መነሻ ገጽ The BiG Interview በአሰልጣኝ ውበቱ ድል አሰልጣኝ አብርሃምም ይሞገስ ማለት ቼልሲ ባሳካው የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ከቶማስ ቱሂል ጋር ላምፓርድም ይሸለም እንደማለት እንዳይሆን እሰጋለሁ”አቶ ባህሩ ጥላሁን (የኢት.እግር ኳስ ፌዴ. ዋና ፀሐፊ)
The BiG Interviewዜናዎችየኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን

በአሰልጣኝ ውበቱ ድል አሰልጣኝ አብርሃምም ይሞገስ ማለት ቼልሲ ባሳካው የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ከቶማስ ቱሂል ጋር ላምፓርድም ይሸለም እንደማለት እንዳይሆን እሰጋለሁ”አቶ ባህሩ ጥላሁን (የኢት.እግር ኳስ ፌዴ. ዋና ፀሐፊ)

አጋራ
አጋራ

“በአሰልጣኝ ውበቱ ድል አሰልጣኝ አብርሃምም ይሞገስ ማለት ቼልሲ ባሳካው የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ከቶማስ ቱሂል ጋር ላምፓርድም ይሸለም እንደማለት እንዳይሆን እሰጋለሁ”

“የተቀመጥኩበት ወንበር እስካሁን አልቆረቆረኝም፤ እንደ እሳትም አልፈጀኝም”
አቶ ባህሩ ጥላሁን (የኢት.እግር ኳስ ፌዴ. ዋና ፀሐፊ)

የዛሬው እንግዳችን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆነው አቶ ባህሩ ጥላሁን ነው፡፡
ብዙዎች ሰው የማይበረክትበት፣ እንደ እሣት የሚፋጅ ምቾት የማይሰጥና የሚቆረቁር ነው በሚሉት የፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊነት ወንበር ላይ እስከዛሬ ከተቀመጡት ሁሉ በእድሜው ትንሹ ሰው በመሆንም ባለ ታሪክ ለመሆን በቅቷል፡፡

ለቦታው የሚታጩ ወይም የሚቀመጡ ሰዎች “ትንሽ ምራቅ ዋጥ ያደረጉ፣ ሽበት የወረራቸው ቢሆኑ” የሚለውን አሮጌ አመለካከት ለመስበር የእድሜው ለጋነት ያልገደበውና የፌዴሬሽኑን ቁልፍ ቦታ በመዳፉ የጨበጠው አቶ ባህሩ ጥላሁን “ይፋጃል የተባለው ወንበር እስከአሁን አልፈጀኝም፤ ይቆረቁራል የተባለው ወንበርም እስካሁን ሳይቆረቁረኝ የሀገሬን እግር ኳስ ባለኝ አቅም ለማገልገል እየጣርኩ ነው በማለትም ይናገራል፡፡ አቶ ይድነቃቸው ተሰማን ጨምሮ በርካታ ታላላቅ የእግር ኳስ ሰዎች ባገለገሉበት ወንበር ላይ ተደላድሎ የተቀመጠውን በእድሜው ትንሹ በስራው ግን ትልቅ የሆነውን በJournalism and Communication MA በLeadership MAውን በመስራት በእውቀት የታጠቀውን ሰው ለመሆኑ ባህሩ ወደ ፌዴሬሽኑ ከመጣህ በኋላ ሀብታም ሆነሀል ይባላል እውነት ነው? የሚል አስደንጋጭ ጥያቄን አስቀድሞ ስለ ጽህፈት ቤት ኃላፊነቱ፣ ፌዴሬሽኑ ራሱን በራሱ ሸለመ ስለመባሉ፣ ለኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እውቅናና ሽልማት ነፍጋችኋል በሚል ስለመታማታቸው፣ ትልቅ ህልም አለኝ በሚለውና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ እንደተለመደው ተናግሮ አናግሮት ከዚህ በታች ባለው መልኩ አቀናብሮታል፤ አብራችሁን ሁኑ፡፡

ሀትሪክ፡-የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽ የጽ/ቤት ኃላፊ ወንበር ላይ የሚቀመጡ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ቦታው ላይ አይበረክቱም…ወንበሩ እንደ እሳት ይፋጃል…ይቆረቆራል…የሚል አባባልና ልምድ ቢኖርም…ባህሩ ግን ወንበሩ ከመቆርቆር፣እንደ እሳትም ከመፍጀት ይልቅ…ይበልጥ ተመችቶት ቦታው ላይ ተደላድሎ ተቀምጧል ልበል…?…

አቶ ባህሩ፡- …(በጣም ሳቅ)…እንግዲህ እስከ አሁን ሠላም ነኝ…ቦታው ላይ ትንሽ በርከት ብዬ የቆየሁም ይመስለኛል…(ሣቅ)…እውነት ነው አንተም በጥያቄህ እንዳነሳኸው አሁን እኔ የተቀመጥኩበት ወንበር ላይ ሰው የማይበረክተበት ወንበር ነው ሲባልምእሰማለሁ…አሁን ያለው ነገር ወይም የበረከትኩበት ምክንያት ምንድነው? ለሚለው አሁን ያለው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ቀናኢ አስተሳሰብ ያላቸው፣የስራ ነፃነትን የሚያከብሩና ተግባብቶ በመስራት በኩል ችግር የሌለባቸው ሰዎች የተሰባሰቡበት በመሆኑም ይመስለኛል፤እስካሁን የበረከትኩበት ከችግር የፀዳው ሰው ስለሆንኩ ሣይሆን በስራ ሂደት እንኳን ችግር ቢኖር…ችግሮችን የማጋነን ሣይሆን የማረም ነገር መፈጠሩ ነገ የተሻለ ሊሆን ይችላል የሚል እሳቤ መኖሩ የስራ ስሜቱን ጤናማ ያደረገው ይመስለኛል…ከዚህ ውጪ የሚሰሩትን እያንዳንዳቸው የዕለት ተዕለት ስራዎች…አመራሮቹ፣ክቡር ፕሬዝዳንቱ እንዲያውቁት እያደረኩ እንደ ዋና ፀሐፊ የራሴ ማንዴት /ኃላፊነት/ የሆኑ እንደ ኦፊስ ማናጀር ስራዎችን መስራቴ ወንበሩ እንደ እሳት እንዳይፈጀኝ ወይም ቆርቁሮ ቶሎ እንዳልነሳ ያደረገኝ ይመስለናል…

ሀትሪክ፡- …አሁን አንተ የተቀመጥክበት የፌደሬሽኑ ወንበር ላይ በሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን በአለም እግር ኳስ ታላላቅ ስራዎችን ሰርተው ያለፉ እንደ ታላቁ የስፖርት ሰው ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ፣አቶ ካሳ ገ/ጊዮርጊስ፣አቶ አበባው ከልካይና አቶ አሸናፊ እጅጉን የመሳሰሉ ሰዎች ተቀምጠውበታል…እነዚህ ታላላቅ ሰዎች የተቀመጡበት ወንበር ላይ መቀመጥህ በውስጥህ ምን አይነት ስሜት ፈጠረ…?…

አቶ ባህሩ፡- …ይሄ በጣም ትልቅ መታደልም…ትልቀ ክብርም ነው…የሰዎቹን ፕሮፋይል (ታሪክ) ስታይ በጣም ያስደነግጥሃል…በጣም የገዘፈና…ትልቅ ታሪክ በእግር ኳሱ ያላቸው ሰዋች ተቀምጠውበት ያለፉበት ወንበር ነው… ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካና ለአለም እግር ኳስ ጭምር ሁሌም ታሪክ በመልካምነት ሲያነሳው የሚኖር ትልቅ ታሪክ ሰርተው ያለፉ ሰው ናቸው…በተለይ የአፍሪካ እግር ኳስ ማህበር አሁን የሚመራበትን ፕላት ፎርም በደንብ ዲዛይን ያደረጉት እሳቸው ናቸው…በዚህ ደረጃ የገዘፈ ታሪክና ትልቀ ስም ያላቸው ሰው የተቀመጡበት ወንበር ላይ ወይም ኃላፊነት ላይ መቀመጥ ትልቅና ወርቃማ የሚባል ዕድል ነው…ራሴን እሳቸውን ከሚያክሉ ትልቅ ታሪክ ከሰሩ የተከበሩ ሰው ጋር ለማነፃፀር የምሞክር አይነት ደፋር ሰው አይደለሁም…ነገር ግን አጋጣሚው ራሴን እንደ አንድ በጣም ዕድለኛ ሰው አድርጌ እንዳይ ያደርገኛል…

ሀትሪክ፡-… እነዚህ ታላላቅ ሰዎች ተቀምጠው ባለፉበት ወንበር ላይ የተቀመጥክ በዕድሜ ትንሹ ሰው መሆንስ በራሱ የተለየ ስሜት አይፈጥርም…?…

አቶ ባህሩ፡- …እውነት ለመናገር በጣም የተለየ ስሜት ይፈጥራል…ምክንያቱም ሰዎች ለዚህን መሰሉ ታላላቅ ቦታዎች ሲታጩ ዕድሜ እንደ አንድ ትልቅ መስፈርት የሚታይበት አጋጣሚ ስላለ ቦታው በዕድሜ አነስ ላሉ ወይም ለወጣቶች የመሰሰት ነገር አለ…እንደውም የሚባለው ምንድነው “ምራቅ ዋጥ ያደረገ” የሚል አባባል ነበር… ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያት ሲቀመጥ የነበረው ነገር ምንድነው ምራቅ ዋጥ ያደረጉ ሰዎች ወደ አመራርነት ሲመጡ ከችኩልነት፣ከስሜታዊነት የወጣ ስራን ሊሠሩ ይችላሉ፣አርቀው ያስባሉ የሚል ነገር በምክንያትነት ይቀርባል…በተቃራኒው ወጣቶች ከሆኑ ችኩልነት፣ስሜታዊነት ይኖርባቸዋል ከሚል ስጋት የመግፋት ነገር ይስተዋላል…አሁን አሁን ግን አለም ራሱ ከዚህ አመለካከት በመውጣት በሀገራችንም በሌሎችም…ወጣቶች ይሄንን አለም የመቀየር ትልቅ አቅም ያላቸው ናቸው የሚል እምነት እየተፈጠረ መጥቷል…ደፍሮ ኃላፊነትን ለወጣቶች የመስጠት…በዚህም ለውጦቶች እየታዩ መምጣት ጀምረዋል…ይሄ በጣም ትልቅ ነገር ነው..የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሁን ያለው ሥራ አስፈፃሚም ይሄንን አሮጌ አመለካከት ሰብሮ እድሜዬን ሣይሆን “ይሠራል” ብሎ እምነት ጥሎ ይሄንን ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት ስለሰጠኝ በጣም ነው የማመሰግነው…ሌሎች እኔን መሰል ወጣቶች አቅሙ እያላቸው “ምራቅ ዋጥ ያረጉ” በሚል ማሠሪያ ቃሎች እንዳይገፉ ትልቅ መልዕክት የሚያስተላልፉ ነገር ነው ፌዴሬሽኑ ያደረገው…ወደዚህ ኃላፊነት ከመጣሁ ጀምሮ እምነት የጣሉብኝን…ሀገሬንም ላለማሳፈር የተቻለኝን ሁሉ እየጣርኩ ነው…ይሄን ስል ሰርቻለሁ እያልኩ እየታበይኩ ሣይሆን የተሻለ ስራ ለመስራት እየጣርኩ መሆኑን ለማሳየት ነው…

ሀትሪክ፡- የ110 ሚሊዮን ህዝብ ስሜትን ሰቅዞ የያዘውን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቁልፍ ቦታ ለሆነው የጽ/ቤት ኃላፊነት ቦታ ስትታጭ ለራስህ ምን ቃል ገባህ…?…

አቶ ባህሩ፡- …በወቅቱ ይሄ ኃላፊነት ልክ እጄ ላይ ሲገባ በቃ መስራት እንደምችል ማሳየት…“ወጣቶችም ትልቅ ኃላፊነት ቢሰጣቸው ለካ መስራት ይችላሉ” የሚል አመለካከትን መፍጠር አለብኝ አልኩ…በወቅቱ ኃላፊነቱ ሲሰጠኝ ልክ ራሴን ገበያ ላይ እንዳወጣሁ ነው የቆጠርኩት…ገበያ ላይ ከወጣሁ ደሞ ምን መስራት እንዳለብኝ… ማንነቴን በስራ ማሳየት አለብኝ አልኩኝ…ምከንያቱም ገበያ ላይ ወጥተህ ራስህን ካላሰየህ…በስራህ ሰውን ካልገዛህ… አልሸጥ ያለ…የማይፈለግ እቃ ነው የምትሆነው…አልሸጥ ያለና ፈላጊ ያጣ እቃ ላለመሆን እንዲሁም ከመቶ ሚሊዮን ህዝብ በላይ መወከል ቀላል ስላልሆነ ይሄንን ታሪካዊ አጋጣሚ ማበላሸቱ የታሪክም ተወቃሽ ስለሚያደርገኝ በተቻለኝ መጠን የተሻለ ሥራ መስራት አለብኝ ብዬ ለራሴ ራሴው ቃል ገባሁ…እንደገባሁ በአንዳንዶች አካባቢ ያለማመንና የመስጋት ነገር ነበር፤ በእኔ በኩል ግን “I Can’’ እችላለሁ የሚል የጠነከረ ስሜት በውስጤ ተፈጥሮ ስለነበር…በዛ ስሜት ውስጥ ሆኜ እስከ አሁን ለመጓዝ ችያለሁ…

ሀትሪክ፡- …ባሩህ ምን አይነት የጽ/ቤት ኃላፊ ነው…?…ብልህ መልሰህ ምንድነው…?…

አቶ ባህሩ፡- …በተቻለው መጠን እውነትን መመሪያው አድርጎ…የወረደለትን ብቻ ሣይሆን ህግና ደንብን ጠብቆ ከስራ አስፈፃሚውና ከሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ጋር ተግባብቶ የሀገሩን እግር ኳስ አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የሚተጋ የጽ/ቤት ኃላፊ ነው መልሴ… በዚህ ደረጃ ነው ራሴን የምንገልፀው…ነገር ግን በዚህ ሂደት ውስጥ ብሳሳት ታርሜ…የተሻለ ሥራ ከሰራሁ ይበልጥ ተበረታቶ ማገልገልን መርሄ አድርጌ የምሰራ መሆኔን ነው መግለፅ የምፈልገው…

ሀትሪክ፡- …ከዚህ በፊት አንተ በተቀምጥክበት ወንበር ላይ የተቀመጡ የጽ/ቤት ኃላፊዎች ከሚዲያዎች ጋር የመጋጨት፣የአለመግባባት ችግሮች ያጋጥሟቸው እንደነበር አስታውሳለሁ…አንተ ግን በተቃራኒው ከሁሉም ሚዲያ ጋር ጋር በመግባባት ስትሰራ ነው የምትታየው…ምናልባት ወደዚህ ቦታ ከመምጣትህ በፊት በጋዜጠኝነትና በህዝብ ግንኙነት ሠርተህ ማለፍህ ጠቅሞህ ይሆን…?…

አቶ ባህሩ፡- …በእርግጥ አንድ የማይካደው ነገር በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ማለፌ…ጋዜጠኛ ምን ይፈልጋል…?… የሚለውን በተግባር እንድረዳ አድርጎኛል…በአንድ ወቅት ደግሞ public Relations and Media የሚል ኮርስን በኒው ጄኔሬሽን ዩኒቨርሲቲ የማስተማር እድሉ ነበረኝ…እነዚህን ኮርሶችን ለተማሪዎቼ ለማስተማር ከመሄዴ በፊት የማነባቸው፣የምጎረጉራቸው በርካታ መረጃዎች ነበሩ…እነዚህ ነገሮች…አንድ ተቋም ከሚዲያ ጋር ምን አይነት ግንኙነት ሊኖረው ይገባል…?…የሚለውን በተጨማሪ በደንብ እንዳውቅ አድርጎኛል…ከእነዚህ ውጪ ሚዲያው የሚፈልገውን ሳትደብቅ፣ሳትመርጥ፣ሳትዋሽ ከሰጠኸው በመካከላችሁ የሚፈጠር ችግር አይኖርም…የምትሰጠው መረጃ…የሚያሳስተው፣የምታበላልጠው ወይም ልዩነት የምታደርግ ከሆነ ልዩነቶች ይፈጠራሉ…እምነትም ያጣብሃል…ይሄ ግንኙነትን ያበላሻል…ቦታው ላይ እስከተቀመጥክ እንዲያምንህ ሆነህ መገኘት አለብህ…የተሳሳተም፣ እውነት የሆነ መረጃ ይዞ ቢመጣ…አውነት የሆነውን እውነት…የተሳሳተውን ውሸት ነው ማለት…መጋፈጥ ያለብንህም መጋፈጥ ይኖርብሃል…የእነዚህ ነገሮች ድምር ለአልከው ነገር የጠቀመኝ ይመስለኛል…

ሀትሪክ፡- …ብዙ ተጨዋቾች ሲጠየቁ ለብ/ቡድን የመጫወት፣ፕሮፌሽናል የመሆን ህልም እንዳላቸው ሲናገሩ ይደመጣል…የጽ/ቤት ኃላፊነት ህልም አለው…?….

አቶ ባህሩ፡- …(ሣቅ)…የጽ/ቤት ኃላፊ ሰው ስለሆነ እንደማንኛውም ሰው ህልም ማለሙ አይቀርም…እኔም እዚህ ቦታ ላይ ከተቀመጥኩ ጀምሮ ህልም ማለሜን አላቆምክም…አንደኛው አሁን በቅርብ ተሳክቶልኝ ብደስትም የራሴ ታላላቅ ህልሞች አሉኝ…ገና ወደዚህ የኃላፊነት ወንበር ስመጣ በእኔ የጽ/ቤት ኃለፊነት ዘመን ከስራ አመራሩ፣ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመስራት ሀገሬ ለአፍሪካ ዋንጫ ብታልፍ የሚል ህልም ነበረኝ…ምስጋና ለስኬቱ ለተረባረቡት ሁሉ ይሁንና ህልሜ በአጭር ጊዜ ተሳክቶልኝ በጣም ተደስቻለሁ…በእርግጥ ብ/ቡድኑ በየሁለት አመቱ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ አለበት…በየ31 አመቱ ወይም በየ8 አመቱ ቀን እየቆጠረ ማለፍ የለበትም ከሚሉ ሰዎች ተርታ ብሆንም…በእኔ የጽ/ቤት ኃላፊነት ዘመን ወደመሰረትነው የአፍሪካ ዋንጫ በማለፋችን ተደስቻለሁ… አንደኛውን ህልሜንም አሳክቼያለሁ…

ሀትሪክ፡- …ሁለተኛው ህልምስ ምን ነበር…?…

አቶ ባህሩ፡- …ሁለተኛው ህልሜ ደግሞ ኢትዮጵያን በአለም ዋንጫ ላይ ከእነ ብራዚልና አርጀንቲና እኩል ቀርባ ማየት…ይሄ ሌላኛውና ትልቁ ህልሜ ነው…

ሀትሪክ፡- …ትልቅ ህልም ማለምህን ባልቃወምም ይሄ ህልምህ የተለጠጠ ወይም ሩቅ ህልም አይሆንም ብለው የሚጠይቁኝ ቢፈጠሩ ምን መልስ ልስጣቸው…?…

አቶ ባህሩ፡- በፍፁም ሩቅ ህልም አይሆንም…ከጠነከርን ከሰራን ሩቅ የሚመስለው ወይም ማሳካት የማንችለው የሚመስለውን የአለም ዋንጫ ተሳትፎ በጣም ቅርብ በሚባል ጊዜ ማሳካት እንችላለን…ግን ይሄ በምኞትና በማለም ብቻ እንደማይሳካ…ለማሳካት ቁልፉ ነገር ጠንክሮ መስራት ብቻ እንደሆነም አይጠፋኝም…

ሀትሪክ፡- …እንደ ግለሰብስ…?…በግሌ ይሄን አሳክቼ ማለፍ እፈልጋለሁ ወይም አልማለሁ የምትለው አለ…?…

አቶ ባህሩ፡- …እንደ ድፍረት እንዳታይብኝ እንጂ እንደ ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በአህጉርና በአለም አቀፍ ደረጃ የራሴንም የሀገሬንም ሥራ የሚያስጠራ በጣም የገዘፈ ህልም አለኝ…ይሄንን ስልህ በእነዚህ አህጉራዊ ቦታዎች እኝህን ታላቅ ሰው መተካት እችላለሁ እያልኩ እየታበይኩ አይደለም…ቢያንስ እሳቸው ካደረጉት ዘርፈ ብዙ አስዋፅኦ በጣም ኢምነቷን አንድ ሁለት ነገሮችን እንኳን ማድረግ ብችል ብዬ አልማለሁ…የአፍሪካ እግር ኳስ መስራቾች ሆነን፣ፊፋ ውስጥ ተደማጭ እንዳልነበርን አሁን ድምፃችንን የሚያሰማ አንድ ወኪል ማጣታችን ሁሌም ያመኛል…ከእኔ የተሻለ አቅሙም እውቀቱም ያላቸው ሰዎች እንዳሉ ባምንም ይሄንን ታሪክ ለመቀየር ሰፊ የሚመስለውን ጋፕ የማጥበብ ህልሙ አለኝ…

ሀትሪክ፡- …ባለፈው ሀዋሳ ላይ ፌዴሬሽኑ ለብ/ቡድኑ ተጨዋቾችና ከስፖርት ኮሚሽን ጋር በጋራ በመሆን ሽልማት ሰጥታችኋል….ይሄ የሚያስመሰግን መልካም ነገር ቢሆንም…ፌዴሬሽኑ በደገሰው ድግስ ራሱን ደጋሽና ራሱን ተጋባዥ እንግዳ አድርጓል…ራሱ ባዘጋጀው ሽልማት ባልተለመደ መልኩ ራሳቸውን ሸልመዋል ብለው የወቀሷቸው አሉ ይሄ ወቀሳ ይዋጥልሃል… ?…ራሳችሁን መሸለማችሁስ ተገቢ ነበር…?…

አቶ ባህሩ፡- …ወቀሳው አይዋጥልኝም…!…ከመጨረሻው ስመልስልህ ራሳችንን መሸለማችንም ተገቢ ነው የሚል እምነቱ ነው ያለኝ…

ሀትሪክ፡- …(በመገረም ስሜት)…ጭራሽ…?…ተገቢ ነው ስትል…?…

አቶ ባህሩ፡- …ምን መሠለህ…በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ መከባበርን መመሰጋገንና መሸላለምን መጀመር ያለብን ከራሳችን ነው የሚል እምነት አለኝ…መጀመሪያ ራሳችንን ስናከብር ነው ሌሎችን ልናከብርና ልንከበር የምንችለው …ይሄ ውጤት እንዲመዘገብ ስራ አስፈፃሚውን ጨምሮ ሁሉም የየራሱ አስተዋፅኦ ነበረው…የሁሉም አስተዋፅኦ ተደምሮ ነው የተገኘው ስኬት እንዲመጣ ያደረገው የሚል እምነት አለን…ከዚህ አንፃር አስተዋፅኦ ላደረጉት እውቅና መስጠት ማመስገን አለብን የሚል የጠነከረ እምነት አለኝ…ከዚህ እምነት በመነሳት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን “እናመሰግናለን” ለማለት ለእያንዳንዱ የስራ አሰፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ሰርተፌኬት ሰጥቷል…

ሀትሪክ፡- …ምን ሠርተፌኬት ብቻ የገንዘብ ሽልማትም ነው ራሳችሁ ለራሳችሁ የሰጣችኋት…?…

አቶ ባህሩ፡- …አዎን ትክክል ነህ…የገንዘብ ሽልማትም ተሰጥቷል…ምንም የሚደበቅ ነገር የለም…በአደባባይ የሰጠነውም የሚደበቅ ነገር ስለሌለው ነው…ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር አንድ ሥራ አስፈፃሚ ገንዘቡን፣ ጊዜውን ዕውቀቱን ሁሉን ነገሩን ሰውቶ ላገለገለበት ሌላውን ተወውና እንዲት ብጣሽ የምስክር ወረቀት እንኳን አይሰጠውም…ለብ/ቡድን የተጫወቱ፣ብዙ ያገለገሉ ተጨዋቾችም ለሀገራቸው ስላደረጉት ነገር የሚገልፅ የሚያመሰግን ሠርተፊኬት እንኳን ሲሰጣቸው አታይም…እኛ ይሄን ማስቀጠል አልፈለግንም…ይሄ ትልቅ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው…ይሄንን ታሪካዊ አጋጣሚ ዝም ብለን ማለፉ አልፈለግንም…በእውቅናና በሽልማት በማጀብ በታሪክ ሲታወስ እንዲኖር ማድረግን ነው የመረጥነው…ደሞ መመሰጋገንና እውቅና መሰጣጠትን ከራስ መጀመር ምንድነው ክፍቱ…?…እንደውም ይሄ በመጀመሩ ለሀገራቸው የሠሩ ጊዜአቸውን፣ገንዘባቸውን፣ዕውቀታቸውን የሰጡ ሰዎች መመስገናቸውና መሸለማቸው ሊበረታታ የሚገባው ነገር ነው እንጂ…ራሳችሁ…ራሳችሁን ሸለማችሁ በሚል ለወቀሳ የሚያበቃ ነው ብዬ አላምንም…

ሀትሪክ፡- …የኢትዮጵያ ብ/ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ የራሱን አሻራ ያሳረፈውን ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱን እውቅናና ሽልማት ነፍጋችሁታል…ይሄ የምትናገረው ነገር ከዚህ ጋር አይጋጭም…?…ነው ወይስ ሃሣቡ የመጣው አብርሃምን እውቅናና ሽልማት ከነፈጋችሁት በኋላ ነው…?…መሸለሙን እውቅና መስጠቱን ተወውና በቦታው እንዲገኝ እንኳን አለመጋበዛችሁ አያሳፍርም…?…

አቶ ባህሩ፡- …አትሳሳትም…ኢንስትራክተር አብርሃም በፕሮግራሙ ላይ እንዲገኝ ጠርተነዋል…

ሀትሪክ፡- …(ድንገት አቋረጥኩትና)…በምንድነው ጥሪ ያደረጋችሁት…?…ባለፈው ኢንስትራክተር አብርሃም ከሀትሪክ ጋር በነበረው ቃለ-ምልልስ…“…እውቅና ሊሰጠኝ ቀርቶ በሽልማት ስነ-ሥርዓቱ ላይ እንኳን እንድገኝ ጥሪ አላዳረጉልኝም…”…ብሎ ተናግሮ ነበር… ከጠራችሁት እንዴት እንደዚህ ይላል…?…

አቶ ባህሩ፡- …አሁንም ደግሜ እነግርሃለሁ…እና ጠርተነዋል…አለመምጣቱንም አዳራሽ ውስጥ ስናጣው ነው ያረጋገጥነው…በምንድነው ጥሪ ያደረጋችሁት…?…ላልከው በኢ-ሜይል ነው ጥሪ ያደረግንለት…

ሀትሪክ፡-…(አሁንም ድንገት አቋረጥኩትና)…በኢ-ሜይል…?…ሽልማቱ የሚካሄድበት ሀዋሳ እያለ በኢ-ሜይል…?… ምናልባት የኢንተርኔት መቋረጥ ወይም የኢ-ሜይል ለውጥ አድርጎ መልዕክቱ ባይደርሰውስ…?…የሚል ሃሣብ ላላቸው መልስህ ምንድነው…?…

አቶ ባህሩ፡- …ከኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ጋር ብቻ አይደም…ከሁሉም አሰልጣኞች ወይም ባለድርሻ አካላት ጋር ቀላሉ ወይም ዘመናዊ ኦፊሺያል(ይፋዊ) የመገናኛ መንገዳችን ኢ-ሜይል ነው…ለእሱም በዚህ መንገድ የአለው እዚህ ምን????? በዚህ ብቻ ሳናበቃ ለክለቡም በደብዳቤ አሳውቀናል…ከዚህ አንፃር ሌሎቹ እንደተገኙት በቦታው ላይ ይገኛል ብለን ነበር…አዳራሽ ውስጥ ስናጣቸው እንዳልተገኙ አረጋግጠናል…ላለመገኘታቸው ደግሞ የራሳቸው ምክንያት ሊኖራቸው ይችላል…

ሀትሪክ፡ …የጥሪው ጉዳይ አከራካሪ ነው…ከላይ መከባበርና እውቅና መስጣጠት መለመድ አለበት ከማለትህ አንፃር በእለቱ…ኢንስትራክተሩ ለሠራው ሥራ ተገቢው እውቅናና ሽልማት ሊሰጠው አይገባም ትላለህ…?…

አቶ ባህሩ፡- …እዚህ ጋር ነገሮች ተቀላቅለው ሲነገሩ ይታያል…ሀዋሳ ላይ የተካሄደው ሽልማት ዋነኛው ምክንያት በኮትዲቯርና የማዳጋስካር ጨዋታ ላይ ስኬታማ በመሆናቸውና ለአፍሪካ ዋንጫ በማሳለፋቸው ብቻ የተዘጋጀ ነው…ኢንስትራክተር አብርሃም ብ/ቡድኑ እንዲያልፍ የሰሩት ስራ የለም አስተዋፅኦም የላቸውም እያልኩ አይደለም…አላቸው…ለዚህ አስተዋፅኦቸው ደግሞ ከዚህ በፊት ኮትዲቯርን እንዳሸነፉ የእውቅና፣የምስጋናና የሽልማት ፕሮግራም ተካሄዷል…የአሁኑ ፕሮግራም ግን ምክንያቱ ከላይ እንዳልኩህ ነው…

ሀትሪክ፡- …ምናልባት ወደ ፖለቲካው ገባህ ብለህ ካልወቀሰከኝ…በቅርቡ የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ሲመረቅ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ…“…ኢንጂኒዬነር ታከለ ኡማ የጀመረውን ከንቲባ አዳነች አበቤ ጨርሰው ለዚህ አበቁት…”…በሚል ያለፈውም አሁን ያሉትን አስተዋፅኦ የማይዘነጋ እውቅና ሲሰጡ አስተውለናል…ከዚህ አንፃር እናንተም ኢንስትራክተር አብርሃም የጀመረውን አሰልጣኝ ውበቱ ጨረሰው በሚል የሁለቱንም ክሬዲት ማሰቀመጥ አልነበረባችሁም…?…

አቶ ባህሩ፡- …በመጀመሪያ እግር ኳስና ፖለቲካን አንደበላልቃቸው…አሁን ያነሳኸው ሌላ ጉዳይ ነው የሚሆነው… ኢንስትራክተር አብርሃም ብ/ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆን የእሱ አስተዋፅኦ አልነበረም ብለን አልካድንም…ነበረበት… ለዚያም ኮትዲቯርን ካሸነፉ በኋላ እውቅና ሰጥተናል፣ሽልመናል…የቼልሲው አሰልጣኝ ቶማስ ቱሀል ላምፓርድ ከተባረረ በኋላ መጥተው የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን በማንሣት ታሪክ ሠርተዋል..ይሄንን ድል አስመልክቶ ቱሀልም ላምፓርድም አኩል እውቅና መስጠትና መሸለም አለባቸው አይነት ሙግት እንዳይሆን እሰጋለሁ…ለዚህም ይመስለኛል የእንግሊዝ ሚድያዎችም ለላምፓርድ እውቅናም ሽልማትም አልተሰጠውም ብለው ሲጮሁ ያልተሰማው…አሁንም ደግሜ የምነግርህ ኢንስትራክተር አብርሃም አተዋፅኦ የላቸውም እያልኩኝ አይደለም አላቸው…ግን በወቅቱ እውቅናም ሽልማትም ተሰጥቷል…የሀዋሳው ፕሮግራም እንዳልኩህ የኮትዲቯርና የማዳጋስካር ጨዋታን እንዲሁም ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸውን ተከትሎ ነው…ነገር ግን ሰፋ ያለ ፕሮግራም ማለት የእስከዛሬ ጉዞአችንን አስመልክቶ የተዘጋጀ ቢሆን ኖሮ ትክክል አልነበረንም እንላለን፡፡

ይሄ ግን ከዛ የተለየ ነውና በዚህ መልኩ ቢታይ ደስ ይለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ሶስቱ የትግራይ ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ እንዲሳተፉ ጥረት እያደረጋችሁ እንደሆነ ስትገልፁ ነበር፤ አሁን ባለው ሁኔታ ይሄ ይሳካል…?

አቶ ባህሩ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከዚህ ቀደም በነበረው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አንድ ውሣኔ መወሰኑ ይታወሳል፤ በ2014 የፕሪሚየር ሊግ ውድድር የትግራይ ክልል ክለቦች ቦታቸው ክፍት ሆኖ እንዲጠበቁ የሚል ነበር… በዚህ መሠረት ፌዴሬሽኑ እስከ አሁን ጠብቆ ከትግራይ ክልል ክለቦች ጋር ውይይት ማድረግ ተችሏል… ክለቦቹም ፍላጎት እንዳላቸው አሳውቀው ነበር… አሁን ባለው ሁኔታ ግን የፋይናንስ ችግር፣ ወቅታዊ ጉዳዮች ትልቅ ችግር ሊሆንባቸው እንደሚችል ተሰግቷል፡፡ ያም ሆኖ ግን እስከ ሐምሌ 15 ባለው ጊዜ ውስጥ ውሣኔያቸውን እንዲያሳውቁና እንዲመዘገቡ ስለተባለ የምዝገባው ጊዜ እስከሚደርስበት ቀን እንጠብቃለን፡፡

ሀትሪክ፡-አሁን ባለው ሁኔታ በ2014 ይካፈላሉ ተብሎ መጠበቁ የሚይታሰብ ነው የሚሉ አሉ፤ ምናአልባት ዘንድሮ የማይሳካ ከሆነ በ2015ም ይጠበቃሉ ማለት ነው….?

አቶ ባህሩ፡- እኔ እስከማውቀው ከዚህ በኋላ እንደዚህ አይነት እድል አይኖራቸውም… ምክንያቱም ለአንድ አመት ክፍት እንዲሆን ነው የተወሰነው፤ በእኔ አረዳድ ከዚህ በኋላ ፕሪሚየር ሊጉን እንቀላቀላለን ቢሉ እንኳን በሌላ ፎርማት ተወዳድረው ነው መምጣት ያለባቸው የዚህ የመጨረሻ መግለጫ ውሣኔ የሚሆነው የስራ አስፈፃሚው ነው፡፡

ሀትሪክ፡-.. የትግራይ ክለቦች በ2014 እንሳተፋለን ቢሉ አሁን ሀዋሳ ላይ እየተካሄደ ያለው ወደ ፕሪሚየር ሊግ የመግባት ፍልሚያ መጨረሻው ምን ሊሆን ነው? በገንዘብ፣ በጊዜና በጉልበት መቀለድ አይሆንም…?

አቶ ባህሩ፡- ይሄንን አንተ ነህ ያልከው እንጂ በገንዘብም በጉልብትም መቀለድ አይሆንም… ክለቦቹ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ የማይመጡ ከሆነ ፕላን ቢ ያስፈልግ ስለነበር ነው ይሄ ውድድር የተጀመረው፡፡ አሁን እንዳለው ስጋት የሚይመጡ ከሆነ ምንድነው መደረግ የነበረበት የሚለውን ፈትሾ ፌዴሬሽኑ ከፍተኛ ገንዘበ መድቦ ነው ይሄንን ውድድር ያዘጋጀው፤ በጣም የሚገርምህ ፌዴሬሽኑ ከፍተኛ ሪስክ (ውሣኔ) ነው የወሰደው… በዚህ ውድድር ከ1.3 ሚሊዮን ብር በላይ ነው ወጪ የተደረገው… ከዚህ ውስጥ ክለቦች እያንዳንዳቸው 70 ሺ ብር ወደ 400 ሺ ብር ገደማ ነው ያዋጡት… ሌላው የፌዴሬሽኑ ወጪ ነው… እንዳልከው የትግራይ ክለቦች እንሳተፋለን ቢሉ ትልቁን ኪሣራ የሚከስረው ፌዴሬሽኑ ነው፡፡ ሪስክ አለው ግን አምነንበት ነው የገባነው…

ሀትሪክ፡ የሊግ ካምፓኒው የፕሪሚየር ሊጉን ውድድር መምራት ከጀመረ በኋላ አድናቆትም፣ ሙገሣዎችም ወደ ሊግ ካምፓኒውና ወደ አመራሮቹ እየሄደ ነው፤ ይሄ ነገር ፌዴሬሽኑ ምንም እንዳልሰራ የሚያስቆጥር ስሜት በሰው ላይ እንዲፈጠር ያደርጋል ከሚሉ ሰዎች አሉ ይሄንን ነገር እናንተንስ አበሳጭቷችኋል…..?

አቶ ባህሩ፡-በመጀመሪያ ደረጃ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ትልቁ ስኬት አሁን ያለው ስራ አስፈፃሚ በዘመኑ ከሠራቸው አስገራሚ ስራዎች ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ከማለፉ ውጪ ክለቦች የራሣቸውን ሊግ ራሣቸው ለማስተዳደር ላቀረቡት ጥያቄ ጥናት አድርጎ ምላሽ የሰጠበት ነው፤ የሊግ ሼር ካምፓኒው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የወለደው ልጅ ማለት ነው… የልጅህ ስኬት የአንተም ስኬት ነው… ውድቀቱም የአንተ ውድቀት ነው… የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ ስኬታማ መሆንን የምናየው እንደ ፌዴሬሽኑ ስኬት ነው እንጂ ተሸፈንን ወይም ክሬዲቶች ሁሉ ለእነሱ ተሰጠ ብለን የምንበሳጭበት፣ ቅር የሚለን ነገር የለም፤ ለመነጣጠል መሞከሩ ያን ያህል አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም፤ አንዳንድ ጥላቻ ያላቸው “ስኬቱ የእከሌ ብቻ ነው” ብሎ ነጥሎ የመውሰድ ነገር ይታያል ወደ እውነታው ስንመጣ ስኬቱ የመጣው በጋራ ነው… የተከበሩ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ከፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ኢሳያስ ጅራ ጋር ከጽ/ቤቱና ከሊግ ካምፓኒው ሥራ አኪያጅ ጋር በመነጋገር ነው እየተሠራ ያለው፤ ይሄንን ካለመረዳት ብዙ ሊባል ይችላል፤ እንደ ፌዴሬሽን ግን ሊግ ካምፓኒው የወለደው ልጁ ነው…. የልጁ ስኬት የእሱም ስኬት ነው፤ ሊግ ካምፓኒው ሲወድቅ እኛም እንወድቃለን ብለን ነው የምናምነው፤ በአጠቃላይ በእነሱ ጥላ ሥር ተደብቀናል ብለን ሣይሆን የአመቱ ስኬት የሊግ ካምፓኒውም የእኛም ስኬት ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡

ሀትሪክ፡-… ለነበረን ቆይታ አመሰገንኩህ፤ የመጨረሻ ነገር እንድትናገር እድል ልሰጥህ ብለህ ምን ትላለህ…?

አቶ ባህሩ፡-የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለማሳደግ ሁሉም ፖዘቲቭ ኢነርጂ ይዞ ከመልካም፣ ከቅን አስተሳሰብ ተነስቶ ፌዴሬሽኑንና እግር ኳሱን በማገዝ ቢጥር ደስ ይለኛል፤ ይሄ መጠላለፍ ቢቀርም እንደዛው፤ እርስ በእርሳችን ስንጠላለፍ ወደ ኋላ ተጓተን እንቀራለንና ወደፊት እንድንጓዝና ከመጠላለፍ ወደፊት መግፋት ቢኖር፤ እግር ኳሳችን የተሻለ እንዲሆን አስተዋፅኦ ብናደርግ ሀገራችን ተጠቃሚ ትሆናለች ብዬ አስባለሁ አመሰግናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-…. ቆይ ቆይ አንድ የቀረኝ ጥያቄ አለ እሱን ልጠይቅህ ባህሩ ወደ ፌደሬሽኑ ከመጣ በኋላ ሀብታም ሆኗል ብለው የሚያሙህ አሉ.. እውነት ሀብታም ሆነሃል…?

አቶ ባህሩ፡- … (በጣም ያላባራ ሣቅ)… ተመኝተውልኝ ታይቷቸው ከሆነ በጣም ደስ ይለኛል.. አመሰግናለሁ በልልኝ…. ከዚህ በተረፈ በገንዘብ ወይም በንብረት ደረጃ የሚጠቀስ ያፈራሁት ነገር የለም… ደስ የሚለኝ ነገር በገንዘብ የማይታመን የህዝብ ፍቅርን አትርፊያለሁ… ከዚህ ሌላ ብ/ቡድኑ በእኔ የጽ/ቤት ኃላፊነት ዘመን ማለፉ ትልቁ ስኬቴም ሀብቴም ነው፡፡

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየዲሲፕሊን ውሳኔዎችዲሲፕሊን ውሳኔ

የዲሲፕሊን ውሳኔዎች

ገዛኸኝ ደሳለኝ (ሸገር ከተማ) : ክለቡ ከ ኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረገው የ26ኛ...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በዝናባማው ጨዋታ በመቻል ሲረታ የጣናው ሞገድም አሸንፏል

እጅግ በከባድ ዝናብ ታጅቦ በተደረገው ጨዋታ መቻል የሊጉን መሪ ሲዳማ ቡናን 3ለ1...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ሀድያ ሆሳዕና ፣ ፋሲል ከነማ እና ወላይታ ድቻ ወሳኝ ድል አግኝተዋል

በሊጉ የሳምንቱ የሁለተኛ ቀን መርሀግብር ሀዋሳ ከተማ ወደ ሊጉ መሪ የሚጠጋበትን ዕድል...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ፈረሰኞቹ በድል ሲቀጥሉ ንግድ ባንክ እና ድሬዳዋም አሸንፈዋል

ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታታይ ድሉን ወደ ቋቱ ሲከት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከጨዋታ ብልጫ...