“አሠልጣኝ አብርሃም ኮትዲቯርን ሲረታ ሸልመውት አንድም ቀን ማስጠንቀቂያ ሳይሰጡ ማሰናበት ተገቢ አይደለም” አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው/የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ/

“አሠልጣኝ አብርሃም ኮትዲቯርን ሲረታ ሸልመውት አንድም ቀን ማስጠንቀቂያ ሳይሰጡ ማሰናበት ተገቢ አይደለም”
አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው/የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ/

“ከአንዴም ሁለቴ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል ቡድኑም ልፍስፍስ መሆኑ በአንድ ድምፅ ነግረነዋል” ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል


የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱን አሰናብቶ አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ቢሾምም ይፋ ማድረግ አለመቻሉ እያነጋገረ ነው፡፡
ለወትሮው ፈጣን መረጃ የሚያስተላልፈው የህዝብ ግንኙነት ክፍል ዝምታም የፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት መረጃውን ይፋ አለማድረጉ ለተለያዩ አሉባልታዎች በር ከፍቷል፡፡ ሀትሪክ ግን ባገኘው መረጃ በፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት የተሰበሰቡት ፕሬዚዳንቱ አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ አቶ ኢብራሂም መሐመድ፣ አቶ አበበ ገላጋይ፣ አቶ አብዱራዛቅ ሀሰን፣ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ፣ አቶ አሊሚራ መሀመድና አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ በሰጡት ድምፅ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱን 6ለ1 በሆነ ሰፊ ድምፅ በመብለጥ ቀጣዩ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ እንዲሆን ወስነዋል፡፡ አመራሮቹ ለቴክኒክ ኮሚቴ የአሰልጣኞችን ዝርዝር በመያዝ ለምርጫ በሚረዳ መልኩ ምክረ ሃሣብ እንዲያቀርብ መመሪያ ቢሰጡም የቴክኒክ ኮሚቴው የአሰልጣኝ አብርሃምን ስም ብቻ ይዞ መቅረቡ የልዩነቱ ምክንያት መሆኑ ታውቋል፡፡ መረጃውን ለሀትሪክ ያቀበለው ታማኝ ምንጭ ቴክኒክ ኮሚቴ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ቢሆን ያለውን ጥቅም የሚገልፅና 9 ዝርዝር ሃሳብ የያዘ ፕሮፖዛል ቢያቀርብም በስራ አስፈፃሚው ተቀባይነት አጥቷል፡፡ ስራ አስፈፃሚው ግን ቴክኒክ ኮሚቴው አማካሪ ነው አማካሪ መሆን ባለባችሁ ጉዳይ ላይ የአንድን አሰልጣኝ ስም ይዛችሁ መምጣታችሁ ልክ አይደለም ጊዜ ይሰጣችሁና እንደገና ተመልከቱት ቢባሉም አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከዚህ በኋላ የምናመጣው ስም የለም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ እንደ ታማኝ ምንጫችን ኢትዮጵያ ውስጥ ሌላ አሰልጣኝ የለም እንዴ? ሌሎችን ለምን ቼክ አታደርጉም ሲባሉ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው “ከአሰልጣኝ አብርሃም ውጪ ሌላ አሰልጣኝ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም” ብለዋል፤ ይህን ምልልስ ተከትሎ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ሰው ታሞብኛል በማለት ስብሰባውን ረግጠው ሳይሆን አስፈቅደው ወጥተዋል በማለት ያለውን ሂደት ተናግሯል፡፡

ከዚህ ውዝግብ በኋላ ሰባቱ የስራ አስፈፃሚው ኮሚቴ አባላት ከኛ ጋር ውል ለሌለው አሰልጣኝ ውለታ ለምን እንፈፅማለን ከሌሎቹ አሰልጣኞች ጋር ይታይና ምርጫውን እናድርግ ተብሎ ወደ ምርጫ መግባታቸው ታውቋል፡፡ ቋሚ የብሔራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች የሉም፣ በርካታ ጨዋታ የተጫወቱትና 50 በመቶ የተሳተፉት 4 ተጨዋቾች ብቻ ናቸው በማለት በአብርሃም ጊዜ ቋሚ ቡድን የለንም የሚል መረጃ ይዘው የመጡ አመራሮች መኖራቸው ተሰምቷል፡፡ 17 ጨዋታዎች አድርጎ 5 ሲረታ 5 አቻ ወጥቶ 7 ጊዜ ጊዜ ተሸንፏል፡፡ ካሸነፋቸው ቡድኖች ትልቁ ኮትዲቯር ነው ሌሎቹ ሶማሊያና ጁቡቲን ነው ይህም ውጤታማ አለመሆኑን ያሳያል በማለት የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸው ታውቋል፡፡ አመራሮቹ አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ከመቐለ 70 እንደርታ ውል አለኝ በማለቱ የባህር ዳር ከተማው አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ደግም ስልክ ባለመነሳቱ ከምርጫ ውጪ አድርገዋቸዋል፡፡ በመጨረሻም በአሰልጣኝ ውበቱ አባተና በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ መሀል ውድድር አድርገው በድምፅ ብልጫ ውበቱ አባተ በ6ለ1 የበላይነት የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ እንዲሆኑ መመረጣቸው ታውቋል፡፡ አመራሮቹ እንዲህ በሰፊ ድምፅ ምርጫውን ያድርጉ እንጂ ውጤቱ ይፋ አለመደረጉ ትልቅ መነጋገሪያነትና ለተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች አሉባለታ በር የከፈተ ሆኗል፡፡ ወደ ማተሚያ ቤት እስክንገባ ድረስ ፌዴሬሽኑ የምርጫውን ሂደት ይፋ አለማድረጉ ታውቋል፡፡

አመራሮቹ ቴክኒክ ኮሚቴ ይዞ በቀረበው 9 ዝርዝር ምክር ሃሣብ ላይ የምትቃወሙት ነገር አለ ወይ ሲባሉ አይ አሳማኝ ነው ነገር ግን ለምን ሌላ አማራጭ አላቀረባችሁም በሚል መመለሳቸውም ታውቋል፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት አሳማኝ ነጥብ ከሆነ ለምን ሌላ አማራጭ እናቀርባለን በማለት ምላሽ መስጠታቸው ታውቋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ አዲሱን ተሿሚ አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ተንቀሳቃሽ የግል ስልኩ ዝግ በመሆኑ ሳይሳካ ቢቀርብም ተሰናባቹ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ግን ለሀትሪክ እንደተናገሩት “በጣም ቅር ብሎኛል ሰው የለፋበትን ውጤት መጣል ተገቢ አይደለም፡፡ ሁለት አመት ስሰራ አንድም ቀን የቃልም ሆነ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ሰጥተውኝ አያውቁም ሁለት አመት የሰራ ባለሙያ ሠላማዊ በሆነ መንገድ ጨርሶ ለምን አየር ላይ መጣል ፈለጉ? ለማንኛውም ሁሉን የምጠብቀው ከፈጣሪ ነው” ሲል የተሰማው ስሜት አስረድቷል፡፡

በምርጫው ሂደት ዙሪያ ለሀትሪክ አስተየያትቸውን የሰጡት ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ግን ሙሉ በሙሉ አካሄዱ ላይ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ሲናገሩ “ሲጀመር በምንም አይነት መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአብርሃም ውጪ ሌላ አሰልጣኝ አላውቅም አልልም አሉባልታ ነው ምክረ ሃሣብ ስጡን አሉ 9 ነጥብ ያዘለ ደብዳቤ ሰጠን ከአብርሃም ውጪም አላልንም ቅጥር ከሆነ በሕጋዊ መንገድ ማስታወቂያ ይውጣና ሁሉም አሰልጣኝ ይወዳደር ነገር ግን አብርሃም የቀረው 5 ጨዋታ ነው ኮትዲቯርን ሲረታ ሸልማችሁታል 2 አመት ቡድኑን ሲመራና ሲሸነፍም አንድም ቀን ማስጠንቀቂያ አልፃፋችሁም ህዝብና መንግሥት ተደስቷል ህዝብ ተስፋ ጥሎበታል የማለፍ እድል አለን ካለው ጊዜ አንፃር አሰልጣኝ አብርሃም ይቀጥል ከፈለጋችሁ የኒጀር ጨዋታ ላይ ከተሸነፈ አባሩት እንጂ እርሱ በጀመረው ላይ ሌላ ሰው ማስገባት በቴክኒክ ኮሚቴ እምነት ሀገር የሚጎዳ ነው አናምንበትም የሚል አቋም ይዘናል” ሲሉ መልሰዋል፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት እንደሚሉት “ማንም አሰልጣኝ ቢመጣ ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆን ማገዝ ነው የኔ ስራ…ውበቱ አሰልጣኝ የመሆን እድል አለው ለምን ውበቱ መጣ ያለ የቴክኒክ ኮሚቴ የለም ከ4ቱ ውጪ ሌላ አሰልጣኝ እኔም መወዳደር መብቴ ነው ቢል ምላሻችን ምን ሊሆን ነው? ይሄ አካሄድ መቅረት አለበት ከውበቱ መምጣት በፊት ማንም አሰልጣኝ ሲመጣ የራሱን ፍልስፍና ለማስረፅ ሲሞክር ጊዜ ይወስዳል ያለን ጊዜ ደግሞ አጭር ነው በኛ አካሄድ ተስፋው ቢጠፋ ጭላንጭሉ ቢዳፈን ማን ሊጠየቅ ነው?” ሲሉም ይናገራሉ፡፡ በ6ለ1 የሁለቱ አሰልጣኞች ድምፅ አሰጣጥ ላይ እንዳልነበሩና ወጥተው መሄዳቸውን የሚናገሩት አሰልጣኙ “አሁንም አቋማችን የጀመረው አሰልጣኝ ቀሪውን 4 ጨዋታ ይጨርስ ነው” ሲሉ የቴክኒክ ኮሚቴውን አቋም አንፀባርቀዋል፡፡
“አሰልጣኝ ውበቱ በመምጣቱ ተቃውሞ የለኝም መልካም የስራ ዘመንነው የምለው የምቃወመው ፕሮሲጀሩን ነው፡፡ አሁን ነገ ቢሸነፍ ውበቱ ተሸነፈ የውበቱ ቡድን ተሸነፈ ሊባል ነው? ተጠያቂኮ የለም የኛን ውሣኔ የሚሽር አካል አለሁ ብሎ ውድቅ ካደረገ የሚመጣውን አብረን እናያለን አንድ ሜዳካል ዶክተርን በእጅ ብልጫ አንተ ዶ/ር ነህ አይደለህም ማለት ከቻልክ ትልቅ አደጋ ነው በስራው እንጂ በእጅ ብልጫ የሚወሰነው ውሣኔ በምንም መመዘኛ የትም ሊያደርሰን አይችልም መስተካከል አለበት” ሲሉ አሰልጣኝ ሰውነት ተናግረዋል፡፡

ከአሰልጣኝ አብርሃም ጋር የተለየ ግንኙነት ስላሎት ይሆን ለርሱ የወገኑት የሚል ጥያቄ ከሀትሪክ የቀረበላቸው አሰልጣኝ ሰውነት “ማንንም ሰው የመቅረብ ችግር የለብኝም አሰልጣኝ አብርሃምን በስራ ስለምንገናኝ በካፍ ኢንስትራክተር ፓናል ላይ በተደጋጋሚ ከመገናኘት ውጪ ከማንም ጋር የተለየ ግንኙነት የለኝም” በማለት መልሰዋል፡፡ “የስራ አስፈፃሚው ውሣኔ ተገቢ አይደለም ስራ አስፈፃሚውን የሚገመግም ካለ የዚያ ወገን ስራ ይሆናል የኢትጵያን እግር ኳስ ከላይ እስከታች አይቼዋለው አካሄዱ እንዲህ ነው አስተዳደሩን አየሁት ስልጠናውን ከፋብሪካ ቡድን እስከ ብሔራዊ ቡድን ተመለከትኩ፡፡ ሙያን ለባለሙያው ያለመስጠት ለዘመናት የነበረውን አካሄድ ካላስተካከልን የአሁኑ ስራ አስፈፃሚ የሀገሪቱን እግር ኳስ መለወጥ አይችልም ሙያ መከበር አለበት ከዚህ ውጪ መፍትሔ የለም ቴክኒክ ኮሚቴ ያቀረበውን ምክረ ሃሣብ ስራ አስፈፃሚው ውድቅ ማድረጉ የባለሙያውን ስሜት ይጎዳል” ያሉት የብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ ለሀትሪክ እንደተናገሩት “የትኛውንም አሰልጣኝ አልተቃወንም ኮሚቴው ለማንም ብሎ አይሰራም ተከፍሎትም አይደለም እየሰራ ያለው… ይሄ መጥፎ ባህላችን ኖረንበት የመጣነውን መጥፎ ጉዞ ካላረምን ለሀገር ትልቅ ጉዳት ይሆናል ቴክኒክ ኮሚቴ ማለት እግር ኳሱ ማለት ነው በእግር ኳሱ ዙሪያ ኮሚቴው የወሰነው ውሣኔ የመጨረሻ መሆን አለበት ማንም ሊያፈርሰው አይገባም የካፍና ፊፋ ዋነኛ አካል ቴክኒካል ዲፓርትመንቱ ነው በኛ ሀገር ይሄ የማይከበር ከሆነ ትልቅ ስህተት ነው የጀርባ አጥንት የሆነውን ቴክኒክ ኮሚቴ ውሣኔ ከተሻረ ከዚህ በኋላ የሚመጣው ውጤት ሀላፊነት የኛ አይደለም” ሲሉ አስተያየታቸውን ለሀትሪክ ሰጥተዋል፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ግን አሰልጣኝ አብርሃም አንድም ጊዜ የቃል ማስጠንቀቂያ ሳይሰጠው የሚለውን ሃሣብ አጣጥለውታል፡፡ “ፍፁም ውሸት ነው ጠርተን በሁለት መደበኛ ስብሰባችን ላይ ማስጠንቀቂያ ሰጥተነዋል፡፡ በአዲስ አበባ ስታዲየም መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ኃላፊነቱን በያዘ በስድስት ወር ውስጥ ጠርተን ደስተኛ እንዳልሆንን ልፍስፍስ ቡድን እንደያዘ በአንድ ድምፅ ነግረነዋል፤ ሁለተኛው የዛሬ አመት ጠቅላላ ጉባኤ ልናደርግ ቀናቶች ሲቀርቱ ጠርተን አነጋግረነዋል የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰውነት የዚህ አሰልጣኝ አካሄድ አልጣመኝም ምንም አይነት ዕቅድ የለውም ሲሉ ተናግርዋል፡፡ ዕቅዱን አይሰጠኝም በማለት በተደጋጋሚ ጊዜያትም አሰልጣኝ ሰውነት ለስራ አስፈፃሚው ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡ ስለዚህ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አልተገመገመም ይላሉ ብዬ አላምንም” በማለት ተናግረዋል፡፡ እኚሁ የፌዴሬሽኑ አመራር ሲናገሩ “ቁርጥ ያለና ተገቢ ውሳኔ ነው ብዬ አምናለሁ ለምንስ ይሄን ያህል አጀንዳ ሆነ? ረዘም ያለ ጊዜ አሰልጣኝን በማቆየት የተሻልን ነን ቴክኒክ ኮሚቴ ሃሳቡን ከማምጣት ውጪ ቅጥሩን የመወሰን መብትና ኃላፊነት የስራ አስፈፃሚው ኮሚቴ ብቻ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ “የዛሬ 2 አመት በቴክኒክ ኮሚቴ አሰልጣኝ አብርሃም አልመጣም ኮሚቴው ወደ አራት የሚጠጉ አሰልጣኞችን አምጥቷል አሰልጣኝ አብርሃም ግን የለበትም፤ ከመጡት አሰልጣኞች ውጪ ስራ አስፈፃሚው ተነጋግሮ አብርሃምን ሾሟል ዛሬስ ምን አዲስ ነገር አለው? አሰልጣኝ ውበቱ በቴክኒክ ኮሚቴ አልመጣም ከሁለት አመት በፊት እንደነበረው ስራ አስፈፃሚው ከቴክኒክ ኮሚቴ ምርጫ ውጭ አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ሾሟል፤ ያን ያህል መጋነን አለበት ብዬ አላምንም” ሲሉ ለሀትሪክ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሀትሪከ ባላት መረጃ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ከወራት በፊት በሰጡት መግለጫ “የብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ በሚያቀርበው የውሣኔ ሃሣብ መሰረት የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ቅጥር ይፈፀማል” ቢሉም አሁን ግን በተቃራኒ ቴክኒክ ኮሚቴ ውሣኔ ውጪ ቅጥር ለመፈፀም መወሰኑ ሙያን ለባለሙያ የመተው ችግር እንዳለ አመላካች ሆኗል፡፡ ትላንት በተገኘ መረጃ አሰልጣኝ አብርሃም አሰልጣኝ ውበቱን በማግኘት መልካም የስራ ዘመን የተመኘለት መሆኑ ታውቋል፡፡ ወደ ማተሚያ ቤት እስክንገባ ድረስ ፌዴሬሽኑ የምርጫውን ሂደት ይፋ አለማድረጉ ታውቋል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport

One thought on ““አሠልጣኝ አብርሃም ኮትዲቯርን ሲረታ ሸልመውት አንድም ቀን ማስጠንቀቂያ ሳይሰጡ ማሰናበት ተገቢ አይደለም” አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው/የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ/

  • September 26, 2020 at 6:32 pm
    Permalink

    ለመረጃው ከልብ እናመሰግናለን

Comments are closed.