መነሻ ገጽ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ “ጥሩ ጎናችን የያዝነውን አጨዋወት አለመልቀቃችን ነው፤ ያ እንቅስቃሴም ነው ለኮንፌዴሬሽን ካፑ ያሳለፈን”አማኑኤል ዩሃንስ /ኢትዮጵያ ቡና/
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግኢትዮጵያ ቡናዜናዎች

“ጥሩ ጎናችን የያዝነውን አጨዋወት አለመልቀቃችን ነው፤ ያ እንቅስቃሴም ነው ለኮንፌዴሬሽን ካፑ ያሳለፈን”አማኑኤል ዩሃንስ /ኢትዮጵያ ቡና/

አጋራ
አጋራ

ኢትዮጵያ ቡና የ2003ቱን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ሲያነሳ የዛሬው የቡድኑ ካፒቴን በአዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በመገኘት ጨዋታውን የመከታተል ዕድሉን ባያገኝም የመስቀል አደባባይ ላይ በተሰቀለው ስክሪን ላይ ግን ከሙገር ጋር የነበረውን ግጥሚያ ተከታትሎ በቡድኑ ድል መደሰቱን ይናገራል።

ያኔ የቡድኑ ደጋፊ የነበረው አማኑሄል ዩሃንስ አሁን ላይ ደግሞ ክለቡን በካፒቴንነት እየመራ ባለበት ሰዓት ምንም እንኳን የቡድናቸው ዋንኛው እልምና ምኞት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማሸነፍ ቢሆንም የእዚህ ቡድን ቀጣዩ ግብ የነበረውን ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ኢንተርናሽናል የውድድር ተሳትፎው መመለስን በውድድር ዘመን ተሳትፎአቸው ሊያሳኩት መቻላቸው እንዳስደሰተው ለሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ገልፆለታል።

ሀትሪክ ስፖርት ከኢትዮጵያ ቡናው የአማካይ ስፍራ ተጨዋችና የቡድኑ ካፒቴን አማኑሄል ዩሃንስ ጋር ሐሙስ ምሽት በዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአቸው፣ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ስለሚያደርጉት የኢንተርናሽናል ውድድር፣ ስለ ራሱና ሌሎችንም ጥያቄዎች አጠር ባለ መልኩ አቅርበንለት የሰጠን ምላሽ በሚከተለው መልኩ ቀርቧል።

ሀትሪክ፦ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ከተጠናቀቀ በኋላ የአንተ የእስካሁን ውሎ የት ሆነህ?

አማኑኤል፦ የእረፍት ጊዜዬ ላይ ስለሆንኩ ከቤተሰቦቼ ጋር ነው እያሳለፍኩ ያለሁት። ከዛ ውጪም አሁን አሁን ላይ ደግሞ በሳምንት ሁለት ቀናት ልምምድን እየሰራሁኝ ነው።

ሀትሪክ፡- የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ለኢትዮጵያ ቡና ዘንድሮ እንዴት አለፈ…?

አማኑኤል፡- እንደ ቡድን ዋንኛው ግባችን የነበረውን የሊጉን ዋንጫ ከፍ አድርገን ባናነሳም ቀጥሎ የነበረው ግባችን ክለቡን ከራቀበት የኢንተርናሽናል የውድድር ዘመን ተሳትፎው ዳግም እንዲመለስ ማድረግ ነበርና ክለባችን የያዘውንና የምንታወቅበትን የጨዋታ እንቅስቃሴ ባለቀቀ መልኩ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ የክለቦች ውድድር ማለፋ ችለናልና ይሄ ዓመት ለእኛ በጣም አስደሳች ሆኖልናል፡፡

ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ቡና የዘንድሮው ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ተሳትፎው እንደ ጥሩ እና ሊስተካከል ይገባዋል የምትለው ጎን የትኞቹን ነው ?

አማኑኤል፡- እንደ ኢትዮጵያ ቡና ተጨዋችነቴ ከሁሉም በተለየ መልኩ ዘንድሮ በጥሩ ጎንነት የማነሳው ነገር ቢኖር እኛ በአጨዋወት ደረጃ ያሰብነውንና የራሳችን የሚባለውን የጨዋታ ታክቲክ በሜዳ ላይ እንተገብር ስለነበርን ነው፤ ይሄን እኛን የሚገልፀንን ዓላማችንንም ከአምናው አሻሽለን በመምጣት በእንቅስቃሴ ደረጃም ያሰብነውን እያሳካን መጥተናልና ይሄ መሆኑ በጣም ደስ ይላል፡፡ ሌላው ሊስተካከል የሚገባው ነገር ቢኖር ደግሞ ቡድናችን ላይ በራሱ የጨዋታ ፍልስፍና ላይ የሚታይ ነገር አለና እሱ ላይ የበለጠ ብንሰራበት ቡናን በሙሉ ቡድንነትና ምርጥ አቋሙ ላይ የምንመለከትበትጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና ሊሰራበት ይገባዋል የምትለው ያ ነገር ምንድን ነው?

አማኑኤል፡- ቡድናችን ኳስ በሚያጣበት ሰዓት እንደ ቡድን ምን ማድረግ እንዳለብን የሚጎድለን ነገር አለና እነዛን ስህተቶችንና ክፍተቶችን በመቀነስ የእርምት ስራን ልንሰራ ይገባል፤ ያን ማድረግ ስንችልም ወደ ስኬታማነቱ የውጤት ማማው በፍጥነት የምንመጣ ይሆናል፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና ከዘጠኝ አመት በኋላ ወደ ኢንተርናሽናል የውድድር መድረክ በመመለሱ እንደ አንድ የቡድኑ ተጨዋች የሚሰማህ ስሜት ይኖራልና ያ በአንተ እንደበት እንዴት ይገለፃል? ከዛ ባሻገር የእዚህ ቡድን የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የውድድሩ ተሳትፎስ የት ድረስ ሊጓዝ ይችላል…?

አማኑኤል፡- ወደ ኢንተርናሽናሉ የውድድር መድረክ ተሳትፎ ከረጅም አመት በኋላ ዳግም ልንመለስ መቻላችን ስሜቱ ቀላል ነገር አይደለምና ያ እድል በመገኘቱ በጣም ደስ ብሎኛል፤ የእዚህ ቡድን አካልና አባል በመሆኔም ደስ ብሎኛል፤ እንደዛም ሆኖ ግን ይሄ ውድድር ራስህን ለዓለም መድረክ የምታስይበት ስለሆነም ዘንድሮ ከቡድናችን ብዙ ነገርም ይጠበቃል፡፡ ቡና በኢንተርናሽናል የውድድር ተሳትፎው ከዚህ ቀደም ያስመዘገበው ውጤት ወደ ሁለተኛው ዙር ማለፍን ነበር፡፡ በ1990ዎቹ ጅማሬም ወደ ምድብ ድልድሉ ሊገባ ከጫፍ ደርሶም ነው እልሙን ሳይሳካም የቀረውና ለቡድኑ በጊዜው ጥሩ የነበረውን ይህን ውጤት ከዚህ አመት መጨረሻ አንስቶ በሚኖረው የጨዋታ ተሳትፎው ግን ለእዚህ ውድድር እንዲበቃ ያስቻለውን እንቅስቃሴ ባለቀቀ መልኩ ከዚህ በፊት ተመዝግቦ ከነበረው የተሻለ የሚባለውን ውጤት ልናስመዘግብ ከወዲሁ ዝግጁ ነው ልንሆን የሚገባን፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና በአንተ የካፒቴንነት ዘመን ወደ ኢንተርናሽናል ውድድር ተመልሷል፤ ከዚህ በፊት ደግሞ በዚህ የውድድር መድረክ የተሳተፈው የ2003ቱን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ሲያነሳ ነበር፡፡ ያኔ አንተ የትና ምን በማድረግ ላይ ነበርክ…?

አማኑኤል፡- በጊዜው ኳሱን ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም የመግባት እድሉን ብዙ ሰልፍ ስለነበር ሳላገኝ ቀርቼ ለመከታተል ባልችልም እንደ ኢትዮጵያ ቡና ደጋፊነቴና በሰፈር ውስጥም ኳስን ገና የምጫወትበት ወቅት ላይ ስለነበርኩኝ የመስቀል አደባባይ ላይ በተተከለው ስክሪን ላይ ነው ጨዋታውን ስከታተልና በተገኘው የድል ውጤትም ልደሰት የቻልኩት፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡናን በካፒቴንነት መምራት ምን ይመስላል..?

አማኑኤል፡- ይሄን ኃላፊነት ያገኘሁት ወደ ዋናው ቡድን ባደግኩኝ 2 አመት ውስጥ ነው፡፡ ገና የቢጫ ትሴራ ተጨዋችነት ጊዜዬን ሳልጨርስም ነበር በካፒቴንነት ቡድኑን የመራሁትና መጀመሪያ ላይ ከብዶኝ ነበር፤ ምክንያቱም የቡድኑ ሲኒየር ተጨዋቾች የነበሩት እነ ጋቶች ፓኖም፣ መስዑድ መሐመድና ኤልያስ ማሞን የመሳሰሉ ተጨዋቾች ከቡድኑ ሲለቁ ነው ካፒቴንነቱን የተረከብኩትና እነ መስዑድን የመሳሰሉት ተጨዋቾች ካላቸው ልምድ አንፃር ትንሽ ቢቆዩልኝ ኖሮም ብዬ ስለ ሀላፊነቱ በደንብ ግንዛቤ እንዲያስገኙል ሳስብም የነበርኩት፤ እንደዛም ሆኖ ግን እነሱ ከለቀቁ በኋላም በሂደት ቡናን በኃላፊነት መምራት ምን ማለት እንደሆነ ራሴን ጭምር በደንብ ጠየቅኩትና በዚህ ደረጃ ላይ ሆኜ በጥሩ ሁኔታ ክለቡን ለመምራት ቻልኩ፤ ቡናን በዚህ ሀላፊነት ለመምራት በመቻሌም ራሴን እድለኛም አድርጌዋለው፡፡ በተለይ ደግሞ በዘንድሮ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊጉ በእኔ የኃላፊነት ዘመን ደጋፊዎቻችን አጥብቀው ወደሚፈልጉት ወደ ኢንተርናሽናል የውድድር ዘመን ተሳትፎ ከረጅም ጊዜ በኋላ ስለተመለስንም በጣምም ነው ደስ ያለኝ፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ቡናን የእዚህ አመት የተጨዋቾች ስብስብን በተመለከተ ምን ትላለህ…?

አማኑኤል፡- የቡድናችን የተጨዋቾች ሰብስብ ከሞላ ጎደል ጥልቅ ነው ባይባልም አሪፍ ነው፡፡ አብዛኛዎቻችን ተጨዋቾችም ወጣቶች ነን፡፡ በአመት አመት ከስር በማደግ እየመጣን የምንጫወትም ተጨዋቾች ነን፡፡ ለምሣሌ እኔን ውሰድ የመጣሁት 2ዐዐ8 ላይ ነበር፤ እነ አቡበከር ናስርና ሚኪያስ መኮንን ደግሞ 2ዐዐ9 ላይ መጡ ከዛ እነ ሀይሌ ገ/ትንሳሄ 2010 ላይ ብቅ አሉ፤ እያለ እያለም ጥሩ አቅም ያላቸው እነ ሬድዋን ናስርና የመሳሰሉት ተጨዋቾችም እየመጡ ያሉበትና ዋናው ቡድንም እንዲጠናከር እያደረጉም ያሉ ናቸውና ይሄን ስብስባችንን በሂደት ጥሩ እያደረገልን ነው የሚገኘው፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡናን በቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ተሳትፎው ከሌሎች ቡድኖች ምን ይለየዋል…?
አማኑኤል፡- እኛን የሚለየን የራሳችን የሆነ አጨዋወትና መንገድ ስላለን ያን የያዝነውን እንቅስቃሴ አለመልቀቃችን ነው፡፡ ሌላው በቀጣይነት የምጠቅሰው ደግሞ ብዙ ወጣት የክለቡ ተጨዋቾች በአንድ አንድ አመት የልዩነት ጊዜ ውስጥ ወደ ዋናው ቡድን በማደግና በውድድሩም ላይ እንዲጫወቱ በማድረግ ተጠቅመንባቸው ቡድናችንን ለአፍሪካ የኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድደር እንዲያልፍ ከማድረጋቸው ባሻገር ለወደፊቱም ለክለቡ ሊጠቅም የሚችል አይነት አዳዲስ ስራን ልንሰራባቸውም ስለቻልን ይሄ ቡናን ከሌሎች ቡድኖች አንፃር ለየት እንዲል ያደርገዋል፡፡

ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ ቡና ዘንድሮ ፈታኝ የነበረው ግጥሚያ የቱ ነው…?

አማኑኤል፡- የሁለተኛው ዙር ላይ ከፋሲል ከነማ ጋር የነበረን፡፡ ያን ጨዋታ አሸንፈን ቢሆን ኖሮ መሪነታችንን የምናጠናክርበት እድል ነበረን፡፡ መያዝ የሚገባንን ነጥብ ስላጣን እነሱን እንድንከተል አድርጎናልና እኛን የጎዳን ጨዋታ ነበር፡፡

ሀትሪክ፡- በጣም የተቆጫችሁበትና የቀለላችሁስ ጨዋታ…?

አማኑኤል፡- የተቆጨንበት አሁንም ከፋሲል ጋር የነበረንን ነው፡፡ ግጥሚያውን ብናሸንፍ ልዩነቱን የአራት ነጥብ እናደርገው ስለነበር ነው፡፡ ሌላው የቀለላችሁ ጨዋታ ላልከው ብዙ ቡድኖች ለእኛ ተዘጋጅተው ቢመጡብንም እነዚህን ጨዋታዎች በያዝነው ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ብዙም ሳንጨናነቅ እናሸንፋቸው ነበርና እነዛ ሊቀሉን ችለዋል፡፡ ከሁሉም በተሻለ የቀለልን ደግሞ ሲዳማ ቡናን በመጀመሪያው ዙር ላይ በሰፊ ግብ ስናሸንፍ በተለይም ደግሞ ከእረፍት በኋላ የበለጠ ጨዋታው ቀሎናልና ያ ግጥሚያ የማደረሳኝ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና በመጪው ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎው በተለይ መልኩ ለውድድር ይቀርባል..?

አማኑኤል፡- በሚገባ አሁን የእረፍት ሰዓት ላይ ነን፤ ቡድኑ የሚጎድለው ነገር ይታወቃል፡፡ ያን ደግሞ የቡድኑ አሰልጣኞች እና አመራሮችም የሚያውቁት ነገር አለና ለሻምፒዮናነት እስከምንጫወት ድረስ መስተካከል ባለበት ቦታ ላይ ክፍተቱን አስተካክሎና የሚጠቅሙንንም ተጨዋቾችን አስመጥቶ በዝግጅት ወቅት ላይ ከቡና የጨዋታ ፍልስፍና ጋር በማቀናጀት ጥሩና ስኬታማ ቡድንን ለኢንተርናሽናሉም ሆነ ለሀገር ውስጥ ውድድራችን ይዘን እንደምንቀርብ እምነቴ የፀና ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ቡናን መለያ አጥልቀህ በመጫወትህ የተለየ አይነት ስሜት ይሰማሃል…?

አማኑኤል፡- አዎን፤ ምክንያቱም ይሄን ቡድን ከልጅነቴ እድሜ አንስቶ ስደግፈው የኖርኩት ነው፡፡ ከዛ ውጪ የትኛውን ተጨዋችም የት ክለብ መጫወትን ትፈልጋለህ ስትለውም ለጥያቄው መልስ ቡናን በኩራት ቀዳሚው ምርጫ ያደርገዋልና ለቡና በመጫወቴ ከፍተኛ ክብር ይሰማኛል፡፡

ሀትሪክ፡- አንተን በተፈጥሮ የሚያስደስትህና የሚያስከፋ ነገር ምንድን ነው..?

አማኑኤል፡- የሚያስከፋኝ አስመሳይ የሆነን ሰው መመልከት ነው፤ የሚያስደስተኝ ደግሞ ግልፅ እና ንፁህ የሆነን ሰው ማግኘት፡፡

ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ከፍ አድርጎ አንስቷል፤ የእናንተው ቡድን ተጨዋች አቡበከር ናስር ደግሞ የኮከብ ተጨዋችነቱን ክብር ጨምሮ የተለያዩ ሽልማቶችን ሊያገኝ ችሏል፤ በእነሱ ዙሪያ ምን አልክ…?

አማኑኤል፡- ለሁለቱም የዘንድሮ ስኬታማነታቸው ይገባቸዋል ነው የምለው፤ ፋሲል ከነማ በዘንድሮው የሊግ ውድድር በጣም ጠንካራና ጥሩ ቡድን ነበር፤ የእኛ ቡድን በእሱ ተሸንፎ ነጥብ ማጣቱ ወደ ኋላ እያስቀረን ለመሄዱ አንዱ ምክንያት ቢሆነንም የራሳቸው ጥንካሬም ነበራቸው፡፡ እንደ አንድ ሻምፒዮና ቡድንም ነበር ማግኘት የነበረባቸውን ነጥብ አግኝተው የውድድር አሸናፊ የሆኑትና የሚገባቸውን ክብር ነው ያገኙት፡፡ የእኛውን አቡበከርን በተመለከተ ስለ እሱ ምን ብዬ ልግለፅልህ፤ ለአቡኪ ይሄ ብቻ አይደለም የሚገባው፤ ከእዚህ የበለጠ ብዙ ነገሮች ቢደረግለት ራሱ ያንሰዋል፤ ታምረኛ እና የማይታመን ችሎታውንም ነበር በዘንድሮ የውድድር ዘመን ላይ ያሳየንና ለእሱም ከፍተኛ ክብሩ ይገባዋል፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ የክረምት ወራት በመጣ ቁጥር ማን ከክለቡ ይለቃል? ማንስ ወደ ክለቡ ይመጣል የሚለው ነገር የክለቡን እድገት ከመፈለግ አኳያ ደጋፊውን ብዙ ጊዜ እንዲጨነቅበት ያደርገዋልና እንደ አንድ የቡድኑ ተጨዋችነትህ አንተስ በዚህ ዙሪያ ምን አልክ…

አማኑኤል፡- ኢትዮጵያ ቡናን ለትልቅ ደረጃ ማብቃት ዋንኛው ስራ የክለቡና የአሰልጣኙ ውሣኔ ቢሆንም እኔም እንደ አንድ የቡድኑ ተጨዋች በሚጎድሉን ቦታዎች ላይ ጠቃሚ ተጨዋቾችን በአሰልጣኙ መልማይነት ከሌላ ቡድን አስመጥተንና እዚህም ሊጠቅሙን የሚችሉ ልጆችን አስቀርተን ካሉብን ትላልቅ ውድድሮች አኳያ ቡድናችንን በማቀናጀት ከወዲሁ ስራን ብንሰራ የምደግፈው ጉዳይ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- አማኑኤል ዘንድሮ ራሱን እንዴት ይገልፃል..?

አማኑኤል፡- የዘንድር የሊግ ተሳትፎዬ ላይ ብዙ ጉዳት ስለነበረብኝ ቡድንን በጣም በምፈልገው መልኩ አላገላገልኩትም፤ ወደ ጤንነቴ ከተመለስኩ በኋላ ግን አበረታች ነገርን በራሴ ላይ ለመመልከት ስለቻልኩ የመጪው የውድድር ዘመን ላይ ደግሞ በሚጎድሉኝ ደካማ ጎኖቼ ላይ በመስራት ቡድኔን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መልኩ ለመጥቀም እንደምመጣ እርግጠኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጋችን በዲ. ኤስ.ቲቪ ተላልፏል፤ በዚህ ዙሪያ ምን አልክ…?
አማኑኤል፡- የጨዋታዎቹ መተላለፍ ለእኛ ሀገር ተጨዋቾች ያላቸውን ብቃት እንዲያሳዩበት መንገድን ከፍቶላቸዋል፤ ወደ ፕሮፌሽናል ተጨዋችነትም እንዲያመሩም መልካም እድልንም እያመጣልን ይገኛልና ይሄ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ይህን ካልኩ ይህን እድል ላመጡት የሊግ ካምፓኒው አመራሮችና ለራሱ ዲ.ኤስ.ቲቪም ምስጋና ይገባቸዋል፡፡

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ… ?

አማኑኤል፡- በኢትዮጵያ ቡና በቆየሁባቸው ጊዜያቶች የዛሬው ደረጃ ላይ እንድደርስ ፈጣሪዬ፣ ቤተሰቦቼ፣ የቡና ደጋፊዎችና አጠቃላይ የቡድኑ አመራሮች፣ አሰልጣኞች፣ እንደዚሁም ደግሞ የክለቡ አባላቶች ከጎኔ ነበራችሁና እና እስካሁን ለሰጣችሁኝ ክብርና ድጋፍ ምስጋናዬን አቀርብላችዋለሁኝ፡፡

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በዝናባማው ጨዋታ በመቻል ሲረታ የጣናው ሞገድም አሸንፏል

እጅግ በከባድ ዝናብ ታጅቦ በተደረገው ጨዋታ መቻል የሊጉን መሪ ሲዳማ ቡናን 3ለ1...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ሀድያ ሆሳዕና ፣ ፋሲል ከነማ እና ወላይታ ድቻ ወሳኝ ድል አግኝተዋል

በሊጉ የሳምንቱ የሁለተኛ ቀን መርሀግብር ሀዋሳ ከተማ ወደ ሊጉ መሪ የሚጠጋበትን ዕድል...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ፈረሰኞቹ በድል ሲቀጥሉ ንግድ ባንክ እና ድሬዳዋም አሸንፈዋል

ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታታይ ድሉን ወደ ቋቱ ሲከት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከጨዋታ ብልጫ...

ዋልያዎቹዜናዎችየኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን

አንጋፋው አሰልጣኝ በስማቸው የእግር ኳስ ማሰልጠኛ አካዳሚ ሊገነባላቸው ነው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውን ለማመስገን እና ዕውቅና ለመስጠት...