“የውጤት ድምሩ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ቢያሳልፈንም ትልቁን ምስጋና ማግኘት ያለበት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ነው” ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ

በዮሴፍ ከፈለኝ

ሀትሪክ፡- ኢንስትራክተር አብርሃም እንደ ኢትዮጵያዊ ድሉ ላይ እጁ እንዳለበት ባለሙያ እንኳን ደስ አለህ ማለት እፈልጋለሁ?

አብርሃም፡- አመሰግናለሁ እንኳን አብሮ ደስ አለን… መላው ኢትዮጵያዊያንም እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችን አንተ ላይ ምን ስሜት ፈጠረ?

አብርሃም፡- እጅግ በጣም ነው ደስ ያለኝ… ታስታውስ እንደሆነ ኃላፊነቱን ስለቅና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ሲተካ በፌስቡክ ገጼ ላይ የመልካም ምኞት መግለጫ አውጥቼ ነበር የተጀመረውን ወደ አፍሪካ የማለፍ ተስፋ ጠብቀው እንደሚያስቀጥሉም ኢትዮጵያን ለአፍሪካ ዋንጫ እንደሚያበቁት አደራ ጭምር አስተላልፌ የነበረውን ጠብቀው ተግባራዊ ስላደረጉት ደስ ብሎኛል አሰልጣኙ ውበቱ አባተና ረዳቶቹ ተጨዋቾቹና የፌዴሬሽኑ አመራሮች የጋራ ቅንጅት ኢትዮጵያንን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ስለመለሷት የምንፈልገውን ነገር ስላላኩና ስላስቀጠሉ ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ከድሉ በኋላ ለቡድኑ አባላት እንኳን ደስ አላችሁ አልካቸው?

አብርሃም፡-ማለፋችን ከታወቀ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ መልካም ምኞቴን እንደገለፅኩት ሁሉ ድሉ በመሳካቱ ደግሞ የተሳተፉትን በሙሉ አመስግኜ እንኳን ደስ አላችሁ ብያለሁ… በድጋሚ የኢትዮጵያ ህዝብንም እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ… ነገር ግን ለቀጣዩ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው መግለፅ እወዳለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- አንድ የፌስቡክ ገፅ ላይ ቤተክርስቲያ ሄደህ ተንበርክከህ ስትፀልይ የሚያሳይ ፎቶ አየሁ… ከስር አሰልጣኝ አብርሃም ለአፍሪካ ዋንጫ ስላለፍን እመቤታችንን ሲያመሰግን ነው ይላል.. እውነት ነው?

አብርሃም፡- አይ ከእለቱ ጋር ስለተገጣጠመ ነው እንጂ ፎቶው የቆየ ነው… ግብፅ ለካፍ ሴሚናር በሄድኩበት ጊዜ የግብፅ ገደማት ከሆኑት አንዱ “ዘይቱና ማርያም” የምትባል ገዳምን ስጎበኝ ያስጎበኙኝ ኢትዮጵያዊያን ለመታሰቢያነት ያነሱት ፎቶ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በፕሪሚየር ሊጉ ግምገማ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና ማህበራዊ ድረ ገፅ ላይ ላንተ ምስጋና አቅርበዋል… ምንድነው ምላሽህ…?

አብርሃም፡-ይሄ እንግዲህ የበለጠ እንድንሰራ እንድንነቃና እንድንተባበር የሚያግዘን ነው ስፖርት ውስጥ የሰራኸውን ስራ ያፈራኸውን ፍሬ ያስገኘኸውን ውጤት ህዝብ መቼም ቢሆን እንደማይዘነጋው የሚያሳይ ነው፡፡ በፌስ ቡክና በድረ-ገፅ ከተሰጠው አድናቆት በተጨማሪ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ሁሉም እንኳን ደስ አለህ ብሎኛል ሁሉንም እግዚአብሔር ያክብርልኝ ማለት ነው የምንፈልገው፡፡ ክቡር ፕሬዚዳንቱም ኢንተርኮንቴኔታል በነበረው ግምገማ ላይ ኮትዲቯርን ባናሸንፍ ኖሮ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችን ላይሳካ ይችል ነበር 3 ነጥብ የተገኘው ባንተ ጊዜ ነውና ክሬዲቱን አንነፍግህም እናመሰግናለን ብለዋል እርሳቸውንም ማመስገንን እፈልጋለሁ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡

ሀትሪክ፡- የጋርዲዮላ ባርሴሎና የተመሠረተው በራይካርድ ባርሴሎና ነው የሚሉ ወገኖች አሉ አይ ቦታውን የያዘው ጋርዲዮላ ነው መጠራት ያለበትም እሱ ነው የሚሉ ወገኖችም አሉ በአሰልጣኝ አብርሃም እይታስ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈው ቡድን ክሬዲት የኔ ነው ብሎ ያምናል?

አብርሃም፡- ፍርዱን የሚሰጠውማ ህዝቡና ተመልካቹ ነው ብዬ አምናለሁ እንደኔ ግን ከአሰልጣኝ ውበቱ ጋር ቅርበት ስላለኝ በፊትም ኃላፊነት ላይ ሳለው ብሔራዊ ቡድኑን በማሸነፍና በመሸነፍ ውስጥ ስገነባ ለዚያ ቡድን ውበቱ አስተያየቱን ምክሩን አድናቆቱን ይገልፅ ነበርና እርሱ ደግሞ ኃላፊነቱን ከተረከበ በኋላ ምክርና አድናቆት ይሰጥበት የነበረው የኔ ቡድን እንዳስቀጠለ ይሰማኛል…. ያየሁትም ይህን ነው በአጋጣሚውም በአጨዋወት ፍልስፍና ተመሳሳይ ነን እርሱ ደግሞ የጨመራቸው ነገሮችም አሉ… ያ ለውጤት አብቅቷል ይሄ ለወደፊትም መለመድ ያለበት ነገር ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ኢንስትራክተር አብርሃም ልብ ውስጥ መንፈሳዊ ቅናት አልተከሰተም? ምነው እኔ ይዤው ቢሆን ኖሮ የሚል ስሜት….

አብርሃም፡-በፍፁም አልተስማኝም በዚያ ላይኮ ዋና አሰልጣኝ ሆኜ አይቼዋለው ነገር ግን በተለያየ ምክንያት ወጥቻለሁ ስለዚህ ከመቅናት ይልቅ በተገኘው ውጤት መደሰትን መርጫለሁ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችን ለሌሎች ባለሙያዎች ትልቅ መነሳሳት የሚፈጥር በመሆኑ ደስተኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- በተለየ መንገድ እንኳን ደስ አለህ ያሉህ ባለሙያዎች ይኖሩ ይሆን…?

አብርሃም፡- ካፍ ውስጥ ያሉት ኤሊት ኢንስትራክተሮች በቁጥር ትንሽ ነን ሁሉም ቡድኑን ባለፉት ሁለት አመታት ይዤው እንደነበር ያውቃሉ… ኮትዲቯርን ስናሸንፍም ያውቃሉ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ሲያልፍ ሁሉም ኮንግራ ብለውኛል ውጤቱ በአፍሪካ መድረክ ለምንሰራ ኢንስትራክተሮች ጭምር ቀና የሚያደርገንና የሚያኮራን ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ከ31 አመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ስናልፍ ክሬድቱ የአልጣኝ ሰውነት ቢሻው ነው ከ8 አመት በኋላ ስናልፍ ክሬዲቱ የኢንስትራክተር አብርሃም ወይስ የአሰልጣኝ ውበቱ…?

አብርሃም፡- ቦታውን በአሰልጣኝነት የያዘው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ነው… የውጤት ድምሩ ነው ወደ አፍሪካ ዋንጫ እንድናልፍ ያደረገን… ነገር ግን የመጀመሪያውና ትልቁን ምስጋና ማግኘት ያለበት አሰልጣኝ ውበቱና ይህን ያሳኩት የቡድኑ አባላት ናቸው፡፡

ሀትሪክ፡- የመጨረሻ ቃል….?

አብርሃም፡- ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ በሀገርም ሆነ በውጪ ላሉት በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ ለሰጡኝም ክሬዲት እግዚአብሔር ይስጥልኝ ይሄ ቡድን አልፏል ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆኖን በቀጣይ ካለንበት ምድብ አለም ዋንጫ አልፈን የተሻለ አቋም እንድናሳይ መንግሥት፣ ባለሀብቶች ሙያተኞች የስፖርት ቤተሰቡ ለብሔራዊ ቡድኑ የቅርብ ድጋፍ አድርገው ከዚህ የተሻለ ከፍታ ላይ እንድንገኝ እመኛለሁ አመሰግናለሁ፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport