“ያሸነፍነው በደረጃ የምትበልጠንን ኒጀር እንጂ ደካማዋን ሀገር አይደለም”አስቻለው ታመነየኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን /ዋልያዎቹ/ ጠንካራው የተከላካይ ስፍራ ተጨዋች አስቻለው ታመነ በአፍሪካ ዋንጫው የማጣሪያ ጨዋታ ላይ ሀገራችን ኒጀርን በመስዑድ መሐመድ፣ በያሬድ ባየህ እና በጌታነህ ከበደ ሶስት ግቦች 3-0 ማሸነፏ የሚታወስ ሲሆን ይህን ጨዋታ አስመልክቶ “ዋልያዎቹ ያሸነፉት በእግር ኳሱ ደካማ የሆነችውን ሀገር ነው” በሚለው የአንድ አንድ የስፖርት አፍቃሪዎች እና የባለሙያተኞች ሀሳብ ዙሪያ የተሰማውን አስተያየት ለዝግጅት ክፍላችን ሰጥቷል፡፡


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ረዳት ካፒቴን አስቻለው ታመነ ከጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ጋር በነበረው የአጭር ሰዓት ቆይታው ኒጀርን በሰፊ ግብ ልዩነት ስለማሸነፋቸው ተከትሎ ሰዎች በሰጡት ሀሳብ ዙሪያ ምላሹን ሲሰጥ “በአፍሪካ ዋንጫው የማጣሪያ ጨዋታ እኛ ያሸነፍናት ሀገር በዓለም የእግር ኳስ ደረጃ የምትበልጠንን ኒጀር እንጂ በእግር ኳሱ ደካማ የሆነችውን ሀገር አይደለም፤ የእኛን ውጤት ለማጣጣል ካልሆነ በስተቀር አንድአንዶች እየሰጡት ባለው አስተያየት ቅርም ተሰኝቻለው” በማለት ምላሹን ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎችን አስመልክተንና በሌሎች ተያያዥ በሆኑ ጥያቄዎች ዙሪያ ከአስቻለው ጋር ያደረግነው ቆይታም ይሄንን ይመስላል፡፡ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ 3 ኒጀር 0 የሚል ውጤት ማክሰኞ ዕለት ተመዝግቧል፤ ስለ ጨዋታው እና ድሉ ምን ትላለህ?

አስቻለው፡- በአፍሪካ ዋንጫው የማጣሪያ ጨዋታችን ኒጀርን በሰፊ ግብ ያሸነፍንበት ግጥሚያም ሆነ የተመዘገበው ውጤት ለእኛ በጣም ጥሩ ነው፤ በጨዋታው ጥሩ መንቀሳቀሳችንና ተጋጣሚያችንን መብለጣችን እንደዚሁም ደግሞ ያገኘናቸውን የግብ አጋጣሚዎችንም መጠቀማችን ለድል አብቅቶናልና ውጤቱ ጨዋታውን ይገልፀዋል፡፡

ሀትሪክ፡- በኒጀር ተሸንፋችሁ ከመጣችሁ በኋላ ነው እዚህ በሰፊ ግብ ልታሸንፉ የቻላችሁት ይህን የድል ውጤት ጠብቃችሁት ነበር?

አስቻለው፡- በሰፊ የግብ ልዩነት እናሸንፋለን በሚለው ዙሪያ ከሆነ በእዛ ደረጃ በፍፁም ውጤቱን አልጠበቅንም፤ ያም ሆኖ ግን በእነሱ ሀገር ላይ ካደረግነው ጥሩ ጨዋታ በመነሳት ይሄን ግጥሚያ እንደምናሸንፍ ግን በጣም እርግጠኞች ነበርን፡፡

ሀትሪክ፡- የኒጀር ብሔራዊ ቡድንን ካሸነፋችሁ በኋላ በውጤቱ በጣም የተደሰቱ እንዳሉ ሁሉ እኛ ያሸነፍነው የእግር ኳሷን ደካማ ሀገር ኒጀርን ነው በሚል አስተያየትም የሚሰጡ አሉ፤ በእዚህ ዙሪያ ምን አልክ?


አስቻለው፡- ይሄ የእኛን ልፋትና ክሬዲታችንን ለማሳጣት የተሰጠ አስተያየት ነው፤ ለእኛ የሚሰጠን ግምት ስለሆነ እንጂ ኒጀር እንደተባለው ደካማዋ የእግር ኳሷ ሀገር አይደለችም፤ አሁንም እደግመዋለው እኛ ያሸነፍነው በዓለም የእግር ኳስ ደረጃ የምትበልጠንን ኒጀር እንጂ ደካማዋን ሀገር አይደለም፤ ከእኛ የተሻለችውንና በፈረንሳይ ሀገርም የሚጫወቱ ተጨዋቾች ያላትን ሀገር ነው ያሸነፍነውና ውጤታችንን ማጣጣል ተገቢ አይደለም፤ ውጤቱን ባጣጣሉት አንድ አንድ ሰዎችም ቅር ልሰኝ ችያለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- በኒጀር የደረሰባችሁ ሽንፈት አስቆጪ ነው?

አስቻለው፡- በጣም፤ በተለይ ደግሞ እነሱን በሜዳችን 3-0 አሸንፈን ከወጣን በኋላ ምናለ ከዛ ጨዋታ ቢያንስ አንድ ነጥብ እንኳን አግኝተን ብንመለስም በሚል ነው የቁጭት ስሜት ያደረብን፤ ምክንያቱም ኒያሚ ላይ ባደረግነው ጨዋታ ቡድናችን ጥሩ ተንቀሳቅሶ ነበር፤ በጨዋታ ብልጫም እኛ ተሽለን ታይተናል፤ ወደ እነሱ የግብ ክልልም በተደጋጋሚ ጊዜም ደርሰናልና ካገኘናቸው የግብ አጋጣሚዎች ውስጥ ቢያንስ አንዱን አለመጠቀማችን ለሽንፈታችን አስተዋፅኦም አድርጓልና ይሄ ነው በእኔም ላይ ሆነ በሁሉም የቡድናችን አባላቶች ላይ የቁጭት ስሜት ሊፈጥርብን የቻለው፡፡


ሀትሪክ፡- በአፍሪካ ዋንጫው ቀጣይ የማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ከማዳጋስካር እና ከኮትዲቯር ጋር ትጫወታለች፤ ከእነዚህ ግጥሚያዎች በመነሳት በካሜሮን አስተናጋጅነት ወደሚካሄደው ውድድር የምታልፉ ይመስልሃል?


አስቻለው፡- ይሄ እንግዲህ እግር ኳስ ነው፤ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ማለፍ የሚቻለውም ከወቅታዊ እና በእዛን ዕለት ከምታሳየውም አቋም በመነሳት ነውና በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ግጥሚያዎቹ በጣም አስቸጋሪ እና ጠንካራ ሊሆኑብን ቢችሉም የራሳችንን እድል በራሳችን በመወሰን ማዳጋስካርን በማሸነፍ ከኮትዲቯር ጋር በሚኖረን ጨዋታ ደግሞ ከተቻለ ለማሸነፍ ካልተቻለ ደግሞ ነጥብ ተጋርተን በመመለስ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎአችንን እውን ለማድረግ እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ እንታገላለን፡፡


ሀትሪክ፡- ከማዳጋስካር እና ከኮትዲቯር ጋር በሚኖረን ጨዋታ የተሻለ ውጤት ለማምጣትና ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል?


አስቻለው፡- የመጀመሪያው ተጋጣሚዎቻችንን አክብደንም፤ አቅለንም መግባት አይኖርብንም፤ ምክንያቱም እነዚህ ሁለቱ አገራት በአሁን ሰዓት የምድቡ መሪና ጠንካራ ቡድኖችም ስለሆኑ ለእነሱ በደንብ ነው ልንዘጋጅ የሚገባው፤ ከዛ ውጪም በተለይ ደግሞ ወደ ኮትዲቯር ስናመራ በሞራል ደረጃ ከእዚህ ፈፅሞ ተሸንፈን መሄድም አይኖርብንምና ይሄን ማድረግ ከቻልን የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ እልማችንን እናሳካለን፡፡


ሀትሪክ፡- በብሔራዊ ቡድናችን ውስጥ ያለው የቡድን መንፈስ ምን ይመስላል?


አስቻለው፡- አሁን ላይ ጥሩ እና ደስ የሚል ነገርን እየተመለከትን ነው፤ ኒጀርን ካሸነፍን በኋላም በሁሉም ተጨዋቾች ላይ የሚታየው የቡድን መንፈስ እና የመነቃቃት ስሜትም በጣም የጨመረበትን ሁኔታ ስላየው ለቀጣዮቹ ሁለት የማጣሪያ ግጥሚያዎቻችን ይሄ መሆን መቻሉ የሚጠቅመን ነው፡፡


ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተጨዋችነት ዘመን ቆይታህ አቋምህ ሳይዋዥቅ ጠንካራ የመከላካል ብቃትን እያሳየህ ይገኛል፤ ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ?


አስቻለው፡- በእዛ ደረጃ ልጫወት የቻልኩት ሁሌም ልምምዴን ጠንክሬ ስለምሰራ ነው፤ የእግር ኳስ ጨዋታ በህዝብ ዘንድ የሚታይ እና የሚሰጥህም አድናቆት ከዛ በመነሳትም ስለሆነ ራስህን በሚገባ ልታዘጋጀው ይገባል፤ በስራዬ እና በእንጀራዬ ወደኋላ የምልበት ጊዜ የለም፤ ለምኔም ሳልሳሳ በተደጋጋሚ ጊዜ የአቅሜን አውጥቼም ነው ኳስን የምጫወተውና ይሄን ማድረጌ ነው አቋሜ ሳይዋዥቅ እንድጫወት እያደረገኝ ያለው፡፡


ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ለቅዱስ ጊዮርጊስም በኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ላይ ስትጫወት ከተቃራኒ ቡድን አጥቂዎች ላይ ብቻ ለብቻ ስትገናኝ ኳስን የምትነጥቅበት እና በጉልበትም የምትቋቋምበትን ሁኔታ ለመመልከት ችለናል፤ በእዚህ ደረጃ ለመጫወት እንድትችል የረዳ ዋናው ጉዳይ ምንድን ነው?


አስቻለው፡- በእንደእነዚህ አይነቶቹ የኢንተርናሽናል ግጥሚያዎች ላይ ብዙ ጊዜ ጥሩ ለመጫወትም ሆነ ጎልቼ ለመውጣት የቻልኩበት ዋንኞቹ ምክንያቶች በአካል ብቃት በኩል ጥሩ ስለሆንኩ ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያ የፕሮጀክት አሰልጣኜ ገብረ ክርስቶስ ቢራራ ያኔ ከባላጋራ ቡድን አጥቂዎች ላይ አህምሮዬን በመጠቀም ኳስን እንዴት አድርጌ መንጠቅ እንዳለብኝ ያሳየኝና ያስተማረኝ የጨዋታ ታክቲክ ስለነበርና ያንንም በሜዳ ላይ ስለምጠቀም ነው፤ በተለይ ደግሞ እሱ በልምምድ ወቅት ካሳየኝ የጨዋታ ታክቲኮች መካከል ብዙ ጊዜ ከአንድ አጥቂ ጋር ስትገናኝ ጊዜውን /ታይሚንግህን/ በጠበቀ መልኩ ጠንካራ የሆነውን እግርህን በማስቀደም እና ወደ እሱ እግር ስርም ቀድመህ በማስገባት ኳስን የምትነጥቅበት እንደዚሁም ደግሞ በአቋቋም ደረጃም በተከላካይ ስፍራው ላይ እንዴት መቆም እንዳለብኝም ስላወቅኩኝ በጥሩ መልኩ ለመጫወቴ በጣም ነው የረዳኝ፡፡


ሀትሪክ፡- በሜዳ ላይ ካለህ ጥሩ ብቃት በመነሳት አስቻለውን በሀገር ውስጥ ክለቦች ብቻ ማየት ይመጥነዋል?


አስቻለው፡- ብዙ ሰዎች በእዚህ ሊግ ደረጃ መጫወቴን አስመልክተው ሁሌም አይመጥነውም ይሉኛል፤ እንደዚህ ያሉ ነገሮችን ስታደምጥ ደግሞ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃ ወደ ውጪ ሀገር ወጥተህ መጫወትን ታልማለህና እኔም ይሄን እድል ለማግኘት ያልጣርኩበት ጊዜ የለም፤ ያም ሆኖ ግን ብዙ ጊዜ እንደዚህ ያሉ እድሎችን የማገኝባቸው አጋጣሚዎች ለምጫወትበት የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ፊርማዬን ካኖርኩ በኋላ እና ኮንትራትም በሚቀረኝ ጊዜ በመሆኑ የሚመጡት የመጫወት እልሜን እስካሁን ሳላሳካ ቀርቻለው፤ አሁን በቅርብ እንኳን ኮቪድ ወደ አገራችን በገባበት ሰሞን ያገኘሁት ሌላ እድልም ነበር፤ የፈለገኝ ቡድንም ከክለቤ ጋር መነጋገሩም ይታወሳል፤ ሆኖም ግን ለክለቤ የምጫወትበት ኮንትራት ስላለኝ ወደ ውጪ ሀገር ወጥቶ ሳልጫወት ቀርቻለው፤ ከእዚህ በኋላ ግን በፕሮፌሽናል ደረጃ ወጥቶ ለመጫወት አሁንም ሰፊ እድሉ ስላለኝ ያንን እልሜንና ምኞቴን ማሳካቴ አይቀሬ ነው፡፡


ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ሁሌም ጠንካራ ለማድረግ ምን መሰራት አለበት ትላለህ?


አስቻለው፡- በቅድሚያ ለእዚህ ምላሽ ይሆናል ብዬ የማስበው አሰልጣኞች በየጊዜው ባይቀያየሩ ጥሩ ነው የምለው፤ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ አሰልጣኞች ሲቀያየሩ የየራሳቸውን ልጆችና ለእነሱም የሚመቻቸውን ተጨዋቾችም ስለሚያመጡ ቀጣይነት ያለውና ጠንካራ ቡድንን ለመስራት ሲቸገሩ ይታያሉ፤ የተሰራ ቡድን ባይፈርስ ጥሩ ነው፤ ቡድኑ ከሚፈርስ ባሉት ላይ የተወሰኑ ልጆችን መጨመር ነው የሚያዋጣው፤ ሌላው ለዋናው ቡድን የሚበቁ ብቁ ተጨዋቾችን ለማግኘትም ዕድሜያቸው ከ20 እና ከ23 ዓመት በታች ያሉ ቡድኖችንም ሁሌ ማዘጋጀት ያስፈልጋልና በእዚህ መልኩ ስራ ቢሰራ መልካም ነው፤ ይሄም ነው ለእግር ኳሱ እድገታችን ተጠቃሚም የሚያደርገን፡፡


ሀትሪክ፡- 2013 ከገባ በኋላ ምን ምን ነገሮችን ነው ያቀድከው?


አስቻለው፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ለአፍሪካ ዋንጫው ማሳለፍ፤ በቀጣይነትም ወደ ውጪ ሀገር ወጥቶ ስለመጫወትና የሊግ ውድድራችን በሰላም ይጀመር እንጂ ከክለቤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋርም ባለፉት ሁለት ዓመታት ያጣነውን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ በማግኘት የክለቡን የቀድሞ ሀያልነት ማስቀጠል እፈልጋለውና እነዚህ ናቸው ዋናዋናዎቹ እቅዶቼ፡፡


ሀትሪክ፡- የፕሪምየር ሊጋችን በዲ.ኤስ.ቲቪ ሊተላለፍ ነው፤ በእዚህ ዙሪያ ምን አልክ?
አስቻለው፡- ይሄ ለእኛ ሀገርም ሆነ ተጨዋቾቻችን ትልቅ እድል ነው፤ ጨዋታዎቹ የቀጥታ ስርጭት አግኝተው መተላለፋቸውም ሊጋችንን ለማሳደግም ይጠቅማል፤ ለእኔም ቢሆን እነዚህ ጨዋታዎች መተላለፋቸው ወደውጪ ወጥቶ ለመጫወት ጊዜዬን ያፋጥንልኛልና መረጃውን ስሰማ በጣም አስደስቶኛል፡፡


ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…?


አስቻለው፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች በአገራችን አሁን ላይ በተከሰተው የእርስ በርስ ግጭትና በመከላከያ ሰራዊታችንም ላይ በተሰነዘረው አደጋ ማዘናችንን እየገለፅኩ፤ ከእዚህ በኋላ ሁላችንም እንደ አንድ በመሆን የሀገራችንን ስም በኳሱ የምናስጠራበትና የየራሳችንንም የቤት ስራ በመስራት ሰላማችን የሚመለስበትን ሁኔታም ልንፈጥር ይገባል፤ ጥሩ ነገር እንዲመጣም ፈጣሪ ይርዳን፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website