መነሻ ገጽ መሸሻ ወልዴ ታዋቂው ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ የምስጋናና የዕውቅና ፕሮግራም ሊካሄድ ነው፤ ሁሉም ከባለውለተኛው ጎን እንዲቆም ተጠይቋል
መሸሻ ወልዴዜናዎች

ታዋቂው ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ የምስጋናና የዕውቅና ፕሮግራም ሊካሄድ ነው፤ ሁሉም ከባለውለተኛው ጎን እንዲቆም ተጠይቋል

አጋራ
አጋራ

ባለፉት 25 አመታት የሀገር ውስጥ ስፖርትን ለሰማ የስፖርት ቤተሰብ ጋዜጠኛ መሽሻ ወልዴ ለሚል ስም እንግዳ አይሆንም። ይህ ባለሙያ ግን ተገቢውን ክብርና እውቅና አልተሰጠውም በሚል የተዋቀሩት ኮሚቴዎች የእውቅናና የምስጋና መርሃግብር መንደፋቸውን በዋቢ ሽበሌ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ አድርገዋል። የሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ከኮሚቴዎቹ መሃል የቀድሞ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ደንድርና አቶ አብዱረህማን መሀመድ/ አቡሸት/ ስለ አጠቃላይ ሂደቱ አነጋግሯቸዋል።

 

ሀትሪክ:- ጋዜጠኛ መሽሻ ወልዴን የማመስገንና ዕውቅና የመስጠት መርሃግብር መነሻው ምንድነው?

ኢሳያስ:- ዕውቅና አሰጣጥ መርሀግብሩ መነሻ መላው ስፖርት ቤተሰብ ውስጥ ስለ መሸሻ ያለው አመለካከት ነው። መሸሻ የተመረጠው ለሀገራችን ስፖርት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ባለሞያዎች መካከል አንዱና በመጀመሪያው ረድፍ የሚቀመጥ ስፖርትን እንደ ስራ ሳይሆን እንደ ህይወቱ በማየት ከ 25 ዓመታት በላይ ሙያውን በጥልቅ ፍቅር፣ ፍላጎትና ጥረት ያከናወነ የስፖርት ዓይነትንና የውድድር ደረጃን ሳይለይ በሁሉም ቦታ በመገኘት ለስፖርት ቤተሰቡ መረጃ ሲያደርስ የነበረና በማድረስ ላይ ያለ ታላቅና ተወዳጅ ባለሞያ በመሆኑ ነው።

አቡሽት:- መነሻውማ የኢትዮዽያ ህዝብና እግር ኳስ አፍቃሪው የሚስማማበት መሆኑ ነው።የመሼ ታላቅነትና ለስፖርት ያለው ፍቅር በውስጣችን አለ እሱ ህዝቡ ውስጥ ያለ ባለሙያ ነው ፕሮግራሙ ይፋ ከመደረጉ 6 ቀናት አስቀድሞ አግኝቼው አይዞህ የስፖርት ቤተሰቡ ላንተ ያለውን ፍቅር የሚገልጽበት ቀን ይመጣል ብዬ ነግሬው ከቀናት በኋካ የበጎ ስራዎች ጠንሳሽና ሳይሳሳ ያለውን የሚሰጠው የቀድሞ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ክለብ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ደንድር ደውሎ ስለዚህ ጉዳይ ሲያዋየኝ ተደስቼ ስራውን በጋራ ጀመርን…ህዝቡ የሚስማማበት ጋዜጠኛ መሆኑ ለመነሻነት ጠቅሞናል።

ሀትሪክ:- በመርሃግብሩ ላይ ምን ምን ተካቷል?

ኢሳያስ:- በእውቅና አሰጣጡ/በፕሮግራሙ ከተካተቱት ጉዳዮች ውስጥ:-

* መሸሻ ለስፖርት የሰራቸውን ስራዎችና አጠቃላይ ህይወቱን በተመለከተ ዘጋቢ ፊልም ማዘጋጀት፣

* መሸሻ የስፖርት የመረጃ ማህደር ነው። እነዚህን መረጃዎች ለመላው ስፖርት ቤተሰብና ባለሙያዎች ተደራሽ የሚደረጉበት አውደርእይ የማዘጋጀትና መረጃውን ከማድረስ ጎን ለጎን ገቢ ሊያስገኝ የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣

* ለመሸሻ በሚሰጠው እውቅና ላይ መላው የስፖርት ቤተሰብ በተላይ ደግሞ የተመረጡ አካላትና በውጭ ሀገራት ያሉ አላማውን የሚደግፉ ሁሉ እንዲሳተፉ በማድረግ መሸሻ ለሰራው ስራ ትርጉም ያለው ሽልማት መስጠትና በቀጣይም ስራውን በተሻለ መልኩ የሚሰራበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገኙበታል።

አቡሽት:- መሼን የሚመጥን የእውቅና መስጠት ፕሮግራም እንደሚሆን እናምናለን ዋናው ለሰራኸው ስራ እናመሰግናለን ለማለት ተዘጋጅተናል የፎቶ አውደ ርዕይ ይኖራል ማንም የሌለው የኢትዮዽያ እግር ኳስ ታሪክ ያለው መሸሻ ወልዴ ጋር ነው። ዶክመንተሪ ታስቧል.. መሼ ብዙ ነገር ይገቡታል ኢኮኖሚውን በደንብ ማገዝ እንፈልጋለን ያለው ክፍያ ጋዜጠኛውን የሚመጥን ነው ብለን አናምንም ኢኮኖሚካሊ ክፍተቱን የመድፈን እቅድም አለን ሰርፕራይዝም ሊኖረን ይችላል።

ሀትሪክ:- እንዲህ አይነት መርሃግብር መኖሩ ምን አይነት አስተማሪነት አለው?

ኢሳያስ:- እውቅና መስጠት ዘርፈብዙ ጠቀሜታዎች አሉት። ለአንድ ግለሰብ እውቅና ሲሰጥ ለግለሰቡ ብቻ ሳይሆን ለሙያውም ጭምር ነው። እውቅና ቀደምብሎ ለተሰራው ስራ ምስጋና ሲሆን በቀጣይ ለሚሠራው ደግሞ ኃላፊነት/አደራ የሚተላለፍበት ነው። እውቅና ሌሎችን ለተሻለ ስራ የሚያነሳሳም ጭምር ነው። እውቅና አሰጣጥ በሚፈለገው ደረጃ አይደለም በዚህ ዙሪያ መስራት ተገቢ ነው። ሰዎችን በህይወት እያሉ ማመስገን መለመድ አለበት የዚህ ጊዜያዊ ኮሚቴ ስራም ለሌሎች በአርአያነት ሊወሰድ ይችላል።

አቡሽት:- ማንኛውም ባለሙያ ለስራው እውቅና ሊሰጠው ይገባል ብለን እናምናለን የዛሬ አመት ለአሽናፊ በጋሻው ዘንድሮ ለመሼ ሆኗል ባለሙያው ከሞተ በኋላ ሳይሆን በህይወት እያለ ሊደገፍ እውቅና ሊሰጠው ይገባል ባይ ነን ያኔ ወደ ኋላ ቀረሁ ብሎ እንዳይከፋ ያደርገዋል ያቀደውን ይፈጽማል በቀጣይ ወደ ሌሎች ሙያዎች እንዘልቃለን ዳኞች ተመልካቾች እየመረጥን እውቅና እንሰጣለን እንዲሁም በዚህ ደረጃ የኢትዮዽያ እግር ኳስ አዋርድ ሊኖር ይገባል… ተግቶና ታምኖ ለኖረ ባለሙያ እውቅና መስጠቱ መቀጠል አለበት።

ሀትሪክ:- እስከ ስንት ብር ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል?

ኢሳያስ:- በእውቅና አሰጣጡ የተቀመጠ የገንዘብ ገደብ/መጠን የለም። ለመሸሻ ሊደረጉ የሚችሉና እሱንና መላውን የስፖርት ቤተሰብ ሊያስደስቱ የሚችሉ አማራጮች ግን ተዘጋጅተዋል።

አቡሽት:- ፕላን የምናደርገው ብር የለም እውቅና መስጠት ስለሆነ አላማችን ብሩ ላይ አላተኮርንም ምንም ነገር ባይሳካ እንኳን ዋንጫ ሸልመነው አመስግነን መሄዳችን አይቀርም። ነገር ግን እንደዚህ እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ መሼን የሚወድ በሙሉ ሊደግፈው ይገባል ከጎናችን ይሆናል ብለን እናምናለን እንደ ግብ የያዝነው ገንዘብ ግን የለም

ሀትሪክ:- የመጨረሻ ቃል?

ኢሳያስ:- ይህንን እውቅና (ድጋፍ ሳይሆን እውቅና ነው) የሚሰጠው መላው የስፖርት ቤተሰብ ነው። በልዩ ሁኔታ እንዲሳተፉ የተለዩ አካላት የተሳትፎ ጥሪ ካርድ ይደርሳቸዋል። በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት አስደሳች ተሳትፎ እንደሚደረግ ባለሙሉ ተስፋ ነን። እውቅና አሰጣጡን ከማስተዋወቅ ጀምሮ ስራውን በመስራት ረገድ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበርና የስፖርት ጋዜጠኞች ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደምታበረክቱ እርግጠኞች ነን። ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማህበርና የሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ማህበር እውቅና አሰጣጡ የተሳካ እንዲሆን ከወዲሁ የጀመሯቸውን ስራዎች አጠናክረው እንደሚቀጥሉበትና አንድ ላይ ሆነን ከፈጣሪ ጋር የምንመኘውን የተሟላና የተሳካ እውቅና በ 2014 አዲስ አመት ዋዜማ ለማከናወን የተያዘውን እቅድ እውን እናደርገዋለን።

አቡሽት:- መሼ ማለት ለሙያ አጋሮቹ ምን እንደሆነ መናገር የለብኝም አሁንም የተማመነው በሙያ አጋሮቹ ነው ያላችሁን ፍቅር ታሳዩናታላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። እንዲሁም መሼ ለተጨዋቾች ባለውለታ ነው የመሼን ኢንተርቪው ይዞ ያልዞረ ተጨዋች የለም ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተጨዋቾች ማህበር፣ የእግር ኳስና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች፣ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፣ የደጋፊ ማህበራትን እጠብቃለሁ። ለመሼ መልካም ስም የሚመጥን እውቅና እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ መሼን መሸለም በሀገር ውስጥ ዘገባዎች ላይ ለሚያተኩሩ ሁሉ ማበረታታት እንደሚሆን ርግጠኞች ነን አሜሪካ ፣ አውሮፓና ደቡብ አፍሪካ ያሉ ተጨዋቾችም ጥሩ ምላሽ እየሰጡን በመሆኑ ጥሩ ፕሮግራም እንደሚሆን ርግጠኞች ነን።

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየዲሲፕሊን ውሳኔዎችዲሲፕሊን ውሳኔ

የዲሲፕሊን ውሳኔዎች

ገዛኸኝ ደሳለኝ (ሸገር ከተማ) : ክለቡ ከ ኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረገው የ26ኛ...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በዝናባማው ጨዋታ በመቻል ሲረታ የጣናው ሞገድም አሸንፏል

እጅግ በከባድ ዝናብ ታጅቦ በተደረገው ጨዋታ መቻል የሊጉን መሪ ሲዳማ ቡናን 3ለ1...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ሀድያ ሆሳዕና ፣ ፋሲል ከነማ እና ወላይታ ድቻ ወሳኝ ድል አግኝተዋል

በሊጉ የሳምንቱ የሁለተኛ ቀን መርሀግብር ሀዋሳ ከተማ ወደ ሊጉ መሪ የሚጠጋበትን ዕድል...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ፈረሰኞቹ በድል ሲቀጥሉ ንግድ ባንክ እና ድሬዳዋም አሸንፈዋል

ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታታይ ድሉን ወደ ቋቱ ሲከት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከጨዋታ ብልጫ...