“ከአዛውንቶችና የጎዳና ልጆች ያገኘሁት የእንኳን ደስ አለህ ለኔ ትልቅ ትርጉም አለው…” አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

በዮሴፍ ከፈለኝ

ሀትሪክ፡- እንኳን ደስ አለህ…?

ውበቱ፡- እንኳን አብሮ ደስ አለን፤ በተመዘገበው ድል ተደስቻለሁ ህዝቡም በመደሰቱ ትልቅ እረፍት ተሰምቶኛል፡፡

ሀትሪክ፡- የህዝቡን ደስታ እንዴት አገኘኸው?

ውበቱ፡- በጣም የሚገርምና ከጠበኩት በላይ ሆኖ ነው ያገኘሁት በጣም ተደስቻለሁ… ሰው በዚህ ደረጃ ይደሰታል ብዬ አልጠበኩም… ከአገርና ከአገር ውጪ በአጠቃላይ ከመላው አለም የእንኳን ደስ አለህ መልዕክቶች ደርሶኛል፤ ይሄ ድጋፍ ከማለፋችን በፊትም ስለነበር ጥሩ ስሜት ተሰምቶኛል ድሮ አብረውኝ የተጫወቱ ጓደኞቼ በተለያየ ቦታ አብረውኝ ያሳለፉ ሰዎች በሙሉ ጎረቤቶቼ ሳይቀሩ በየሄድኩበት ቦታ ሁሉ ያገኘሁት ሙገሳ ሰው ላይ ያየሁት ደስታ ትልቅ ክብር እንዲሰማኝ አድርጎኛል፡፡

ሀትሪክ፡- በአንድ ቃለ ምልልስ ላይ ስለ ኢትዮጵያ ቡና ድልህ ሳወራህ ባለፈ ታሪክ ላይ ቆሜ አልገኝም ለቀጣይ ድል ነው የማስበው.. ብለኸኝ ነበርና ለዚህ ነው ይህን ድል ያሳካሁት ብለህ ታምናለህ…?

ውበቱ፡- አዎ ሁሌ የማስበውና የምጥረው ነገዬ ላይ ነው ባለፈ ታሪክ ላይ መቆም አልሻም፤ ዛሬን ለነገ መንደርደሪያ ማድረግ ያስደስተኛል ከትላንትናው የተሻለ ሆኖ መገኘት ነው ህልሜ…

ሀትሪክ፡- የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ግንቦት ላይ ይጀመራል.. ያ ውድድር ላይም ተስፋ እናደርግ?

ውበቱ፡-/ሳቅ/ ለምን አይሳካም? ይሆናል ከእግዚአብሔር ጋር መሻገር የምፈልገው ወደ አለም ዋንጫው ነው ከዚያ በላይ ግን የቅድሚያ ፍላጎቴ የአፍሪካ ዋንጫው ላይ ጥሩ ቡድን ይዤ የመግባት ህልሜን ማሳካት ነው፡፡ ሌሎች ጠንክረው የደረሱበት ደረጃ መድረስ እፈልጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የሀገሬን ውለታ መለስኩ ብለህ ታምናለህ?

ውበቱ፡- በፍፁም በፍፁም…. አይደረግም… በሙያዬ አገልግያለሁ የምወደው ሙያ ላይ ነኝ ያለሁት በምወደው ሙያ ላይ ስሰራ ለሌሎች መትረፍ አለብኝ ብዬ አስባለው ገና ለሀገሬ የምሰራው ስራ አለ በግሌ ገና የምሠራው ስላለ ገና ነኝ ብዬ አስባለው.. ከዚህ በፊት ከሠራሁት ይልቅ ከዚህ በኋላ የምሰራው ይበልጣል በእርግጥ ከእስከዛሬው ታሪኬ አንዱ የደስታ ጊዜዬ ነው ወደፊት ከዚህ በላይ መስራት ይጠበቅብኛል ብዬ ነው አስባለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- እንኳን ደስ አለህ ከሚለው የህዝቡ ምስጋና ልብህን የነካህ የማን ነው…?

ውበቱ፡- ለሁሉም እንኳን ደስ መልዕክት ትልቅ ክብር አለኝ ከቅርብ እስከሩቅ ከዘመድ እስከ ጓደኞቼ የስፖርት ቤተሰቡ ሳይቀር ለሰጡኝ ክብር ዋጋ አለኝ፡፡ ነገር ግን ሀሙስ ጠዋት በግልፅ መኪና ስንዞር አዛውንቶች የጎዳና ላይ ልጆች ላይ ያየሁት ደስታ ገርሞኛል ብዙ ነገር እየጎደላቸውም ያንን ደስታ በነርሱ ላይ ማየቴ አስደስቶኛል… ከአዛውንቶችና የጎዳና ልጆች ያገኘሁት የእንኳን ደስ አለህ ለኔ ትልቅ ትርጉም አለው…

ሀትሪክ፡- የመጨረሻ የምስጋና ቃል?

ውበቱ፡- ከጅምሩ በማጣሪያው ላይ ለተሳተፉት ለኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱና አብረውት ለነበሩት አሰልጣኞች፣ ከባዱን ኃላፊነት አምነውብኝ ለሰጡኝ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትና የጽ/ቤት ሰራተኞች፣ በማጣሪያው ላይ ከመጀመሪያው ጀምሮ ለነበሩ ተጨዋቾች፣ ሊጉ ላይ ለሚገኙ አሠልጣኞችና የክለብ መሪዎች፣ በፀሎታችሁ ከጎናችን ለነበራችሁ ኢትዮጵያዊያን፣ ለውዷ ባለቤቴ ውባለም ወ/ወርቅ፣ ልጆቼ፣ እህት ወንድሞቼ ቤተሰቦቼ አብሮ አደግ ጓደኞቼን በሙሉ አመሰግናለሁ ለቸሩ መድሃኒያለም ክብር ምስጋና ይሁን፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport