“ለትልልቆቹም ይሁን ለደካማዎቹ ቡድኖች እኩል ትኩረት አለመስጠታችን ጎድቶናል ውጤትም ቀይሮብናል”
“ርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ስለራሴ ነው በግሌ ለአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ታዛዥም ሆነ ታማኝ ነበርኩ”
ፍጹም ዓለሙ/ባህርዳር ከተማ/
በፍጥነቱ በእይታውና ድግግሞሽ ባለው አስጨናቂነቱ ያውቁታል፡፡ ብዙዎች “የደሴው አምባሳደር” ቢሉትም እርሱ ግን ሙገሳው ይበዛብኛል ሲል ይናገራል፡፡ ከሀድያ ሆሳዕናው ሚካኤል ጆርጅ ጋር በፕሪሚየር ሊጉ የሚጫወቱ የደሴ ልጆች መሆናቸው ደሴዎች በኩራት እንዲያዩዋቸው አድርጓል፡፡ “2ኛ የመሆን እድላችንን ያጣነው በትኩረት ማነስ ነው” ሲል የሚሰማውን ለሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ የገለፀው የባህርዳር ከተማው ፍፁም ዓለሙ ለቢ.ዲ.ደጋፊዎች ያለው ክብርና ፍቅር የተለየ ነው፡፡ ከሀትሪክ ጋር በነበረው ቆይታ ለቀረበለት በርካታ ጥያቄዎች ምላሹን ሰጥቷል፡፡
ሀትሪክ፡- እረፍትህን የት እያሳለፍክ ነው…?
ፍፁም፡- እረፍት አሪፍ ነው ቤተሰቤ ጋር ሄጄ ዘና እያልኩ ነው..ደሴ ነው የምገኘው.. አመት ሙሉ እረፍት ስለሌለ አሁን ጊዜ አግኝቼ ዘና እያልኩ ነው፡፡ ከነርሱ ጋር አሪፍ ጊዜ እያሳለፈኩ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ቤተሰብ ስትል….?
ፍፁም፡-/ሳቅ/ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ነኝ፡፡ ባለቤቴ ቅድስት ወ/አምላክ ትባላለች ልጄ ደግሞ ናታኒየም ፍፁም ይባላል ረዘም ያለ ጊዜ ባለመገኘታችን አሁን የተገኘውን ጊዜ እያጣጣምነው ባለቤቴም ብቻዋን ኃላፊነቱን ስትወጣ ነበርና አመሰግናለሁ በርሷ ደስተኛ ነኝ ረጅም ዘመን እንድትኖርልኝ እመኛለሁ
/ሳቅ… አይበቃም/

ሀትሪክ፡- የ2ዐ13 የውድድር አመትን እንዴት አገኘኸው…?
ፍፁም፡- የአመቱ የውድድር ጊዜ አሪፍ ነው ማለት ይቻላል በተለይ የባህርዳር ከተማ አጀማመር ደስ የሚል ቢሆንም አጨራረሱ ቅር ያሰኛል 9 ጨዋታ ላይ ማሸነፍ አለመቻል ያበሳጫል ያንን ብናሸንፍ ኖሮ የተሻለ ነገር ማድረግ ይቻል ነበር 2ኛ ሆኖ በኮንፌዴሬሽን ካፕ የመካፈል እድላችንን አሳልፈን ሰጥተናል፡፡
ሀትሪክ፡- የባህርዳርን ውጤት ነው የገለፅክልኝ…የሊጉ ሂደትስ ምን ይመስላል…?
ፍፁም፡- በፕሪሚየር ሊጉ ጥሩ ጎኑ ይበዛል… በርካታ ግቦች ተቆጥረዋል፣ እስከዛሬ ይታይ የነበረው የሜዳ ላይ ረብሻ የለም… ምናልባት በዲ.ኤስ.ቲቪ ምክንያት ይሁን ባላውቅም ሁሉም በተያዘለት ፕሮግራም ተጠናቋል ምንም አይነት መንዛዛት አልታየም በዲ.ኤስ.ቪ መተላለፉ ደግሞ ሊጉን አድምቆታል… ዳኝነቱን ብናይ ግን መስተካከል አለበት ውጤት የሚለውጡ የዳኝነት ስህተቶች ታይተዋል በቀጣይ እነርሱም ይማሩበታል ብዬ አስባለው፡፡
ሀትሪክ፡- ከ24ቱ ጨዋታዎች በማሸነፋችሁ የተደሰትክበት በመሸነፋችሁ ያዘንክበት ጨዋታ የትኛው ነው?
ፍፁም፡- ሲዳማ ቡናን ገና በመክፈቻ ጨዋታችን ድል ያደረግንበት ጨዋታ ተደስቼበታለሁ በጣም ጥሩ አቅምና ብቃት አሳይተናል ድሉ ይገባን ነበር በሽንፈታችን የተበሳጨሁበት አዲስ አበባ ላይ በወልቂጤ ከተማ የተሸነፍንበት ጨዋታ አበሳጭቶኛል በወቅቱ ምርጥ አቋም ነበረን በርካታ የግብ ማግባት እድሎችን ፈጥረናል ማሸነፍ የሚገባን ጨዋታ አቻ እንኳን ማጣታችን ቅር ብሎኛል በርግጥ ጥሩ ሆነን ቀርበናል አንዳንዴ ግን እግር ኳስ ነውና ጥሩ ሆነን ቀርበህ ላታሸንፍ ትችላለህ፡፡
ሀትሪክ፡- ሲዳማ ቡናን የረታችሁበት ጨዋታ ላይኮ ያሳያችሁት ብቃት ልዩ ነበር ያን ጨዋታ አይተን መሀል ላይ ደከማችሁ… ምንድነው ምክንያቱ?
ፍፁም፡- ጥሩ ሆነን መገኘት አለብን ብለን አስበን ተገኝተን ሜዳ ላይ የሚገጥመን ሌላ ይሆናል፡፡ አንዳንዴ ጥሩ ሆነን ማሸነፍ ላንችል እንችላለን… አንዳንዴ የተጋጣሚ ክለብን አቅም ገምተን እናሸንፋለን ብለን እንገባለን የሚገጥመን ሌላ ውጤት ሲሆን አይተናል ከምንም በላይ ለሁሉም ክለቦች እኩል ትኩረት አለመስጠታችን ጎድቶናል በቃ ለሁሉም በእኩል ደረጃ የመዘጋጀት ዝግጁነት ጎድሎናል ለዚህ ነው እየወረድን የመጣነው፡፡ በተጨማሪ ብዙ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች የሉንም አብዛኛው ተጨዋች ወጣት ነው ልምድ ያላቸው ሲኒየር ተጨዋቾች መኖራቸው በልምዳቸው ተጠቅመው ቡድኑን ሊያነሱት ይችላሉ፡፡ የግድ ሲኒየሮቹ መኖር አለባቸው ወጣቶቹ መሪ ያስፈልገዋል ሲኒየሮች መጉደላቸው ጎድቶናል.. ከዚያ ውጪ በትንሽ ነገር መደሰታችን ነጥብ አስጥሎናል ኳስ በትንሽ ነገር መደሰትን አይፈልግም.. ርግጠኛ ነኝ ለ2ዐ14 ተምረንበታል ብዬ አስባለው፡፡
ሀትሪክ፡- ካስቆጠርካቸው ግቦች ቆንጆ ያልከው ግብ የትኛው ነው…?
ፍፁም፡- የግብ ቆንጆና ፉንጋ ግብ የለም የምታገኘው ነጥብ 3 ነው ..አይደለም ?/ሳቅ/ ግን የግድ መምረጥ ካለብኝ ሲዳማ ቡናን… በረታንበት የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ስታዲየም ግጥሚያ ላይ ያስቆጠርኳትን 2ኛ ግብ መርጫለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ተከላካዮች ይሁኑ ሌሎቹ በተደጋጋሚ ሲመቱህ ፋውል ሲሰሩብህ አያለው.. ተናዳጅ መሆንህን አውቀው? ወይስ የተሻልን መሆንህ ስለገባቸው…?
ፍፁም፡- አንዳንዴ እንደዚህ አይነት ቻሌንጆች ይገጥማሉ ከተጨዋቾቹ መጋፈጥ ይጠበቃል ድብደባው ይበዛል በተለይ አጥቂ ላይ ያልተገባ አጨዋወት ታያለህ… ይሄ መታረም አለበት ሲበዛ አደገኛ ፋውሎች ይገባሉ… ዳኞች ይህን ማለፍ የለባቸውም ተጨዋቾቹም ይህን ማወቅ አለባቸው የሁላችንም እንጀራ ኳሱ መሆኑን ማወቅ አለባቸው ዳኞች የማይሰማቸው ተጨዋቾችን ማረም አለባቸው…ብንሰበር የሚፈጠረውን መርዳት አለባቸው ማንም የየትኛውንም ሪስክ አይወስድም ይህን ተጨዋቾች ማወቅ አለባቸው ይህን እውነት ረስተው ወይም ወደ ጎን አድርገው በሚገቡ ተጨዋቾች እበሳጫለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ገጥሞህ ካወቀ እስቲ ምሣሌ ንገረኝ…?
ፍፁም፡- ባህርዳር ከተማ ከሰበታ ከተማ ጋር ስንጫወት ተደጋጋሚ ጊዜ ፋወል ተሰራብኝ ተቆጣሁ ማንም አልተረዳኝም የሰበታ ከተማ ተከላካይ አዲስ ተደጋጋሚ ጊዜ መታኝ መጋጫው ተሰንጥቋል አጥንቴም ደምቷል አሁን ድረስ ጠባሳ አለው ይሄ ፋውል አላስፈላጊ ነበር የጨዋታው አርቢትር ቢጫ ካርድ ሰጠው ቅር ብሎኛል አንዳንዱ ዳኛ ጨዋታውን ለማስቀጠል በቢጫ ሊያልፍ ይችላል ያ ከባድ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የፋሲል ከነማ አሸናፊነትና የአቡበከር ናስር ኮከብ ተጨዋች ምርጫ አሳመነህ…?
ፍፁም፡- አዎ.. የፋሲል ከነማ ድል ያለተቀናቃኝ የተገኘ ነው ተቀናቃኝ አለው እንዳይባል ሁለተኛው ኢትዮጵያ ቡናን ከ10 ነጥብ በላይ ርቀት በልጦ ነው ድሉን ያጣጣመው የአቡኪ ድልም መላው ኢትዮጵያን ያሳመነ በልዩ ብቃት የተገኘ ነው የአቡበከር ናስር ምርጫም ተቀባይነት አለው ምርጥ ብቃቱን አሳይቷል፡፡ ሙሉ የስፖርት ቤተሰቡን አሳምኗል፡፡
ሀትሪክ፡- አዲስ አበባ ላይ በጎዶሎ ልጅ ገብታችሁ ከፋሲል ከነማ ጋር አቻ ወጣችሁ… ባህርዳር ላይ ደግሞ ሪጎሬ ተከለከላችሁ ዐለዐ መለያየታችሁ ምን ይመስል ነበር…?
ፍፁም፡- ጠንካራ ቡድንኮ ነው ያለን 2ኛ ከወጣው ኢትዮጵያ ቡና ጋር ሁለቴም አቻ ነው የወጣነው፡፡ ነጥብ ይዘን የምንወጣበትን ጨዋታ ነው ያጣነው… ብዙ ኳሶች ተስተዋል ከፋሲል ከነማ ጋር ደግሞ ደርቢ መሆናችን ጠንካራ አድርጎናል እዚህ ላይ እኩል ቡድን ላይ በእኩል ዝግጅት አልቀረብንም ታላላቆቹ ክለቦች ሲሆኑ የሚኖሩን ዝግጅት ከደካማዎቹ ጋር እኩል አልነበረም ለትልልቆቹም ይሁን ለደካማዎቹ ቡድኖች እኩል ትኩረት አለመስጠታችን ጎድቶናል ውጤትም ቀይሮብናል… እርግጠኛ ለቀጣይ መማርያ ይሆነናል ብዬ አስባለው፡፡
ሀትሪክ፡- የባህርዳር ከተማ ተጨዋቾች ሙሉ በሙሉ ለአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ታማኝና ታዛዥ ነበሩ…?
ፍፁም፡- ራሴን ወክዬ ነው መናገር የምችለው… ርግጠኛም ሆኜ የምናገረው ስለራሴ ነው/ሳቅ/ በግሌ ለአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ታዛዥም ሆነ ታማኝ ነበርኩ፡፡
ሀትሪክ፡- ሌሎቹስ ተጨዋቾችስ ይህን መናገር አይችሉም…?
ፍፁም፡-እነርሱ ይመልሱት እንዲህ ይላሉ ብዬ መናገር አልፈልግም በርግጠኝነት ግን ሁሉም ይወደዋል ያከብረዋል ብዬ ነው የማስበው…. አሁን ባልከው ደረጃ ችግር የተፈጠረበት ሁኔታ የለም፡፡ ሁሉም ስራውን አክብሮ ይሰራል ግባ ሲባል ይገባል ሲቀንስም የሚጮህ የለም በዚህ በኩል ባህርዳር ከተማ ላይ ስጋት የለም፡፡
ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ለፍፁም… ምን ጨመረለት ?
ፍፁም፡- አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ወደ ኋላ ተመልሼ እንድጫወት አይፈልግም በነፃነት እንድጫወትና ወደ ግብ እንድቀርብ ነው የሚያደርገኝ ልምምድ ላይ በደንብ ያሰራኛል እንዴት ክፍት ቦታ እንደምፈጥር ያሳየኛል ጓደኞቼም በተደጋጋሚ ክፍት ቦታ እንዲፈጥሩ ልምምድ ላይ ያሰራናል ለዚያም ነው ብዙ ጎሎች የተቆጠሩትም.. ነፃነቴን ጠብቆልኛል
ያ ደግሞ ምቾት ሰጥቶኛል፡፡
ሀትሪክ፡- በስንት አሰልጣኞች ሰልጥነሃል…? የት .. የትስ ተጫውተሃል…?
ፍፁም፡- በብሔራዊ ሊግ ጥቁር አባይ፣ በፕሪሚየር ሊጉ 4 አመት ለፋሲል ከነማ 2 አመት ለባህርዳር ከተማ ተጫውቻለሁ በአጠቃላይ አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ምንተስኖት፣ አሠልጣኝ መሳይ፣ ውበቱ አባተና አሁን ፋሲል ተካልኝ አሰልጥነውኛል በዚህ አጋጣሚ ያሰለጠኑኝን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- አብረህ ረጅም ጊዜ እንደመጫወትህ ፋሲል ከነማ ዋንጫ ሲያገኝ ምን ተሰማህ…?
ፍፁም፡- በፋሲል ከነማ ከብሔራዊ ሊግ ጀምሮ 4 አመት ተጫውቻለሁ.. ዋንጫው ይገባቸዋል ደውዬም እንኳን ደስ አላችሁ ብያቸዋለው፡፡
ሀትሪክ፡- በ2ዐ14 ይሁን በሌላው አመት አብሬው ብጫወት የምትለው ተጨዋች ማነው…?
ፍፁም፡- ከኢተዮጵያ ቡናው ታፈሰ ሰለሞን ጋር አብሬው ብጫወት ደስ ይለኛል…
ሀትሪክ፡- አሁን ያለሁበት ብቃት የአቅሜ ጣራ ነው ትላለህ… ወይስ በ2ዐ14 የተሻለው ፍፁም እንጠብቅ?
ፍፁም፡- በየአመቱ እየተሻሻልኩ እየተለወጥኩ አቅሜን እያጎለበትኩ መሄድ ነው የምፈልገው ገና መስራት የሚጠበቅብኝን አልሰራሁም ገና መድረስ ያለብኝ ቦታ አልደረስኩም ገና እየጀመርኩ እንዳለ ነው የሚሰማኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ኮቪድ 19 ለፍፁም ፈተና አልነበረም…?
ፍፁም፡- እርሱማ ምን የኔ ብቻ የሀገራት ፈተና ሆነኮ… ገና ማቆም አልተቻለም ድሬደዋ እያለሁ አለብህ ተብዬ ይዞኝ ለቆኛል ድሬደዋ ተመርምሬ አለብህ ተባልኩ ሀረር ሄድኩና ስመረመር ደግሞ የለብህም አሉኝ ለ4 ቀናት ተፈትኜ ነበር.. ሁሉም ማለት በሚያስችል ኮቪድ ላይ የተዘናጋ ይመስላል ድሬደዋ የንግድ ከተማ በመሆኗ ብዙ ሰው ስለሚሄድ ኮቪዱ በስፋት ተስፋፍቶ ነበር ሰውም አይጠነቀቅም ለመላው ህብረተሰብም ራሱን እንዲጠብቅ አደራ እላለው ማክስ በማድረግ፣ ርቀት በመጠበቅ፣ ሳንቲይዘር በመጠቀም ራሱን መከላከል አለበት፡፡ ሁሉም ሰው ራሱን ስለሚወድና ራሱን ስለሚጠብቅ በመጠንቀቅ ራሱን ከኮሮና ቫይረስ መጠበቅ አለበት ሁሉም ሰው ለራሱ ያለውን ፍቅር ለራሱ ሲል በመከላከል ማሳየት አለበት፡፡ አሁንም ኮቪዱ ሰው እየነጠቀን ነውና ህብርተሰቡ ራሱን በደንብ እንዲከላከል አደራ ማለት እፈልጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- 2ዐ13 ማሳካት ፈልገህ ያልተሳካልህ ምንድነው?
ፍፁም፡- በርካታ ግቦች እስቆጥሬ ደረጃ ውስጥ በመጨረስ በተለይ በኮንፎዴሬሽ ካፕ ባህርዳር ከተማ ለማሳለፍ እችላለሁ ብዬ አስቤ ነበር በተለይ ጨዋታውን ተጀምሮ 5 ጨዋታ ድረስ የነበረን ብቃት አይቼ ተስፋ አድርጌ ነበርና ያ ባለመሳካቱ ቅር ብሎኛል፡፡
ሀትሪክ፡- 2ኛ የመሆን እድለ ከእጃችሁ ማፈትለኩ ግን ብዙዎችን አስገርሟልኮ?
ፍፁም፡- አዎ ለሁሉም ጨዋታ እኩል ትኩረት አለመስጠታችን ነው ዋጋ ያስከፈለን.. እድሉ በደንብ እጃችን ላይ ነበር ጊዮርጊስና ቡናን ሀዋሳ ላይ በተከታታይ ገጥመናል.. ያን ሁሉ የማሳካት እድል እያለን ራሳችን ነን እድሉን አሳልፈን የሰጠነው ብዬ ነው የምቆጨው፡፡
ሀትሪክ፡- በአንተ እይታ ጥሩ ይሆናል ብለህ የወረደብህ ስትገምተው በጥሩ አቅሙ ያስገረመህ ቡድን ማነው…?
ፍፁም፡- ብዙ ሳልገምተው ምርጥ ቡድን የነበረው ሀዲያ ሆሳዕና ነው ጠንካራ ተፎካካሪ አስቸጋሪ ቡድን ሆኖብኛል ወላይታ ድቻም በተመሳሳይ ጥሩ ነበሩ በተለይ ወደ መጨረሻ ላይ ብቃታቸውን አሳይተዋል፡፡ ጠብቄው የወረደው ቡድን ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው አስገርሞኛል፡፡ በነበረው ስብስብ የአለም ዋንጫ ራሱ ያሸንፋል ብዬ ጠብቄው ነበር /ሳቅ/ ሀገር ወክሎ ቢሄድ ይረታል ብዬ የምገምተው ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- ከፋሲል ከነማ ውጪ ሌሎቹ ክለቦች መሀል የነበረው ፉክክር ተመጣጣኝ ነው.. ተለይቶ የወጣ የለም የሚሉ አሉ አንተስ… ?
ፍፁም፡- አዎ ተመሳሳይ ፉክክር ነው የነበረው.. የክለቦች አቅም አልተራራቀም.. ችግር ላይ ያለ ክለብኮ አንዳንዴ ተስፋ ቆርጦ ነው የሚመጣው ያኔ ሜዳ ላይ ያልጠበከው ነገር ይገጥምሃል.. በርግጥ የሊጎች ፉክክር ገና ነው ተከታታይ ምርጥ አቋም አሳይቶ በዚያው መጠን መጨረስ ከባድ ነበር…
ሀትሪክ፡- ለዋሊያዎቹ ግልጋሎት ስትሰጥ አትታይም አቋምህ… ወይስ ፍላጎት የለህም…?
ፍፁም፡- አገሩን ማገልገል የማይወድ ማን አለ? ለነገሩ ተመርጬ ተጠባባቂ ሆኜ ነበር እንጂ በቡድኑ ውስጥ ተካትቻለሁ፡፡ ቋሚ የነበሩት ደግሞ የተሻለ ስለነበሩ አልተከፋሁም.. እነ ሽመልስ በቀለ… ሱራፌል ዳኛቸው…፡፡

ሀትሪክ፡- ለባህርዳር ከተማ ደጋፊ የምትለው ነገር ካለ?
ፍፁም፡- ቡድናቸውን የሚወዱ ትክክለኛ 12 ቁጥር ለኔ የኛ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ በቡድናቸው ጀርባ የማይጠፉ የሚያበረቱ ውጤቱ ቢደክምም ከጎናችን ሆነው የሚያጠነክሩ ለክለቡ ሟች የሆኑ ምርጥ ደጋፊዎች አሉን ዘንድሮ ጥሩ ውጤት አይደለም በቀጣይ በ2ዐ14 ምርጥ ውጤት አምጥተን እንክሳቸዋለን ብዬ ተስፋ አደርጋሁለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- የመጨረሻ የምታመሰግነው ካለ….?
ፍፁም፡- አመሰግናለሁ…. ባለቤቴን፣ ቤተሰቦቼን፣ ጓደኞቼንና ያሰለጠኑኝ አሰልጣኞቼን፣ የባህርዳር ከተማ አመራሮችና ደጋፊዎችን በአጠቃላይ በኔ ነገር ላይ ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
አስተያየት ይስጡ