ታሪክ ሰሪዎቹ!! HISTORY MAKERS!!

“ከ8 አመት በኋላ ለዚህ ትልቅ ድል በቅተናል መላው ህዝቡንም የሚያሳተሳስር ለሀገራችን ከኳስም በላይ ትርጉም ያለው ድል በመሆኑ ደስታችንን እጥፍ ድርብ አድርጎል”…ከዋሊያዎቹ ካምፕ የሚደመጥ የደስታ መግለጫ መልዕክት ነው ዋሊያዎቹ ኮትዲቯርን ተከትለው በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመሩ ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸው መላው ህብረተሰቡን በአንድነት ስሜት ውስጥ ከትቷል፡፡ ከ31 አመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ አለፍን ከሚለው ዜና ከ8 አመት በኋላ ወደመሰረትነው የአፍሪካ ዋንጫ አለፍን ወደሚለው ተቀይሯል፡፡ የኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውን ሌጋሲ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ አስቀጥሏል እንደማለት ነው፡፡

ከድሉ በኋላ ቡድኑ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ማክሰኞ ምሽት አዲስ አበባ ሲገባ የሞቀ የጀግና አቀባበል ተደርጎለታል፡፡ ከዚህ ትልቅ ደስታ ውስጥ እያሉም ቢሆን የሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ኮትዲቯር ላይ ግብ ያስቆጠረውን አጥቂውን ጌታነህ ከበደን /ሰበሮምን/፣ ግብ ጠባቂውን ተክለማርያም ሻንቆ /ጎሜዝን/ ስልክ ደውሎ አነጋግሯቸዋል… ተከታትሉት፡፡

ሀትሪክ፡- እንኳን ደስ አለህ….?

ጌታነህ፡-እንኳን አብሮ ደስ አለን፡፡ ህዝቡንም እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ…

ሀትሪክ፡- በደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ነበርክ.. አሁንም በካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተካፋይ ነህ አስቲ ልዩነቱን አውራኝ…?

ጌታነህ፡- የመጀመሪያው የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለማለፍ ሜዳችን ላይ ሱዳንን ማሸነፍ ይጠበቅብን ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ስታዲየም በደጋፊው ታጅበን ያደረግነውን ጨዋታ አሸንፈን ከ31 አመት በኋላ ስናልፍ የነበረው ደስታና ፈንጠዝያ የሚዘነጋ አይደለም፤ ድሉ በህዝቡ ፊት በነበረ ትልቅ ጨዋታ የተገኘ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ለዚያ ጨዋታ የተለየ ስሜትም አለኝ… የአሁኑ ደግሞ ከኳሱ ውጪ የሀገራችን ሁኔታ ትንሽ የከፋ ችግሮች ባሉበት ጊዜ የተገኘ ድል ነው ለሁለም ከፍተኛ ደስታ ፈጥሯል.. ትርጉሙ ብዙ ነው ይሄም ድል የራሱን የቻለ ታሪክ ስላለው የማይረሳ አድርጎልኛል ሁለቱም በየራሣቸው ያላቸው ታሪክ በመሆኑ ባላወዳድር ደስ ይለኛል እንዲያውም ተመሳሳይነታቸው ይጎላብኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችን ለሀገሪቱ ምን ትርጉም አለው ትላለህ…?

ጌታነህ፡- ማሸነፍና ማለፋችን ትልቅ ትርጉም አለው ይሄ ወሳኝ ጊዜ ነበር የሀገራችን እግር ኳስ በዲ.ኤስ.ቲቪ የሚታይ መሆኑ ትልቅ እድል ፈጥሯል፤ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ ስኬት ይመስለኛል ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሁሌ መገኘት አለባት ይሄ የግድ ነው በፊት ያለፍነው ከ31 አመት በኋላ ነው አሁን ደግሞ ከ8 አመት በኋላ መሆኑ የተሻለ ያደርገዋል በዚያ ላይ የምድብ ጨዋታ ላይ ሙሉ ማጣሪያ አድርገን ሁለተኛ ሆነን ማለፋችን ትልቅ ለውጥ ይመስለኛል፡፡ ለደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ስናልፍ ግን በጥሎ ማለፍ መልክ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ አሁን ባለፈው ቡድኑ ውስጥ ያሉት ተጨዋቾች ጥሩ አቅም ያላቸው ናቸው ይሄ ስራ ቀጥሎ በእግር ኳሳችን ላይ የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ከኳሱ ውጪስ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችን ምን ትርጉም ይሰጣል?

ጌታነህ፡- በጣም ትልቅ ትርጉም ያለው በመሆኑ ትልቅ ደስታ ተፈጥሮብኛል፡፡ ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ማወቃችን ከጨዋታው በፊት ትልቅ ጫና ፈጥሮብን ነበር፤ በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾችና ሚዲያዎች የሚወጡት ሃሣቦችን ስንመለከት ምን ያህል ድሉ ትርጉም እንደነበረው ስለገባን… ከጨዋታው በፊት በጣም ተጨናንቀን ነበር በጣምም ጓጉተን ነበር፡፡ በጨዋታው 3 እድል ይዘን ነው የገባነው ማሸነፍ፣ አቻ መውጣትና የማዳጋስካር ነጥብ መጣል የሚያሳልፍን ስለነበር አንድ ታሪክ እንደምንሰራ ተስፋ አድርገን ገብተን ስለተሳካልንና ሀገሪቷን አንድ የሚያደረግ ድል በማስመዝገባችንም ኩራት ተሰምቶናል፡፡

ሀትሪክ፡- ከሀገር ውጪ ስንጫወት ደካማ አቋም ነው የምናሳያው ለሚሉ ምን ምላሽ አለህ?

ጌታነህ፡- በሰው ሜዳኮ የተሻልን ሆነን በልጠን ባልተጠበቁ ትናንሽ ስህተቶች ነው የምንሸነፈው… ከማዳጋስካር ጋር አንታታናሪቮ በተደረገው ጨዋታ ላይ አልነበርኩም ነገር ግን ጥሩ ነበሩ የተሻለ አቋም አሳይተዋል ግብ የሚሆኑ ኳሶች ቢገኙም በአጨራረስ ድክመት ነው ያልተሳከው… ኒጀር ላይም ተመሳሳይ ነው ባለቀ ሰዓት ላይ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው አሸንፉን እንጂ ኒጀርን አሸንፈን ቀድመን ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችንን ማረጋገጥ ነበርብን ግን ዘግይቶም ቢሆን አሁን አልፈናል ስህተታችን ላይ ሰርተን ጠንካራ አቋም በመያዝ በካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ጥሩ ተፎካካሪ ለመሆን እንጥራለን፡፡

ሀትሪክ፡- ኮትዲቯር ላይ ግብ ያስቆጠርከው አንተ ነህ ምን ስሜት ፈጠረብህ?

ጌታነህ፡- በጣም ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል ትልልቅ ቡድን ላይ ስታስቆጥር ደስታ ይፈጥራል በአፍሪካ ትልቅ ቡድን በሆነው አልጄሪያ ላይም ሆነ አይቬሪኮስት ላይ ግብ ማስቆጠር ያስደስታል በራስ መተማመንንም ይጨምራል እንደገና ከሜዳ ውጪ ግብ ማስቆጠር ራሱን የቻለ የደስታ ስሜት ይፈጥራል… የኔን አቅምንም ይጨምራልና ተመችቶኛል፡፡

ሀትሪክ፡- የዋሊያዎቹና የኮትዲቯር ጨዋታ ተቋርጦ ስታዲየም ውስጥ የኒጀርና ማዳጋስካር ጨዋታን የተከታተላችሁበት ሂደት ምን ይመስል ነበር…?

ጌታነህ፡- የኛ ጨዋታ 10 ደቂቃ ሲቀረው ተቋረጠና ሜዳ ውስጥ ሆነን የእነ ማዳጋስካርና ኒጀር ጨዋታን መከታተል ጀመርን በጣም የሚያስጨንቅ የሚረብሽ ጊዜ ነበር ከላይ ሆነው ጨዋታውን ሲከታተሉ የነበሩ ጨዋታው 0ለ0 አለቀ ብለው ሲነግሩን የተፈጠረብን ደስታ ልዩ ነበር… የነበረውን ቀሪ ጨዋታ ሁሉ ረስተነው ጨፈርን ትልቅ ደስታ ነው የተሰማን… ድሉ ልዩ ስሜት ፈጥሮብናል በማለፋችን ደስታና እረፍት ተሰምቶኛል…

ሀትሪክ፡- የመጨረሻ ለህዝቡ የምታስተላልፈው መልዕክት ካለ እድሉን ልሰጥህ…?

ጌታነህ፡- ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፋችን ህዝቡንም አንድ የሚያደርግ ውጤት በማስመዝገባችን ትልቅ ደስታ ፈጥሮልኛል መላው ኢትዮጵየዊያንን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለው ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫም ጥሩውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጠብቁ ማለት እፈለጋለሁ፡፡

…..
ሀትሪክ፡- እንኳን ደስ አለህ….?

ተክለማርያም፡- እንኳን አብሮ ደስ አለን አመሰግናለሁ

ሀትሪክ፡- ድሉ ከኳስም ድል በላይ ነው የሚሉ አሉ ትስማማለህ…?

ተክለማርያም፡- አዎ ትልቅ ትርጉም አለው ወሳኝነት ያለውም ጉዳይም ነው ህዝባችን ተከፋፍሏል የሀገሪቷ ሁኔታ ደስ አይልም ይህን ለማስተካከልና በጋራ አንድ ኢትዮጵያን ብቻ እንድንሰብክ ያደርጋል ብዬ አስባለው ምክንያቱም ድሉ በአንድነት ስለ ሀገር እንድናስብ ብቻ ያደርገናል ብዬ አስባለውና ትልቅ ትርጉም አለው ብዬ አምናለው…

ሀትሪክ፡- የኒጀርና የማዳጋስካር ቀሪ ጨዋታን በስታዲየም ውስጥ ስትከታተሉ የሚያሳይ ቪዲዮ እያየሁ ነበርና ያን ጊዜን እስቲ አስታውሰን …?

ተክለማርም፡- በጣም የሚገርም የጭንቀትና የደስታ ስሜት የተፈራረቀበት ጊዜ ነበር በህይወቴ መቼም የማልዘነጋው ገጠመኝ ነው እየተመራን ነው ዳኛው በሙቀቱ ኃይል ራሱን ስቶ ወድቆ ጨዋታው ተቋርጧል… በዚህ የድንጋጤ ጊዜ ውስጥ የኒጀርና የማዳጋስካር ጨዋታ 7 ደቂቃ ቀረው ተብለን እየሰማን ነው… 0ለ0 ናቸው ሲባል ያ ጊዜ የተፈጠረው ጭንቀት የማይረሳ ነው ከአዲስ አበባ የተነሣነው ኮትዲቯርን አሸንፈን ወይ አቻ ወጥተን እንመጣለን የሚለው ነገር ባለመሳካቱ ደግሞ ብዙ ጭንቀት ተፈጥሮብን ነበር…የኒጀር ጨዋታ 3 ደቂቃ ቀረው 2 ደቂቃ እየተባለ ሲሄድ ትልቅ ፍርሃትና ጭንቀት ፈጥሮብን የነበረበትን ደቂቃ መቼም አልረሳውም… ሁሉም በየእምነቱ ተበታትኖ ይፀልይ ነበር ሙስሊሙ እዚያ ጋር ይሰግዳል ፕሮቴስታንቱም እዚያ ጋር ተንበርክኮ ይፀልያል ኦርቶዶክሱም ወደላይ ቀና ብሎ አምላኩን ይማፀናል… የሚገርም ጊዜ ነበር /ሳቅ/ እግዚአብሔርም ፀሎታችንን ሰምቷል የሀገራችንን ሁኔታ አይቶ እግዚአብሔር ረድቶናል ብዬ አምናለው፡፡

ሀትሪክ፡- የዚህ ብሔራዊ ቡድን አባል በመሆንህ ምን ተሰማህ…?

ጌታነህ፡- እጅግ በጣም ደስተኛ የሆንኩት የዚህ ታሪክ አባል በመሆኔ ነው.. ትልቅ ደስታ ላይ ነኝ፡፡ ከ31 አመት በኋላ ኢትዮጵያ ስታልፍ ከቡድኑ ጋር ብዙ ታሪክ የሰሩ ተጨዋቾች አሉበት ሌሎች አስርት አመታትን አለመጠበቃችን ትልቅ ደስታ ይፈጥራል.. በ8 አመት ውስጥ አልፈን ሌላ 31 አመት አለመጠበቃችን ትልቅ ለውጥ ነው… የዚህ ምርጥ ታሪክ አባል በመሆኔም ኩራት ይሰማኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ክለብህ ላይ ተጠባባቂ ነህ… ለብሔራዊ ቡድን ደግሞ ቋሚ ተሰላፊ… ምን ስሜት ይፈጥራል…?

ጌታነህ፡-ያለኝን አቅም ማየቱ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በኔ ላይ እንዲተማመን አድርጎታል ማለት ይቻላል ክለብ ላይ ተጠባባቂ የሆንኩት በአቋም መውረድ ወይም በዲሲፕሊን ችግር አይደለም…ቀይ ካርድ ካየሁበት ጨዋታ በኋላ ቡድናችን እያሸነፈ ሄዷል ከቅጣት ስመለስም ጥሩ አቋም ላይ ስለነበረ ቋሚነቴን ልይዝ አልቻልኩም ይሄ ነው እውነቱ… ይሄ ደግሞ ኳስ ላይ ያለ በመሆኑ ጊዜው ደርሶ ቦታውን እስክይዝ ከኔ የሚጠበቀው ጠንክሮ መስራት ነው፡፡ በክለቤ ቋሚ አይደለሁም ማለት ችሎታ የለኝም ማለት አይደለም.. ምክንያቱምም ያለኝን ችሎታ ብሔራዊ ቡድኑ ላይ እያሳየሁ ነው፡፡ የጊዜ ጉዳይ እንጂ በክለቤ ቋሚ ሆኜ የምሰለፍበት ጊዜ ይመጣል፡፡

ሀትሪክ፡- ማለፋችን ከተረጋገጠ በኋላ የመጀመሪያ የእንኳን ደስ አለህ የስልክ መልዕክት ከማን ደረሰህ?

ተክለማርያም፡- /ሳቅ በሳቅ/ ገና ቤት ስገባ የደወልኩት ባለቤቴ ጋር ነበር እርሷ ግን አላነሳችም፡፡ ቤተሰቦቼ ግን ቤት ተሰብስበው ደውሉልኝ እናቴ አባቴ እህቶቼ እየጨፈሩ ስለ ኢትዮጵያ እየዘመሩ ደስታዬን ተጋርተውኛል ቤተሰቦቼ ቤት ጎረቤትም ነበርና ደስ የሚል ጊዜ ነበር ትልቅ ደስታ ፈጥሮብኛል የመጀመሪያ ደዋዮቼም እነርሱ ሆነዋል፡፡

ሀትሪክ፡- አንተ በብሔራዊ ቡድን ላለህ አስተዋፅኦ ድጋፍ ያደረገልህን ሰው አመሰግን ብትባል ያንተ ምስጋና የሚደርሰው ለማን ነው?

ተክለማርያም፡- በዋሊያዎቹ ዙሪያ የመጀመሪያ ተመስጋኝ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ነው ምክንያቱም አሰልጣኝ ውበቱ አምኖብኝ አሰልፎኝ ለዚህ ታሪክ ያበቃኝ እርሱ ስለሆነ ነው… ከእሱ ውጪ የአሰልጣኞች ቡድን አባላት እንዲሁም የበረኛ አሰልጣኜ ደሳለኝ ገ/ጊዮርጊስን በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ያለኝን አቅም አውጥቼ እንድጠቀም ያለኝን አቅም አምነው ያሰለፉኝን እነኚህን ባለሙያዎች በጣም አመሰግናለሁ እኔም ስላላሳፈርኳቸው ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡

ሀትሪክ፡- የመጨረሻ መልዕክት… ?

ተክለማርያም፡- መላው ህዝባችን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ ለብሔራዊ ቡድንም ሆነ ለኢትዮጵያ ትልቅ ድል ነውና በተገኘው አስደሳች ድል ደስታዬ እጥፍ ሆኗል… ሕዝቡንም በጣም አመሰግናለው በቀጣይ የአፍሪካ ዋንጫ አሪፍ ጊዜ እንደሚኖረን ተስፋ አደርጋለሁ…ከዚያ ውጪ ለመላ ኢትዮጵያዊያን ያለውን የፖለቲካ ልዩነት ወደ ጎን ብለን ስለ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ልንሰብክ ይገባል ይሄንንም አደራ እላለሁ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር አመሰግናለሁ፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport