“ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሰበሰቡትን ኮከቦች ማኔጅ የሚያደርግ አሰልጣኝ አግኝቷል ብዬ አላምንም” አብዱልከሪም መሃመድ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

“ቅዱስ ጊዮርጊስ አራት ዓመት ዋንጫ ያጣው በኛ ጊዜ መሆኑ ለታሪክ ተወቃሽነት ዳርጎናል”

“ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሰበሰቡትን ኮከቦች ማኔጅ የሚያደርግ አሰልጣኝ አግኝቷል ብዬ አላምንም”
አብዱልከሪም መሃመድ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ባለፉት አራት አመታት ቅዱስ ጊዮርጊስ የዋንጫ መደርደርያ ላይ የተጨመረ ዋንጫ የለም ይሄ ደግሞ በክለቡ ታሪክ ላይ አልነበረም ባለፉት አራት አመታት ጅማ አባጅፋር፣ መቐለ 7ዐ እንደርታ፣ ኮቪድ 19ና ፋሲል ከነማ የዋንጫው ቁጥር በፈረሰኞቹ ቤት እንዳይጨመር አድርገዋል፡፡ ለ2ዐ14 ደግሞ ቆም ብሎ የማሰቢያ ጊዜው አሁን ነው… 2ዐ13 እንዴት አለፈ? የውጤት እጦቱ ዋነኛ ምክንያት ምንድነው? በናንተ የፊርማ ዘመን ቅዱስ ጊዮርጊስ ለምን ተዳከመና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ከቅዱስ ጊዮርጊሱ አብዱልከሪም መሀመድ /ተርሚኔተር ጋር ያደረገው ቆይታ ይህን ይመስላል፡፡

ሀትሪክ፡- እረፍቱን እንዴት አገኘኸው…?

አብዱልከሪም፡- ጥሩ ነው…ለቀጣዩ አመት መዘጋጀት የግድ ስለሚል በተወሰነ ጊዜ ልምምዴን አላቋረጥኩም… እግር ኳስ ተጨዋች ዝም ብሎ ማረፍ የለበትም… በእረፍት ጊዜዬ ትልቁ ጉዳይ ቤተሰቦቼን በደንብ ማግኘቴ ነው ፡፡

ሀትሪክ፡- የ2ዐ13 የውድድር አመትን እንዴት አለፈ…?

አብዱልከሪም፡-ከኮቪድ 19 እና ከውጤት አንፃር ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል ብዬ አላስብም.. በኮቪድ 19 ምክንያት ተመልካች የለም… ውድድሩ ላይም ውጤት የለምና በጥሩ ጎኑ አላየሁትም… በተለይ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተሰብ ጥሩ ጊዜ ነበር ማለት አልችልም፡፡

ሀትሪክ፡- ጫና ነበረባችሁ አይደል?

አብዱልከሪም፡- ጫና ውስጥ ነበርን እውነቱ ጥሩ ጊዜ አልነበረንምና ውጤት መጥፋቱ ጫና ውስጥ ከቶናል ጊዮርጊስ ትልቅ ክለብ እንደመሆኑ ውጤት ይጠበቅብሃል ውጤቱ ከሌላ ደግሞ ጫናው ይቀጥላል፡፡

ሀትሪክ፡- በኮቪድ 19 የተቋረጠው አመትን ጨምሮ ባለፉት 4 አመታት ዋንጫ የለም… ለጊዮርጊሶች አይከብድም…?

አብዱልከሪም፡-ይሄ ደግሞ የሚያበሳጭ ነው ክለባችን ባለፉት ዘመናት ይህን መሠል ታሪክም የለውም በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ውጤት መጥፋት ያልተለመደ ነው… እንደግል ለጊዮርጊስ ከፈረምኩ ጀምሮ ዋንጫ አልወሰድኩም ምናልባት ለሻምፒዮናነት ተቃርቤያለው ብዬ የማስበው በ2ዐ1ዐ ላይ ነው ያው ጅማ አባጅፋር ተገቢ ባልሆነ መንገድ ዋንጫውን ማንሣቱ ይታወቃል፡፡ ከዚያ ውጪ በነበሩ አመታቶች ሻምፒዮቹ የተሻለ ነጥብ አምጥተው ያሸነፉበት ነው በየአመቱ ሻምፒዮን መሆን የለመደ ቡድን እንዲህ መሆኑ ቅር ያሰኛል የዋንጫ አሸናፊነቱን አለማስቀጠላችን እንደግል ደስተኛ አይደለሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ አራት አመት ዋንጫ ያጣው በእኛ ጊዜ መሆኑ ለታሪክ ተወቃሽነት ዳርጎናል ውጤት በመጥፋቱም ጥሩ ስሜት እየተሰማን አይደለም፡፡

ሀትሪክ፡- የፋሲል ከነማ ድል አሳመነህ…?

አብዱልከሪም፡- የዘንድሮ የፋሲል ከነማ ድል ምርጥ ነው ጥሩ ቡድን በመሆኑ በአሳማኝ ውጤት ሻምፒዮን ሆኗል ይሄም እውነት ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ውጤት ያጣው በተጨዋቾች፣ በአሰልጣኞች ወይስ በተጋጣሚ ክለቦች ጥንካሬ…?

አብዱልከሪም፡-ዋንጫ ያሳጣን የተቃራኒ ቡድን ጥንካሬ አይደለም የትኛውም ክለብ ከኛ የተሻለ ስብስብ አለው ብዬም አላምንም ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሰበሳቡትን ኮከቦች ማኔጅ የሚያደርግ አሰልጣኝ አግኝቷል ብዬ አላምንም አሰልጣኞቹ ያለውን ስብስብ ማኔጅ ቢያደርጉ ኖሮ ከሁሉም የተሻለ ስኳድ ስላለን ውጤታማ እንደሆን ነበር ብዬ ነው የማስበው.. ያ ነው ችግሩ፡፡

ሀትሪክ፡- ቡድኑ ውስጥ አንድነት አልነበረም ተከፋፍለዋል የሚሉ መረጃዎች ነበሩ… እውነት ውሸት…?

አብዱልከሪም፡-ቡድናችን ውስጥ መከፋፈል ብሎ ነገር የለም፡፡ ውስጡ እንዳለ አንድ ተጨዋች አልተከፋፈልንም ይሄ ውሸት ነው ምናልባት በዲሲፕሊን ችግር ከታገዱት ተጨዋቾች ውጪ ቡድኑ ውስጥ ጥሩ ግንኙነት እንጂ መከፋፈል አልነበረም፡፡

ሀትሪክ፡- ፉክክሩን እንዴት ገመገምከው? በ13ቱ ቡድኖች መሃል ልዩነት የለም የሚሉ ወገኖች አሉ…?

አብዱልከሪም፡- /ሳቅ/ ፉክክሩ አሪፍ ነበር ፋሲል ከነማ በርቀት መርቶ ሻምፒዮን መሆኑን አስቀድሞ አረጋግጧል ከዚያ በኋላ ሁለተኛ ለመሆን የነበረው ፉክክር ቀላል የሚባል አልነበረም እንደበፊቱ የጥሎ ማለፍ ውድድር ስላልነበረና በኮንፌዴሬሽን ካፕ ለመሳተፍ ፍልሚያው ለሁለተኝነት ነበርና ጥሩ ፉክክር ነበር በተለይ በአራት ቡድኖች መሃል የነበረው ፍልሚያ ከባድ ነበር፡፡ ደመወዝ የተከፈለውም ይሁን ያልተከፈለው ክለብ መሀል ተቀራራቢ ፉክክር ነበር ምናልባት ማንም ተጨዋች ደመወዝ ተከልክሎም ቢሆን ለቀጣይ ዝውውር ጥሩ ሆኖ ራሱን ማሳየት ስለሚፈልግ ገንዘቡን አስቦ ወርዶ ሲጫወት አላየሁም ራሱን ለገበያ የሚያቀርበው ጥሩ ሲሆን ነውና… የቡድኖቹ አቋም ላይ ልዩነት ብዙም የለም የሚለው ልክ ይመስለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ከአቋም በታች መጫወትም ሆነ መላቀቅ እግር ኳሱ ላይኮ አለ… የለም እያልክ ነው…?

አብዱልከሪም፡-ከዚህ በፊት ይሄ ጉዳይ በኛ ሊግ ላይ ተከስቶ ይታወቃል መላቀቅም ሆነ ከአቅም በታች መውረድ ነበር አሁን ግን ይሄ አለ ብዬ አላምንም ጨዋታዎቹ በዲ.ኤስ.ቲቪ መታየታቸውና ግጥሚያዎቹ ሁሉ መቀረፃቸው ሁሉም ጠንካራ ሆኖ እንዲቀርብ አድርጓል፡፡ መላቀቁም ከአቅም በታች ወርዶ መጫወቱም ብዙ የሚቻል አይመስለኝም፡፡
ሀትሪክ፡- የኮከቦቹን ምርጫ ተቀበልከው…?
አብዱልከሪም፡-አዎ ምርጫው ለኔ ተመችቶኛል አቡበከር በሜዳ ላይ አራት ሀትሪክ በሽልማቱም መድረክ ላይ ተጨማሪ ሀትሪክ መስራቱ ጥሩ ጊዜ እንደነበረው ያሳያል፡፡

ሀትሪክ፡- ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የምትለው ነገር አለ…?

አብዱልከሪም፡-ባለፉት 4 አመታት ዋንጫ አለማሸነፋቸው ያልለመዱት ነገር ነው በዚህ አመት ሻምፒዮን መሆን ባንችል ሁለተኛ ሆነን በአፍሪካ መድረክ አለመሳተፋችን ቅር ያሰኛል ደጋፊው ፕሪሚየር ሊግ ማሸነፍ የለመደ ነው በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ተሳታፊ ለመሆን እያሰበ ከዚያ በታች መሆን ደጋፊው ላይ የሚፈጥረው ህመም አለ.. ያንን ለመርሳት ቀጣይ አመቶች ላይ የምንችለውን ማድረግ አለብን ያሳለፍናቸው አመታቶች እንዴት አለፉ? ዋንጫስ ለምን አላገኘንባቸውም ብለን ትምህርት መውሰድ አለብን በፊት የነበረው አልሸነፍ ባይነቱ የት ሄደ? ብለን መመርመር የግድ ነው ከዚህ ተምረን ለቀጣዩ አመት የተሻለ ቡድን እንደሚሰራ ተስፋ አደርጋለሁ… ካለፉት አመታት ውጤት ተነስተን ተጨዋቹም አሰልጣኙም ሙሉ ቡድኑ ይማርበታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ከዚህ አንፃር የተሻለውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ማየት ይቻላል ብዬ አስባለው፡፡

ሀትሪክ፡- ነጥብ በመጣላችሁ የተከፋህበት ጨዋታ የትኛው ነው…?

አብዱልከሪም፡-በጣም ቅር የተሰኘንበት ጨዋታ ባህርዳር ላይ በፋሲል ከነማ 1ለዐ መረታታችን ነው፡፡ ቢያንስ ጨዋታው በአቻ ውጤት አለቀ ብለን እያሰብን ባለንበት ሰዓት የተሰጠብን የፍፁም ቅጣት ምት መቆጠሩና መሸነፋችን አበሳጭቶኛል ፋሲል ከነማ ጨዋታውን ማሸነፉ ብዙ ትርጉም ነበረው እኛን መርታታቸው ይበልጥ ለዋንጫው እንዲንደረደሩ እኛን ደግሞ ከዋንጫው እንድንርቅ ማድረጉ ቅር ያሰኛል አሁን ድረስ ነው የምቆጨው፡፡

ሀትሪክ፡- ግን ግን… የኢንተርናሽናል አርቢትር ቴዎድሮስ ምትኩ ውሣኔ ልክ አልነበረም…?

አብዱልከሪም፡- በሰዓቱ ከሜዳ ሳንወጣ ውሣኔው ልክ አልነበረም ብለን ነበር…በኋላ ላይ ግን ቪዲዮውን ስመለከት የዳኛው ውሣኔ ትክክል እንደነበርና የፍፁም ቅጣት ምት ያሰጥ እንደነበር አምኛለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ኮንትራትህ ሰኔ 3ዐ/2ዐ13 ይጠናቀቃል…ኮንትራት ስለማደስ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እየተነጋገራችሁ ነው…?

አብዱልከሪም፡-እስካሁን ከማንም ጋር አልተነጋግርኩም ያወራሁት ክለብም የለም ከማንም ጋር የተፈጠረ ግንኙነት የለም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ውሌን ለማደስ ከፈለገ በሬ ክፍት ነው ለፊርማ ክለቤ ቅድሚያውን ይወስዳል ጊዜው ገና ስለሆነ ይሆናል… እስካሁን ድረስ ማንንም አላወራሁም…የክለባችንን አመራሮች ስልክ ግን በመጠበቅ ላይ እገኛለሁ፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport