ኢሳያስ ጅራ /የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት/

ዋሊያዎቹ ከማዳጋስካር አቻቸው ጋር በሚኖራቸው ጨዋታ ድል ከቀናቸው ጠቀም ያለ ማበረታቻ እንደተዘጋጀላቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በተለይ ለሀትሪክ እንደገለፁት “ማላዊን በረታው ቡድናችን ደስተኞች ነን ምርጥ ብቃታቸውን አውጥተዋል ያሸነፍነውም ከእኛ በላይ የሆነች ሀገርን መሆኑ መታወቅ አለበት ግቦቹ በእውቀት የተቆጠሩ ናቸው የህብረት ስራም የታየባቸው መሆኑ አስደስቶኛል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አቶ ኢሳያስ ሲናገሩ “እኔ እንደ አመራር ነው የማየው አሰልጣኙ ቴክኒካል ያለው ነገር ተመልክቶ ቡድኑን የማጠናከር ስራ ይሠራል ብዬ አስባለው ተሸንፈን አቋማችንን አይተናል ከምንል አሸንፈን ደካማውን ክፍል ማየቱ ይመረጣል ማሸነፍ ስነ-ልቡናችንን ከፍ የሚያደርግ መሆኑ መታወቅ አለበት” ሲሉም ለሀትሪክ ገልፀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ እንደሚሉት “ፌዴሬሽኑ አሁንም ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ከብሔራዊ ቡድኑ ጎን ነው ውጤታማ ከሆኑም ዳጎስ ያለ ማበረታቻ እንሰጣለን ምንም የምንቆጥበው ነገር የለም ለቡድኑ አባላትም መልካም ውጤት እመኛለሁ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አቶ ኢሳያስ ከሀትሪክ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ እንደገለፁት “የወዳጅነት ጨዋታ አላማ ማሸነፍና መሸነፍ አይደለም አሰልጣኙ የቡድኑን አቋም የሚለካበት በመሆኑ ማላዊን 4ለ0 መርታታችን ያለንን ጠንካራ አቋም አሳይቶናል ደካማ ጎናችንንም በማሸነፍ ውስጥ እንደሚያይ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ “ከዚህ በፊት በነበረው ልምድ የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ከፍተኛ ስቃይ ነበር አሁን ያ ባለመኖሩ ደስ ብሎኛል ትልቅ ለውጥም አምጥተናል” ያሉት አቶ ኢሳያስ “ከዚህ በፊት እንደነበረው የወዳጅነት ጨዋታ ለማግኘት ይገጥመን የነበረው ስቃይ አሁን የለም በፈለጉበት ሰዓት የወዳጅነት ጨዋታ የማግኘት አቅም ገንብተናል ማላዊ ከአለም 123ኛ ነው ከኛ ጋር ለመጫወት በ23 ደረጃ በልጠውንም አላንገራገሩም 146ኛ ደረጃ መሆናችን እንቢ እንዲሉ አላደረጋቸውም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ “ማላዊ በአቋሙ ጥሩ ባለመሆኑ የንቀት አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች ገጥመውኛል 4ለ0 ብናሸንፍም ክፍተት እንደነበረብን አይካድም” በማለት ተጋጣሚውን መናቅ ዝቅ አድርጎ ማየት ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከማላዊ ብሔራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታው የተካሄደው አቶ ኢሳያስ ጅራ ከማላዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጋር ካሜሩን ላይ ተገናኝተው ከተነጋገሩና ከተሰማሙ በኋላ ሲሆን ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት ፌዴሬሽኖች መሀል ግንኙነት እንዲፈጠር አድርጎ ጨዋታው ሊካሄድ ችሏል፡፡ ከሱዳን ብሔራዊ ቡድን ጋር ወሳኝ ጨዋታ ያለባቸው ማላዊያኑ ባህርዳር ላይ የመዘጋጀት እድል ማግኘታቸውን በበጎ ጎን ወስደውታል፡፡ የማላዊ ብሔራዊ ቡድን የቲኬቱን ወጪ ብቻ የሸፈነ ሲሆን የሆቴልና የሀገር ውስጥ ትራንስፖርት ሙሉ ወጪ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መቻሉ ታውቋል፡፡

“ለበርካታ ጊዜያት የዘለቀው የወዳጅነት ጨዋታ የማግኘት ችግራችንን ቀርፈናል” የሚሉት አቶ ኢሳያስ “ላይቤሪያ፣ ጋና፣ታንዛኒያና ማላዊ ለወዳጅነት ጨዋታ ቢስማሙም ታንዛኒያ ሌላ ወገን ጣልቃ በመግባቱ ጋናና ላይቤሪያ አክራና ሞኖሮቪያ ሄደን እንድንጫወት በመጠየቃቸው ሳይሣካ ቀርቷል፡፡ ሀገራችን ላይ ጨዋታ እያለብን ወደ ሌላ ሀገር መጓዝን ሳንቀበለው በመቅረታችን ከማላዊ ጋር ለመጫወት ችለናል” በማለት አሁን ያለበትን ሁኔታ አስረድተዋል፡፡
“ማንም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር መጫወት ይፈልጋል ከኮትዲቫዋር ድላችን በኋላ ከኛ ብሔራዊ ቡድን ጋር ለመጫወት የማይፈልግ ሀገር የለም አንድ ትልቅ ቡድን ማሸነፋችን ከፍ ያለ ግምት እንዲሰጠን አድርጓል፡፡ ማዳጋስካር አገሯ ላይ ብታሸንፈንም በልጠን ነው የተጫወትነው ኒጀር ላይ የጣልነው ነጥብም የሚያስቆጭ ነው” በማለት አቶ ኢሳያስ ተናግረዋል፡፡

ስለ ማላዊ ብሔራዊ ቡድን ሲናገሩም “በወዳጅነት ጨዋታ ማሸነፋችን ትልቅ የስነ ልቦና ግንባታ እንድናደርግ ረድቶናል ያሸነፍነውም በደረጃ የሚበልጠንን ቡድን ነው የማላዊ አብዛኞቹ ተጨዋቾች በደቡብ አፍሪካ ፕሮፌሽናል ሊግ የሚጫወቱ መሆናቸው የተጨዋቾቻችንን ሞራል የመገንባት አቅም አለው የማላዊ ብሔራዊ ቡድን ከደቡብ ሱዳን ጋር ላለበት ጨዋታ ሙሉ ቡድኑ ይዞ ነው የመጣው የቡድናችንን አባላት ማድነቅ ነው ያለብን ምርጥ ብቃታቸውን አሳይተውናል በማዳጋስካር ላይም እንደሚደግሙት አልጠራጠርም” በማለት ለሀትሪክ አስረድተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ አቶ ኢሳያስ ጅራ ሉሲዎቹን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት “በፊፋ የወዳጅነት ጨዋታዎች ካላንደርን በሚገባ እየተጠቀምን ነው በሚያዚያ የፊፋ ካላንደር ሉሲዎቹ ከደቡብ ሱዳን ጋር እንዲጫወቱ ለማድረግ ቀጠሮ ይዘናል ተስማምተናል ለፊፋ የሚሞላውን ፎርም ሞልቶ መላክ ብቻ የቀረው ለሁሉም ብሔራዊ ቡድኖቻቻችን የወዳጅነተ ጨዋታ ለማግኘት እንሰራለን” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ስለ ፌዴሬሽኑ የፋይናንስ አቅም የሚናገሩት አቶ ኢሳያስ “የወዳጅነት ጨዋታዎች በርግጥ ከፍተኛ በጀት ይጠይቃሉ የሚመጣውን ቡድን ሙሉ ወጪ መሸፈን ይጠበቅብናል ይህን የማድረግ አቅም መገንባታችን በራሱ የሚያኮራን ነው” ሲሉ ለሀትሪክ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport