“የአቡበከር አስናደቂ አቋም አስደንግጦኛል፤ ኮከብነቱን በማግኘቱ አልከፋም” ሀብታሙ ተከስተ /ፋሲል ከነማ/

“ዘንድሮ ለፍተናል ደክመናል ዋንጫው ይገባናል ይሄ እውነት ነው ከዚያ ውጪ ብዙዎች ለፍተዋል ጥረዋል ግን ከነበረን ርቀት አንፃር የተሻልን መሆናችን ታይቷል፡፡”

“ምናልባት ጥሩ የተፎካከረው ኢትዮጵያ ቡና ሊወስድ ቢችል ይመጥናል አጨዋወታቸውም ማራኪ ነው፡፡”

“የአቡበከር አስናደቂ አቋም አስደንግጦኛል፤ ኮከብነቱን በማግኘቱ አልከፋም”
ሀብታሙ ተከስተ /ፋሲል ከነማ/


ለዳሽን ቢ፣ ለደብረብርሃን፣ ለመቐለ 7ዐ እንደርታ ተሰልፎ ተጫውቶ አሁን በዋንጫ ድል አመቱን በስኬት ላጠናቀቀው ፋሲል ከነማ የመሀል ሜዳ ማገር ሆኖ እየገለገለ ነው፡፡ መቐለ 7ዐ እንደርታ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ሲያድግና ባደገበት አመት 4ኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ የዚህ ታጋይ ግልጋሎት ነበረበት አሁን ደግሞ ወደ ኮከብነት በማደግ የ2ዐ13 የአመቱ ኮከብ ተጨዋች ለመባል እድል ካላቸው ሁለት ተጨዋቾች መሀል አንዱ ነው፡፡ የጎንደርዋ ብሉኮ መንገደር አምባሳደር የሆነው የፋሲል ከነማ አይነኬ ተጨዋች ሀብታሙ ተከሰተ ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ያደረገው ቆይታ ይህን ይመስላል፡፡

ሀትሪክ፡- ከቡድኑ ቀድመህ ባህርዳር ገብተሃልና ህብረተሰቡ እንዴት ተቀበለህ…?

ሀብታሙ፡- ቀድመን ወደ ባህርዳር የገባነው እኔ ሙጅብ፣ ያሬድና አምሳሉ /ሣኛ/ ነበርን ስንገባ ላዳ የሚነዱ ሹፌሮች ጋር ስገናኝ በቃ ደስተኛ ናቸው ነገ ባህርዳር ላይ ዝግጅት አለ ባህርዳር ላይ እንዲህ ከሆነ ጎንደር ላይ የሚኖረው ምን ይሆን እያልኩ እንዳስብ ነው ያደረጉኝ፡፡ /ቃለ ምልልሱን ያደረግነው ሀሙስ ምሽት ነው/ ሙሉ ቡድኑ ባህርዳር ጠዋት ሲደርሱ የሞቀ አቀባበል በጋራ ይደረጋል የክልሉ መንግሥት የራት ግብዣ አዘጋጅቷል፡፡

📸 ©Alex Picture

ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ ዋንጫውን ባያነሳ ሌላ ሊወስድ ይገባዋል የምትለው ክለብ አለ?

ሀብታሙ፡-ዘንድሮ ለፍተናል ደክመናል ዋንጫው ይገባናል ይሄ እውነት ነው ከዚያ ውጪ ብዙዎች ለፍተዋል ጥረዋል ግን ከነበረን ርቀት አንፃር የተሻልን መሆናችን ታይቷል፡፡ ምናልባት ጥሩ የተፎካከረው ኢትዮጵያ ቡና ሊወስድ ቢችል ይመጥናል አጨዋወታቸውም ማራኪ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የአመቱ ኮከብ የሚያስብለኝን ብቃት አሳይቻለሁ ብለህ ታምናለህ…?

ሀብታሙ፡- የለፋሁትና የሰራሁት ለቡድኑ ነው የምችለውን አድርገያለሁ ከኔ የተሻለ አስተዋፅኦ ያደረጉ ተጨዋቾችም በቡድኑ ውስጥ አሉና የእኔ ብቻ ነው ብዬ አላስብም ኮከብ ተብዬ ብመረጥ ደስ ይለኛል ባልመረጥም ጥሩ ተጨዋቾችን ስለያዝን እነርሱ ቢመረጡ አልከፋም፡፡

ሀትሪክ፡- በጣም ዲፕሎማት እየሆንክ ነው…?

ሀብታሙ፡- /ሳቅ በሳቅ/ ኧረ አይደለም እውነቴን ነውኮ

ሀትሪክ፡- ለኮከብነት የታጫችሁት በይበልጥ አንተና አቡበከር ናስር ናችሁ… ከሁለታችሁ አይወጣም እየተባለ ነው እዚህ ላይስ ምን ትላለህ..?

ሀብታሙ፡-ያሬድ ባዬስ…? ጠንካራ ተፎካከሪ ነው እሱም እድል አለውኮ

ሀትሪክ፡- ቀንደኛ ተፎካካሪ የሆነውን አቡበከር ናስር እንዴት አገኘኸው..?

ሀብታሙ፡- የአቡበከር የዘንድሮ ብቃቱ አስደግጦኛል የሚገርም ነው መስከረም ላይ ለብሔራዊ ቡድን ተጠርተን አግኝቼዋለው ተቃራኒ ሆነንም ተፋልመናል በጣም የሚገርም ነው ክህሎቱ… አስተሳሰቡ ልዩ ነው… የዘንድሮ ብቃቱ አስገርሞኛልና አድናቂው ሆኛለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- አቡበከር ናስር ኮከብ ተጨዋች ተብሎ ቢመረጥ ትቀበለዋለህ…?

ሀብታሙ፡- በደንብ እንጂ… እድሜ ለዲ.ኤስ.ቲቪ ሁሉን ነገር እያየን ነው አቡበከር ኮከብነቱን ቢወስደውም ይገባዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ግቦች አብዛኞች የርሱ ናቸው ምርጥ አቋሙን አሳይቷል ከነርሱ ጋር ስንጫወት የነበረው ጨዋታ ላይ አስቸግሮናል እና ጓደኛዬ ጭምር ነው ኮከብነቱን ቢወስድ ቅር አልሰኝም ስለ እውነት ለመናገር የአቡበከር አስደናቂ አቋም አስደንግጦኛል ኮከብነቱን በማግኘቱ አልከፋም፡፡

ሀትሪክ፡- ከቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ጋር የነበራችሁ የደርሶ መልስ ጨዋታን እንዴት ገመገምከው…?

ሀብታሙ፡- አዲስ አበባ ላይ የመጀመሪያውን ጨዋታ ያደረግነው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነው… እነርሱ ምንም ጨዋታ አላደረጉም እኛ ግን የውጪ ጨዋታ አድርገን ነበር የገባነው ያ ረድቶን ጨዋታውን በሙጅብ ግብ ማሸነፍ ችለናል ያቺ ግብ የሊጉ የመጀመሪያ ግብ ሆና ተቆጥራለች ቀጥሎ ቡናን ስንገጥም እኔን ብቻ አይደለም በቀይ ወጥባቸው በጎዶሎ ተጫውተው ማሸነፋቸው ብዙውን የፋሲል አባላት አበሳጭቷል ስሜታችንን ጎድቶናል፡፡

ሀትሪክ፡- ይሄ ሽንፈት ነው ለዋንጫ ጉዞ አንድ ብለን እንድንጀምር ያደረገን የሚሉ ተጨዋቾች አሉ…. እውነት ነው?

ሀብታሙ፡- ትክክል… በጎዶሎ ልጅ ሲያሸንፉን ቁጭ ብለን ተወያየን ተነጋግረን በአመራር ደረጃም ሆነ በተጨዋች ደረጃ ቈጭ ብለን አወራን ያ ነው ችግራችንን ፈትተን አይተን መከረን ወጣን…የቡና ሽንፈት ለአሁኑ ዋንጫ መነሻ ሆኖናል ጠንክረን ሠራን ከዚያ ውጭ ባህርዳር ላይ ጊዮርጊስን አግኝተን ፈታኝ በሆነ ጨዋታ አቻ ስናስብ ባለቀ ሰዓት በሪጎሬ አሸንፈን ጣፋጭ ድል ተቀዳጀን… በእውነት ደስ ያለኝ ውጤት ይሄ ነው በቀይ ወጥቶባቸው እንዴት አሸነፉን የሚለውን ቁጭት ተወጣን በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡ የዋንጫ እድላችን ከ5ዐ በመቶ በላይ ከፍ ማለቱን ያረጋገጥነው ያኔ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ሰበታ ከተማን ማሸነፍ ግን አልቻላችሁም የአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ቡድን ከበዳችሁ እንዴ…?

ሀብታሙ፡- ሰበታ ከተማ ካየኋቸውና ካስገረሙኝ ቡድኖች መሀል አንዱ ነው… ባህርዳር ላይ 1ለ1 ነው የተለያየነው… ያኔም ከብደውናል ጠንካራ ተፋላሚ ነበሩ አቻ መውጣታቸው ጥሩ እንደነበሩ ያሳያል ዛሬ ግን ብዙዎቹ ከጨዋታ የራቁና አዲሶች ከታች የመጡ ናቸውና ዐለዐ መለያየታቸው አልገረመኝም እንዲያውም ሰበታ ባለማሸነፉ የኛን ልጆች እንዳደንቅ አድርጎኛል፡፡ አሰላለፉን ስታይ ከጨዋታ የራቁ ናቸው ከጨዋታ ስታርቅ የጨዋታ አቅምና በራስ መተማመንህ ይርቅሃል ይሄ ችግር ሳይኖርባቸው አቻ መውጣታቸው የኛ ልጆችን ማበረታታት ይገባል፡፡

ሀትሪክ፡- ከባህርዳር ከተማ ጋር 2ለ2 ስትለያዩ እነርሱም በጎዶሎ ልጅ ነው የተጫወቱትና ይሄ ጎደሎ ቡድን ሲገጥማችሁ መቸገራችሁ ምንድነው..?

ሀብታሙ፡-/ሳቅ/ በኛ ቡድን ላይ የተቃራኒ ቡድን ተጨዋቾች በቀይ መውጣት ሲታይ የማሸነፍ የፉክክር መንፈሳችን አብሮ ይወርዳል ግን በጣም ተቆጭተናል ያውም ደርቢ ነው አሸንፈን የበላይ መሆናችንን ማረጋገጥ ፈልገን ባለመሳካቱ ተናደድን ድሬደዋ ላይም ዐለዐ ነው የወጣነው

ሀትሪክ፡- ይሄ ጨዋታ ላይ ባህርዳር ከተማ ሪጎሬ ተከልክሏል ታዲያ ከሽንፈት አልተረፋችሁም..?

ሀብታሙ፡- የፍፁም ቅጣት ምት ነው የሚሉ ሰዎች አሉ… በድጋሚ ክስተቱን አላየሁትምና ትክክለኛ ምስክር መሆን አልችልም፡፡

ሀትሪክ፡- ተወልደህ ያደከው ጎንደር በተለምዶ ብሉኮ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው… እዚያ ማንን እያየህ አደክ…?

ሀብታሙ፡- ጎንደር ላይ ከታች ስመጣ ለፋሲል ከነማ የሚጫወቱ አድነው እና ተመስገን የሚባሉ ተጨዋቾች ነበሩ ወደ ሜዳ ሲሄዱ አይ ነበርና እነርሱን እያየሁ አድጌያለሁ በጣም ታዋቂ አይደሉም ለብሔራዊ ቡድን ሲጫወቱም አላየኋቸውም ግን መነሳሳት ፈጥረውብኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ጥሩ ተፎካከሪ ይሆናሉ ብለህ አቋማቸው ወርዶ ያገኘኃቸው እነማን ናቸው…?

ሀብታሙ፡ በዚህ መልኩ በአጠቃላይ እንደ ሊግ እንደጠበኩት ያልሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው፡፡ ሁለትና ሶስት አመት ዋንጫ ስላልወሰዱ ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ብዬ ጠብቄ እንዳሰብኩት አልሆኑም ሌላው ኢትዮጵያ ቡናም በተወሰነ መልኩ የጠበኩባቸውን አላየሁባቸውም የተወሰነ ድረስ መጡና አፈትልከን አመለጥናቸው አስገራሚ ቡድን ይሆናል ብዬ የተጠበኩት ሌላው ቡድን ባህርዳር ከተማን ነው አዲስ አበባ ላይ ጥሩ ቡድን በውጤትም የተሻሉ ነበሩ በኋላ ላይ መጨረሻቸው ላይ ጥሩ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

ሀትሪክ፡- በስነ ምግባር መጓደል ያልተተቹ ክለቦች መሀል ፋሲል ከነማ አንዱ ነው.. ተደብቆላችሁ ነው ወይስ የምር ለዲሲፕሲን ተገዢ ነበራችሁ?

ሀብታሙ፡- ያለምንም ማመንታት ነው የማወራህ… ሁሉም ተጨዋች ለዲሲፕሊን ተገዢ ነበር ልባችን ውስጥ ዋንጫና ዋንጫ ብቻ ነበር የነበረው… መጥፎ ባህሪ ያላቸውም አልነበሩም በእውነት ጥሩ ፍቅርና ህብረት ነበረን እውነት ነው ምንም ሳይደበቅና ሳንቸገር በጥሩ ባህሪ በድል ጨርሰናል ብል አላጋነንኩም፡፡

ሀትሪክ፡- የእውነት ግን በድሬደዋ ከተማ 3ለ1 ስትሸነፉ አለቀቃችሁም?

ሀብታሙ፡-በእኔ እምነት ፋሲል ቤት መልቀቅ ብሎ ነገር አይታሰብም… በጨዋታው ድሬደዋዎች ልዩ ሆነው ነው የቀረቡት ማሸነፍም ይገባቸዋል፡፡ በእኛ በኩል ዋንጫውን መውሰዳችንን በማረጋገጣችን ዘና እያልን ስለነበር በምንታወቅበት አቋም ላይ አልነበርንም እንጂ ሌላውን ለመጉዳት በፍፁም አለቀቅንም፡፡ ይሄ የእኛን ታሪክ አይመጥንም፡፡

ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በቡድኑ አባላት ይከበራል.. ወይም ተቀባይነት አለው…?

ሀብታሙ፡- ይሄ ውዝግብ ብዙም አይመቸኝም በኔ እምነት አሰልጣኝ ስዩም ለድሉ ዋነኛ ተዋናይ ነው ቀጥተኛም ባለ ድርሻ ነው ለምሣሌ አሰላለፍ አውጥቶ ወደ ሜዳ የምንገባው በእሱ ውሣኔ ነው ምክር ሰጥቶ ውጤታማ ያደረገን አሪፍ አሪፍ ልምምድ ሰርተን ውጤት እንዲመጣ ያደረገው አሰልጣኙ ነው ለኔ ውጤት ሲመጣ አሰልጣኙ የሚረሳበት ውጤት ሲጠፋ አሰልጣኙ የሚሰደብበት ሁኔታ አይመቸኝም መሆን ካለበት በውጤት መምጣትም ሆነ መጥፋት ተጠያቂ አሰልጣኙም ተጨዋቾቹም መሆን አለባቸው፡፡ ዋንጫ ለማንሣታችን የአሰልጣኙ ሚና ትልቅ ነው ይሄ የግሌ ሃሣብና እምነቴ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ አልፈናል ስኬቱ ላይ እንዳለ ባለታሪክ ምን ትላለህ…?

ሀብታሙ፡- በጣም ደስ ብሎኛል ይሄ ህዝብ ለአንድ ቀን መጨፈሩ ሀገራችን ከነበረችበት ችግር አንፃር ድላችን ሁሉን አንድ ማድረጉ አስደስቶኛል… ውስጤ በኩራት ተሞልቷል በታሪኩ ውስጥም ተካፋይ በመሆኔ እኮራለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የውጪ ኳስ ትመለከታለህ…?

ሀብታሙ፡-ብዙም አላይም… ተጫውቼ ማረፍ ስላለብኝ ለእረፍት ጊዜ ስለምወስድ ኳስ መመልከቱ ላይ ብዙም አይደለሁም ግን በአቅሜ ለትምህርቴ የባርሴሎናው ቡሽኬትን ቪዲዮ አውርጄ በተደጋጋሚ ጊዜ አይቻለሁ ተምሬበታለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ለፋሲል ደጋፊዎች የምትለው ነገር አለ…?

ሀብታሙ፡-ትክክለኛ 12 ቁጥር ማለት የኛ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ ህይወታቸውን የሰዉ፣ የቆሰሉ የተራቡ የተቸገሩ ደጋፊዎች ናቸው ያሉን… እነሱን ማመስገን እፈልጋው የሚገርም ልብ ነው ያላቸው በነርሱ ደስተኛ ነኝ ለናንተ ሳቅና ደስታ ምክንያት በመሆናችን ኩራት ይሰማናል የዋንጫው መታሰቢያነቱም ለእናንተ ይሁን፡፡

ሀትሪክ፡- ፍቅረኛ አለህ… አገባህ… ?

ሀብታሙ፡- /ሳቅ በሳቅ/

ሀትሪክ፡- ምነው አንዲት ቆንጆ አልጠበስክም…?

ሀብታሙ፡-ወደ መጥበሱ ነኝ /ሣቅ በሳቅ/

ሀትሪክ፡- የመጨረሻ የምታመሰግነው ሰው ካለ…

ሀብታሙ፡- ከሁለም በፊት ደርሳ ለድል ላበቃችኝ ለጌታዬ እናት ኪዳነምህረት ምስጋና ይሁንልኝ ልሞት የደረስኩበት ጊዜ ላይ ደርሳ አድና ለአሁኑ ድል አብቅታኛለች፡፡ ለቤተሰቦቼ፣ ለጓደኞቼ፣ አብሬውኝ ለተጫወቱ፣ ለፋሲል ከነማ ደጋፊዎች፣ ለመቐለ 7ዐ እንደርታ ስጫወት ሙሉ ድጋፋቸው ላልተለየኝ የክለቡ ደጋፊዎች፣ ለአጠቃላይ የፋሲል ከነማ አባላት ምስጋና አቀርባለው፡፡ በትልቅ ደረጃ ላሰለጠኑኝ… ከ 23 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ለመረጠኝ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ፣ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ፣ ለአሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ለአሠልጣኝ ስዩም ከበደ እንዲሁም ዳሽን ቢ ያለው ላሰለጠነኝ ተገኝ እቁባይ ትልቅ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለው፡፡ ሀትሪክም እንግዳዋ ስላዳረገችኝና ስላከበረችኝ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport