የአቶ መኮንን ኩሩ ዝምታን የሠበረ አነጋጋሪ ቃለ-ምልልስ “ውጪ ተምረን መጥተናል፣ ኢንተርናሽናል ላይሰንስ አለን የሚሉ ሰዎች ነገሮች ሁሉ ዓሣ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል እንዳይሆንባቸው እሰጋለሁ”

 

የአቶ መኮንን ኩሩ ዝምታን የሠበረ አነጋጋሪ ቃለ-ምልልስ

“ውጪ ተምረን መጥተናል፣ ኢንተርናሽናል ላይሰንስ አለን የሚሉ ሰዎች ነገሮች ሁሉ ዓሣ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል እንዳይሆንባቸው እሰጋለሁ”


የተቀመጡበት ወንበር ከየአቅጣጫው የትችና የወቀሳ ናዳ ቢወርድበትም እሳቸውን ገፍትሮ ከጽ/ቤት ሊያስወጣቸው አልቻለም፤አሁን በቅርቡ ግን የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳይሬክተር ለሚሰነዘርባቸው ትችና ወቀሳ ተሸንፈው እጅ ሰጥተው ከኃላፊነታቸው በገፃ ፍቃዳቸው ለቀዋል፤ የሚል ወሬ በስፋት በመናፈሱ የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዴተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ወደ አቶ መኮንን ኩሩ የእጅ ስልክ ደውሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር ማነው?ብሎ እራሣቸውን የቴክኒክ ዳይሬክተሩን ጠይቆ ቢያስደነግጣቸውም “ከእኔ ውጭ ማን?”የሚል የጠነከረ በራስ የመተማመን ስሜት የተሞላበት ምላሽም ሰጥተውታል፡፡ የብዙዎች አይንና ቀልብ ያረፈበትን ቦታ በበላይነት ይዘው የሚመሩት አቶ መኮንን ኩሩን ጋዜጠኛው “ከኃላፊነት ለቀቁ” የሚለውን ጫፍ ይዞ ገብቶ የሆዳቸውን አናዟቸው ተመልሷል፡፡ አቶ መኮንን ኩሩ ራሳቸውን ከማርዮ ባላቶሊ ጋር በማመሳሰል ለማሳየት ስለሞከሩበት ጉዳይ፣ከዚህ በፊት ሪዛይን አድርገው ዳግም ስለመመለሳቸው በሚደርስባቸው ትችት የእሳቸውም የቤተሰቦቻቸውም ስሜት ምን እንደሚመስል ለጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ምንም ሳይደብቁ አጫውተውት እሱም…ከዚህ በታች ባለው መልኩ ለአንባቢያን አቅርቦታል፡፡


ሀትሪክ፡- በቅድሚያ ለቃለ ምልልሱ ስለተባበርከኝ አመሰግናለሁ ከማለቴ በፊት በየትኛው ኃላፊነትህ ነው የምጠራህ…?…የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር…?…ብዬ ወይስ የቀድሞ …የቴክኒክ ዳይሬክተር…?

አቶ መኮንን፡- …ማለት አልገባኝም…እንደዚህ የሚያሻማና የቀድሞ የሚያስብል ምን ነገር መጣ…?

ሀትሪክ፡- …እሺ ይሄንን ተወው… በአሁን ሰዓት የኢትዮ ጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር ማነው…?

አቶ መኮንን፡- …ሰውዬ ምን ሆነሃል…?…እኔው ነኛ…?…ማን ይሆናል ብለህ ነው…?…ቦታውን ጥቂቶች ተመኝተውት ይቃዣሉ እንጂ…እስከ አሁን ቦታው ላይ…ቢሮው ውስጥ…በስራ ላይ ያለው መኮንን ኩሩ ነው…፡፡

ሀትሪክ፡- ….እርግጠኛ ነህ…?…ለቀሃል…..ሪዛይን አድርገሃል ተብሎ እኮ በስፋት እየተወራ ነው…?

አቶ መኮንን፡- …(በጣም ያላባራ ሣቅ)…ህልመኞች የማያወሩት…የማያስወሩት ነገር የለም…፤ እውነታውን ንገረኝ ካልከኝ እስከ አሁን ሪዛይን አላደረኩም…እንደዚህ አይነት ነገርም የለም፤ስራዬንም በአግባቡ አክብሬ እየሠራሁ ነው፤ከቦታው እንድለቅ ብዙዎች እንቅልፍ አጥተው እየሰሩ ነው… ለአመታትም ፌዴሬሽኑ የእኔ የግሌ እስኪመስል ድረስ ግለሰባዊ ዘመቻ ተከፍቶብኝ ነው ያለሁት፡፡ የተከፈተው ዘመቻና የተቀነባበረው ሴራ ቦታው ላይ የሚያስቀምጥ አልነበረም፤ሁሉንም በፅናትና በጥንካሬ ተቋቁሜ ቦታ ሳልሰጥ የወደፊቱን ባለውቅም አሁን ግን እየሰራሁ ነው፤ሪዛይን አላደረኩም።

ሀትሪክ፡- …አንተ የምትለው ሌላ…እኔ የሰማሁት ደግሞ ሌላ ነው…ባለፈው ከጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጋር ተጋጭተህ ሪዛይን አድርገሃል መባሉስ…እሱም ውሸት ነው?

አቶ መኮንን፡- …እኔ ከጽ/ቤት ኃላፊው ጋር አልተጋጨሁም፤የሚያጋጨንም የሚያገናኘንም ነገር የለም፤ የጽ/ቤት ኃላፊው ገና ወጣት ነው፤ብዙ ሊሠራ…ሊማር…ሊያስተምር የሚችል ልጅ ነው፤ከእሱ ጋር ተጋጭቷል የሚባለው…ከየት መጥቶ እንደሆነ አላውቅም…ይሄ ለእኔ አዲስ ነገር ነው….፡፡

ሀትሪክ፡- እንዴ አቶ መኮንን ሁሉም የፌዴሬሽኑ ዲፓርትመንቶች ሪፖርት አቅርቡ ሲባሉ አለማቅረብህ የግጭቱ የልዩነት ምክንያት እንደሆነ ነው እየተነገረ ያለው…ሪፖርትስ አላቀርብም ብለሃል?
አቶ መኮንን፡- ..ሪፖርት ለምን አላቀርብም እላለሁ?ሪፖርት ማቅረብ ለእኔ አዲስ ነገርም አይደለም ፤ሪፖርት በማቅረብ ችግርም የምታማ አይደለሁም፤ላለፉት 27 አመታት እንኳን የአንድ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ቀርቶ…የአንድ ሚኒስቴር መ/ቤትን ሁሉ BPR፣ BPS እያልን እያቀናጀሁ ሳዘጋጅ ሳቀርብ የነበርኩ ሰው ነኝ…አንዳንዴ ከኪስ እየወጡ የሚወሩ ወሬዎች ለእኔ It is so funny (በጣም አስቂኝ) ናቸው፤ይሄን የሚያወሩ ሰዎች እነማን እንደሆኑ እኔም ህዝብም በደንብ ስለምናውቃቸው ብዙም አልገረምም፡፡
ሀትሪክ፡- በአንተ ጉዳይ ላይ በዝርዝር እናወራለን…ከዚያ በፊት ግን አንድ ነገር ልጠይቅህ…ኢትዮጵያ በአሁን ሰዓት ኢንስትራክተር ተብለው የሚጠሩ ባለሙያዎች አሏት?

 

አቶ መኮንን፡- …መጠርጠሩስ…?…አዎን አሏት…?

ሀትሪክ፡- …የኢንስትራክተርነት ፈቃድ የሚታደስ (Renew) የሚደረግ በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን ኢንስትራክተሮች ደግሞ ይሄን ባለማድረጋችሁ ኢንስትራክተርነታችሁ እንደተሰረዘ እየተወራ ህዝቡ ውዥንብር ውስጥ ገብቷል፤ፕሬዚዳንቱ ኢሳያስጅራም ይሄን አረጋግጠዋል የሚሉ አሉ እውነት ነው?

አቶ መኮንን፡- ተራ ውሸት ነው…ፕሬዚዳንቱም እንደዚህ አይነት ስህተት አይሰሩም፤በእርግጠኝነት የማረጋግጥልህም ፕሬዚዳንቱ ዝም ብለው የሚብጠለጠሉ አይነት ሰውም አይደሉም፤ከዋናው ጥያቄህ በፊት ስለ እሣቸው አንድ ነገር ብዬህ ባልፍ ደስ ይለኛል…ለበርካታ አመታት ከ86 አመት ጀምሮ ፕሬዚዳንቱን አውቃቸዋለሁ፤በወጣትነት ዘመናችን ምንአልባት እኔ ትንሽ ሳልበልጣቸው አልቀርም ምርጥ የመረብ ኳስ ተጨዋች እንደነበሩ ነው የማስታውሰው…ቁመናቸውም ሁሉ ነገራቸውም ለዛ የሰጠ ነው፤ከዚያ በኋላ በኃላፊነት ላይ ተቀመጡ…ትልቅ ስራ ሲሰሩ…ክለበ ሲመሩ የነበሩ ሰው ናቸው፤ ተምረዋልም፤ስለዚህ ህይወታቸው ከስፖርት ጋር የተሳሰረ በመሆኑ በቀላሉ የተሳሳተ ነገር ይናገራሉ ብዬ አላስብም…ይሄ ተራ ወሬና ውሸት ነው…፡፡

ሀትሪክ፡- …እስቲ አንተ ራስህ በአንደበትህ አረጋግጥልኝ…ኢትዮጵያ በአሁን ሰዓት በእርግጥም ኢስትራክተሮች አሏት?

አቶ መኮንን፡- …አዎን በትክክል አሏት…፤…ያውም በጣም የተከበሩ ኢንስትራ ክተሮች አሏት፡፡

ሀትሪክ፡- …የኢንስትራክተርነት ሰርተፌኬቱ ሳይታደስላችሁ ኢንስትራክተር ብሎ መጥራት እንዴት ይቻላል ?

አቶ መኮንን፡- ምን መሰለህ ይሄ የካፍ ጉዳይ ነው፤እድሳት የማድረግ ያለ ማድረግ ጉደይ የካፍ ነው የሚሆነው፤አሁን ደግሞ ጊዜው ይታወቅል…ካፍ በሪፎርሜሽን ላይ ነው ያለው፡፡ከኢሳ ሃያቱ ቢሮ መልቀቅ ጋር በተያያዘ እነሱ የለውጥ ሥራ ላይ ናቸው፡፡ አይተህ ከሆነ የላይስንስኒግ ስራዎች ቆመዋል፤ካፍ በሪፎርም ላይ ነው፤በዚህ ምክንያት ጊዜ ወስዷል፤አሁን ወደ ኮንፌቬሽን መጥቷል… ኮንፌቬንሽን ለሁላችንም አድሏል በዚያ በኮንቬንሽን መሠረት ከሆነ ለመራት ጥረት እያደረግን የለነው፡፡ ድሮ ታውቅ እንደሆነ አላውቅም ከእነ ማንዋሉ ነበር የሚልክልን…ኮንቬንሽን አልነበረም ካፍ C.D.A ላይ ማንዋል ልኮልናል…አሁን ግን እያደረገ ያለው ምንድነው…እውቀት ለምንድነው ከአንድ ቦታ የሚፈሰው… ደግሞ ናሽናል ፌዴሬሽኖች ለምን የራሳቸውን ማንዋሎች አያዘጋጁም በሚል ኮንቴንቱን ብቻ ልኮልን ሲሌበሱንና ማንዋሉን እንድናዘጋጅ ልኮልን ሄደንበታል፡፡ በአጭሩ ግን ኢስትራክተሮቻችን ታደሰላቸው አልታደሰላቸው የእውቀት ሰዎች ናቸው፤ማሳደስ አላማሳደስ ማለት ተዓምር ተደርጎ መወራት የለበትም፤ማሳደስ ማለት እኮ ሁለት ቀን ሶስት ቀን ሄደህ በሆነ አርአስት ላይ ተገናኝተህ እንደገና መምጣት ሰርቲፋይድ መሆን ማለት ነው፤ይሄ ደግሞ የአውቀት መጨረሻ ተደርጎ ሊታይ አይገባም፤ትልቁ ነገር አንተ ማንበብ መቻልህ ነው፤አልታደሰም …ሪፍሬሽ…አልተደረገም የሚለው ተራ የማምታቻ ነገር ካልሆነ በስተቀር ትርጉም የለውም፤ስለዚህ ኢንስትራክተሮቻችን አሉ፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ደካማ እግር ኳስ ይዛ ኢንስትራክተሮቿ በጣም በዝተውባታል የሚሉ አሉ ይሄ ሃሳብ ይመቸሃል?

አቶ መኮንን፡- በፍፁም አይመቸኝም፡፡ ሃሳቡም ጤነኛ ነው ብዬ አላስብም፡፡ አንተ እንዳልከው እኔም እሰማለሁ፡፡ በየሚዲያው እየቀረቡ ይሄ ሁሉ ኢንስትራክተር ምን ይሰራል? ይላሉ፡፡ ለ100 ሚሊዮን ሕዝብ ባለበት ሀገር 100 ኢንስትራክተር ያንስ እንደሆነ እንጂ አይበዛም፡፡ 100 ኢንስትራክተር በዝቷል ማለት ጤነኝነት አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች እኮ እውቀት የሚያሸጋግሩ የሚያበቁ ናቸው፡፡ ሊመሰገኑ እንጂ በዙ ተብለው ለወቀሳ መቅረብ የለባቸውም፡፡

 

ሀትሪክ፡- ይሄን ነገር ካነሳን ኢንስትራክተሮቹ የብቃት ችግር አለባቸው በሚልም ይታማሉ? እውነት ይሄ ችግር ኢንስትራክተሮች ላይ አለ?

አቶ መኮንን፡- እየሰማን ያለው ነገር በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ በድፍረት “ኢትዮጵያዊያን ኢንስትራክተሮች አቅም የላቸውም አይመጥኑም” እስከማለት ተደርሷል፡፡ ይሄ ትልቅ ስድም ነው፤ እነዚህ ሰዎች እኮ ተጠቃሚ አይደሉም፤ ስፖርቱን ነው የሚያግዙት፡፡ አሰልጣኝ እኮ ስትሆን ደሞዝተኛ ነህ ተጠቃሚ ነህ ልብ አድርግ በራሳቸው ፍላጎት ሪፈር አድርገው ማንዋል አዘጋጅተው በመመሪያው መሠረት ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት እስከማታ 12 ሰዓት አንዴ በክፍል አንዴ በሜዳ ላይ የሚያስተምሩ ሰዎች ናቸው፡፡ በቀን 250 የሚያገኙ ሰዎች ለአንተ 250 ብዬ ጊዜዬን አላጠፋም ቢሉ ማን እውቀት ትራንስፈር ያደርጋል? እነዚህ ሰዎች ሊከበሩ፣ ሊመሰገኑ ሲገባቸው እንደገና የሚብጠለጠሉበት ምክንያት የለም፡፡ እንደዚህ የሚሉ ሰዎች ከዳር ሆነው ድንጋይ ከሚወረውሩ ዕውቀት አለን የሚሉ እስቲ ይቀላቀሉንና በጋራ እንስራ አሁን የሚታየው በየሚዲያው እኔ እንዲህ ነኝ የሚል ባዶ ፉከራ ነው፡፡ ከውጪ ይዘን የመጣነው እውቀት፣ ልምድ አለን የሚሉ ከሆነ እውነት ካላቸው እስቲ ይምጡና አብረን እንስራ አሁን የእኔ ቦታ ከሆነ ራስ ምታታቸው ይምጡና አብረን እንስራ አገሪቷ ሰፊ ናት፡፡ እውቀት አለ ሀብት አለ ምን የሚያጣላን ነገር አለ ይሄ ነገር እንደውም አንድ ተረት ያስታውሰኛል፡፡

ሀትሪክ፡- .. ምንአይነት ተረት..?

አቶ መኮንን፡- “ሬሳው ያለው መሬት ላይ ነው፤ አሞራዎች ግን ሰማዩ ላይ ይጣላሉ” የሚል (በጣም ሳቅ) ስራው መሬት ላይ ነው እነሱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ላይ ወጥተው መጣላትን ይመርጣሉ፡፡

ሀትሪክ፡- አብዛኞቻችሁ ለሌሎች የመጣውን የኢንስትራክተርነት ዕድል ወስዳችሁ ነው ኢንስትራክተር የሆናችሁት የሚባል ሀሜትም አለ..?. ሀሜቱ ይዋጥልሃል?

አቶ መኮንን፡- መዋጥ አይደለም ያቅረኛል፡፡ ምክንያቱም ውሸት እንዴት ይዋጥልሃል፡፡ ይሄ ፍፁም ውሸት ነው እኔ ሃይማኖት፣ እምነት ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ ለሰው መብት የምታገል እንጂ የአንዱን ዕድል ለሌላ አሳልፌ የምሰጥ አይነት ሰው አይደለሁም፡፡ ጥያቄህን አክብሬ ልመልስ ብዬ እንጂ እንደዚህ አይነት ተራ ወሬ አይመጥነኝም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የማውቀው ነገር የለም፡፡ እንደውም ይሄን በተመለከተ የሰማሁት ነገር ምንድነው አንድ የስራ ባልደረባችን ወደ ካይሮ ተጠርቶ በእሱ ምትክ ሌላ ሄደ ነው 2010 ላይ፡፡ 2010 ላይ ደግሞ መኮንን ኩሩ የለም፡፡ 2009 ላይ ወጥቼ 2011 ነው የተመለስኩት፡፡ ስለዚህ በሌለሁበት ነው እየተጠራው ያለሁት፡፡ እኔ በተፈጥሮዬ (Evill) ሰይጣናዊ የሆነ ነገር የለብኝም፡፡

ሀትሪክ፡- ከውጭ ተምረው ሰልጥነው ለመጡ ሰዎች ጥሩ ስሜት የለህም ወደ ፌዴሬሽኑ እንዲጠጉም አትፈልግም ይባላል…?

አቶ መኮንን፡- በመጀመሪያ እነማን ናቸው ከውጪ የመጡት? ውጪ ሰልጥነው ለመምጣታቸው ምንድነው ማስረጃው? የሚለው መፈተሽ አለበት፡፡ አሁን ሕዝቡን እያምታታ ያለው ይሄ ነው፤ ውጭ ተምረው መጥተዋል ሰልጥነዋል ለማለት በየሚዲያው በማውራት ብቻ ሳይሆን ትክክለኛውን ማስረጃ በማቅረብ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ፎቶ ኮፒ አቅርበህ ብቸኛ የፕሮ ላይሰንስ ያለኝ ስላልክ አይደለም፤ እኔ እንደውም በዚህ አጋጣሚ እነዚህ ውጪ ተምረን ኢንተርናሽናል ላይሰንስ ምናምን ለሚሉ ሰዎች አንድ ተረት ባስታውሳቸው ደስ ይለኛል፡፡ ነገሮች ሁሉ “ዓሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል” እንዳይሆንባቸው እሰጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ከውጭ ተምረን መጥተናል ላይሰንስ አለን ከሚሉ ጋር አብሮ የመስራት ዝግጅነቱስ አለህ?

አቶ መኮንን፡- ትክክለኛውን ነገር ይዘው ለሚመጡ ትክክለኛ ማስረጃ ካላቸው ጋር አብረን እንስራ ብዬ ጠይቄያለሁ፡፡ አብሬ ለመስራትም ሞክሬ ነበር፡፡ አብሮ ለመስራት ግን ማን ከለከለ… ኢትዮጵያ እኮ ሰፊ ናት ከውጪ የመጣውን ዕውቀት ሼር ሊያደርጉ እንጂ እኔን ወደ ጎን በመግፋት ቦታውን ለመቆጣጠር እንቅልፍ ማጣት አልነበረባቸውም፡፡
“እኔ ይሄን ተምሬ መጥቻለሁ፤ የብቸኛ ላይሰንስ ባለቤት ነኝ” ምናምን እየተባሉ የሚወሩ ነገሮች ጥንቃቄ ቢወስድባቸው መልካም ይመስለኛል ነው ምክሬ፡፡

ሀትሪክ፡- ባለፈው ከዚህ ከውጪ መጥተናል ተምረናል የሚሉትን ሰዎች የሚያጠቃ የመልስ ምት የሚመስል አስተያየት ለሚዲያ ሰጥተህ ሰምቼ ነበር ከውጭ ስልጥነን መጥተናል የሚሉት የማሳጅ ስልጠና ወስደው ነው የሚል አነጋጋሪ አስተያየት ሰጥተሃል ምን ማለት ነው አልገባኝም?

አቶ መኮንን፡- እንደውም ይሄን ነገር እንኳን አነሳኸው በሰዓቱ ማሳጅ ብዬ የተናገርኩት ተሳስቼ ነው በዚህ አጋጣሚ ማሳጅ የሚለውን የአምቡላንስና የተጎዱ ተጨዋቹን በስትሬቸር ከሜዳ የማውጣት ስልጠናን ከሚድልስብሮ ክለብ መውሰዳቸውን የሚያሳይ ስልጠና ዶክመንት ነው እጄ ላይ የደረሰው፤ ለአንተም ላሳይህ እችላለሁ (ከእጅ ስልካቸው ላይ እያሳዩኝ) እኔ ይሄንን ሁሉ የማንሣት ፍላጎትም የለኝም፤ ሙያ ነው ሙያቸው ደግሞ መከበር አለበት፤ ግን እኔ እንዲህ ነኝ ሀገር እየጠሩ እዚህ ተምሪያለሁ የፕሮ ላይሰንስ ባለቤት ነኝ የሚባለው ተረትም ይመስለኛል ፕሮ ላይስንስ የለም አለም አቀፍ ላይሰንስ አይሰጥም፡፡ ማንኛውም ተቋም አለም አቀፍ ላይሰንስ አይሰጥም በዓለም ላይ ያሉ ላይሰንሶች ሁለት ናቸው፤ አንደኛው ብሔራዊ ላይሰንስና ኮንትኔንታል ወይም ፊፋ፣ ካፍ የኤሺያ የአውሮፓ ካልሆነ በስተቀር ወይም የኢትዮጵያ፣ የካናዳ፣ የአሜሪካ፣ የጀርመን፣ የጣሊያን የሚሰጡት ካልሆነ በስተቀር የለም፡፡ አንዳንዴ የሚያወሩት ደግሞ ያስቅሃል የህይወት ዘመን ላይሰንስ ሁሉ አለኝ ተብሎ በድፍረት ነው የተነገረው እንዴት የህይወት ዘመን ላይሰንስ ይሰጣል?

ሀትሪክ፡- በዚህ አይነት ህዝቡ ጋር ሲደርስ የነበረው የተሳሳተ መረጃ ነው ማለት ነው?

አቶ መኮንን፡- .. እንግዲህ በለው… ከወሬው በስተቀር መሬት ላይ ወርዶ ያየነው ነገር የለም እንደዚህ አይነት አቅም ላይሰንስ ያለው የተማረ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ሲጨቃጨቅ እግር ኳሱን ሲያተራምስ አይደለም ላለፉት ሰባት ስምንት አመት ይሄን ሲያወሩ ከመስማት በስተቀር መሬት ላይ ወርዶ የተሰራ ነገር የለም፡፡ አዲስ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ፣ አዲስ የቴሌቪዥን ጣቢያ በተከፈተ ቁጥር እየተንጠለጠሉ ሰው ማብጠልጠል ነው ስራቸው ይሄ እነሱ በየሬዲዮ ቴሌቪዥን ጣቢያ እየተንጠለጠሉ ባወሩ ቁጥር ለእኔም እሳት የማጥፋት ስራ ፈጥሮልኛል፡፡ ተረት አበዛህ አትበለኝ እንጂ ይሄም አንድ ተረት ያስታውሰኛል..

ሀትሪክ፡- ምን አይነት ተረት…. ?

አቶ መኮንን፡-በልጅነቴ ምን ትዝ ይለኝ መሰለህ አይጦች ከአንዱ ጉድጓድ ወደ ሌላው ጉድጓድ ይገባሉ እዚህ ገብተዋል ብለህ ወደ ጉድጓዱ ስትሄድ ወደ ሌላኛው ጉድጓድ ይገባሉ የእነሱ ድርጊትም የእነዛን አይጦች ነገር ነው የሚያስታውሰው፡፡

ሀትሪክ፡- ለቦታው አይመጥንም የሚለው አስተያየትስ ስሜት ይሰጥሃል?

አቶ መኮንን፡-የት ያውቁኛል አንተ እኮ የአንድን ሰው ለቦታው መመጠንና አለመመጠን መጀመሪያ አንተ ማወቅ አለብህ፤ ከሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል ያልዘለለ እውቀት ያላቸው እንዲህ ሊሉኝ አይቻሉም፤ እኔ እኮ በትምህርት ራሴን ለማስታጠቅ ሞክሬያለሁ እውነተኛ ዲፕሎምና የእውነተኛው የሁለተኛ ድግሪ ባለቤትም ነኝ የ27 አመት ልምድም ያለኝ ሰው ነኝ በብዙ ቦታ ከብዙ ታላላቅ ሰዎች ጋር የዋልኩ ነኝ፤ የእኔ ስምም በእነሱ ሊነሣ አይገባም ይሄ ለእኔ ተራ የሆነ ድፍረት ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በስልጠናው አለምስ ያለህ ታሪክ…?

አቶ መኮንን፡- እኔ የተመረቅኩት በስፖርት ነው ነገር ግን የባዮሎጂና የጂኦግራፊ መምህር ነበርኩ፤ ከተመረኩበት ውጪ በኃላፊነት መስራት ማለት በዲፕሎማ አስተምርም ነበር በሙያዬ የምታማ ሰው አልነበርኩም፡፡ ከዚያ ውጪ አልተጫወተም ብለው የሚያወሩት ወሬ አለ እግር ኳስ በእኔ የተጀመረ ይመስል፤ አሰልጥኜያቸው እስከ ብ/ቡድን የደረሱ ልጆች አሉ ብ/ቡድን ኢት.ቡና የተጨወቱ በጣም በርካታ ልጆች አሉ፤ ስማቸውን ጥራ ካልከኝ እነ አቤጋ ሊናገሩ ይችላሉ ደረጄ ኃይሉ /ባቢ/ብሩክን የመሳሰሉ ልጆችን መጥራት ይቻላል ከትላልቅ አሰልጣኞች ጋርም አብሬ ሰርቻለሁ፤ ከሟቹ ተስፋዬ ገብሩ፣ ከሟቹ ተረፈ ደጉ ጋር፣ ከሟቹ ታምሩ /ሙገር/ ጋር ሰርቻለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ለምስክርነት የጠራኋቸው በሙሉ አልፈዋል?

አቶ መኮንን፡- በአጋጣሚ የጠራኋቸው ሞተዋል በህይወት ቢኖሩ ዋቢ ይሆኑኝ ነበር፡፡ ከእነሱ ዉጪም ዋቢ የሚሆኑ አሉ በዚህ ደረጃ የሰራሁትን ሰው ምንም እንዳልሰራሁ ለመደምሰስ መሞከሩ ያሳዝነኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ውስጥህ ይሄ ሁሉ ዘመቻ ለምን እኔ ላይ ብሎ ጠይቆህ ያውቃል…?

አቶ መኮንን፡-በተለይ መጀመሪያ አካባቢ በጣም ብዙ ጊዜ ይጠይቀኛል አሁን ግን እኔ ብቻ ሣልሆን ሰውም ለአመታት ይሄ ዘመቻ ሲቀጥል ነገሩን እያወቀ እየታዘበ ሲመጣ ብዙም ቦታ አልሰጠውም፤ ይሄ ነገር ምን እንደሚያስታውሰኝ ታውቃለህ ማርዮ ባላቶሊን?

ሀትሪክ፡ ማርዮ ባላቶሊን እዚህ ጋር ደግሞ ምን አመጣው?

አቶ መኮንን፡-ማርዮ ባላቶሊ ማንቸስተር ሲቲ እያለ ትዝ ይልሃል ካልተሳሳትኩ ከማን.ዩናይትድ ጋር ተጫውተው 6ለ1 ባሸነፈበት ጨወታ የመጀመሪያውን ግብ ሲያስቆጥር ይመስለኛል የለበሰውን ማልያ ከፍቶ “Why Always me” የሚል ፅሁፍ ያስነበበው ትዝ ይለኛል፡፡ ባላቶሊስ በነጮች አገር ሄዶ በመጫወቱ የዘረኝነት ጥቃት ደርሶበት ነው እኔ ግን በሀገሬ ምን አድርጌ ነው? ሰዎች መደበኛ ስራ አድርገው ከሬዲዮ ጣቢያ ሬዲዮ ጣቢያ፣ አዲስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲከፈት እየተንጠለጠሉ እኔን የአፋው ማሟሻ አድርገው ያለ ኃጢአቴ ያለ ጥፋቴ ጥቃታቸውን ሲፈፅሙ ሳይ ሁልጊዜም እኔን ለምን? ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ፤ መጀመሪያ ላይ እነዚህ ጥያቄዎች በውስጤ ይመላለሱ ነበር፤ አሁን ግን እኔም የስፖርት ቤተሰቡም ህዝቡም አላማቸውን ማንነታቸውን ስለተረዳ ያን ያህል ቦታ አልሰጠውም፡፡

ሀትሪክ፡- አንዳንድ ሰዎች ያለውን እስጠ ገባ ታዝበው ይሄ ሁሉ ውዝግብ ምንድነው? ቦታው ላይ ነዳጅ ይፈልቃል እንዴ? ብለው የመገረማቸውን ልክ በጥያቄ ያነሣሉ?

አቶ መኮንን፡- እኔንም ግራ የሚገባኝ ይሄ ነው፤ የእውነት ነዳጅ ተገኝቶ ይሄ ሁሉ ጦርነት ቢከፈት ምንም አይደለም ለነዳጅ ሲባል ነው ብለህ ትችለዋለህ ምንም በሌለበት ሌላውን ተወውና ደሞዝ ነው እንዳትል ደሞዜ እንኳን ሊያጣላን ሊታዘንልኝ የሚችል እንደሆነ ነው የሚሰማኝ ደሞዜ ተጣርቶ ስንት እንደደረሰኝ ታውቃለህ…

ሀትሪክ፡- አንተ ካልነገርከኝ በምን አውቃለሁ… ?

አቶ መኮንን፡- ደሞዜ ተጣርቶ እጄ ላይ የሚደርሰኝ 10 ሺ ብር ነው 10 ሺህ ብር ደግሞ እንኳን እኔ ማንኛውም ሰው የሚያገኘው ገንዘብ ነው፡፡ ይህች ገንዘብ ሆና በዚህ ዘመን ከሰው ታጥላለች ብሎ ማሰብ ይከብደኛል፡፡ ምናልባት እኔ የማላውቀው ነዳጅ ቦታው ላይ ካለ አብረን ሆነን ቆፍረን ብናወጣው ደስ ይለኝ ነበር፡፡ እኔ እንደውም እንደ እውነት ልንገርህ ቦታው ይሄን ያህል የሚያጨቃጭቅ አይደለም ከዚህ ይልቅ እኔ አንድ በጣም የምጠረጥረው ነገር አለ፤ ግን አሁን አልናገርም፡፡

ሀትሪክ፡- የምትጠረጥረውን ነገር ለህዝብ ይፋ ብናደርገው መልካም አይሆንም…?

አቶ መኮንን፡- እንዳልኩህ ነው ለዚህ ሁሉ ችግር ምክንያት ነው ብዬ የምጠረጥረው አንድ ነገር አለ እሱን አሁን አልናገርም…. ጊዜ ራሱ ያወጠዋል፡፡

ሀትሪክ፡- አንድ ጊዜ በአንድ ሚዲያ የውስጥ የውጪም ጠላቶች አላሠራ ብለውኛል ብለህ ተናግረህ ነበር…. ማነው የውስጡ? ማነው የውጪው?

አቶ መኮንን፡- የውስጦቹ እንኳን በተለያየ ጊዜ ይቀያየራሉ አሁን እንኳን የውስጥ ጠላቶች አላሰራ አሉኝ ብዬ የምፈርጃቸው የለም፡፡ ከውጪ ያሉትንም ጠላት ብለህ ከፍ አድርገህ የምታነሣቸውም አይደሉም፤ ጠላት የምትለው የተደራጀ አንተን ጠንክሮ ገፍቶ የሚጥል አይነቱን ነው እነዚህን ከወሬ ፍጆታ የማያልፉትን ጠላት ብዬ አልጠራቸውም፡፡ ጅሎችም አልላቸውም ክፍዎች በክፋትና ተንኮል የታወሩ ግን የትም የማይደርሱ የሚለው ቃል ብቻ የሚገልፃቸው ናቸው፡፡ እነዚህ እንኳን ስራህን ሊረዱ የሚችሉ አይነት አይደሉም ረቂቆችን /ድራፍቶችን ይዘው ቴሌቪዥን ላይ የሚያብጠለጥሉ ደካሞች ናቸው፤ በነገራችን ላይ ረቂቅ ሰነድ በቢሮ ሕግ ለቀረበለት ሰው አስተያየት ሰጥተህ ትመልሳለህ እንጂ አየር ላይ አውጥተህ የምታብጠለጥልበት አይደለም ይሄንን እንኳን በቅጡ የማይረዱ ሰዎች ጠላቶች ናቸው አልልም አላዋቂዎች እንጂ፡፡

ሀትሪክ፡- ከላይ ስንጋገር ጀምሮ እነዚህ ሰዎች የሚያጠቁት ምናምን ትላለህ? ለመሆኑ እነማን ናቸው ግልፅ ብታደርግልኝ…?

አቶ መኮንን፡- .. ልታደክመኝ ፈልገህ ካልሆነ አንተም ህዝቡም ታውቋቸዋላችሁ… ሰባት አመት ሙሉ ተደራጅተው ሲያጠቁኝ ህዝቡ ታዝቦ ንቋቸዋል፡፡ አለማቸውም ገብቶዋቸዋል ከወሬ ውጪ ስራ የሌላቸው በስም ጠርቼ ክብርና እውቅና አልሰጣቸውም፤ ህዝቡም ሁሉም ስለሚያውቃቸው ስም ጠርቼ አላሰለችም፡፡

ሀትሪክ፡- በተደጋጋሚ በሚደርስብህ ትችትና ወቀሳ ቤተሰባቦችህና አካባቢያዊ ተፅዕኖስ አልፈጠረብህም…?

አቶ መኮንን፡- አሁን አሁን እንኳን የለም መጀመሪያ አካባቢ ግን እንኳን ሰውን እኔንም አንገቴን አስደፍቶኝ ነበር ያለ ስራዬ ቢሆንም፤ አሁን ግን ሁሉም ተረድቷል፡፡ ትዝብት ላይ የወደቁት ሰባት አመት ሙሉ መኮንን መኮንን ሲሉ የከረሙት ናቸው ቤተሰቦቼ፣ ባለቤቴ፣ ልጆቼ ወጣ ብላ ያለችው እህቴ ጭምር መኮንን ምንድነው ይሄ ነገር ያለችኝ ጊዜ ሁሉ ነበር፡፡ ግን አሁን ነገሮች ተቀይረዋል፤ መጀመሪያ ብዥታ የፈጠረባቸው ነበሩ፤ አንዳንድ አጀንዳ፣ የማጥቃት ዘመቻ መሆኑን ሲያዩ ነገሩ ሁሉ ገባቸው፡፡ ህዝብ በሚመለከት ሚዲያ አቅምህን ፍላጎትህን የሚፈታተን ነገር ሲሰራ እንደ ሰው ይሰመሃል፤ በተለይ መጀመሪያ ተፅዕኖ ነበረው በዚህም ሰለባ ሆኛለሁ፤ ኢሊባቡር ከሰራሁባቸው ቦታ ከማስተምርበት ቦታ ሁሉ ምንድነው ብለው የሚጠይቁኝ ነበሩ፡፡ ላለፉት 27 አመታት ትልቅ ስም ነበረኝ፤ አስተማሪም ነበርኩ፡፡ ያስተማርኳቸው በርካታ ልጆች አሉ ዛሬ የተሻለ ቦታ የደረሱ በርካታሰዎች አሉ፡፡እነዚህ ሁሉ ይጠይቁኛል፡፡ በተለይ ባለቤቴ “መኮንን ምንድነው ነገሩ ለምን አትተወውም” ትለኝ ነበር፡፡ አሁን ግን ነገሩ ስለገባት መተው የለብህም ብላ አንደኛ የምትሟገተኝ እሷ ናት፡፡

ሀትሪክ፡- ፌዴሬሽኑ እንደ አንድ ዲፓርትመንት ሲከላከልለት አይታይም ስታፋችን ነው ብሎ ብዙ የመከላከል ርቀት መሄድ ሲገባው አልሄደም አልተከላከለም የሚሉ ልክ ናቸው?
አቶ መኮንን፡-እውነት ነው በዚህ በኩል እኛ የፌዴሬሽኑን ስራ እንደመስራታችን ብዙ ድጋፋች መከላከ ሎች ያስፈልጉ ነበር፤ በምንፈልገው ልክ አግኘተናል ብዬ መዋሸት አልፈልግም ከዚህ ይልቅ እኛው ራሳችን ነን ብሮድካስትና ሬዲዮ ጣቢያዎች ድረስ እየሄድን ስንከላከል የነበረው፤ ከእኛ አልፎ ለተቋሟችን ነው ስንከራከር የነበረው፤ እኛ አለአግባብ ስንነካ ስንወቀስ ፌዴሬሽኑም የተወቀሰ ያህል በመሆኑ መከላከሎች ያስፈልጉን ነበር ከዚህ ይልቅ እኛ እራሳችንን ስንከላከል ነው የኖርነው ብል አልተሳሳትኩም፡፡ ከራሴ ይልቅ ፌዴሬሽኑን ተከላክያለሁ፤ በዚህም ተሳክቶልኛል ብዬ አስባለሁ፤ እስከ መቼ ግን ምንም ለማትጠቀምበት ነገር እየተሰደብክ ትኖራለህ ነው ጥያቄው፡፡

ሀትሪክ፡- በሚቀርብብህ ትችት ጥያቄ ያነሱ እንግዳ ሁሉ አጋርነታችውን ያሳዩህስ አሉ?

አቶ መኮንን፡- በዘመቻው አብረው ከጎኔ የማላውቃቸው በርካታ ሰዎች አሉ፤ በየሄድኩበት መ/ቤት ለእኔ ከበሬታ ሲሰጡኝ አያለሁ ይሄ ያስደስተኛል፡፡ ግን የማልዋሽህ በባለጌዎች ስሜ ሲጠፋ ይሰማኛል አዝናለሁ መንግሥት 27 አመት እምነት ጥሎ ኃላፊነት የሰጠኝ ስለሰራው ነው፤ በእነዚህ የ27 አመታት አገልግሎቴ 3ቱን አመት ብቻ በማስተማር ነው ያሳለፈኩት ሌላውን በተለያ ኃላፊነት ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የቀድሞ ተጨዋቹ ወደ ስልጠናው እዲመጡ አትፈልግም ትባላለህ?

አቶ መኮንን፡- እየተመ ዘዘች የምትወራው የእድሉ ደረጀ ጉዳይ ነው፤ እድሉ ምን አልባት ታናሽ ወንድሜ ነው ልጄ ብለውም ደስ ይለኛል በነገራችን ላይ እድሉን በጣም ከሚያደንቁት ሰዎች አንዱ እኔ ነኝ፤ በራሱ ጥረት ብዙ የሰራቸው ስራዎች አሉ፤ ይሄንንም ነግሬዋለው እኔ የማይመቸኝን ሰው ዝም እላለው የሚመቻችን ሰው ነው በግልፅ የምናገረው እድሉ ከማደንቀው ከማደንቃቸውና በራሳቸውጥረት ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ከሚሯሯጡ ወጣት አሰልጣኞች አንዱ እሱ ነው፡፡ ጥሩ ሚድ ፊልድር ነው፤ ቁጭ ብዬ የተመለከትኩት የማደንቀውም ተጨወች ነው፡፡ ባርሴሎና ድረስ ሄዶ በራሱ ጥረት ያገኘውን እውቀት እንዲያካፍል መድረክ ሁሉ አዘጋጅቼ ቆንጆ ስራ ሰርተናል፡፡ ግንቦት ላይ ሲ ላይሰንስ ወስዶ ሰኔ ላይ ቢ ላይሰንስ ልውሰድ ሲል አይቻልም ብዬዋለሁ፡፡ ምክንያቱም በካፍ ሕግ ይሄ ስለማይፈቀድ፡፡ ታዲያ በወቅቱ እድሉ አንተ በዚህ ኮርስ ውስጥ ልትሳተፍ አትችልም ለምን ሲለኝ ይሄን የሚከለክለው እኔ አይደለሁም የካፍ ሕግ ነው አልኩት፡፡ ከሲ ወደ ቢ ለመምጣት የግድ ሁለት አመት ልትቆይ ይገባሀል አልኩት፤ እንደ አስራትና ሰውነትን የመሳሰሉ ታላላቅ አሰልጣኞች ከሲ ወደ ቢ የመጡት ሁለት አመት ቆይተው ነው፡፡ እድሉ ግን በሁለት ወር ሁለቱንም መያዝ ፈለገ፡፡ ፍላጎቱን አድንቅለታለሁ፤ እኔ ግን እዚህ የተቀመጥኩት ኃላፊነቴን ለመወጣት ነው የሰው ቦታ አታጣብ ስለው እሽ ብሎ ተግባብተን ተለያየን፡፡ ይሄነገር ከተፈጠረ በኋላ እንዳልኩህ ከእድሉ ጋር ብዙ ስራዎችን ሰርተናል፡፡ እድሉ ግን አጋጣሚዎችን ጠብቆ ቂም ልበለው ወይም ሌላ አለአግባብ የተከለከለ ያህል ቆጥሮ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ድረስ ሄዷል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ጋር ሄዶምን መልስ እንደተሰጠው ባላውቅም እድሉ ለምን እንዳደረገ ግን አይገባኝም፡፡ አሁን ከእድሉ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ተነጋግረን ፈተናዋል፡፡ ታሪኩይሄ ነው ከዚህውጪ የተፈጠረ ነገር የለም፡፡ እኔ እንደውም ስልጠና በመከልከል ሳይሆን ሁሉም የስልጠና ተጠቃሚ ሆነው እግር ኳሱን እንዲያግዙ ነው ፍላጎቴ፡፡

ሀትሪክ፡- በመጨረሻ?

አቶ መኮንን፡ -ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ብዙ የሰሩ ሰዎች ዝም ብለው ተቀምጠው ከአራት እና አምስት ጨዋታዎች ያልበለጠ ያደረጉ ሰዎች የእግር ኳሱ ውክልና ለእኛ ተሰጥቶናል በሚል መልኩ ብዙ እየተናገሩ ብዙ የሚናገራቸው አንደበታቸው በጣም ብዙ ሰው እየታዘባቸው ነው እነ ሙሉጌታ ከበደ፣ ንጉሴ ገብሬ፣ እነ ገ/መድህን ኃይሌ፣ እነ ሙሉጌታ ወልደየስ ከአሁኖቹ እነ አዳነ ግርማ፣ሳላሀደን ሰይድን የመሳሰሉ ተጨዋቾች ለሀገር ብዙ ሰርተው ብዙ ቢናገሩ የሚያምርባቸው ሆኖ ሁለትና ሶስት ጨዋታ የተጫወቱ ሰዎች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከእኔ ወዲህ ላሳር ብለው ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ ሰው እየታዘበ ነው፡፡ ይሄ ነገር እንደውም “የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ” የሚለው ተረት ያስታውሰኛል እና ወደ ልባቸው እንዲመለሱ ነው ምክሬ፡፡

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.