የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ህልም ይሳካ ይሆን?

የኢትዮጵያ ቡናው አለቃ ካሳዬ አራጌ ዳዊት እስጢፋኖስና ነስረዲን ኃይሉን የማግኘት እድሉ እየጠበበ ነው፡፡ ግብ ጠባቂውን አቤል ማሞና የግራ መስመር ተመላላሹ ዘካርያስ ቱጂን ካስፈረመ በኋላ ፊቱን አንድ አንድ አመት ውል ያላቸው የሰበታ ከተማው ዳዊት እስጢፋኖስና የመከላከያው ነስረዲን ኃይሉ ላይ ቢያደርግም ከውስጥና ከውጪ ያለበት ተቃውሞ ዝውውሩ ላይ ሳንካ እንዲፈጥር አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናው ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ አሰልጣኞቹ ከመከላከያው ነስረዲን ኃይሉ ጋር እየተደራደሩ ለመሆናቸው ሪፖርት እንደቀረበላቸው የዳዊት እስጢፋኖስን በተመለከተ የቀረበላቸው ተጨባጭ መረጃ እንደሌለ ገልፀዋል፡፡ ከክለቡ የውስጥ አዋቂ በተገኘ መረጃ ግን ስራ አስኪያጁና የክለቡ ቦርድ የመሀል ሜዳው ኮከብ ዳዊት እስጢፋኖስ ዳግም ወደ ክለቡ እንዲመለስ የማይፈልጉ መሆናቸውና ከአሰልጣኙ ጋር ከውይይት በዘለለ ክርክር ውስጥ ገብተው እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

አሰልጣኝ ካሳዬ ከዳዊት ውጪ ሌላም ጠንካራ ትግል የገጠማቸው ከመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ነው ነስረዲን አምና ለኢትዮጵያ ቡና ቢፈርምም ክለቡ ውስጥ ውሣኔውን አፅንቶ ማቆየት የሚችል ወሳኝ ሰው ባለመገኘቱ ፊርማው ተቀዶለት ለመከላከያ ለመፈረም ችሏል፡፡ ቀሪ የአንድ አመት ውል እንዳለው የሚናገሩት የመከላከያ ቡድን መሪ ኮ/ል ደሱ የኮንትራት ዘመኑን መጨረስ የግድ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ “መልቀቂያ የጠየቁን ሌሎች ተጨዋቾችም አሉ ለማናቸውም እንደማንሰጥ ነግረናቸዋል የነስረዲንም ከዚህ አይለይም፡፡ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ እንደሚፈልጉትና ጥያቄ ካለው ግን እንዲስተናገድ ወደኛ መርተውት ተነጋግረናል፡፡ በፍፁም እንደማንለቀውና የአንድ አመት ውሉን መፈፀም እንዳለበት አስረድተነዋል” ሲሉ በምንም መንገድ መልቀቂያ እንደማይሰጠው ገልፀዋል፡፡ “ተጨዋቹ ጨዋ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ጎበዝም በመሆኑ ፈላጊ እንደሚኖረው እንገምታለን ሌሎች ክለቦች ከውል ውጪ አነጋገሩት የሚባለው ነገር አያሳስበንም ከኢትዮጵያ ቡናም የቀረበልን ይፋዊ ጥያቄ የለም” ሲሉ ኮ/ል ደሱ ለሀትሪክ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ይህም አሰልጣኝ ካሳዬ ለፍልስፍናዬ ይጠቅሙኛል ያላቸው ሁለቱ ተጨዋቾችን የማግኘት እድሉን የጠበበ አድርጎታል፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport