የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ሚያዝያ 07 2016 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች)ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በሳምንቱ መርሃ ግብር በተደረጉ ጨዋታዎች አራት በመሸናነፍ ቀሪ አራቱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ 18 ጎሎች በ16 ተጫዋቾች ተቆጥረዋል። 40 ቢጫ ካርድ ለተጫዋቾችና ቡድን አመራሮች ሲሰጥ አንድ ቀይ ካርድ ተመዝግቧል።
በሳምንቱ በስድስት ተጫዋቾች ላይ የዲሲፕሊን ውሳኔ ተላልፏል። ሄኖክ ሀሰን(ድሬደዋ ከተማ)፣ ሃብታሙ ንጉሴ(ሻሸመኔ ከተማ)፣ የዓብስራ ተስፋዬ(ባህርዳር ከተማ) እና ሐብታሙ ታደሰ(ባህርዳር ከተማ) በሳምንቱ ጨዋታ አምስተኛ የጨዋታ ቢጫ ካርድ በመመልከታቸው ለፈፀሙት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍሉ እንዲሁም ሀቢብ መሀመድ(ፋሲል ከነማ) የተጋጣሚን ቡድን ግልፅ ግብ ዕድል በማበላሸት በቀይ ካርድ ከጨዋታ የተወገደ ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 3 ጨዋታ እንዲታገድና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 /ሶስት ሺ/ እንዲከፍል ተወስኗል።
መቻል ከኢትዮጵያ መድን ጋር ባደረገው ጨዋታ የመቻል ቡድን ተጫዋች የሆኑት አስቻለው ታመነ፣ ነስረዲን ሀይሉ፣ ሺመልስ በቀለ፣ ከነአን ማርክነህ እና ግሩም ሃጎስ በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ክለቡ የገንዘብ ቅጣት ብር 5000 /አምስት ሺ/ እንዲከፍል ተወስኗል።