በኢትዮጵያ እግር ኳስ ሰማይ ላይ እያበራ ያለ አዲሱ አንፀባራቂ ኮኮብ- አቡበከር ናስር (መሳጭ ቃለ- ምልልስ)

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ሰማይ ላይ እያበራ ያለ አዲሱ አንፀባራቂ ኮኮብ- አቡበከር ናስር
(መሳጭ ቃለ- ምልልስ)

” ቤተሰቦቼ ልጃቸውን በኢትዮጵያ ህዝብ ፊት እንደዳሩ ተሠምቷቸዋል በእነርሱም ደስታ ተደስቻለሁ ።

“አንገታቸውን ቀና አድርገው በመሄዳቸውም ትልቅ እርካታ ተሠምቶኛል” አቡበከር ናስር


በይስሐቅ በላይ

ኢትዮጵያ ቡና ግብ ካስቆጠረና ካሸነፈ የእሱ ስም አለ… የክለቡ ከፍተኛ ግብ አግቢዎች ዝርዝር ከታየም የእሱ ስም ቀድሞ አለ… በአንድ የውድድር ዘመን አራት ሀትሪክ የሠራ ተጨዋች ማነው? ከተባለም አሁንም ከሁሉም ስሞች ቀድሞ የሚጠራው ይህው ስም ነው… የሀገሪቱ የምንጊዜም የግብ አግቢዎች ሪከርድስ በማን እጅ ነው? ከተባለም አሁንም ቀድሞ የሚጠራው ይሄው ስም ነው… የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የአመቱ ወጣት ኮከብ ተጨዋችስ? ከተባለም አሁንም የሚጠራው ይሄው ስም ነው… መቼ ይሄ ብቻ የአገሪቱ እግር ኳስ ኮከብ ተጨዋች ክብርም አሸናፊ ይሄው ስምና ይሄው ስም ብቻ ነው፡፡

በቃ… ! አቡበከር ናስር የሚለው ስም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ሰማይ ስር ከሌሎች ስሞች በበለጠ ከፍ ብሎ የሚውለበለብ የቤተሰባችን አንዱ አካል የሆነ ስም ያህል ከሆነ ውሎ አድሯል… በአጭር ቃል እያሳየ ባለው ተዓምርአዊ በሆነ ብቃቱ እግር ኳስ ለአቡበከር ናስር ተፈጥሯል ሳይሆን አቡበከር ናስር ለእግር ኳስ ተፈጥሯል ቢባል ቃሉ ግነት የለውም…

በሸራተን አዲስ ሆቴል በተዘጋጀው የቤቲኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የኮከቦች ሽልማት ስነ ሥርዓት የኮከብ ግብ አግቢነት፣ የኮከብ ተጨዋችና የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የአመቱ ወጣት ተጨዋች ክብርን ጠራርጎ በመውሰድ ወደ እግር ኳሱ ንግስና የተንደረደረውን አቡበከር ናስርን ሁሉም በአንድ ቋንቋና በአንድ ድምፅ “እሰይ አበጀህ… ይገባሀል… እደግልን… ከአይን ያውጣህ” በማለት ጣሪያ ለነካው ብቃቱ ሁሉም ከመቀመጫው ተነስቶ ባርኔጣውን ከፍ አድርጎሎታል፡፡

“አዲስ የእግር ኳስ ንጉስ ተወለደ” የሚል ስሜት በውስጡ የተፈጠረበት የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ከሀዋሳ በስተቀር 11ዱ ክለቦች ላይ ግብ ያስቀጠረውን በ23 ጨዋታ 29 ጎል ያስቆጠረውን አዲሱን ንጉስ አቡበከር ናስርን ከሽልማቱ በኋላ ያለው የጋለ ስሜቱ ሳይበርድ ተናግሮ አናግሮት በሚከተለው መልኩ አቀናብሮታል፡፡


…ልቡን ስለነካው ነገር…

“…በርካታ ሰዎች ስትኬህ ስኬታችን ነው በማለት ላስመዘገብኩትና ላገኘሁት ነገር ከጎኔ በመሆን ደስታቸውን በተለያየ መንገድ ገልፀውልኛል…ሁሉም ለሰጡኝ ፍቅርና አድናቆት ከፍተኛ ክብር ቢኖረኝም አንድ አካል ጉዳተኛ የሰጠኝ ፍቅርና አድናቆት ግን ፍፁም ልብ የሚነካ ሆኖ አግኝቼዋለሁ…በዚህ ደረጃ ስለ እኔ ያውቃል…በቃላት የማይገለፅ ፍቅር ይኖረዋል ብዬ ስላልጠበኩ ነው መሠለኝ…ያሳየኝ ፍቅርና ክብር ልብን የሚነካ ብቻ ሳይሆን ሁሌም ሳስታውሰው እንድኖር የሚያደርግ ነው…”

እባክህ አቡኪ ማልያህን ስጠኝ” የሚል ፅሁፍ ቲ-ሸርቱ ላይ አፅፎ እያለቀሰ አድናቆቱን ስለገለፅለት ደጋፊ…

“…ዘንድሮ የማየው ሁሉ ከአቅሜ በላይ ነው የነበረው…አውነት ይሄ ሁሉ ክብርና ፍቅር ለእኔ ነው…?…ደግሞስ ይሄ ሁሉ ክብርና ፍቅርስ ይገባኛል…?…ቆይ ይሄን ያህል ምን ሰርቼ ነው…?…ብዬ ራሴን በጥያቄ እስካፋጥጥ ድረስ ከህዝቡ በማየው ነገር በጣም ተገርሜያለሁ…ሀዋሳ በነበርንበት ሰዓት አንድ ደጋፊ በቲ-ሸርቱ ላይ [እባክህ አቡኪ ማልያህን ስጠኝ] የሚል ፅሁፍ አፅፎ እያለቀሰ ሲጠይቀኝ በጣም ነው የደነገጥኩት…በዚህ ደረጃ የሚለቀስልኝ አይነት ሰው አይደለሁም

…እባክህ ተረጋጋ…አታልቅስ…ይባስ አኔንም አታስጨንቀኝ ብለውምሊያቆም ነው…ፍቅሩንና ክብሩን በእንባው ጭምር ነው የገለፀልኝ…ይሄ ነገር ለእኔ ከአዕምሮዬ በላይ ነው…ሰው በልቡ ውስጥ ምን ያህል እንደከተተኝም ፍቅሩን ያለስስት እንደሰጠኝ ብቻ ሣይሆን ትልቅ አደራም እንድሸከም እያደረገኝ እንደሆነ ነው የተረዳሁት…ለዚህ ሁሉ ፍቅርና ክብር ምላሽ ለመስጠት ጠንክሬ መስራት እንዳለብኝም የተረዳሁበት አጋጣሚ ነው…በነገራችን ላይ በቲ-ሸርቱ ላይ [ማልያህን እባክህን ስጠኝ] ብሎ ለጠየቀኝ ልጅ እስከአሁን አልሰጠሁትም…ግን እያመቻቸሁለት ነው…ብዙ ተመሳሳይ ጥያቄዎች ቀርበውልኛል… ሁሉንም ለማስደሰት ቢቸገረኝም…ለእሱ ግን ለመስጠት እያመቻቸሁለት ነው…”

ሶስት ሽልማቶችን በማግኘት የሽልማት ሀትሪክ በሰራበት፣በኢትዮጵያ እግር ኳስ መንገሱ ከተረጋገጠበት ምሽት በኋላ ስላሳለፈው ሌሊት…

“…ኡ…ያ ሌሊት በጣም የተለየ ሌሊት ነበር…የተኛሁ መስዬ ያልተኛሁበት…እንዲሁ ስገላበጥ አይኔን ሳልከድን ያነጋሁበት ሌሊት ነበር…ከበርካታ ሰዎች ጋር ለማስታወሻ የሚሆን ፎቶ እንደዛን ቀን ተነስቼ ስለማላውቅ እውነቴን ነው የምልህ በጣም ደክሞኝ…ወገቤን ሁሉ አሞኝ ስለነበር እንደገባሁ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ይወስደኛል ብዬ ነበር የተኛሁት…ግን የሆነው ሁሉ በተቃራኒው ነው…የማያባራ ደስታው፣ ድካሙ፣የእንኳን ደስ አለህ መልዕክቱ ጋጋታ የሠላም እንቅልፍ እንድተኛ አልፈቀደልኝም…በቃ ስገለባበጥ በአዳራሽ ውስጥ የሆነውን ሁሉ እንደፊልም ወደፊትና ወደ ኋላ እያመላለስኩ በምናቤ እያየሁ ነበር ያነጋሁት…እንቅልፍ ባይኔ ባይዞርም ደስ የሚል ምሽትና ሌሊት ነበር ያሳለፍኩት…ነገሮች ሁሉ በእውን ሣይሆን በህልም ዓለም የሆኑ ነበር የሚመስሉት…”

በሸራተን አዲስ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣በርካታ ታላላቅ ሰዎች ፣ታላላቅ ተጨዋቾችና አሰልጣኞች፣የስፖርት ቤተሰቦችና ጋዜጠኞች በተገኙበት የአቡበከር ናስር ስም ተደጋግሞ ስለመጠራቱ…

“…መድረኩ ላይም ተመላለስኩባችሁ አደል…?…ብዬም ተናግሬ ነበር…በጣም ያስጨንቃል…አዳራሹም በጣም ያስፈልራል…እንኳን ሁለቴ ሶስቴ አንድ ጊዜም ወጥቶ መቆም ያስጨንቃል…በአዳራሹ ውስጥ የተሰበሰቡት በሙሉ ከእኔ አቅም በላይ የሆኑ ሰዎች ናቸው…በእነዚህ የተከበሩ ታላላቅ ሰዎች ፊት የትንሹ አቡኪ ስም ተደጋግሞ ሲጠራ ስታይ ደስታ ብቻ ሣይሆን ያስደነግጥህል…የሆነ የማታውቀው የተለየ ስሜትም እንዲሰማህ ያደርጋል…ትንሹ አቡበከር በእነዚህ ታላላቅ ሰዎች ፊት እንዲቆም ስሙ እንዲጠራ ያደረገውን አላህን በጣም ነው የማመሰግነው…እንደዚህ አይነት እድል ስለገጠመው ተጨዋች የሰማሁት ነገር የለም…ከዚህ አንፃር በጣም እድለኛ ነኝ…ሁኔታውን በቃላት ለመግለፅም ይከብዳል…”

ከዚህ በኋላ ግንቦት 23 ለአቡበከር ናስር…

“…በእስካሁን ህይወቴ በመልካምነት የማነሣቸው በርካታ ቀኖች ቢኖሩም…ይሄንን ቀን ግን ከዚህ በኋላ በተለየ ታሪካዊ ቀንነቱሁሌም የማነሣው፣መቼም የማልረሣው ቀን ነው የሚሆነው…የመንግሥት ኃላፊዎች፣ታላላቅ ሰዎች፣የስፖርት ቤተሰቦችና በእግር ኳሱ የራሣቸው ታሪክ ያላቸው ሰዎች በተገኙበት ትልቅ ክብር ያገኘሁበት እለት በመሆኑ በተለየ መልኩ የማነሣው ቀን ይሆናል…”

ለዚህ ክብር በመብቃቱ በቤተሰቦቹ ላይ ስለተፈጠረው ስሜት…

“…አንድ ሰው ወልዶ አሳድጎ ደክሞ ልጁን ለወግ ለማዕረግ ሲያበቃ ታውቃለህ…?…በቃ ያ ስሜት ነው የታየባቸው…ቤተሰቦቼ ልጃቸውን የዳሩ፣የሞሸሩ ያህል ነው የተሰማቸው…በኢትዮጵያ ህዝብ ፊት እንደዳሩኝ እንደሞሸሩኝ ያህል ነው ተሰምቶአቸው በጣም ነው የተደሰቱት…አለማቸውን ያዩበት ሠርግ ያህል ቆጥረው በጣም በጣም ነው የተደሰቱት…ደስታቸው እኔ ከምገልፅልህ በላይ ነው የነበረው… አምላክ ይሄንን ደስታቸውን ስላሳየኝ እኔም በጣም ተደስቻለሁ…”

የአቡበከር ስም ከፍ ብሎ መጠራት በመጀመሩ የናስር ቤተሰቦች አሁን አንገታቸውን ቀና አድርገው መሄድ ስለመጀመራቸው…

“…ከዚህ በፊት በሰይፉ ሾው ላይ ቀርቤ የቤተሰቦቼን የህይወት ውጣ ውረድና በፈተና ውስጥ አልፌ አሁን ለምገኝበት ደረጃ መድረሴን በግልፅ ተናግሬ ነበር…ከዚህ ሾው በኋላ በርካቶች ማንነቴን ሳልደብቅ በግልፅ በመናገሬ ከስፖርቱ ውጪ ያሉ ሰዎች ሳይቀሩ በጣም ተደስተዋል…አርአያ የምትሆን ነህ በማለት አበረታተውኛል…በሄድኩበት ቦታ ሁሉ አድናቆታቸውን፣ፍቅራቸውንም ይለግሱኛል… አሁን ቤተሰቦቼም መከበር ጀምረዋል…በሰፈርም አካባቢም በተለያየ ቦታም ሁሉም ክብርን አድናቆትን ያለስስት እየሰጣቸው እንኳን ደስ አላችሁ እያላቸው በመምጣቱ እንደትናንቱ አንገታቸውን ደፍተው ሣይሆን ቀና ብለው ኮርተው መሄድ ጀምረዋል…ከህዝቡ የሚያገኙት ክብርና ፍቅር ብርታትም ኩራትም ሆኖአቸዋል…የክለባችን ደጋፊ የሆነው እንዲኖሩ ፈልጎኢንጂኒየር የሱፍ የመጨረሻ ጨዋታ እለት ሀዋሳ ድረስ ይዟቸው መጥቶ ሰርፕራይዝ አድርጎኛል…ኢንጂኒየርየሱፍ የተሻለ ሆቴል አሳርፎአቸው ተገቢውን ክብር ሰጥቶአቸው ስታዲየም ገብተው ስጫወት በማየታቸው በጣም ነው የተደሰትኩት…በዚህ አጋጣሚ ኢንጂኒየር የሱፍን ለመልካሙ ስራውናለቤተሰቦቼ ለሰጠው ክብር ከልብ ነው የማመሰግነው… አንድ ጊዜም ሪከርድ በሰበርኩበት ወቅትም መሀመድ ሰማ ከልጆቹ ጋር እቤቴ ድረስ መጥቶ ኬክ ቆርሶ ማዘርና ፋዘርን ካድሞ ነው የሄደው…አሁን አሁንማ አባቴ እንደ ድሮው መስጊድ በእግሩ ሲሄድ የሚያሳልፈው የለም…ሁሉም መኪናውን አቁም ካልሸኘንህ የሚል ሽሚያ ነው የሚገቡት…ዛሬ ዛሬ ብዙ ነገር እየተለወጠ እየመጣ ነው…ከሰው በሚያዩት ነገር እየኮሩ እንደሆነ ያስታውቃል…ደግሞም እኔን ጨምሮ በፈተና ደክመው ያሳደጓቸውን ሶስት ልጆች ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ያበረከቱ በመሆናቸው በዚህ ደረጃ መከበራቸው ያስደስታል…እኔ የቤተሰቦቼ ትልቅ እዳ አለብኝ…ከአላህና ከህዝቡ ጋር ሆኜ አንድ ቀን ብድራቸውን እንደምከፍል አምናለሁ…ሁሉንምመጥቀስ ስለማልችል እንጂ ክብሩን ልነግር አልችልም…”

የዓመቱ ታዳጊ ተጨዋች፣የዓመቱ ኮከብ ጎል አግቢና የዓመቱ ኮከብ ተጨዋች ሽልማትን በመውሰድ አምስተኛ ሀትሪኩን በሽልማት መስራቱ ስለፈጠረበት ስሜት…

“…እውነት ለመናገር የዚህ ሁሉ ሽልማትና ክብር ባለቤት እሆናለሁ ብዬ ስላልጠብኩ ነው መሠለኝ በጣም ነው የተደሰትኩት…የኮከብ ግብ አግቢነት ሽልማቱ የሚታወቅ ስለነበር ስጋቱ አልነበረኝም… ሌሎቹን ግን እውነት ለመናገር የእርግጠኝነት ስሜት በውስጤ አልነበረም…በተለይ የቤትኪንግ የዓመቱ ምርጥ ታዳጊ ተጨዋች ሽልማት መኖሩና ለእኔ ስለመሰጠቱ የማውቀው ነገር አልነበረም…ለሁሉም ሽልማቶች ትልቅ ክብር ቢኖረኝም የዓመቱ ወጣት ተጨዋች ተብዬ ስሸለም በጣም ነው ደስ ያለኝ… ምክንያቱም የእኔን ዱካ ተከትለው ለሚመጡ ወጣቶች ትልቅ ትርጉም ይሰጣል…ለካ እኛም ተስፋ አለን ብለው እንዲያስቡ ያደርጋል…በዚህ ጉዳይ ላይ መደባበቅ ያለብን አይመስለኝም…ከእኔ የሚበላልጡ ትልቅ ችሎታ ያላቸው ግን እድሉን ያላገኙ፣ሳይሳካላቸው ወደ ኋላ የቀሩ ተጨዋቾች አሉ…እነሱን ወደፊት ማምጣት ያስፈልጋል…እድሉን እንስጣቸው…እግር ኳሱም ሀገርም ትጠቀማለች…በየሄድኩበት ቦታ በታዳጊዎች ላይ የማየው ነገር ይገርማል…ለእኔ ያላቸው ክብርና ፍቅር የተለየ ነው…ልክ የእነሱ ወኪል ወይም ምልክት ያህል አድርገው ነው የሚያዩኝ…አሁን ባለፈው ሀዋሳ እያለን ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ተጋብዤ ሄጄ ነበር…ስሄድ ት/ቤቱ በወጣቶች ተሞልቶ ጠጠር መጣያ ሁሉ አልነበረውም… ያልጠበኩትን ነገር ነው ያየሁት…ስሄድ እኔ ለፎቶ ብቻ መስሎኝ ነበር…ንግግር አድርግ ስባል መናገር ሁሉ አልቻልኩም…ባለፈው ሸራተን ለማውራት ስቸገር ነበር…ከሀዋሳው አንፃር እንደውም ሸራተን ተናግሬያለሁ ማለት እችላለሁ…8ዐ٪ ከመቶ የሚሆነው ወጣት እግር ኳስ ወዳድ ነው…ደፍረን እድሉን እንስጣቸው…የአመቱ ወጣት ተጨዋች የሚለውን ሽልማት ለእነዚህ ወጣቶች በተለይ እድሉን ላጡት ማስታወሻ እንዲሆንልኝ ነው የምፈልገው…ሶስት ሽልማት አገኛለሁ ብዬ አልጠበኩም…ተሸላሚ ስሆን በቃላት የማልገልፅልህ የደስታ ስሜት ነው የተሰማኝ…”

ከዚህ በፊት የሀገሪቱ የጎል አግቢ ሪከርድ ባለቤት ከነበረው ዮርዳኖስ አባይ እጅ ሽልማቱን ሲያገኝ ስለተሰማው…

“…ኡ… በጣም ነው የተደሰትኩት…ዮርዳኖስ አባይ ሲጫወት ባላየውምበኢትዮጵያ እግር ኳስ በጣም ትልቅ ታሪክ ያለው የተከበረ ተጨዋች እንደሆነ ግን እሰማለሁ…ከሁሉም የስፖርት ቤተሰብ የማይጠፋ የእግር ኳስ ታሪክ ካለው ተጨዋች እጅ ሽልማቱን መቀበል እድለኛነት ነው ለእኔ…ዮርዳኖስ፣አሰግድ እነ ሳላህዲንና እነ ጌታነህ ከበደ ያደረጉትን ማድረግ ነው የምፈልገው…በዚህ ደረጃ ከማደንቃቸው አንዱ ከሆነው ዮርዳኖስ አባይ እጅ ሽልማቱን ስቀበል በጣም የተደሰትኩትም ለዛ ነው…አሁን ዮርዳኖስ ወደ ስልጠናው ገብቷል…የእሱ ወደዚህ ሙያ መግባት ትልቅ ጥቅም አለው…ነገ የእሱን አይነት ታሪካዊ ተጨዋች የማፍራት እድልም ይኖረዋል…”

ለዚህ ክብር እንዲበቃ የካሳዬ አራጌ ድጋፍ ምን ያህል እንደሆነና ምን እንደጨመረለት…

“…ካሳዬ ብዙ ነገር ጨምሮልኛል…የመጀመሪያውየካሳዬ አጨዋወት ጥሩ እንድንቀሳቀስና ጎል እንዳስቆጥር ጠቅሞኛል…ካሳዬ ጥሩ የተጨዋች አያያዝ ክህሎትም አለው…ማንንም አያበላልጥም… አቡኪ ልሁን ገና አዲስ ተጨዋች የእሱተጨዋች እስከሆንክ ድረስ በእኩል አይን ነው የሚያይህ…በጣም ከምወዳቸው አሰልጣኞች አንዱ ካሳዬ ነው…በቀጣይም ለኢት.ቡና ብቻ ሳይሆን ለሀገርም የተሻለ ነገር ይሠራል ብዬ አምናለሁ …ኢት.ቡናን ወደ ተሻለ ታሪክ ለማሸጋገር እየደከመ ያለ አሰልጣኝ እንደሆነም አውቃለሁ…በእኔ ስኬት ላይ ብቻ ሳይሆን በቡድኑ ስኬት ላይም የካሳዬ ድጋፍ በጣም ከፍተኛ ነውና በዚህ አጋጣሚ እሱን ላመሰግነው እወዳለሁ…”

ያለ ቡድን ጓደኞቼ ድጋፍ ይሄን ስኬት ላስበው አልችልም ስለማለቱ…

“…ያገኘሁት ስኬት በእኔ የግል ጥረት ብቻ የመጣ ስኬት አይደለም…ለእኔ ስኬት የቡድን ጓደኞቼ ድጋፍ በጣም ከፍተኛ ነውና ከልቤ ላመሰግናቸው እወዳለሁ…29 ጎል ያስቆጠርኩትና ጥሩ ለመንቀሳቀስ የሞከርኩት ብቻዬን አይደለም…የእነሱ ድጋፍ ታክሎበት ነው…ያለ እነሱ አሁን ያገኘሁትን ስኬት ማግኘት ፍፁም የማይታሰብ ነው…”

በቀጣይ የውድድር ዘመን ምንአይነቱን አቡበከርን እናያለን…

“…እኔ ሁሌም በየአመቱ እየተሻልኩ፣እየተለወጥኩ ነው መቅረብ የምፈልገው…አሁን ደግሞ ከደጋፊው፣በአጠቃላይ ከህዝቡ እየደረሰኝ ካለው አድናቆትና ድጋፍ አንፃር ከእኔ ከዘንድሮው የተሻለ ነገር ነው የሚጠበቀው…ኢንሽአላህ…ከአላህ ጋር በቀጣይ የተሻለ ነገር ለማድረግ ነው የምጥረው…”

ጭብጨባና ሙገሳ ከየአቅጣጫው መውረዱና መብዛቱ አቡኪን ያጠፋው ይሆን ብለው ለሚሰጉ…

“…ሁሉንም ነገር እንደአግባቡ ተቀብሎ የማስተናገድ ተሰጥኦው አለኝ ብዬ እሰባለሁ…ጭብጨባና ሙገሣ መብዛቱ የበለጠ እንድሆን ያግዘኛል…ሽልማት ያሳድገኝ ይሆናል እንጂ እያጠፋኝም…”

አቡበከር ሽልማቶችን ጠራርጎ ከመውሰዱ የተነሣ ራሱን የሀገሪቱ ብቸኛና ትልቁ ተጨዋች አድርጎ ያስብ ይሆን? ስለመባሉ…

“…በፍፁም…!እኔ የምታበይና ካለ እኔ ተጫዋች የለም የሚል አይነት ስብዕና ያለኝ ሰው አይደለሁም…ምንም ሳልሠራ አስከመታበይ አልደርስም… ምክንያቱም…በሀገሬ ከእኔ በላይ ስንት ታሪክ የሰሩ የእግር ኳስ ጀግኖች አሉ…ኮከብ ተጨዋችነትንና ግብ አግቢነትን ደራርበው የወሰዱ ከአንድም ሁለቴ ሀገራቸውን ለአፍሪካ ዋንጫ በማሳለፍ ታሪክ የሠሩ ተጨዋቾች እያሉ እኔ አልታበይም…ጌታነህ ከበደ ባለሪከርድ ነበር…በየአመቱ ብዙ ግብ የሚያገባ ከአንድም ሁለቴ ሀገሩን ለአፍሪካ ዋንጫ ያሳለፈ ተጨዋች ነው… ሽመልስንም ብትወስድ እንደዛው ኮከብ ተብሏል…ሀገሩን ሁለቴ ለአፍሪካ ዋንጫም አሳልፈዋል…እነ ሳላሀዲንም በየአመቱ ኮከብ በመባል ያሳለፉ ተጨዋቾች እያሉ ራሴን የተለየ አድርጌ አላይም…እንኳን በዚህ ደረጃ ለማየት ይቅርታ በጭራሽ አጠገባቸው እንኳን የምደርስ አይነት ተጨዋች አይደለሁም…ምንም ሳልሠራ በጠዋት አልኮፈስም”

ከልጅ ልጅ እንደማይበላለጠው ሁሉ ጎሎችን ማበላለጥም ከባድ ነው…ግን አቡኪ ከ29 ጎሎቹ ይበልጥብኛል የምትለውን እንኳን ጎል ምረጥ ብለው የትኛውን ይመርጣል…?…

“…ሁሉም ለእኔ ምርጦች ናቸው…ከሁሉም ጎሎቼ በተለይ የማየት ጎል ጊዮርጊስ ላይ ያስቆጠራኳት ናት…አዲስ አበባ ስታዲየም ከጊዮርጊስ ጋር በነበረን የደርቢ ጨዋታ ፔናሊቲ ስቼ ነበር…በእንደዚህ አይነት ትልቅ ጨዋታ ፔናሊቲ መሳት በጣም ከባድ ነው…ኮንፊደንስ ሁሉ ያሳጣል…ከዚህ ሌላም ወንድሜ ሬድዋን ራሳችን ላይ ግብ አስቆጥሮ ነበር…ነገሮች በጣም ከባድ ነበሩ…2ለ2 ለመለያየት በተቃረብንበት በመጨረሻ ሰዓት ያስቆጠርኳት ጎል ለእኔ ከ29ኙም ጎሎች የበለጠ ትልቅ ቦታ የምሰጣት ናት…

 

የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት እድሎች በሩን እያንኳኩ ስለመምጣታቸው…

“…ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ጥያቄዎች እየቀረቡልኝ ነው…በተለይ ከአፍሪካ ሀገሮች ብዙ እየመጡ ነው…ግን አሁን ገና ያላለቀና እየተነጋገርንበት ያለ ነገር ስለሆነ እንደዚህ ነው የምልህ ነገር የለም እንጂ ጥያቄዎችማ ብዙ ናቸው…”

ሽልማቱን አስመልክቶ የኢት.ቡና ደጋፊዎች ስለተሰማቸው ደስታና ስላሳዩት ክብር…

“…ስለ ኢት.ቡና ደጋፊ የልቤን ለመናገር ቃላቶች ያንሱኛል…የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ሀገር የሚያውቀው ነው…በጣም የተለዩና ክለባቸውን የሚወዱ ደጋፊዎች ናቸው…እኔ በተሸለምኩት ከእኔ በላይ የተደሰቱትና የቦረቁት እነሱ ናቸው…ደጋፊው ከዳር እስከዳር ነው ደስታውን የገለፀውና በዚህ አጋጣሚ ሁሉንም አመሰግናለሁ…እነሱን የምገልፅበት ቃላትም አላገኝም…”

ከክለቡ ውጪ ያሉትን ደጋፊዎች አሠልጣኞች ስለገለፀበት…

“…በእኔ መሸለም የተደሰተው ሁሉም ነው…የተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች፣ አሰልጣኞች ሁሉም በተለያየ መንገድ ደውለው በመሸለሜ ደስታው የእነሱም እንደሆነ አውርተውኛል…በዚህም አመሰግናቸዋለሁ…ሁሉም አሰልጣኞች ማለት እችላለሁ ደስታቸውን ከመግለፅ በዘለለ ምክራቸውንም ለግሰውኛልና እነሱንም በተመሳሳይ ላመሰግናቸው እወዳለሁ…”

የአቡበከር ናስር ሪከርድን ከአቡበከር ናስር ውጪ የሚሰብረው የለም ስለመባሉ…

“ኮች ውበቱ አባተ አንድ የሰጠው አስተያየት ነበር…እሱ ለማለት የፈለገው 27 ጎል ባስቆጠርኩበት ሰዓት ሪከርዱን ራሱ ነው የሚሰብረው ለማለት ይመስለኛል…አንተ በጥያቄ ያነሳኸውን አባባል ብዙ ሰዎችም ይጠቀሙታል…እኔ ግን እንደዛ አላስብም…ጌታነህ ከበደ የዮርዳኖስ አባይን ሪከርድ የሰበረው ከ16 አመታት በኋላ ነው…እኔ ግን የጌታነህን ሪከርድ ለመስበር አራት አመት ብቻ ነው የፈጀብኝ…የእኔን ሪከርድ የሚሰብሩ ብዙ ተጨዋች እንደሚኖሩ አምናለሁ…እንደውም እንደ እኛ ብዙ አመት ሊወስድ ይችላል ብቻ አላስብም…በሁለት ወይም በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ሪከርድ የሚሰብርበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችል ይሆናል…”

አመቱ ለእሱ ፍፁም የተለየ ስለመሆኑ…

“ይሄ አመት ለእኔ በጣም የተለየ ነው…የእግር ኳስ ህይወቴን ወደ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ ነው ማለትም ይቀለኛል…በብ/ቡድን ተጫዋችነት ሀገራቸውን ለአፍሪካ ዋንጫ ማሣለፍ ከቻሉ አንዱ ለመሆን በቅቻለሁ…ይሄ ብቻ አይደለም ክለቤ ኢት.ቡና ከዘጠኝ አመት በኋላ ወደ አፍሪካ የክለቦች ውድድር ተመለሰ…እኔ በግሌም የሀገሪቱ ትልልቅ ሽልማት የሆኑትን የኮከብ ጎል አግቢ፣የኮከብ ተጨዋችና የአመቱ ወጣት ኮከብ ተጨዋችነት ክብርን ደራርቤ ወስጂያለሁ…ይሄ ሁሉ ስኬት አመቱን የተለየ አድርጌ እንዳስብ አድርጎኛል…”

ኢትዮጵያ ቡና ከዘጠኝ አመት በኋላ ወደ አፍሪካ መድረክ መመለሱና ለማሳካት ስላሰበው…

“…ከላይም ለመግለፅ ሞክሬያለሁ አሪፍ አመት ነው እንድል ካደረጉኝ አንዱ ክለቤ ኢትዮጵያ ቡና ወደ አፍሪካ መድረክ በእኔ የተጫዋችነት ዘመን በመመለሱ ነው…ከግል ስኬቴ በላይ በጣም የተደሰትኩት የክለቤ ወደ አህጉሪቱ ውድድር በመመለሱ ነው…በብ/ቡድን ያገኘሁት ደስታ ሳያበቃ በክለቤም ስመኘው የነበረው ይሄንን እድል በተለይ ደጋፊው በማግኘቱ በጣም ተደስቻለሁ…ክለባችን ካለው አጨዋወት፣ከደጋፊው የተለየ አደጋገፍ የተለየ ድምቀትም እንሆናለን…በተቻለን መጠን ለክለባችም ለሀገርም መልካም ስም የሚያስገኝ የተሻለ ጉዞ እናደርጋለን ብዬ አስባለሁ…”

ሽልማት በሽልማት መሆኑ ወደ ሚሊየነርነት እያሸጋገረው ይሆን…?…

“…/በጣም ሳቅ/…እኔ አልሀምዱልላሂ ነው የምለው…በፊት በባዶ እግሬ በመጫወት አሳልፌ ዛሬ የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሻለሁ…አሁን የተሻለ ነገር እያገኘሁ ነው…ከዚህ የበለጠ እየሠራሁ ከሄድኩ የተሻለ ነገር ላገኝ እችላለሁ…ዛሬ በብዙ ሺ ብር የሚገዛ ታኬታ (የመጫወቻ ጫማን) እያማረጥኩ ነው የምጫወተው…ብዙውን ጊዜዬን ግን በባዶ እግሬ በመጫወት ነው ያሳለፍኩት…የሚገርምህ ጫማ አደርጎ መጫወት አይመቸኝም ነበር..በጫማ ስጫወት ብዙ ጎል እስትም ነበር…በዚህ የተነሣ ጎል እንዳገባ ጫማህን አውልቅ አባል ሁሉ ነበር…አላህ ያን ሁሉ ውጣ ውረድ አሳልፎ ለዚህ ስለበቃኝ አመሰግነዋለሁ…”

…በመጨረሻ…

“…በመጨረሻ በእኔ ህይወት አሻራቸውን ያሳረፉትን ሁሉ…ለዚህ የበቃሁት በእናንተ ቅብብሎሽ ነውና ሁላችሁንም አመሰግናለሁ…ሀራምቤ እያለን እታች ታዳጊ ቲም ነበር እንጫወት የነበረው…ታዴ ይባላል አሁን ካገኘሁት ብዙ ጊዜ ሆኖኛል…የሸራ ታኬታ ሁሉ ገዝተውልኛል እሱን አመሰግናለሁ…ሰፈር ውስጥ ያሰለጠኑኝ አሉ…እነ ደረጀ ስራ ቤቴ፣ሙሉጌታ፣ዳዊት ቀለመወርቅ እንዲሁም አንድ አሰልጣኝ አለ የነገ ተስፋ ፍሬ ያሰለጠነኝ ደመቀ…ወደ B ስገባ ደግፌ እንድሞክር ረድቶኛል …በሐረር ሲቲ እስማኤል አቡበከርን በጣም ነው የማመሰግነው…በዚህ አጋጣሚ እስማኤል አዲስ አበባ ከተማን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በማሳለፉ እንኳን ደስ አለህ ልለው እፈልጋለሁ…ወደ ብ/ቡድን ስሄድ ወጣት ቡድን እያለን አሰልጣኝ አጥናፉን በጣም ነው የማመሰግነው…
አጥናፉ እንደ አባትም ነው የማየውና እሱም መመሰገን ያለበት ሰው ነው… ወደ ቡና ስትመጣ ትልቁን ሚና የተጫወተው ታዲዮስን ማመስገን እፈልጋለሁ…ኢትዮጵያ ቡና እንድቀላቀል ትልቁን ሚና የተጫወተው እሱ ነው…ቡና እያለን ብዙ ጊዜ የመፈረምና የመሰለፉ እድል ባላገኘንበት ጊዜ እድሉ ደረጃ እኔ ኃላፊነት እወስዳለሁ ብሎ መንገዱን የከፈተልን እሱ ነው…ለሐረር ሲቲ 6ዐ ሺ ብር ተከፍሎ…እንድንዛወር በማድረጉ እድሉ ሊመሰገን ይገባዋል…በኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ የማድረግ እድሉን የከፈተልኝ አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ ነው…በአባይ ግድብ ዋንጫም በፕሪሚየር ሊግም ደፍሮ ያስገባኝ አሱ ነውና በትልቁ መመስገን አለበት…አሁን በቡና ደግሞ ካሳዬን ደጋግሜ አመሰግነዋለሁ…ለአሁኑ ስኬቴ የእሱ ድርሻ ከፍተኛ ነውና መመስገን አለበት..ወደ ብ/ቡድን ስትመጣ የበፊቱ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ያውም ጉዳት ላይ እያለሁ እምነት ጥሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ለብ/ቡድን የመረጠኝ እሱ ነውና አብርሽ ሊመሰገን ይገባዋል…አሰልጣኝ ውበቱም ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማሳለፍ ታሪክ የሠራው ቡድን አባል እንድሆን ዕምነት ጥሎ ስለመረጠኝ አመሰግነዋለሁ…ስማችሁን የዘነጋኋችሁ ካላችሁ ይቅርታ እየጠየኩ በእኔ ህይወት ላይ አሻራ ያሳረፋችሁትን በሙሉ ከልቤ ላማሰግን እወዳለሁ…”

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.