“ለቅ/ጊዮርጊስ ከሻምፒዮንነት ውጪ የሚመጥነው ውጤት የለም፤ ዘንድሮ ግን ሁለተኝነቱ ትርጉም ስላለው ያን ውጤት ልናመጣለት ይገባናል” አማኑኤል ተርፉ /ቅ/ጊዮርጊስ/

“ለፍተናል፤ እንደ ቡድን ጥሩ ስላልነበርን ግን ውጤትን አጥተናል”
“ለቅ/ጊዮርጊስ ከሻምፒዮንነት ውጪ የሚመጥነው ውጤት የለም፤ ዘንድሮ ግን ሁለተኝነቱ ትርጉም ስላለው ያን ውጤት ልናመጣለት ይገባናል”
አማኑኤል ተርፉ /ቅ/ጊዮርጊስ/

የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብብ ዋና ቡድንን በተቀላቀለበት የእዚህ ዓመት ለቡድኑ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው እና በኋላም ላይ ጉዳትን አስተናግዶ የነበረው የተከላካይ ስፍራው ተጨዋች አማኑኤል ተርፉ ቡድናቸው በዘንድሮ የውድድር ዘመን ላይ እያስመዘገበው ያለው ውጤት ፈፅሞ የማይመጥናቸው እንደሆነና ውጤት ያጡት ደግሞ እንደ ቡድን ጥሩ ስላልነበሩ መሆኑን ለሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ መሸሻ ወልዴ አስተያየቱን ሰጥቶታል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስን አስመልክቶ ይኸው ተጨዋች ለሀትሪክ ስፖርት የሰጠው ቃለ-ምልልስም የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ሀትሪክ፡- ለቅ/ጊዮርጊስ የመጫወት ዕድልን ባገኘክባቸው የዘንድሮው የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ግጥሚያዎች ጥሩ ለመንቀሳቀስ ችለሃል፤ በአቋምህ ደስተኛ ነበርክ?
አማኑኤል፡- አዎን፤ ምክንያቱም ለእዚህ ታላቅ ቡድን ጨዋታዎቼን ያደረግኩት ለመጀመሪያ ጊዜ ነበርና፤ ይሄ በቋሚነት ያገኘሁት የመሰለፍ ተሳትፎዬም ለእኔ ከፍተኛ የራስ መተማመንን እንዳዳብርም ያደረገኝ ስለነበር ከደስታ ባሻገር የኩራት ስሜትም እንዲሰማኝም አድርጎኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ለቅ/ጊዮርጊስ መጫወት መቻል የተለየ ስሜትን ይሰጣል?

አማኑኤል፡- በጣም፤ እንደ እኔ ላሉ ወጣት ተጨዋቾች ደግሞ በተለይ ይሄን እድል ማግኘት መቻል መታደልም ጭምር ነው፤ እኔ ወደዚሁ ዋና ቡድን ሳድግ በፍጥነት ይሄን እድል አገኛለው የሚል እምነት አስቀድሞ አልነበረኝም፤ እኔ ግን ስራዬ ላይ በደንብ አድርጌ አተኩሬ ስሰራ እንደ እነ ምንተስኖትና ሌሎች ተጨዋቾች በርታ ጥሩ ደረጃም ላይ ትደርሳለህ እያሉ ምክራቸውን ሲለግሱኝ እና አዲስ አበባም ላይ በነበረን ጨዋታ ላይ የቡድናችን አሰልጣኝ ሚ/ር ማሂር የእኔን በልምምድ ሜዳ ላይ ያለኝን ጥሩ ብቃት አይቶ በዚሁ ቀጥል፤ ማሻሻል ያለብህንም ነገር አሻሽል፤ ጅማ ከተማ ላይ በሚኖረን የውድድር ተሳትፎም የመሰለፍ እድሉን ልሰጥህ እችላለው ሲለኝ በዛ ጠንክሬ ሰርቼ የመጫወቱን እድል አገኘውና ለቅ/ጊዮርጊስ መጫወት ስሜቱ ለየት የሚል ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ለቅ/ጊዮርጊስ ጥሩ መጫወት ብትጀምርም የደረሰብህ ጉዳት ደግሞ ከሜዳ አርቆ ነበር? ህመምህ ጠንከር ያለ ነበር?

አማኑኤል፡- አይደለም፤ የእኔ ጉዳት በቁርጭምጭምቴ ላይ የደረሰብኝ ነበር፤ መጀመሪያም የተጎዳሁት ከሀዲያ ሆሳህና ጋር ባደረግነው ጨዋታ ላይ ተመትቼም ነበር፤ ከዛ ደግሞ ባህርዳር ላይ እንደ ነገ ከአዳማ ከነማ ጋር ልንጫወት ዛሬ ላይ ልምምድን በምንሰራበት ሰዓት ላይ በድጋሚ በመጎዳቴ እና ላነክስ በመቻሌ እንደዚሁም ደግሞ ጉዳቱ ለ2 እና ለ3 ቀንም እንዳልራመድም ስላደረገኝ በዚሁ ሁኔታ ነው ባህርዳር ላይ በነበሩት አምስት ጨዋታዎች ላይ ከሜዳ በመጥፋት ከኳሱ ርቄ የነበርኩት፡፡

ሀትሪክ፡- ለቅ/ጊዮርጊስ በቋሚ ተሰላፊነት እንድትጫወት ዕድሉ ተሰጥቶህ በጉዳት ከሜዳ ስትርቅና አሁን ላይ ድነህ መጥተህ ቦታህ በሌላ ተጨዋች ሲያዝብህ ከፋህ?

አማኑኤል፡- በፍፁም፤ ለምንድንስ ነው የሚከፋኝ? የእኛ ቡድን እኮ አንድ ክለብ አንድ ቤተሰብ ነው፤ ማንም ተጨዋች ገባም፤ ተጫወተም ተረዳድተን እና ተደጋግፈን የምንጫወትበት ቡድንም ነው፤ እኔ እያለው ለክለቡ ጥሩ እየተጫወትኩ ነው፤ የባህርዳር ቆይታችን ላይ ደግሞ አስቀድሞ የእኔን በጉዳት ላይ መሆንን ተከትሎ አስቻለው ታመነና ደስታ ደሙ የመጫወቻ ቦታውን በደንብ አድርገው ፐርፎርምም አድርገውት ስለነበር ያ እኔን በጣም ሊያስደስተኝም ችሏል፡፡

ሀትሪክ፡- አማኑኤል አሁን በሙሉ ጤንነት ላይ ነው የምትገኘው?

አማኑኤል፡- አዎን፤ ከተሻለኝ ቆየ እኮ! ጉዳት በደረሰብኝ ጊዜ በፍጥነት ወደ ሜዳ ለመመለስ በመፈለግ መጀመሪያ ላይ ራጅ እስከመነሳት ደረጃ ላይ ሄጃለሁ፤ በዶክተራችንና በፊዚዮትራፒስታችንም እስከመታየትም ተጉዣለው፤ ከዛ እነሱ ምንም ነገር የለብህም፤ ንፁህ ነህም ሲሉኝ ወደ ሜዳ ተመልሼ ልምምዴን በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው እየሰራሁ ያለሁት፡፡

ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስና ውጤት ማጣቱን እንዴት አገኘኸው?

አማኑኤል፡- በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ እኛ ያስመዘገብነው ውጤት ታላቁን ክለባችንን የሚመጥን ባለመሆኑ ለእዚህ ደጋፊዎቻችንን ይቅርታ ልንጠይቅ ይገባናል፤ እንዲህ ያለ ውጤት በዚህ ቡድን ውስጥ የተለመደ አልነበረም፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይሄ እያጋጠመው ነው፤ የዘንድሮው በተለይ ደግሞ በመሪው ቡድን በሰፊ ነጥብ በመበለጥ በምንገኝበት ደረጃ ላይ ስለሆንን ይሄ ያስከፋናል፤ እግር ኳስ እንግዲህ እንዲህ ነው፤ እንደልፋትህ ውጤትን ላታገኝ ትችላለህምና ዋናው ነገር ከድክመትህ መማር ነው፤ እኛም በቀጣዩ የሊጉ ጨዋታዎች ከስህተቶቻችን ልንማር እና ጠንክረን ለመምጣት ተዘጋጅተናል፡፡

ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ይመራል፤ እናንተንም ከምትገኙበት ደረጃ አንፃር በ12 ነጥብ በልጧችሁ ይገኛል፤ ከዚህ በመነሳት ዘንድሮ ዋንጫውን አጣነው ብላችሁ ነው የተቀመጣችሁት?

አማኑኤል፡- በፍፁም፤ እኛ ከፋሲል ከነማ ጋር ያለን የነጥብ ልዩነት ሰፊ እንደሆነ ብናውቅም ውድድሩ እኮ ግን ገና አልተጠናቀቀም፤ ለምንስ ተስፋ ቆርጠን እንቀመጣለን፤ እኛ እስከ መጨረሻው ሳምንት ድረስ ያለብንን ጨዋታዎች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን ለመጫወት ነው የምንሞክረው፤ በኳስ የማይቀየር ነገር የለም፤ ፋሲል ከነማ ምርጥ እና ጠንካራ ቡድን እንደሆነ ብናውቅም ምንአልባት ወጥ የሆነ አቋሙን ላያሳይ የሚችልበት እድልም ሊኖር ስለሚችል ከእኛ የሚጠበቀው ያሉብንን ቀሪ ጨዋታዎች ማሸነፍ እና የሚመጣውን ነገር መጠባበቅም ነው፡፡ ሌላው ልጨምር የምፈልገው ለቅ/ጊዮርጊስ ከሻምፒዮንነት ውጪ የሚመጥነው ውጤት ምንም የለም፤ ዘንድሮ ግን ይህን ለማግኘት እድሉ ጠቧል፤ ያም ሆኖ ግን ሁለተኝነቱ ትርጉም ስላለው ያን ውጤት ልናመጣለት ይገባናል፡፡

ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስን ያለ ዋንጫ ማሰብ?

አማኑኤል፡- በጣም ከባድ ነገር ነው፤ ካለው የነጥብ ልዩነት አንፃር ይሄ ዘንድሮ ባይሳካ እንኳን በመጪው የውድድር ዘመን ላይ ያሉብንን አጠቃላይ ችግሮች አስተካክለን ወደምንታወቅበት እና ራቅ ወዳለንበትም ውጤታማነታችንም መመለስ የግድም ነው የሚለን፤ እስከዛው ግን በአሁን ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ ከዋንጫው ባለቤትነት ሌላ በአፍሪካ ክለቦች የውድድር መድረክ የሚያሳትፍ የሁለተኛ ደረጃም ውጤት አለና ያን ለማሳካትም ጭምር ነው ቀሪዎቹን ጨዋታዎች ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ የምናካሂደው፡፡

ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስን ውጤት አሳጥቶታል የምትለው ነገር ምንድን ነው? የአሰልጣኙ ከቡድኑ መነሳትስ ችግራችሁን ይቀርፍላችኋል?

አማኑኤል፡- ይሄ ከባድ ጥያቄ ነው፤ የእኛ ውጤት ማጣት ግን የአንድ ወይንም ደግሞ የሁለት ተጨዋቾች ችግር ብቻ አይደለም፤ ክለቡን ጥሩ ደረጃ ላይ ለማድረስ እየለፋን ነበር፤ ያ አልተሳካም፤ እንደ ግለሰብ ሳይሆን እንደ ቡድንም ነው ሁላችንም በሜዳ ላይ ቡድኑ በሚፈልገው ደረጃ ጥሩ ስላልነበርን ውጤትን ልናጣ የቻልነውና በዚህ አሁንም በድጋሚ ደጋፊውን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

ሀትሪክ፡- ዋልያዎቹ ማዳጋስካርን በሰፊ ግብ አሸነፉ እንደ አንድ የሀገሪቱ እግር ኳስ ተጨዋች ስሜትህን በምን ደረጃ ገለፅክ?

አማኑኤል፡- ያገኘነው ውጤት የኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ጊዜ የነበረውንና ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈውን ቡድን እንዳስታውስ ነው ያደረገኝና እንደ አዲስ ነው ስሜቴ ያገረሸው፤ ለብሔራዊ ቡድኑ ተመርጬ እንድጫወትም ጉጉቱ ጨምሮብኛልና በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡

ሀትሪክ፡- (ማስታወሻ – ከዋልያዎቹ ጨዋታ በፊት የተደረገ ቃለመጠይቅ ነው) ኮትዲቯርን ማክሰኞ ገጥመን ለአፍሪካ ዋንጫው የማለፍ እድላችንን እንወስናለን፤ እልማችን ይሳካል?

አማኑኤል፡- አዎ፤ እኔ ብዬአለው፤ በቡድናችንም እተማመናለው፡፡

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…?

አማኑኤል፡- ቅ/ጊዮርጊስ ውስጥ ከስር እንደማደጌ ቡድኑ ጥሩ

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website