መነሻ ገጽ ሀዲያ ሆሳዕና የጨዋታ ዘገባ | ለገጣፎ ለገዳዲ እና ሀድያ ሆሳዕና ነጥብ ተጋርተዋል
ሀዲያ ሆሳዕናለገጣፎ ለገዳዲቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግዜናዎችየጨዋታ ዘገባ

የጨዋታ ዘገባ | ለገጣፎ ለገዳዲ እና ሀድያ ሆሳዕና ነጥብ ተጋርተዋል

አጋራ
አጋራ

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት ቀዳሚ ጨዋታ ለገጣፎ ለገዳዲን ከሀድያ ሆሳዕና አገናኝቶ ግብ ሳይቆጠርበት 0 – 0 ተጠናቋል ።

በጨዋታው በለገጣፎ ለገዳዲ በኩል በ20ኛው ሳምንት በባህርዳር ከተማ በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሶስት ለውጦችን በማድረግ ፍቅሩ አለማየሁ ፣ መዝገቡ ቶላን እና ሱራፌል አወልን በአቤል አየለ ፣ ያሬድ ሀሰን እና ጋብርኤል አህመድ ምትክ ሲያሰልፉ በሀድያ ሆሳዕና በኩል ወላይታ ድቻን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ አስራአንድ ሁለት ለውጦችን ሲያደርጉ ፍቅረየሱስ ተክለብርሀን እና ራምኬል ሎክን በዘካርያስ ፍቅሬ እና ስቴቨን ናይራኮን ተክተው ወደ ጨዋታው ገብተዋል ።

ጨዋታውን በብልጫ ለመጀመር ጥረት ያደረጉ ለገጣፎ ለገዳዲዎቾ ብዙም ሳይቆዩ በተጋጣሚያቸው ሀድያ ሆሳዕና አንፃራዊ ብልጫ ተወስዶባቸው ጨዋታቸውን አድርገዋል ።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በ30 ነጥቦች 5ኛ ላይ ተቀምጠው ጨዋታውን የጀመሩት ሀድያ ሆሳዕናዎቸ በተለይም በመስመር የማጥቃት እንቅስቃሴ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገዋል ።

በጨዋታው የመጀመሪያ ኢላማውን በጠበቀ የግብ ሙከራ በ14ኛው ደቂቃ ላይ ካሌብ በየነ በግራ መስመር ይዞ የገባውን ኳስ ወደ መሀል ቀንሶ ራምኬል አግኝቶ የነበረ ቢሆንም የራምኬል ኳስ ከግብ ጠባቂው ማለፍ የቻለ አልነበረም ።

ከአስር ደቂቃዎች በኋላም ብርሀኑ በቀለ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ።

በ28ኛው ደቂቃ ብርሀኑ በቀለ ከመስመር ያሻገረው እና በፍሬዘር ካሳ በግንባር የተገጨው ኳስ ለሀድያ ሆሳዕናዎች እጅግ አስቆጪ የግብ ዕድል ነበር ።

ሀድያ ሆሳዕናዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን መወሰዳቸውን ተከትሎ አብዛኛው የጨዋታው እንቅስቃሴ በለገጣፎ ለገዳዲ የሜዳ ክፍል ላይ ነበር ።

 

በመጀመሪያው አጋማሽ ለገጣፎ ለገዳዲዎቾ በብቸኝነት ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በደረሱበት አጋጣሚ መሀመድ አበራ ከሱራፌል አወል የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል ።

አጋማሹ ከመጠናቀቁ ሰከንዶች በፊት በሀድያ ሆሳዕና በኩል ብሩክ ማርቆስ ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በግብ ጠባቂው ተመልሶ ወጥቷል ።

በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ የሆነ እና ለመሸናነፍ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ነበር ።

 

በመጀመሪያው አጋማሽ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው የነበሩት ለገጣፎ ለገዳዲዎች በሁለተኛው አጋማሽ ጥቂት ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር ።

በዚህም ተስፋዬ ነጋሽ ከቀኝ መስመር አቅጣጫ በቀጥታ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በግብ ጠባቂው ተመልሷል ።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ በሁለቱም በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ የተቃራኒ የግብ ክልል በመድረስ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢጥሩም የጠራ የግብ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ ቆይተዋል ።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ ሀድያ ሆሳዕናዎች በመጨረሻም ድል አድርገው መውጣት የሚችሉበትን ዕድል ማግኘት ቢችሉም ለጥቂት ሳይሳካ ቀርቷል ።

ተቀይሮ የገባው ሪችሞንድ አዶንጎ ከቆመ ኳስ የተነሳውን አጋጣሚ አግኝቶ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ያደረገው የግብ ሙከራ በለገጣፎ ለገዳዲው ፍቅሩ አለማየሁ ግብ ከመሆን ድኗል ።

በ22ኛው ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ሰኞ ሚያዝያ 23 በ9:00 ለገጣፎ ለገዳዲ ወላይታ ድቻን ሲገጥም በዕለቱ ከአመሻሽ 12:00 ጀምሮ ሀድያ ሆሳዕና ከፋሲል ከነማ ጨዋታውን ያደርጋል።

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየዲሲፕሊን ውሳኔዎችዲሲፕሊን ውሳኔ

የ32ኛ ሳምንት የዲሲፕሊን ውሳኔዎች

የዲሲፕሊን ውሳኔዎች አህመድ ረሺድ (ድሬደዋ ከተማ) : በኢትዮጵያ ዋንጫ ውድድር 1 እንዲሁም...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ሀምራዊ ለባሾቹ እና የጣና ሞገዶቹ ጣፋጭ ሦስት ነጥብን ወደ ቋታቸው ከተዋል

በሊጉ የሳምንቱ የሁለተኛ ቀን ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ባህርዳር ከተማ ወሳኝ...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ሲዳማ ቡና ሲሸነፍ በተጠባቂው ጨዋታ መቻል በጎል ፌሽታ ነገሌን ረቷል

በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ጨዋታ የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በሀድያ ሆሳዕና ሽንፈት ሲያስተናግድ...

ዜናዎችየኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ

ውጤት ለውጧል የተባለው ዳኛ ተባረረ

በዮሴፍ ከፈለኝ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውጤት ለውጠዋል የተባሉ አርቢትሮችን ወደመጡበት መመለሱን አሁንም ቀጥሏል። ከቀናት...