“የሰውነት ሪከርድ ተሰበረ ሲባል እሰማለሁ እኔ የ1ዐ ሺህ ሜትር ሯጭ ነኝ እንዴ ወደ አፍሪካ ዋንጫ መመለስ እንደሚቻል በር በመክፈቴ ደስተኛ ነኝ” ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው

በይስሐቅ በላይ

የኢትዮጵያ ብ/ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የተመለሰው ከ31 አመታት በኋላ በኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው አሰልጣኝነት ነው፤ያ ታሪክ ከስምንት አመት ትዕግስትና ቆይታ በኋላ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ተደግሞ አዲስ ታሪክ ተፅፏል፤ብዙዎች ይሄንን የስኬት አጋጣሚ በመምዘዝ የኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ከ31 አመት በኋላ የሚለው የውጤት ሪከርድ ተሰብሯል በማለት የሪከርድ ባለቤትነቱን ለአሰልጣኝ ውበቱ አባተ አሳልፈው ሲሰጡ ይታያሉ፡፡
የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ የእጅ ስልኩን አንስቶ ወደ ኢንስትራከተር ሰውነት ቢሻው ጋ በመደወል የእንኳን ደስ አለህ ምኞቱን ካስቀደመ በኋላ “ኢንስትራክተር በአንተ ተይዞ የነበረው ከ31 አመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የመለስክበት ሪከርድህ ተሰበረ…ተነጠክ?…”…ሲል ጠይቆታል…“…በአሰልጣኝነትም…በዴሊጌሽን ሄድ…(በልዑካን ቡድን መሪነትም)…ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማለፍ የስኬት ታሪክ አካል በመሆኔም ብ/ቡድኑም በማለፉ በጣም ተደስቻለሁ…”…የሚለው ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው…“…የምን ሪከርድ ነው…የምታወራው…?…100 ሜትር ወይም 10 ሺ ሜትር ያስሮጠኝ ሰው አለ እንዴ…?…”…በማለት ስላቅ የተሞላበት…የሚመስል…ግን በጥያቄ የታጀበ ምላሽ ሰጥቷል…ጋዜጠኛው ከኢንስትራክተሩ ጋር ያነሳውን ብዙ አነጋጋሪ ጉዳይ ከዚህ በታች ባለው መልኩ አቅርቦታል፡፡

ሀትሪክ፡- …እንኳን ደስ አለህ…?…

ኢንስ.ሰውነት፡- …እንኳን አብሮ ደስ አለን…የኢትዮጵያ ህዝብም በተመዘገበው ድል ሲደሰት በማየቴ በጣም ደስ ብሎኛል…እንኳን ደስ አላችሁ ለማለትም እፈልጋለሁ…

ሀትሪክ፡- …ውጤቱን ጠብቀኸው ነበር…?…

ኢንስ.ሰውነት፡- …ቡድኑ ሰፊ እድልን ይዞ ከመሄዱ አንፃር አንድ ነገር ሊፈጠር እንደሚችል ትልቅ እምነት በውስጤ ነበር…የማለፍ እድሉ እንዳለን ነበር ውስጤ ሲነግረኝ የነበረው…

ሀትሪክ፡- …የኢትዮጵያ ብ/ቡድን ላይ ቀድሞ ግብ ሰቆጠርና 3ለ1 ወደ መመራት ሲገባስ ይሄው ስሜት አብሮህ ነበር…በሰፊ ውጤት ወደመሸነፍ እያመራ ባለበት ሰዓት እድሉን ልናጣው ነው የሚል ስጋትስ በውስጥህ አልተፈጠረም…?…

ኢንስ.ሰውነት፡- …የሚገርምህ ነገር እየተመራን በነበረበት ሰዓትም ቢሆንም አንዳችም ስጋትም ሆነ ጥርጣሬው በውስጤ አልነበረም…አንዳንዴ ሰውነትህ፣ስሜትህ እርግጠኛ ሆኖ የሚነግርህ ነገር የለም…?…እኔንም ሲሰማኝ የነበረው ይሄ የእርግጠኝነት ስሜት በመሆኑ…ስለማለፋችን እንዳልጠራጠር አድርጎኝ ነበር…

ሀትሪክ፡- …የማዳጋስካርና የኒጀር ጨዋታ 0ለ0 መጠናቀቁ አልገረመህም…ኒጀሮች በዚህ ውጤት ይለያያሉ ብለህስ አስበሃል…?…

ኢንስ.ሰውነት፡- …የሚገርህም የማዳጋስካርና የኒጀርን ጨዋታ ውጤት እንከታተል ነበር… ከጨዋታው በፊት ኒጀሮች ከመልቀቅ ይልቅ ለክብራቸው፣ለሀገራቸው ሲሉ እንደሚጫወቱ ፕሮፌሽናሎች እንደሆኑ እገምት ነበር…ኮትዲቯሮችም ቀደመ ማለፋቸውን ቢያረጋግጡም…ለክብራቸው፣ለሀገራቸው ስም ሲሉ ጥርሳቸውን ነክሰው እንደሚጫወቱ እምነቱ ነበረኝ…ተጫውተው ማሸነፍን የመጀመሪያ ምርጫቸው እንደሚያደርጉ አውቅ ነበርና ሜዳ ላይ ባየሁት ነገር አልተገረምኩም…ከኮትዲቫር ከምናደርገው ጨዋታ በተጨማሪ ሌሎች እድሉም ስለነበሩ የፈለገ መቶ ጎል ቢገባብንም ማዳጋስካር ካላሸነፈ በስተቀር እንደማንወድቅ ስለምናውቅ ስጋቱም ጥርጣሬው አልነበረኝም…

ሀትሪክ፡- …ከዚህ በፊት ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፋችን በአንተ የተያዘው ሪከርድ ይጠቀሳል፤የአንተም ስም ከ31 አመት ከሚለው ቃል ጋር አብሮ ተያይዞም ይነሣ ነበር…አሁን የሰውነት ሪከርድ ተሰብሮ ከዚህ በኋላ ከስምንት አመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የመለሰው ውበቱ አባተ የሚለው ስም ነው የሚነሣው የሚሉ አሉ…ይሄ አባባል ይረብሸሃል…?…

ኢንስ.ሰውነት፡- …ለምን ይረብሸኛል…?…ግን ከዚያ በፊት አንተንም ሪከርድ ሪከርድ እያላችሁ የምታወሩትን አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ…የሰውነት ሪከርድ የምትሉት የምን ሪከርድ…?….

ሀትሪክ፡- …(ድንገት አቋረጥኩትና)…ከ31 አመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የመመለሱን ሪከርድ የያዝከው አንተ ስለሆንክና ከአንተ በኋላ ይሄን ሪከርድ ያሻሻለ ሰው ስላልነበረ ነው ጥያቄውን ያነሳውልህ…?…

ኢንስ.ሰውነት፡- …ይሄውልህ…ስማ ወንድሜ…!…ሪከርድ የሚባል ነገር የለም…ሪከርድ ለሩጫ ነው…!…ቆይ ሪከርድ…ሪከርድ የምትለው…100 ሜትር ወይም 10 ሺ ሜትር አስሩጦኝ የሰበርኩት ሪከርድ አለ…?…የሰውነት ሪከርድ ተሰብሮ የሚባለው ከማን ጋር አወዳድራችሁኝ…በማነው የተሰበረው…?…እኔ አንተ እንደምትለው ሪከርድ ለመስበርና…አዲስ ሪከርድ እንዲመዘገብልኝ አይደለም የሠራሁት…ለኢትዮጵያ ህዝብና ለሙያው ክብር ነው የሠራሁት…የሰውነትን ስራ ጥላሸት መቀባት የሚፈልጉ የተበላሸ ጭንቅላት ያላቸው ሰዎች ናቸው ሪከርድ ተሰበረ እያሉ ለማወዳደር የሚሞክሩት እንጂ…የሚሰበርም፣የተሰበረም ሪከርድ የለም…እንደዚህ አይነት ነገርም በጥያቄ የሚነሣ አይደለም…

 

ሀትሪክ፡- …ከዚህ በኋላ ከ31 አመት በኋላ ሰውነት ቢሻው ለአፍሪካ ዋንጫ አሣላፊ ሳይሆን…ውበቱ አባተ ከስምንት አመት በኋላ አሳለፊ በሚል ሌላ ታሪክ መቀየሩስ… ያስደስተሃል…?…

ኢንስ.ሰውነት፡- …ለምን ይከፋኛል…?…በጣም ነውየሚያስደስተኝ…የእኔን ውጤትና ታሪክ ማጥፋትና መፋቅ አይቻልም…ከስምንት በፊት ከ31 አመት በኋላ ሀገሬን ለአፍሪካ ዋንጫ በማሳለፍ ለአፍሪካ ዋንጫማሳለፍ እንደሚቻል አሳይቼያለሁ…በሩንም ወለል አድርጌ ከፍቼያለሁ…ከዚህ በኋላ በየሳምንቱ ብትፈልግ በየወሩና በየአመቱም ቢሆን ማሳለፍ የአንተ ፋንታ ነው የሚሆነው…የሰውነት ሪከርድ በቃ ተሰበረ ማለት ምን ማለት ነው…?…የምን ሪከርድ ነው የሚሰበረው…?…ብዙ አታናግረኝ እንጂ እኔ እኮ ለአፍሪካ ዋንጫ፣ለቻን፣በአለም ዋንጫ ማጣሪያ ምርጥ 10 ውስጥ የገባ እንዲሁም በወቅቱ የአፍሪካ ምርጥ ቡድኖች ከተባሉት ሶስቱ ሀገሮች አንዷ ሀገሬ እንድትሆን እንድትመረጥ አድርጌያለሁ…እውነታው ይሄ ከሆነ ከማን ጋር ተወዳድሬ ነው ሪከርድ ተሰብሯል የሚባለው…?…ፍፁም ግራ የሚያጋባና ጤነኛ ያልሆነ አስተያየት ነው…ለእኔ ሪከርድ የሚባለው የአፍሪካንም፣የአለም ዋንጫንም ማምጣት ከተቻለ ነው…ያኔ ስለ ሪከርድ መሰባበር መነጋገር ይቻላል…አሁን በዘህ ደረጃ ማሰብ ግን ጤነኝነት አይመስለኝም…

ሀትሪክ፡- … በሌላ መልኩ ጥያቄዬን ቀየር አድርጌ ልጠይቅህ…ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ታሪካችን ስምንት አመት ሙሉ በአንተ ባለቤትነት ተይዞ በመቀየሩስ ደስተኛ ነህ…?…

ኢንስ.ሰውነት፡- …ሰውዬ ምን ሆነሃል…?…እንዴት አልደሰትም…?…በጣም ደስተኛ ነኝ…እንግዲያውስ ንገረኝ ካልክ አንድ ነገር ልንገርህ…ከ8 አመት በፊት በአሰልጣኝነት…ከስምንት አመት በኋላም የዴልጌሽን ሄድ (የልዑካን ቡድን መሪ) ሆኜ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ካሳለፉ ሰዎች አንዱ ነኝ…በዚህ ደረጃ የተሳካለት ሰው አላውቅም…የነገረኝም ሰው የለም…ይሄ በመሳካቱ ለእኔ ሌላ አዲስ ታሪክ ነው… ብ/ቡድኑ በዚህ ደረጃ አልፎ በማየቴም ትልቅ ደስታዬ ነው የተሰማኝ…የምወደው፣ብዙ የደከምኩለት፣ እድሜዬን የገበርኩበት እግር ኳስ ነው ከፍ ነው ያለው…ከዚህ በላይ ምን ሊያስደስተኝ ይችላል ብለህ ነው…?…ከድሉ በላይ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ በአፍሪካ፣በአለም ዋንጫና በኦሎምፒክም ላይ ለማድረስ ጠንክሮ መስራት እንደሚቻል ማሰብ ነው ትልቁ ነገር…

ሀትሪክ፡- …ከ31 አመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ያለፈው ቡድን አሰልጣኝ ነበርክ…አሁን ያለውን ብ/ቡድንንም በቅርበት የማየትና የማገዝ ነገር ስላለ የሁለቱን ቡድኖች አንድነትና ልዩነት አነፃፅርልኝ ብልህ እንዴት ታነፃፅረዋለህ…?…

ኢንስ.ሰውነት፡- …ሁለቱ ብ/ቡድኖች ባሳኩት ግብ ተመሳሳይ ቢሆኑም የሚያለያያቸው ብዙ ነገር አለ… የአሁኑ ብ/ቡድን ውስጥ ያሉ ተጨዋቾች ገና ወጣቶች ከመሆናቸው አንፃር በጎደለአቸው ነገር እየተጨመረ ጠንካራ ጎናቸውን ይበልጥ እያጠናከሩ መሄድ ከተቻለ ረዥም ጊዜ መጫወት ይችላሉ… ሁለት ሶስት የአፍሪካ ዋንጫ ሊጓዙ የሚችሉ ልጆች ያሉበት ነው…በእኔ ጊዜ የነበሩት ተጫዋቾች ከዚህ የተለየ ታሪክ የነበራቸው ናቸው…ብዙዎቹ ረዥም አመት የተጫወቱ…ወደ ጨዋታ ማቆሚያ ዘመናቸው ላይ የደረሱ ተጫዋቾች ነበሩ…አብዛኞቹ የሴካፋ ዋንጫን ያነሱ…የጨዋታቸው ጀምበር ወደ መጥለቂያዋ የተቃረበ ስለበር…የራሳቸውን ታሪክ ሰርተው ማለፍ የሚፈልጉ ተጫዋቹ የነበሩበት ስብስብ ነው…እነዚህ ተጨዋቾች በአሁን ሰዓት አብዛኛቹ ኳስ አቁመዋል…እንዳልኩህ ለሀገራቸው አንድ ታላቅ ነገር ሰርተው ማለፍ የሚፈልጉ ተጨዋቾች የተሰባሰቡት ነበር…ያንንም አሳክተዋል…በዚህ ደረጃ ይለያያሉ…የአሁኖቹ ላይ በጎዶሎአቸው እየሞላን ከሄድን ጠንካራና ተከታታይ ስኬት ማስመዝገብ የሚችል ብ/ቡድን መፍጠር እንችላለን ብዬ ነው የማምነው…

ሀትሪክ፡- …ብ/ቡድኑ ያስመዘገበው ድል ለአፍሪካ ዋንጫ ከማለፉም በላይ እንደ ሀገር የሚያስተላልፈው መልዕክት አለ ትላለህ…?…

ኢንስ.ሰውነት፡- …ይሄ እኮ እንዳችም ንግግር ሳያስፈልገው በተግባር የታየ ነገር ነው…በየሀገሩ በመላው አለም ያሉ ኢትዮጵያዊያንን አንድ ያደረገ…ያስተቃቀፈ…በኢትዮጵያዊነትህ እንድትኮራ ያደረገ ውጤት ነው የተመዘገበው…ውጤቱ የአንድነት ምልክት ነው ብዬ መናገር እችላለሁ…ወደ አንድነት ወደ ደስታ የመለሰ…መጠቀም ከቻልን የእግር ኳስን አቅም በተግባር ያየንበት ነው…

ሀትሪክ፡- …የኮትዲቯርና የኢትዮጵያ ብ/ቡድንን ጨዋታ በአካል ተገኝተህ ተከታትለሃል…ሙቀቱንና የዳኛውን በቃሬዛ የመውጣት አጋጣሚ እንዴት ታዘብከው…?…

ኢንስ.ሰውነት፡- … ሙቀቱ በጣም ከባድ ነበር…ለሚሮጡት ተወውና እኛ ቁጭ ያልነው እንኳን መተንፈስ ሁሉ አቅቶን ነበር…እንኳን እኛ ከሌላ ሀገርና የአየር ንብርት የመጣነውን ተወውና ኮትዲቯሮች ራሳቸውም መሮጥ አቅቶአቸው ቆመው ነው የታዩት…ወደ ዳኛው ስንመጣ በመጀመሪያ ይሄ ዳኛ ዋና ዳኛ አልነበረም…የመስመር (ረዳት) ዳኛ ነው የነበረው…መጀመሪያ የተመደበው ዋና ዳኛ በኮቪድ በመያዙ ምክንያት ነው…ይሄ የመስመር ዳኛ ዋና ሆኖ ለማጫወት የገባው…ዳኛው ያገኘውን እድል በአግባቡ ለመጠቀም በማሰብና ዋና ዳኛ የመሆን ህልሙን ለማሳካት፣ለማሳየት በሚመስል መልኩ በዚያ ሙቀት እንደ ጄት ነበር እየበረረ ሲያጫውት የነበረው…በዚያ ከባድ ሙቀት በጣም በመሮጡ መተንፈስ አቅቶት እስከመውደቅ ደርሷል…ደም ብዛትና ስኳር ያለበት ሰው ነው ድንገት የሚወድቀው… ይሄ ዳኛ በጣም በመሮጡ ለመተንፈስ ሁሉ ተቸገረ…በመጨረሻም ራሱን መቆጣጠር አቃተው…ዋና ዳኛ ለመሆን ጓጉቷል መሰለኝ…በጣም ተንቀዥቀዥ…መጨረሻውም ያስደነግጥ ይረብሽም ነበር…ብዙ ጊዜ ስሜትህና ውስጣዊ ጥንካሬህ የማይጣጣም ከሆነ የዚህ አይነት ከባድ ነገር ነው ለማስተናገድ የምትገደደው…

ሀትሪክ፡- …ብ/ቡድኑ አሁን ለአፍሪካ ዋንጫ አልፏል…ከባለፈው በመማር በውድድሩ የተሻለ ለመፎካከር ከዚህ በኋላ ምን ቢሠራ መልካም ነው ብለህ ትመክራለህ…?…
ኢንስ.ሰውነት፡- …ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ስምንትና 10 አመታትን መጠበቅ ማስቀረት አለብን… እድሉን ለማሳካትም ቁጭ ብለን መናፈቅና መመኘትም ብቻውን አይጠቅምም…አሁን በውድድሩ ላይ መካፈል የሚያስችለውን ትኬት አግኝተናል…ይሄ ትልቅ ስኬት ቢሆንም በውድድሩ ላይ ጥሩ ለመሆን እንደማይጠቅመን አውቀን ከወዲሁ ብዙ ስራ መስራት ይጠበቅብናል…

ሀትሪክ፡- …በጉዞ ድካም ውስጥ ነህና ከዚህ በላይ ባላደክምህ ደስ ይለኛል…ምንአልባት ይሄን ጨምርልኝ የምትለው ካለ…እድሉን ሰጥቼህ…አመሰግኜህ ብንለያይስ…?…

ኢንስ.ሰውነት፡- …የኢትዮጵያን ህዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ…ስፖርት የአንድን ሀገር ገፅታ የመለወጥ ኃይል እንዳለው…ለሠላም፣ለአንድነት፣ ለመፈቃቀር ያለውን ጉልበትም አይተናል… በህዝቡ ላይ የተፈጠረውን መተቃቀፍ፣ደስታ፣አንድነት ስታይ ስምንት አመት ሙሉ እየጠበቀ ሳይሆን በየጊዜው የድል ባለቤት ልናደርገው ይገባል…ለዚህ ደግሞ ሁሌም እንደምለው በወጣቶች…በታዳጊዎች ላይ መስራት አለብን…በተተኪዎች ላይ በጣም መስራት አለብን…በቤተሰብህ ውስጥ አንተን ሊተካ የሚችለው ታዳጊው ልጅህ ነው…ተተኪ ወጣቶች ያለማቋረጥ ሊኖሩን ይገባል…በመላው ሀገሪቱ ያሉ ወጣቶች በስርዓት ተይዘው ስልጠና እየተሰጣቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ ሀገራቸውን እየወከሉ እንዲያድጉ መደረግ አለበት…8 እና 10 አመት ላለመቆየት…ዝም ብሎ መናፈቅ ወይም ማውራት ሳይሆን በተተኪዎች ላይ በስርዓት መስራት ያስፈልጋል…በትውልድ ላይ መስራት ከተቻለ በተከታታይነት የሚያሸነፍ…ለአፍሪካ ዋንጫ የሚያልፍ ብ/ቡድንን ይኖረናል…በአፍሪካ ደረጃ የሚፎካከር ብ/ቡድን መገንባት የሚቻለው ጠንካራ በሆኑ ወጣቶች ላይ ሲሰራ ነው…የስፖርት ባለድርሻ አካላትም፣ መንግሥትም በዚህ ገዳይ ጣልቃ ገብቶ እንድንሠራ ምክሬን አስተላልፋለሁ…

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.