“ለብሔራዊ ቡድን ዳግም መመረጥ እፈልጋለሁ” ዮናስ በርታ

ውልደቱና ዕድገቱ የበርካታ እግር ኳስ ተጨዋቾች እና የኪነ-ጥበብ ሰዎች መፍሪያ በሆነችው የአዲሱ ቄራ አካባቢ ነው፤
አልማዝዬ ሜዳ ደግሞ የእግር ኳስን የተጫወተበት የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራ ነው፤ ለእግር ኳስ ጨዋታ ከልጅነት
ዕድሜው አንስቶ ጥልቅ ፍቅር ካደረበት በኋላ በአካባቢው በሚገኙት ሜዳዎች ላይ ኳስን ያንከባልል የነበረው ይኸው
ተጨዋች ዮናስ በርታ ሲባል በክለብ ደረጃ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ታዳጊ ቡድን አንስቶ በአሁን ሰዓት እስከሚገኝበት
የወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ክለብ ውስጥ የእግር ኳስን ለመጫወት ችሏል፡፡

ዮናስ በርታ ወጣት እና በመሀል ሜዳ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴን ከሚያሳዩ ተጨዋቾች መካከል የሚጠቀስ ሲሆን ለደቡብ
ፖሊስ በሚጫወትበት ሰዓትም ተስፋ ሰጪን እንቅስቃሴ በሊጉ በማሳየት ለብሔራዊ ቡድን እስከመመረጥ ደረጃም ላይ
ደርሶ ነበር፤ ዮናስ በርታን የሀትሪክ ዌብሳይት ማኔጂንግ ኤዲተር ሙሴ ግርማይ ዘ ቢግ ኢንተርቪው በሚለው ዓምድ ላይ የተለያዩ
ጥያቄዎችን አንስቶለት የሰጠው ምላሽ የሚከተለውን ይመስላል፡


የእግር ኳስ ጨዋታ አጀማመሩ እና ስለተጫወተባቸው ክለቦች፡-

“የእግር ኳስን ለመጀመሪያ ጊዜ መጫወት የጀመርኩት ፓሪስ ለሚባል የቸርች ቡድን ነው፤ ከዛም ለአገራችን የተለያዩ
ትላልቅ ቡድኖች በርካታ ተጨዋቾችን ላፈራው የአክረምና ልጆቹ የፕሮጀክት ቡድን ውስጥ ገብቼ ለመሰልጠንና
ለመጫወት ቻልኩ፤ ይሄ ፕሮጀክት ያኔ በመስራቹና በባለቤቱ አክረም ሲቋቋም በኳሱ ምንም አይነት ገቢን የሚያገኝ
አልነበረምና ለእኛ ሲል ነው ቡድኑን መስርቶ ለወደፊቱ ጥሩ ደረጃ ላይ እንድንደርስ በማሰብ እንድንጫወት ያደረገን፤
ከእዚህ ፕሮጀክት እኔን ጨምሮ እንደ እነ አንዳርጋቸው ይላቅ /ማቲ/፣ ሳሙኤል ወንድሙ፣ አስናቀ ሞገስ /ጀበና/፣
ሄኖክ ካሳ እና እንዳለ ደባልቄን /ካክሽ/ የመሳሰሉ ለቅ/ጊዮርጊስ፣ ለኢትዮጵያ ቡናና ለደደቢት የሚጫወቱ
ተጨዋቾችን ጭምር ያፈራ ነበርና በእዛ ውስጥ ተጫውቼ በማለፌ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ከፕሮጀክት ተጨዋችነቴ በኋላ
ደግሞ በክለብ ደረጃ በመግባት6 ለመጀመሪያ ጊዜ የተጫወትኩት በአሰልጣኝ ዓለምሰገድ አንቼ እና በአለባቸው
ወደሚመራው የባንክ ተተኪ /የታዳጊ ተስፋ/ ቡድን ነው፤ በክለቡ ቆይታዬ ጥሩ እንቀሳቀስም ነበርና በአሰልጣኝ ውበቱ
አባተ የኃላፊነት ዘመን ወደ ዋናው ቡድን ለማደግ ብችልም ዝግጅት ብሄድም የመጫወት እድል ካለማግኘት ጋር ተያይዞ
ወደ ለገጣፎ ለገዳዲ ቡድን ላመራ ቻልኩ፤ ያኔ ቡድኑ በአሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ /ድሬ/ እና ዳዊት ሀብታሙ ድሬ ይመራ
ነበርና ጠንካራ ቡድን ኖሮን ከብሔራዊ ሊግ ወደ ከፍተኛው ሊግ /ሱፐር ሊግ/ ልንሸጋገር ቻልን፤ ከእዚህ ቡድን ቆይታዬ
በኋላ ደግሞ ሌላ የተጫወትኩባቸው ቡድኖች ባህር ዳር ከተማ፣ ደቡብ ፖሊስ፣ አዳማ ከተማ እና የአሁኑ ቡድኔ ወልዋሎ
አዲግራት ዩንቨርስቲ ሲሆኑ በእነዚህ ቡድኖች የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬም ባህርዳርን በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው
/ማንጎ/ የኃላፊነት ዘመን ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲገባ ያስቻልንበት ሁኔታ በደቡብ ፖሊስ ክለብ ቆይታዬ ደግሞ ለቡድኑ
ጥሩ ለመንቀሳቀስ ከመቻሌ በተጨማሪ ለብሔራዊ ቡድንም የተመረጥኩበት አጋጣሚ ስለነበር እነዚህ የማይረሱኝ
ናቸው”፡፡

በልጅነቱ አድንቆአቸው ስላለፋቸው ተጨዋቾች፡-

“ያኔ ሲጫወቱ የተመለከትኳቸው አስራት መገርሳንና መስዑድ መሐመድን ነው፤ በአልማዝዬ ሜዳ ላይም ነው
ሲጫወቱ የተመለከትኳቸው በተለይ ደግሞ አስራትን ስለዚህም እነዚህ ተጨዋቾች ለእኔ አርአያዬ ናቸው”፡፡
በእግር ኳስ የግል ሽልማቶችን አግኝቶ እንደሆነ፡-
“በብሔራዊ ሊግ ደረጃ ለለገጣፎ ለገዳዲ ክለብ ስጫወት ቡድኑን ወደ ከፍተኛው ሊግ እንዲሸጋገር አድርገን ነበር፤ ያኔም
ክለቡ ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ በዓመቱ እንቅስቃሴ የተሻለ ብቃትን አሳይቷል በሚል የዓመቱ ኮከብ ተጨዋችነት
ሽልማትን ያገኘሁበት ጊዜ ለእኔ መቼም የማይረሳኝ ነው”፡፡
በእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኑ ከሁሉም በተሻለ ምርጥ ጊዜን ስላሳለፈበት ክለብ፡-
“በደቡብ ፖሊስ ክለብ ውስጥ ስጫወት የነበረው ነው ለእኔ ምርጡ ጊዜ፤ በተለይ ደግሞ ከቡናና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር
ስንጫወት ብቃቴን በሚገባ አውጥቼ ተጫውቻለው፤ ቡና ላይም ግብ አስቆጥሬያለው፤ ከዛ ባሻገርም ከእዚሁ ክለብ
ለብሔራዊ ቡድንም የተመረጥኩበት ጊዜም ስለነበር ደቡብ ፖሊስ ምርጡን የጨዋታ ጊዜ ያሳለፍኩበት ቡድኔ ነው”፡፡
በወልዋሎ አዲግራት ክለብ ውስጥ በአሁን ሰዓት ስላለው ቆይታ፡-
“በአዳማ ከተማ የመጫወት ዕድልን ካለማግኘት ጋር ተያይዞ የውድድር ዘመኑ አጋማሽ ላይ የተዘዋወርኩበት የወልዋሎ
አዲግራት ቡድን ለእኔ ጥሩ የጨዋታ አጀማመርን ያሳየሁበት ነበር፤ በተሰለፍኩበት ሁለት ጨዋታዎችም ጥሩ ብቃቴን
ለማሳየትም ችዬ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን የኮቪድ መግባት ውድድሩን ሊያቋርጠው በመቻሉ ከዛ በላይ ለመጓዝ
አልቻልኩም”፡፡

በወልዋሎ አዲግራት ክለብ ውስጥ ይቀጥል እንደሆነ፡-

“በክለቡ ቀሪ ውል አለኝ፤ ስለመቀጠሌና አለመቀጠሌ ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው”፡፡
ወልዋሎ አዲግራት ሊጉ በኮቪድ ባይቋረጥ እስከምን ደረጃ ይጓዝ ነበር?
“ይሄን ቡድን አሰልጣኝ ዘማሪያም ከያዘው በኋላ ጥሩ መሻሻል እያሳየ ነበር፤ ሊጉ ባይቋረጥ ኖሮ ውድድራችንን ጥሩ
በሚባል ውጤት የምናጠናቅቅበት እድሉ ነበረን”፡፡

እግር ኳስ ተጨዋች ባይሆን ኖሮ፡-

“የእግር ኳስ ተጨዋች ባልሆን ኖሮ የምሆነው አካውንታንት ነበር፤ ምክንያቱም ከኳሱ ጎን ለጎን ያኔ ትምህርቴን
በእንጦጦ /ቲ. ኤም.ኤስ/ ት/ቤት የ3ኛ ዓመት ተማሪ ነበርኩና በኳሱ ምክንያት ልመርቅ አንድ ዓመት ሲቀረኝ ነው
ዊዝድሮ አድርጌ ላቋርጥ የቻልኩትና ይህን ትምህርቴን መቀጠሌ አይቀርም”፡፡
በተቃራኒ ሆኖ ሲገጥምህ ያስቸገረህ እና የፈተነህ ተጨዋች፡-
“እኔ በምጫወትበት ቦታ ማንም የለም፤ ያም ሆኖ ግን የቅ/ጊዮርጊሱ አስቻለው ታመነን በቦታዬ ላይ ባይጫወትም
ሁሌም ስመለከተው ለሌሎች የአገራችን ሁሉም ተጨዋቾች ፈታኝ የሆነበትን ነገር ልመሰክርለት እችላለሁ”፡፡

በአጨዋወቱ የሚያዝናናህ ተጨዋች፡-

“የቅ/ጊዮርጊሱ አስቻለው ታመነና በግብፅ ሊግ የሚጫወተው ሽመልስ በቀለ እነዚህን ተጨዋቾች ሜዳ ላይ
በሚያሳዩት እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ጊዜ ሳያቸው የኳስ ስሜቴን ይገዙታል”፡፡
በጨዋታ ዘመንህ ከሜዳ ተቀይረሀ ስትወጣ የተናዳጅነት ባህሪህ ይታይበት እንደሆነ፡-
“የተናደድኩበት አጋጣሚ እንኳን ፈፅሞ የለም፤ እንዲህ ያለ ባህሪህም እንዲኖረኝም አልፈልግም፤ ምክንያቱም እኔ
ተቀይሬ በምወጣ ሰዓት ወደሜዳ በሚገባው ተጨዋች ላይ ተገቢ ያልሆነ የስነ-ልቦና /ሳይኮሎጂ/ ሁኔታዎችን
ልፈጥርበት አልፈልግምና ለእዛም ስል ሁሌም ተቀይሬ ስወጣም ሆነ ወደ ሜዳ ተቀይሬ ስገባ ደስ ብሎኝና ተመሳሳይ
ባህሪህንም አሳይቼ ነው መጫወትን ምርጫዬ ሳደርግ የቆየሁት”፡፡

ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች ከቅ/ጊዮርጊስ እና ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሲጫወቱ ያለ የሌለ አቅማቸውን አውጥተው
ለመጫወት ይሞክራሉ ስለመባሉ፡-

“የእውነት ነው፤ይህን እኔም በተቃራኒ ተጫውቼ አይቼዋለሁ፤ በዛ ደረጃ ስጫወትም ጥሩ ሆኜም ነው ግጥሚያውን
ያሳለፍኩት፤ በተለይ ለደቡብ ፖሊስ በተጫወትኩበት ሰዓት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ስንጫወት በእነሱ ላይ ምርጥ ጎል
ከማስቆጠር ባሻገር ስኬታማ የሚባል እንቅስቃሴንም ለማሳየት ችያለው፤ ሌላው ከቅ/ጊዮርጊስ ጋርም ባደረግነው
ጨዋታም ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን ለማሳየት የቻልኩበት አጋጣሚ ስለነበር እነዛ ጨዋታዎች የማይረሱኝ ናቸው፤ ያም
ቢሆን ግን እንደ አንድ እግር ኳስ ተጨዋች ይህን ስመለከት ለሁለቱ ቡድኖች ብቻ ተዘጋጅቶ መምጣት ጥሩ አይደለምና
ሁሉም ተጨዋች ለሁሉም ቡድኖች ነው በተመሳሳይ መልኩ ተዘጋጅቶ ሊመጣና ጥሩ ሊጫወትም የሚገባው”፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እስካሁን በስሙ የተመዘገበ ጎል አንድ ብቻ ስለመሆኑ፡-
“በፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎዬ አዎን አንድ ጎል ብቻ ነው የመሀል ሜዳ ተጨዋች ሆኜ ያስቆጠርኩት፤ እሷም ግብ
በኢትዮጵያ ቡና ላይ ያገባዋት ነበረች፤ በተጨዋችነት ዘመኔ ከዛ በፊት ግን ተደጋጋሚ ጎል ያስቆጠርኩት ለባንክ ተስፋ
ቡድን በምጫወትበት ሰዓት ነበርና አሁን ላይ በፕሪምየር ሊጉ የጨዋታ ዘመን ተሳትፎዬ በጎል ማስቆጠሩ ላይ ያለብኝን
ክፍተት በማስተካከል ሌሎች ተጨማሪ ግቦችን የማስቆጥርበት ጊዜ ሩቅ አይደለም”፡፡

ከአፍሪካ አህጉር በፕሮፌሽናልነት ወደ አገራችን የሚመጡት ተጨዋቾች ከእኛዎቹ በችሎታ ይሻሉ እንደሆነ፡-

“በጭራሽ አይሻሉም፤ አብዛኛዎቹ አሰልጣኞቻችንም አሁን ላይ ከፍተኛ ትኩረት አድርገው ሊሰሩና ሊንቀሳቀሱበትም
የሚገባቸው ነገር ቢኖር የእኛ ልጆች ላይ ስራ መስራት ነው”፡፡
በጨዋታ ዘመኑ ወደ ትልልቅ ቡድኖች ውስጥ ገብቶ ለመጫወት ሙከራን ስለማድረጉ፡-
“ወደ አዳማ ከተማ ምንም እንኳን የመጫወት ዕድሉ ብዙ ባይኖረኝም ይሄ ክለብ ትልቅ ከመሆኑ አንፃር ወደ እነሱ
አምርቼ ነበር፤ ከዛ ውጪ ኢትዮጵያ ቡናም ጋር በአንድ ወቅት ለመግባት ንግግር ብናደርግም ያ ሳይሳካ ቀርቷልና እነዚህ
ናቸው የገጠሙኝ”፡፡

በጨዋታ ዘመኑ የእሱ ምርጥ አሰልጣኝ፡-

“በደቡብ ፖሊስ ክለብ ውስጥ ስጫወት ምርጥ የጨዋታ ጊዜን አሳልፌ ነበር፤ አሰልጣኛችን ገብረክርስቶስ ቢራራም
እኔን በብዙ ነገሮች ቀይሮኝ ነበርና ለእኔ ምርጡ አሰልጣኝ እሱ ነው፤ ከዛ ውጪ ሌላው ምርጡ አሰልጣኜ ደግሞ በሜዳ
ላይ ያለኝን እንቅስቃሴ ተመልክቶ ለብሔራዊ ቡድን የመረጠኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ነው”፡፡

ከእግር ኳስ ውጪ ሌላው መዋያው /ሆቢው/ ፡-

“አብዛኛውን ጊዜዬን በመተኛት ነው የማሳልፈው፤ ከዛ ውጪ መፅሐፍቶችን አነባለው፣ ከጓደኞቼ ጋር ፕሌይስቴሽን
እጫወታለው እንደዚሁም ደግሞ ወደ ቤተክርስቲያንም እሄዳለው፤ እነዚህ ነገሮች በጣም ያስደስቱኛል”፡፡
በተጨዋችነት የሚፈልገው ደረጃ ላይ ደርሶ እንደሆነ፡-
“የእግር ኳስ ጨዋታን መች ጀመርኩና! በኳስ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሰካል ልትባል የምትችለው በክለብ ደረጃ ብቻ
ስለተጫወትክ አይደለም፤ ለሀገርህ ብሔራዊ ቡድን ተመርጠህ ስታገለግልህና ከአንተ የሚጠበቅብህንም ጥቅም ስትሰጥ
ነው፤ ከዛ ውጪም በፕሮፌሽናል ደረጃም ወደ ውጪ ወጥተህ የመጫወት ዕድልንም የምታገኝ ከሆነ አንተ ትልቅ
ተጨዋች ነህና ይሄን ነው እኔ ለማሳካት የምፈልገው፤ ከዛ በተጨማሪም ከዚህ በፊት ወደ ነበርኩበት የብሔራዊ ቡድን
ዳግም መመረጥም እፈልጋለሁ፤ራሴን ለማሻሻልም ሁሌም ተግቼ እሰራለሁ”፡፡

በእግር ኳስ ጎድሎኛል ስለሚለው ክፍተቱ፡-

“ብዙ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፤እነዛ ደግሞ የአሰልጣኝ እና የራሴ ስራዎች ናቸው፤ ስለዚህም በኮቪድ 19 የተነሳ ብዙ
የእረፍት ወቅቶች ስለነበሩና አሁንም ደግሞ የአዲሱ የውድድር ዘመን ገና ስላልተጀመረ በእነዚህ ጊዜያቶች ውስጥ
ጠንካራ ልምምዶችን በመስራት እና እስከዛሬም የነበሩብኝን ድክመቶች በማሻሻል በ2013 ምርጥ ተጨዋች ለመባል
ከፍተኛ ጥረቶችን አደርጋለው”፡፡

ተጨዋቾች ለአሰልጣኞች ገንዘብ እየሰጡ ከክለብ ወደ ክለብ ይዘዋወራሉ፤ እንደዚሁም ተሰልፈውም ይጫወታሉ ስለመባሉ፤
አንተንስ ይህ ሁኔታ አጋጥሞህ ይሆን?፡-

“በጭራሽ አጋጥሞኝ አያውቅም፤ እንዲህ ያሉ ነገሮች ካሉም መቅረት ነው ያለባቸው፤ ማንም ተጨዋች ከክለብ ወደ
ክለብ ሊዘዋወር የሚገባውም ሆነ ሜዳ ገብቶ መጫወት ያለበት በችሎታው እና በችሎታውም ብቻ ነው፤ የእግር ኳስ
ጨዋታ እኮ አጋላጭ ነው፤ ሜዳውም ይኸው ፈረሱም ይኸው የሚባለው እኮ ያለምክንያት አይደለም፤ ሜዳ ገብተህ
ስትጫወት ያለ ችሎታ ከገባህ ህዝቡ ስለሚያይህ ትጋለጣለህ፤ ስለዚህም ጥሩ አቅም ኖሮህ እና ጥረህም ነው መጫወት
ያለብህና እኔ እንደዚህ አይነት ነገርን ሞክሬው አላውቅም፤ ልሞክረውም አልፈልግም”፡፡

የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ማህበር ተመስርቷል፤ በእዚህ ዙሪያ ምን አልክ? አባልስ ነህ?፡-

“አዎን አባል ነኝ፤ ማህበሩም አሁን ላይ ከሚገባው በላይ ጥሩ ነገርን እየሰራም ይገኛል፤ በተለይ ደግሞ ኤፍሬም
ወንድወሰን እና ፍፁም ገ/ማሪያም የተጨዋቾችን ችግር በቅርብ ስለሚያውቁ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ለማህበሩ እየሰሩ
ነው፤ በተለይ ክለቦች ባሳለፍነው ዓመት ለተጨዋቾች የበርካታ ወራትን ደመወዝ እና የጥቂት ወራትንም ደመወዝ

ሳይከፍሉ ቀርተው ነበርና እነሱ ከፍተኛ ግፊት በማድረጋቸው ክፍያው ሊፈፀም ችሏልና በእዚህ አጋጣሚ ለእነሱ አክብሮት
አለኝ፤ ምስጋናም ይገባቸዋል፤ እነዚህ ተጨዋቾች ትልቅ ኃላፊነትን /ሪስክ/ ወስደውም ነው እየሰሩ ያሉትና እኛም
ተጨዋቾች ከጎናቸው ሆነን ልናግዛቸው ይገባል”፡፡

ትዳርን መሰረትክ፡-

“አልመሰረትኩም፤ አሁን የምኖረው ከወላጅ እናቴ ጋር ነው፤ ትዳር የወደፊት እቅዴም ነው”፡፡

ስለ ትውልድ ሰፈሩ፡
“ቄራ ተወልጄ ያደግኩበት ነው፤ ምርጥ እና የአራዶችም የመኖሪያ ስፍራ ነው፤ ከዛ በተጨማሪ በርካታ የእግር ኳስ
ተጨዋቾችም ሆኑ በሌላ ሙያ ላይ ያሉ ታዋቂ ሰዎችንም ለማፍራት የቻለም ሰፈር ነውና በእዛ አካባቢ ተወልጄ በማደጌ
በጣም ደስተኛ ነኝ”፡፡

ስለ 2013ን አዲስ ዓመት ፡-

“የዘንድሮውን አዲስ ዓመት የተቀበልኩት በጣም በአማረ እና ጥሩ ነገርም ይመጣል በሚል የምኞት መልኩ
ነው፤ይህን ስልም ዓመቱ ዓለምን የረበሸው የኮሮና ቫይረስ ጠፍቶና በፖለቲካውም ሰላም ተፈጥሮ ፈጣሪ በቸርነቱ የደስታ
ጊዜንም ያሳየናል ብዬም በመመኘት ነው፤ ከዛ ውጪ ኮቪድ ጠፍቶም ወደምንወደው የእግር ኳስ ውድድራችንም
እንመለሳለን ብዬም አስባለው”፡፡

የ2013 እቅዱ፡-

“እንደ ፈጣሪ ፈቃድ ከሆነ በእዚህ ዓመት በዋናነት ያቀድኩት ነገር ቢኖር ከዚህ ቀደም ከነበረኝ ብቃት አኳያ በጣም
ተሻሽዬ በመቅረብ ምርጥ የሚባል የተጨዋችነትን ስም ማግኘት እና ሌላው እቅዴ ደግሞ ከምጫወትበት ቡድን ጋር
ሆኜ ጣፋጭ ድልን ለመጎናፀፍ መቻልና ለብሔራዊ ቡድንም ተመርጦ መጫወት ነው”፡፡

የመስቀል በዓል አከባበርን አስመልክቶ፡-

“የመስቀል በዓል በአገራችን ሁሌም ቢሆን ደማቅ እና በጉጉትም የሚጠበቅ ነው፤ ለዘመናት በአማረ መልኩም ነው
ሲከበር የቆየው፤ ይህን በዓል ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ቱሪስቶች ጭምርም ናቸው ሲያከብሩት የቆዩት፡፡ ይህን ካልኩ
በእኔ በኩል ስላለው የአከባበር ሁኔታ ደግሞ ልናገር የምፈልገው ቀኑ የተወለድኩበትና ልደቴም በመሆኑ ደስ በሚልና
በልዩ ሁኔታም ነው ቤተሰቦቼን፣ ጓደኞቼንና በቅርብ የማውቃቸውንም ሰዎች በመጥራት ፕሮግራም አዘጋጅቼ እኔም
ሆንኩ እነሱ ተደስተው በሚሄዱበት መልኩ ነው የማከብረውና በዓሉ ለእኔ ልዩ ትርጉም ነው ያለው”፡፡

በመጨረሻ፡-

“በእግር ኳስ ተጨዋችነት አሁን ለመጣሁበት መንገድ በቅድሚያ ፈጣሪዬን ከዛ በመቀጠል ደግሞ ቤተሰቦቼን በጣም
ነው የማመሰግናቸው፤ በተለይ ወላጅ እናቴና አባቴም ቢሆን በህይወት እስነበረበት ጊዜ ድረስ ለእኔ ያደረጉልኝን ከፍተኛ
አስተዋፅኦም የማልረሳው ነው፤ ስለ እናቴ ደግሞ ምን ብዬ እንደምነግርህ አላውቅም፤ብዙ ለፍታና ውጣ ውረዶችን አይታ
ያሳደገችኝ ስለሆነች ስለ እሷ ለማውራትም ቃላቶች ጭምር ናቸው የሚያጥሩኝ፤ ሌላው ልጠቅሳቸው የምፈልገው በእኛ
ቤተሰብ ውስጥ 11 ልጆች አለን፤ በጣም እንተጋገዛለን፤ ለእኔ እዚህ ደረጃ መድረስ ከእናቴና አባቴ ውጪ በባህር ማዶ
የሚገኙት ታምራት በርታ እና መቅደስ በርታ የስፖርት ትጥቆችን በመላክ ይረዱኝ ነበር፤ ሌሎቹ እዚህ ሀገር ያሉት ስዩም
በርታ እና ሰብስቤም ከእኔ ጎን በመሆንና ወደሌላም አልባሌ ስፍራዎች እንዳላመራም ይመክሩኝና ይንከባከቡኝ
ስለነበር በአጠቃላይም ቤተሰቦቼን ፈርቼ በጥሩ ሁኔታ እንዳድግም ስላደረጉኝ በጣም ላመሰግናቸው እወዳለሁኝ፤ ሌላው
ሳልጠቅሳቸው እና ሳላመሰግናቸው ማለፍን የማልፈልገው መካሪዎቼ ከነበሩት ውስጥ የቀድሞ እግር ኳስ ተጨዋች
ጌታቸው ካሳ /ቡቡ/ ቦቼን ብዙ ነገር በሌለኝ ሰዓት ከአጠገቤ የነበረውን ጓደኛዬን ቴዎድሮስ ሸዋአማረን አብሮ አደግ
ጓደኞቼን ሳሙኤል ወንድሙን፣ አንዳርጋቸው ይላቅን፣ የቀበሌ 10 ልጆችንና ከአሰልጣኞች ደግሞ ብዙ ነገሮችን እንዳሻሽል
ያደረገኝን የደቡብ ፖሊስ አሰልጣኝን ገብረክርስቶስ ቢራራን /ገብረየስ/ እና ለብሄራዊ ቡድን መርጦኝ የነበረውን
ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱን በፈጣሪ ስም ለማመስገን እፈልጋለሁ”፡፡


ስለ አባይ ግድብ

“የአባይ መገደብ ለእኛ ኢትዮጵያኖች የሚፈጥርልን ነገር በጣም ጥሩ ነው፤ በተለይ ደግሞ በመጪዎቹ 10 ዓመታት
በኢኮኖሚያችን ላይ ብዙ ለውጦች እንዲኖሩ እና እንዲፈጠሩም ስለሚያደርግ ሁላችንም ለእዚህ እልውናችን ከሆነው
ግድብ ጋር በጋራ አብረን ልንቆም ይገባል፤ ይሄን ግድብ በተመለከተም አሁን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር አብይ
መሐመድም እየሰሩ ያሉት በጎ ስራም የሚያበረታታም ነውና እሳቸውን በእዚህ አጋጣሚ ሳላመሰግን አላልፍም”፡፡

ስለ ኮቪድ 19

“የኮቪድ ወረርሽኝን በሚመለከት በእዚህ ሰዓት ብዙ ኢትዮጵያኖች በጣም ችላ ብለን ነው ያለነው፤ ፈጣሪ
ስለሚጠብቀን እንጂ በእዚህ የአኗኗር ዘይቤያችን እኛ ከአሜሪካ፣ ከጣሊያንና ከሌሎች ሀገሮች የተለየን አይደለምና
እናልቅም ነበር፤ ሆኖም ግን በእሱ ቸርነት አለን፤ ስለዚህም ከአሁን በኋላ ላሉት ወቅቶች አስፈላጊውን ጥንቃቄ
እያደረግን፤ እንደዚሁም ደግሞ በፆም በፀሎት ፈጣሪን እየለመንን ይህን በሽታ ከአገራችን ብቻ ሳይሆን ከዓለምም
እንዲጠፋልን ምኞቴ ነው”፡፡

Managing Editor at Hatricksport Website

FacebookTwitterGoogle+YouTube

ሙሴ ግርማይ

Managing Editor at Hatricksport Website