አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከድል መልስ የመጀመሪያ መግለጫ ሰጡ

ዋሊያዎቹ ለአፍሪካ ዋንጫ ካለፉ በኋላ የመጀመሪያ የሆነው ጋዜጣዊ መግለጫ እየተሰጠ ነው።
ዋና ጸሀፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን “ለአለም ዋንጫ ማጣሪያው ከውድድር ውጪ የሚካሄድ በመሆኑ ወጪ ያስፈልገዋል ይህን ወጪ ለመሸፈን በየክልሉ ጉዞ በማድረግ ከክልል ፕሬዝዳንቶች ጋር በመነጋገር ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዷል ከዚያ ውጪ ባለሀብቶችንና ተቋማትን ለማነጋገር እየተሰራ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። አቶ ባህሩ ጨምረውም የዋሊያዎቹ አማካይ እድሜ 25 መሆኑን አስረድተዋል።

ከሰበታ ከተማ ጋር ስለነበረውና ስለተቋረጠው የአሰልጣኙ ውል ጉዳይ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን ዋና ጸሀፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን በሰጡት ምላሽ “ያኔ ስንነጋገር የነበረው ስለነበረው ውል እንጂ ስለገንዘቡ አልነበረም አሁንም አሰልጣኙ ሳይጨነቅ ነጻ ሆኖ የሚሰራበት እድል ለማመቻቸት ይሰራል” ሲሉ ተናግረዋል። አሰልጣኙ ውበቱ በበኩላቸው “ውል ስፈርም በአትኩሮት አይቼ ነው ነገር ግን አንድ ስህተት ሰርቻለሁ የውሉም የገንዘቡም ጉዳይ ሳይፈታ መፈረሜ ልክ አይደለም መታወቅ ያለበት ውል አፍርሼ አልሄድኩም ከክለብ ወደ ብሄራዊ ቡድን ነው ይሄ መታወቅ አለበት ችግሩን ይፈታሉ ብዬ የማስባቸው ጋር ሄጄ አልተሳካም ለማንኛውም እንደ አንዳንድ ሚዲያዎች ሰበታ አላስጨነቀኝም ስም ማጥፋታቸውን ማቆም አለባቸው ሀላፊነቴን ያልተውኩት በተተራመሰ ሀገር ላይ ሌላ ትርምስ እንዳልፈጥር ብዬ ነው” ሲል ተናግሯል።

አሰልጣኝ ውበቱ “የማዳጋስካርና የኮትዲቯር ጨዋታ ዙሪያ እንደተናገሩት አጨዋወታችን ተመሳሳይ ነው ይሄ በርግጥም መለመድ አለበት ቀጣይም አጨዋወት እንዲህ ነው ነገር ግን የተሸነፍንበትን መንገድ አይተን መገምገም ይኖርብናል ለምንጫወተው አጨዋወት ታማኝ መሆን ይጠበቅብናል ያ እምነት ተጨዋቾቼ ውስጥ እየገባ ነው በዚህም ደስ ብሎኛል” ሲል ተናግሯል።

ስለ ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ የተናገረው አሰልጣኝ ውበቱ “በ3 ጨዋታ 3 ግብ ተቆጥሮበታል 3 ጨዋታ ላይ ደግሞ አልተቆጠረበትም ሲገባበት የምንቀይር ከሆነ ከባድ ስህተት ይሆናል ጎሜዝ ቦታው ርስቱ አይደለም ከጎበዘ ግን ይቀጥላል በቀጣይ ግን ለሁሉም በረኞች በሩ ክፍት ነው ከዚህ በፊት ተጨዋቾች ሲወጡ አላማቸው ወጥቶ ለመቅረትና ገበያ ሄዶ እቃ ለመግዛት ነው አሁን ግን ይሄ ተቀይሮ ለመጫወት ብቻ የሚሄዱበት ሆኗል የብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋች ማርፈድ አይችልም እርስ በርስ መጣላት አይችልም ሞባይል ይዞ መገኘት አይችልም የቡድኑን ሚስጢር መጠበቅ አለበት ይሄን ቢጥሱ የሚሆነውን ያውቃሉ ብሄራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ አልፏል ከዚህ በኋላ ሲጠራ አልመጣም የሚል ተጨዋች ይኖራል ብዬ አላስብም ” ሲል መልሷል።

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport