አዲስ የተሻሻለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደንብ ለፊፋ ተልኮ እንዲፀድቅ በመደረጉ ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ በአዲስ መልክ እንዲዋቀርና ከዚህ ቀደም በኢንተርናሽናል ዳኝነት ሲያገለግሉ የቆዩ ግለሰቦች በአመራርነት እንዲሰሩ መምረጡ ተሰማ።
ኮሚቴው በአዲስ መልክ እንዲዋቀር መነሻ የሆነው ጥቅምት 19/2016 በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የፀደቀው የተሻሻለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መተዳደርያ ደንብ ሲሆን በደንቡ አንቀፅ 46 (ቁጥር 2) ላይ ቋሚ ኮሚቴዎች የሚቋቋሙበት ሁኔታ ሲገልፅ “ከብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ በቀር የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይም ምክትል ሰብሳቢ ሆኖ መስራት ይችላል። ” ይላል። የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴን አወቃቀር እና አሠራር ገለልተኛ ለማድረግም አባላቱ ከሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ውጪ እንደሚሆኑ በደንቡ ላይ ተቀምጧል። ይህን ተከትሎ የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሙሉ ለሙሉ በአዲስ መልክ እንዲዋቀር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ትናንት ባደረገው ስብሰባ ውሳኔ ወስኗል ሲል ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ በነበሩት ኮሚሽነር ሸረፋ ደሌቾ ይመራ የነበረውና ኢንስትራክተር ልዑል ሰገድ በጋሻው ፣ ኮሚሽነር ሰላሙ በቀለ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት አርቢትር በላቸው ይታየውና ኢንተርናሽና አርቢትር አዲስ ነጋሽ የተካቱበት ነባሩ ኮሚቴ ከትላንት ምሽት ጀምሮ በይፋ መሰናበቱን የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ዛሬ ስራውን በይፋ የጀመረው አዱሱ የብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴን ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሸዋንግዛው ተባባል በሰብሳቢነት ሲመራው ኢንተርናሽናል አርቢትር የነበረችው ሊዲያ ታፈሰ በምክትል ሰብሳቢነት እንዲሁም ኢንተርናሽናል ረዳት አርቢትር የነበረው ክንዴ ሙሴ፣ ኢንተርናሽናል አርቢትር ለማ ንጉሴና ኢንተርናሽናል ረዳት አርቢትር ክንፈ ይልማ በአባልነት መካተታቸው ታውቋል። ከነባር ኮሚቴው ድሬዳዋ ላይ ሆነው የዳኛ ምደባ ላይ ሲሰሩ የነበሩት ኮሚሽነር ሰላሙ በቀለ ትላንት ከሆቴላቸው የወጡ ሲሆን በቦታው የአዲሱ ኮሚቴ ምክትል የሆየችው ሊዲያ ድሬዳዋ ከተማ በመገኘት የዛሬውን ምደባ ከሌሎች አካላት ጋር ሆና ማከናወኗ ታውቋል።
- ማሰታውቂያ -
የሁለቱ ኮሚቴዎች ፈጣን ልውውጥ በርካቶችን ያነጋገረ ሲሆን በተለይ ሊጠናቀቅ 9 ጨዋታ በቀረው የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለዋንጫና ላለመውረድ የሚደረገው ትንቅንቅ ሊይ የሚመደቡት ዳኞች ወሳኝ በመሆናቸው በኮሚሽነር ሸረፋ የሚመራው ኮሚቴ እንደጀመረው ቢጨርስ መልካም ነበር የሚሉ ወገኖችም ተበራክተዋል። የክለቦችም ይሁን የተለያዩ ወገኖች ፍላጎቶች በይበልጥ በሚጧጧፍበት የመጨረሻዎቹ ሳምንታት ጨዋታዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚጠይቁ በመግለጽ ለምን አሁን ሆነ የሚሉ ወገኖች ስጋታቸውን ያሰማሉ።
ከ23ኛው ሳምንት ጀምሮ ወደ ሀዋሳ የሚዞረው ፕሪሚየር ሊጉ ለጥሎ ማለፉ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ሲባል ለቀናቶች መቋረጡ የማይቀር መሆኑን የሚናገሩት ወገኖች ለነባሩ ኮሚቴ አመስግኖና ሽኝት አድርጎ የተወሰነም ቢሆን የልምድ ልውውጥ እንዲኖር አለመደረጉ አነጋጋሪ ሆኗል።
አዲሱ ኮሚቴ ሃላፊነቱን እስከወሰደ ድረስ የቀጣዮቹ የፕሪሚየር ሊግ የዋንጫና ላለመውረድ በሚደረገው ፍልሚያ በከፍተኛ ሊግ ደግሞ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለማደግና ወደ አንደኛ ሊግ ላለመውረድ በሚኖረው ፍጥጫ ላይ ተገቢ የሆኑ አርቢትሮችን በመመደብና ውጫዊ ጫና ባለመስማት ተገቢ የሆነ አመራር እንደሚሰጡ አደራ የተጣለባቸው ሆኗል።