“ስም መጥቀስ ባልፈልግም በሁለት አሰልጣኞች ግን ነፃነቱ ተሰምቶኝ ነው የምጫወተው” አማኑኤል ገ/ሚካኤል (ብ/ቡድንና መቐለ 70 እንደርታ)

“ከኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር /አቡኪ/ ጋር በክለብ ደረጃ የፊት መስመር አብሬው
ብመራ ደስ ይለኛል”

“ስም መጥቀስ ባልፈልግም በሁለት አሰልጣኞች ግን ነፃነቱ ተሰምቶኝ ነው

የምጫወተው”

አማኑኤል ገ/ሚካኤል (ብ/ቡድንና መቐለ 70 እንደርታ)

 


በተጫወተባቸቸው አመታቶች ውጤታማ ነው ማለት ይቻላል፤ከዳሽን ቢ የተጀመረው ታሪኩ ዳሽን፣ ደብረ ብርሃን፣ መቐለ
70 እንደርታ በ8 አመታት የተጨዋችነት ዘመኑ የሚጠሩ ክለቦች ናቸው፡፡ በተለይ ባለፉት አመታት በመቐለ የነበረው
ቆይታ የውጤት ነው ማለት ይቻላል በ2009 ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደጉበት አመትን በዋንጫ ፈፅሟል፡፡ በ2010 ደግሞ
በመጀመሪያ የፕሪሚየር ሊግ ቆይታው 4ኛ ደረጃን ይዞ ቢያጠናቅቅም በ2011 ግን ደማቅ ታሪክ የፃፈበት አመት ሆኖ
አልፏል፤ በፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢነትን ክብር ሲቀዳጅ የሊጉን ዋንጫ በጎሎቹ የታገዘው መቐለ 70 እንደርታ
ነግሶበታል፡፡ “በ2012 ዋንጫውን የመድገም እድል ነበረን፣ ኮቪድ 19 አላሳካ አለን እንጂ” በማለት እንግዳችን
ይናገራል፡፡ በዋሊያዎቹ ተሰላፊነቱ በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱና በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስር ተጫውቷል፡፡ በአሰልጣኝ
አብርሃም ስር ኮትዲቯርን 1ለ0 በረታው ውጤታማ ቡድን ውስጥ አባል ነበር ባለፈው ማክሰኞ ኒጀርን 3ለ0 በረታው
የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድን ስር ተካቶ የመክፈቻ ግቡን ከመረብ አሳርፎ በእለቱ ቀኑ ሆኖ ሲከበርለት ለነበረው የሀገር
መከላከያ ሠራዊት ወታደራዊ ሰላምታ በመስጠት ከቡድን አባሎቹ ጋር ድጋፉን ገልጿል፡፡ ሀትሪክ ባገኘችው መረጃ
ከጨዋታው በፊት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሰያስ ጅራ “ድሉን ለመከላከያ ሠራዊታችን መታሰቢያ እናደርገዋለን”
ያሉትን ቃል ጠብቀው መታሰቢያነቱን ለመከላከያ ሰራዊት ሰጥተው በስታዲየም የነበሩትን ኢትዮጵያዊያንን
አስፈንጥዘዋል፡፡ እንግዳችን የመቐለ 70 እንዳርታ ወሳኝ አጥቂ አማኑኤል ገ/ሚካኤል በጁፒተር ሆቴል ከሀትሪኩ ዮሴፍ
ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ምላሹን ሰጥቷል፡፡


ሀትሪክ፡- ኒጀርን ባሸነፋችሁበት ምሽት ከባለቤትህ አርቲስት ሄለን ተክላይ ጋር ደስታህን እንዳጣጣምክ አውቃለሁና ምሽቱ
እንዴት ነበር?

አማኑኤል፡- በውጤት የታጀበው ምሽት ሲፈፅም ከጓደኞቼ ጋር ደስታውን አጣጥሜያለው፤ ከዚያ በኋላ ነው ከምወዳትና
ከማፈቅራት ባለቤቴ ሄለን ጋር ደስ በሚል አቀባበል ተቀብላኝ ምሽቴን የደስታ አድርገዋለች፡፡ ሁሌም ጥሩ ስትሰራ
የሚያደንቅህ አይጠፋም የርሷ ግን የተለየ ነበር፤ እንደሁሌው ነው በጥሩ ሁኔታ ተቀብላኝ ደስታችን ያጣጣምነው፤…
ለአቀባበሏና ላደረገኝችው ሁሉ ማመስገን እወዳለው፡፡

ሀትሪክ፡- ከርሷ ጋር ስላለህ ፍቅር አውራን?

አማኑኤል፡- ፍቅር ካለ ሁሉም ሞዴል ይሆናል ብዬ አስባለው ጥሩ ስነ-ምግባርና ፍቅር አለን፡፡ በጣም ነው የምወዳት
ትውውቃችን በጓዳኛዋ አማካይነት የተጀመረ ነበር መነሻው ያ ነው ደስ የሚል ፍቅር አለን፡፡

ሀትሪክ፡- በቁንጅና አልቦነሰችህም?

አማኑኤል፡- /ሳቅ በሳቅ/ በደንብ ነው የቦነሰችኝ /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- ከርሷ ጋር ወጣ ብላችሁ ስትዝናኑ ነፃነቱ አለህ…?

አማኑኤል፡- በነፃነት ነው የምንኖረው፤. በስነ-ምግባር ተሞልተንም ስለሆነ ከርሷ ጋር አሪፍ ነፃነት ይሰማኛል
ሁለታችንም ላይ ጫና የለም፡፡

ሀትሪክ፡-የሚያማምር የባህል ልብስ ለብሳችሁ አየሁ የባህል ልብስ ወዳጅ ነህ?

አማኑኤል፡- ብዙም አልነበርኩም እርሷ ግን በጥበቡ ዙሪያ ስላለችም ሞዴልነት ስለምትሰራ የሚያምረውን ታውቃለችና
ወደዚህ ህይወት መርታኛለች፡፡ አሁን ደግሞ አይቼው ሲያምር ወደ ሀገር ባህል ልብሱ ተስቤያለው፤በእርግጥ ሁሌ
ባይደረግም የአገር ባህል ልብሱ ተመችቶኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ አለባበስ ላይ ችግር የለብኝም፤ ሙሉ ሱፍም እለብሳለው
ቲሸርት በለው ጃኬት ይመቹኛል የምለብሰው ልብስ እንደቦታው ይወሰናል፡፡

ሀትሪክ፡- የመጀመሪያውን ግብ ካስቆጠርክ በኋላ ወታደራዊ ሰላምታ ሰጥተህ ለመከላከያ ሰራዊታችን ያለህን ፍቅር
ገልፀሃል.. እስቲ ስለ እርሱ አውራኝ?

አማኑኤል፡- ይሄ ጥያቄ ይለፈኝ /ሳቅ/ ቢዘለል ደስ ይለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ኒጀር ላይ ግብ ካስቆጠሩ 3 ተጨዋቾች መሃል አንዱ ነህ… ምን ተሰማህ?

አማኑኤል፡- በጣም ተደስቻለሁ፡፡ በምንችለው ሁሉ ስንጥር ነበር፡፡ በተለይ የተሰለፈው ሁሉ በቦታው ምርጥ አቋም
አሳይቷል፡፡ ድሉና ደስታው አልበረደልኝም ማለት እችላለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-ኒያሚ ላይ በኒጀር መሸነፋችሁ 3 ነጥብና 1 ሚሊዮን ብር ነው ያሣጣችሁ… ተነጋገራችሁበት?

አማኑኤል፡-አዎ ተነጋግረንበታል.. ያው ለጨዋታ ሲገባ አቻ ማሸነፍና መሸነፍ አይቀርም ዋናው ነገር ከስህተታችን
ተምረን በሜዳችን ማሸነፍ መቻላችን ነው፡፡ የማለፍ እድላችንን የምንወስነው ራሳችን በመሆኑ በቀጣይ ያሉት
ግጥሚያዎችን ለማሸነፍ የምንችለውን እናደርጋለን፡፡

ሀትሪክ፡-ኮትዲቯርን ለማሸነፍ ግን ጠንካራ የቤት ስራ ይጠብቀናል አይደል?

አማኑኤል፡- እውነት ነው ከባድ የቤት ስራ ይጠብቀናል፤ አይቬሪኮስት ስለሆነ ብቻ ባይሆን ሁሌም ከሜዳ ውጪ
ስትጫወት በተለይ በአፍሪካ አገራት ግጥሚያው ይከብዳል፤ ለኮትዲቯር እኛም ተዘጋጅተን ስለምንሄድ ይከብዱናል ብዬ
አልሰጋም፤ በግልም በቡድንም ሰርተን ተዘጋጅተን እንሄዳለን፡፡ ግጥሚያው ይህን ያህል አይከብድም፡፡

ሀትሪክ፡- በክለብ ደረጃ አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ፣ በብሄራዊ ቡድን ደግሞ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱና አሰልጣኝ
ውበቱ አባተ አሰልጥነውሃል… በሶስቱ መሀል ያለው ልዩነት ምንድነው? ማነው ምርጡስ?

አማኑኤል፡- በሶስቱም አሰልጣኞች ተጠቅሜያለው ሁሉም በቦታዬ ነው የሚሞክሩኝ በእነሱ የተሻለ ነገር አግኝቻለሁ፤
አሰልጣኝ ከአሰልጣኝ ማወዳደር ግን አልፈልግም ስም ባልጠቅስም ግን በሁለት አሰልጣኞች ነፃነት ተስምቶኝ ነው
የምጫወተው፤ የኛ ሀገር ሁኔታ ይታወቃልኮ /ሳቅ/ በኛ ስራ ትንሽ ከበድ ይላል ለዚያ ነው የማልናገረው፡፡

ሀትሪክ፡- የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎችን የምትላቸው ነገር አለ?

አማኑኤል፡- የመቐለ ደጋፊዎቻችንማ እኔም ባልናገር ማንም የሚያውቀው ነው፤ አንዳንዴ ስሜትህን መግለፅ ይከብዳል
4 አመት ሙሉ ሳውቃቸው በሜዳና ከሜዳ ውጪ ስጫወት ለኔ ያላቸው ስሜት በግልም ስለማውቀው አንድ ነገር ብቻ
ማለት እፈልጋለው… ያው እኔን እንዳከበራችሁ እግዚአብሔር ያክብርልኝ ነው የምለው፡፡

ሀትሪክ፡- በ8 አመት ውስጥ አላሳካሁትም የምትለው ነገር አለ?

አማኑኤል፡-አላሳካሁም ብዬ ቅር የምሰኝበት ጉዳይ የለም፡፡ እንደ አጥቂነቱ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኛለሁ እንደ አሸናፊነት
የሊጉን ዋንጫ አንስቻለው ቅር የሚለኝ ነገር የለም የምለው ለዚህ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የውጪ እድልስ አልተገኘም? ተገኝቶ አልተሳካም? አማኑኤል የቱ ጋር ነው?

አማኑኤል፡-ከሀገር ወጥቶ ለመጫወት የሚያስችል እድሎችን አግኝቻለሁ የተሻለ ነገር ስላልሆነ ነው የቀረሁት ፕሮፌሽናል
ለመባል ብቻ መሄድ አልፈልግም ህይወቴ ላይ ለውጥ የሚያመጣ ካልሆነ ምን ያደርጋል፡፡ በተረፈ ግን ብዙ ዕድሎች
አሁንም ድረስ አሉ፡፡

ሀትሪክ፡- አብሬው ብጫወት ደስ ይለኛል የምትለው ተጨዋች አለ?

አማኑኤል፡- /ሳቅ/ አላውቅም፡፡ በብሄራዊ ቡድን አብሬያቸው ስለተጫወትኩ ይሁን ብዙም አብሬያቸው የመጫወት
ጉጉት ያሳደረብኝ የለም፡፡ ግን ከኢትዮጵያ ቡና አቡበከር ናስር /አቡኪ/ ጋር በክለብ ደረጃ የፊት መስመር አብሬው
ብመራ ደስ ይለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- በግጥሚያው ውስጥ ችግር የሚፈጥርብህ ተከላካይ አለ?

አማኑኤል፡- ማንም የለም፡፡ በተለየ መንገድ አይቼው የምጠራው ተከላካይ የለም፤ ነገር ግን ሁሉም ተከላካይ ጋር
ፍልሚያ አለ፡፡ በየክለቡ ብትሄድ ይሄን ተጨዋቾች ያዙ እንዳይጫወት ጠብቁት መባሉ ስለማይቀር ሁሉም ጋር ፍልሚያ
አደርጋለሁ፡፡ በተለየ መንገድ የምጠራው ግን የለም፡፡

ሀትሪክ፡- የኮሮና ቫይረስ ተከስቶ እግር ኳስ በተቋረጠባቸው 7 ወራት አማኑኤል ምን እያደረገ ቆየ?

አማኑኤል፡- የተወሰነ ጊዜ አርፌያለሁ፡፡ መቐለ 7ዐ እንደርታ ከገባው ጀምሮ ያለ በቂ እረፍት እጫወት ስለነበር ማረፍን
መርጫለሁ፡፡ ከባለቤቴና ከቤተሰብ ጋር ጊዜ የመውሰድ ዕድሉ ነበረኝ፡፡ ቤት ሆኜ ከባለቤቴ ጋር ስፖርት እሰራ ነበር፤
ጂምም የመስራት እድሉ ነበረኝ፤ ቅዳሜና እሁድም አስፋልት ላይ እሮጥ እንዲሁም ከሰፈር ልጆች ጋር ኳስ እጫወት
ነበር፡፡ ከዚያ ውጪ አዲስ ዓመትንና መስቀልን ከቤተሰብ ጋር አክብሬያለሁ፡፡ አልፎ አልፎ የመስቀል በዓልን አስፈቅጄ
አከብር ነበር፡፡በአጠቃላይ የሰባት ወሩ ጉዞ ይሄን ይመስል ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- ከመቐለ 7ዐ እንደርታ የቡድን አባላት ጋር ግንኙነቱ አለህ?

አማኑኤል፡- አሁን ምንም የለኝም፡፡ ሙሉ ለሙሉ ፊቴን ወደ ብሄራዊ ቡድኑ በማዞሬ ላገኛቸው አልቻልኩም፡፡ ከክለቡ
ጋር ያለኝ ውል ዘንድሮ ነው የሚጠናቀቀውና በቀጣይ ምን ይሆናል የሚለውን እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው፡፡
እስከዚያው ባለቤቴ ጋር እዚሁ ሆኜ ያለውን ነገር እከታተላለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ተወልደህ ያደከው መተማ ነው.. ስለመተማ የምትለው ነገር አለ?

አማኑኤል፡- የመተማን እውነት ማወቅ ደስ ይላል፡፡ የታሪክ ቦታም በመሆን ትታወቃለች፡፡ አፄ ዮሐንስ የወደቁበት ቦታ
ናት፡፡ በሀገር ታሪክ ውስጥም ልዩ ቦታ አላት፡፡ የንግድና የጠረፍ ቦታ በመሆንም ትታወቃለች፡፡

ሀትሪክ፡- መቐለ ጦርነት ላይ ነች፡፡ እንደ ኳስ ተጨዋችነትህ የምትለው ነገር አለ?

አማኑኤል፡- ጦርነት ለማንም ጠቃሚ እንዳልሆነ ሁለቱም ወገኖች ያውቁታል፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ ጦርነቱ እርስ በርስ
መሆኑ በጣም ያስጠላል፡፡ ጦርነቱ ቀርቶ ወደ ድሮ ሠላማችን ብንመለስ ደስ ይለኛል፡፡ በይቅርታ ወደ ሰላም ቢመጡ ደስ
ይለኛል፡፡ ሰላም ከሌለ ማንም ሠርቶ መግባት አይችልም፡፡ የጦርነት ጥፋት ለሀገር ነውና ጦርነቱ ቀርቶ በይቅርታ ወደ
አንድነት ወደ ኢትዮጵያዊነት ቢመለሱ ደስ ይለኛል፤ ይሄ የኔም የሕብረተሰቡም ስሜት ይመስለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ጨርሻለሁ… የመጨረሻ ቃል ካለህ?

አማኑኤል፡- ለዚህ ያደረሰኝን እግዚብሔርን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ የቅድሚያ ምስጋናዬ ይድረሰው፡፡ ከእሱ በመቀጠል
በጣም የምወዳትና የማፈቅራት ባለቤቴ አርቲስት ሄለን ተክላይን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ በተለይ በኮሮና ጅማሮ ጊዜ
ከጎኔ ስለነበረች ማመስገንና እንደማፈቅራት መናገር እወዳለሁ፡፡ መላው ቤተሰቦቼ፣ ጓደኞቼ፣ ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች፣
የመቐሌ 70 እንደርታ ደጋፊዎችና በአጠቃላይ መላው የኢትዮጵያን ሕዝብ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡


ስለ ኮሮና

አዲስ ነገር አይደለም ይታወቃል… ቀላል በሽታ ነው ብለን ነው የተረዳነው፡፡ ግን ሁላችንም ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡
ለማንኛውም በሽታኮ ጥንቃቄ እናደርጋለን፡፡ ይሄም በተለየ ጥንቃቄ መታየት አለበት፡፡ ጥንቃቄ ሳይጎድል ስራችንን
ብንሰራ ጥሩ ነው፡፡ የሕክምና ባለሙያዎችን ምክር መቀበል በራሱ ጥሩ ይመስለኛል፡፡

ስለ አባይ ግድብ

በጣም ተደስቻለሁ፡፡ ከረጅም ዓመታት ልፋት በኋላ ተሳክቶ በማየታችን ደስ ብሎኛል፡፡ በኢትዮጵያዊነቴም ኮርቻለሁ፡፡
ከምነግርህ በላይ ተደስቻለሁ፡፡ ጫና እያለም ቢሆን ይህን ታሪክ መሠራቱ ያስደስታል፡፡ የሀገር ለውጥ ነው፡፡ እስከመቼ
አባይ አባይ እያልን እንዘምራለን፡፡ አሁን ደግሞ ሀገራችን ገብቶ ስናየው እንዲሁም በሕብረተሰቡ ተጠቃሚነት ልንደሰት
ይገባል፡፡ ሕብረተሰቡ እስከመጨረሻው ድጋፍ ሊሰጥ ይገባል እላለሁ፡፡ ግዴታም ነው ጥቅሙም ለእኛ መሆኑን መገንዘብ
አለብን፡፡ እስኪፈፀም ድረስ የምንችለውን እናድርግ፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport