ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2015 20ኛ ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች ሰባት ጨዋታዎች በመሸናነፍ አንድ ጨዋታ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ 15 ጎሎች ተቆጥረዋል። በሳምንቱ 39 ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች በቢጫ ካርድ ሲገሰፁ አንድ የቡድን አመራር ቀይ ካርድ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ እሁድ ሚያዝያ 15 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች)ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በተጫዋች እና ቡድን አመራሮች ደረጃ በተላለፉ ውሳኔዎች ተሾመ ሸዋነህ(አርባምንጭ ከተማ) የክለቡ የቡድን መሪ ሆነው የዳኛን ውሳኔ በመቃወምና ቁሳቁስ በመወርወር ከጨዋታ ሜዳ የተወገዱ ስለመሆኑ ሪፖርት
የቀረበባቸው ለፈፀሙት ጥፋት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ደንብ መሰረት 3 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 10000 /አስር ሺ/ እንዲከፍሉ እንዲሁም በተጫዋቾች ምንይሉ ወንድሙ(መቻል) እና ሱሌማን ሀሚድ(ቅዱስ ጊዮርጊስ) 5 ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቅቂያ ካርድ በመመልከታቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍሉ ተወስኗል።
- ማሰታውቂያ -
በክለቦች ደረጃ በታዩ ሪፖርቶች በሶስት ክለቦች ላይ የተለያዩ ውሳኔዎች ተላልፈዋል። አርባምንጭ ከተማ በሳምንቱ ጨዋታ የክለቡ ስድስት ተጫዋቾች በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት የገንዘብ ቅጣት ብር 5000 /አምስት ሺ/ እንዲከፍል ፥ ኢትዮጵያ ቡና በተጫወተበት እለት የክለቡ ደጋፊዎች የእለቱን ዳኛ አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት በመቅረቡ የክለቡ ደጋፊዎች ለፈፀሙት ጥፋት ክለቡ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ብር 50000/ሃምሳ ሺህ/ እንዲከፍል ፥ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጫወተበት እለት የክለቡ ደጋፊዎች በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ስታድየም ጥላ ፎቅ የሚገኙትን 22/ሃያ ሁለት/የፕላስቲክ ወንበሮችን ስለመስበራቸው ሪፖርት የተደረገ ሲሆን ክለቡ የተሰበሩትን ወንበሮች እንዲያሰራ ወይም የዩኒቨርስቲው አሰተዳደር የሚያቀርበውን የንብረትን ዋጋ እንዲከፍል ተወስኗል።