መነሻ ገጽ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ “አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሰልጣኞች ስሜታቸውን አፍነው ተቃጥለው ስለሚሄዱ የጨጓራ በሽተኛ ሆነዋል” አሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግዜናዎችድሬዳዋ ከተማ

“አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሰልጣኞች ስሜታቸውን አፍነው ተቃጥለው ስለሚሄዱ የጨጓራ በሽተኛ ሆነዋል” አሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን

አጋራ
አጋራ

ሰውየው እንዲህ ነው….“የአዲስ አበባ ስታዲየም አንግል በዘፈቀደ የተሰራ ነው በርካታ ኳሶች የተመለሱብን በዚህ ምክንያት ነው” አስገራሚው የአሰልጣኙ መግለጫ ቀጠለ… ከጨዋታው በፊት

“የጅማ ስታዲየም ሜዳው ምርጥ መሆኑ ተናግሬያለው…” በጨዋታው ከተሸነፉ በኋላ ደግሞ “የሜዳውን አስቸጋሪነት ለተጨዋቾቼ ነግሬያቸዋለሁ” ሲል ተናገረ፡፡ ወልቂጤ ከተማ ካሸነፋቸው በኋላ “ሜዳው የእግር ኳስ አይመስልም የወልቂጤ ከተማ ተጨዋቾች በሜዳው ላይ እየወደቁ ሜዳውን ሪፈራል ሆስፒታል አድርገውታል፡፡” በቃ ከላይ ያሉትን አስተያየት የሰጠውና የሊጉ አድማቂ የሚል ቅፅል ያገኘው አሰልጣኝ ፍሰሃ ጥዑመልሳን ከድሬዳዋ ከተማ ጋር መለያየቱ እርግጥ ሆኗል፡፡ አሰልጣኙ ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ስለስንብቱ፣ ውሉ ሳይቋረጥ ሌላ አሰልጣኝ ለማምጣት ስለማሰባቸው፣ ስለነበረው የአሰልጣኝነት ህይወት፣ ውጫዊ የሽንፈት ምክንያት ስለማብዛቱ፣ ስለ ክለቡ ቦርድ፣ ስለ አሰልጣኝነት ብቃቱ፣ ስለአወዛጋቢ አስተያየቱና ሌሎች ጉዳዮች ለቀረበለት ጥያቄዎች ምላሹን ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- አንዳንድ መረጃዎች በይፋ ተለያይታችኋል ይላሉ… እውነት ነው ከድሬደዋ ከተማ ጋር ተለያይታችኋል?

ፍሰሃ፡- የሚገርመኝ ይሄ ነው አንዳንድ መገናኛ ብዙኃንና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ተስማምተው ተነጋግረው ተለያዩ እያሉ ነው ለምን ይሄ ውሸት እንደሚወራ አልገባኝም፡፡ ማንን ጎድቶ ማንን ለመጥቀም ታስቦ እንደሆነም አልገባኝም.. ያለው እውነት የክለቡ ስራ አስኪያጅ ደውሎ ተነጋግረናል ችግር የለም በስምምነት ይቋጫል ብሎኛል ግን እስካሁን በአካል አልተገናኘንም.. ትንሽ አሞኝ ስለነበር ህክምና ክትትል ላይ ነው ያለሁት በቀጣይ ቀናት የምንወያይና ችግሩ የሚፈታ ይመስለኛል ያለው ይሄ ነው ፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ውሌ አለ አልተቀደደም ለቀጣይ አሰልጣኝ ሲባል ግን… ቶሎ ብንወያይና ብንስማማ ደስ ይለኛል ያለው እውነታው ይሄ ነው ከዚህ ውጪ የሚወራው ነገር እኔን አይመለከተኝም፡፡

ሀትሪክ፡- ከምባረር ክለቡን እወደዋለው በክለቡ ስር ካሉ ቡድኖች የአንዱ አሰልጣኝ አድርጉኝ ብለሃል የሚል መረጃ ሰማሁ.. እውነት ነው?

ፍሰሃ፡- ይሄ ውሸት ነው ማንንም እንዲህ ብዬ አልጠየኩም በአካል ማንንም አላገኘሁም በስልክ ነው ያወሩኝ የቤተሰብ ጉዳይ በመሆኑ እናውራና በሠላም እንለያይ ብያቸው ተስማምተዋል እኔም እየጠበኳቸው ነው ምናልባት ውል ስላለኝ ፌዴሬሽኑ ጋር ሄደው በሚችሉት መንገድ ስራውን እንዲጨርሱ ነግሬያቸዋለው ጉዳዩ የቤተሰብ በመሆኑ ልዩነት ተፈጥሮ እንጣላለን ብዬ አላምንም ህይወት ግን ይቀጥላል .. የኔም ህይወት ይቀጥላል፡፡

ሀትሪክ፡- ስንብቱ ተገቢነው ብለህ ተቀበልከው?

ፍሰሃ፡- ምን አማራጭ አለኝ ብለህ ነው? ካልተፈላለግን መለያየቱ የግድ ነው የሚሆነው.. አስተካከል ቡድኑን ወደ ውጤታማነት መልስ ብለውኝ ከአሰልጣኝ ቡድን አባላቶቼ ጋር አውርተን እሺ ይስተካከላል ብለን ምላሽ ሰጠን፡፡ ምን እንደሆነ አላውቅም ሃሳባቸው ተለውጦ ወደ ድሬዳዋ ተመለስና እንነጋገራለን ብለው ከባህር ዳር ድሬዳዋ ተመለስኩ ስንብቱ ተገቢ ነው ብዬ አላስብም ሁለት ቀን ልምምድ የሰሩት በምክትል አሠልጣኙ ነው አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስን ለመቅጠር መስማማታቸውን ሰምቻለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ከአንተ ጋር ያለውን ውል ሳይጨርሱ ሌላ አሰልጣኝ ማነጋገራቸው ቅሬታ አልፈጠረብህም?

ፍሰሃ፡-ትልቅ የስነ-ልቦና ችግርማ ይፈጥራል፡፡ ቅር ይላል ከባድ ቅሬታ ተፈጥሮብኛል ተገቢ አይደለም የሚል አቋም አለኝ በእርግጥ ተደጋጋሚ ሽንፈቱ ትልቅ ስትረስ ፈጥሮብኛል፡፡

ሀትሪክ፡- የድሬዳዋ ከተማ ቆይታህን በስኬታማነት ነው የምታየው?

ፍሰሃ፡- የድሬዳዋ ከተማ ቆይታዬን ስናየው ዘንድሮ ዋና አሰልጣኝ ብሆንም ቡድኑን በምክትልነት ማሰልጠን ከጀመርኩ 4 አመት ሞልቶኛል፤ የድሬደዋ ከተማ ጥሩ ቡድን አልነበረም በየአመቱ ላለመውረድ ሲጫወት ነው የነበረው፤… ዘንድሮ በፕሪሚየር ሊጉ በተሻለ ደረጃ ግብ ላይ መድረስ የሚችል ምርጥ ቡድን ገንብቻለሁ የተነቃቃ በጣም ጥሩ ቲም መሆኑን ማንም ያውቀዋል ነገር ግን የፈጠርናቸውን የግብ እድሎች ስለማንጠቀም ዋጋ እየከፈልን ነው ከማንኛውም የሊጉ ክለብ የግብ ክልል ላይ ቀድመን የምንደርሰው እኛ ነን፡፡

ሀትሪክ፡- እስቲ በማስረጃ አብራራው?

ፍሰሃ፡- የመጨረሻው ጨዋታ ከፋሲል ከነማ ጋር ያደረግነውን ለምሣሌነት ስናይ ከፋሲል ከተማ ጋር ስንጫወት አንግሉ የገጨብን የቴስታ ሙከራ ቢገባ የጨዋታው አካሄድ ይቀየር ነበር ዳኛው የፍፁም ቅጣት ምት ከልክሎናል እሱ ቢሰጠን የውጤት ለውጥማ መከሰቱ አይቀርም ነበር ተመልከት ፋሲሎች ሊያልቅ ሲል ሪጎሬ ያገኛሉ ወይም ግብ ያስቆጥራሉ እድልም አላቸው እኔ ጋር ግን እድልም አልነበረም እድል የግድ ያስፈልጋል ብዙ ጊዜ የፍፁም ቅጣት ምት እንከለከላለን ከፋሲል ከነማ ጋር ያደረግነውን ጨዋታ ደጋግሜ አየሁት ሪጎሬ ማግኘት ነበረብን ቢሰጠን ኖሮ ትልቅ ለውጥ ይመጣ ነበር ነገር ግን አልሆነም ተጨዋቼ ላይ ብዙ ብለፋም እድል አልነበረኝም አሁን ያለውን ሰንጠረዥ ብታይ ከ8ኛ ደረጃ ጀምሮ ያሉት ክለቦች ወደ ታች ብናይ 10 ነጥብ ነው ያላቸው በግብና በእዳ ነው የምንለያየው፡፡ ከፋሲል ከነማ አንድ ነጥብ ባገኝ ከ11ኛ ደረጃ ወደ 8ኛ ደረጃ ከፍ እንል እንደነበር ታውቃለህ? 11ኛ ገባንና ነገሩን አገነነው ማወቅ ያለብን አሰልጣኝ ሲኮን ውጤት እስከሌለ ድረስ ተባራሪ መሆኑን ነው የፈለገ አሪፍ ስራ ብትሰራ ውጤት ከሌለህ በቃ ተባራሪ ነህ አሰልጣኝ ሲሾም የሚሻር መሆኑን አውቆ መትጋት አለበት…. ጊዜው አትሩጥ አንጋጥ የሚል ሆኗል፡፡

ሀትሪክ፡- ውጤት ሲጠፋ የሽንፈቱን ምክንያት በውጫዊ ምክንያት ታደርጋለህ… ልክ ነው?

ፍሰሃ፡- አሁንም ድረስ ተበልጠን ሣይሆን በእድል ማጣትና ውጫዊ ምክንያቶች ተሸነፍን ብዬ ነው የማምነው… በቀጣይ የምንገጥመው ሀዋሳ ከተማን ነው 2ኛ ዙር ሲጀመር ደግሞ ከሰበታ ከተማ ጋር ነው የምንጫወተው ድሬደዋ ከተማ ሁለቱን ቡድኖች ካሸነፈ ቀጥታ የሚመጣው 6ኛ ደረጃ ላይ ነው ቆይ ቆይ እስቲ ቀጣዩ አሰልጣኝ ሃዋሳ ከተማና ሰበታ ከተማን ቢያሸንፍ ይኸው መጥቶ ድሬደዋ ከተማን ከጉድ አወጣው ሊባል ነው? መሰረቱን የተከልኩት ግን እኔ ነኝ፤ ሁልጊዜም መታመን ያለበት ግን ውጤት ከሌለህ ጥሩ ቡድን ብትሰራም መነሳትህ የማይቀር መሆኑን ነው…. ባለሙያዎች ግን የሠራሁትን ምርጥ ቡድን ስለሚያውቁ ሌላ ቦታ ስራ አላገኝም ብዬ አልሰጋም፡፡

ሀትሪክ፡- የክለቡ ቦርድ እኔን ለማሰናበት ቸኩሏል ብለህ ታምናለህ?

ፍሰሃ፡-አይ ቸኩለዋል ሳይሆን ሁለቱን ጨዋታ ሊጠብቁን ይገባን ነበር ብዬ አምናለው 1ኛ ዙር ላይ አይተውን ውጤት ከሌለ በእድልም ይሁን በውጫዊ ምክንያት መልቀቄ የግድ ነው አራት ጨዋታ ስጫወት አራት ተከለካይ ተጎድቶብኛል፡፡ አንዱ ፍሬዘር ብቻ ነው ጤነኛ… ሁለቱም አዩካና ሄኖክ በመርፌ ተወግተው ነው የሚገቡት፡፡ ከሌላ ቦታ አምጥቼ ካስገባኋቸው ውጪ…መከላከሉ ላይ ትንሽ ደካማ ነበርን ምክንያቱ በረከት፣ በፍቃዱ፣ ሄኖክና አዩካ ጉዳት ላይ ስለነበሩ አልተሳካም ይህን ችግር በቦርድ ደረጃ የሚረዳ ሰው ከቦርዱ ውስጥ የለም ይሄ ነው ችግሩ… እነዚህ ልጆች አሁን ቀናቶች ስለነበሩ ለማገገሚያም ጊዜ ነበራቸው በ12ኛው ሳምንት ግጥሚያ አራፊ ነበርን በነዚህ ቀናት ውስጥ ሁለቱን አዲስ አበባ ልኬ ይታከሙ ነበር ከዕረፍት መልስ ጫናው ይለቃል ቤተሰብ ጋር ሄደው ሲመለሱ ተረጋግተው ይመጣሉ ብዬ ነበር የማስበው.. አልተሳካም… ጥሩ ቡድን ይሆናል ብዬ ባስብም እድል ከኔ ጋር አልነበረም፡፡

ሀትሪክ፡- የአሰልጣኝነት ህይወትህ ስንተ አመት ተጓዘ?

ፍሰሃ፡- ባለፉት 25 አመታት በአሰልጣኝነት ህይወት ሰርቻለሁ 25 አመት ስሰራ 20 አመት የሰራሁት በነፃ ነው 5 አመት ብቻ ነው ገንዘብ ያገኘሁት፡፡

ሀትሪክ፡- 25 አመቱን ስትገመግም ስኬታማ ነው ማለት ይቻላል?

ፍሰሃ፡- የእውነት የምናገረው ከ25 አመት ውስጥ 17 አመት አካባቢ ዋንጫ ወስጃለሁ፤ በዲቪዚዮን በመላው ኢትዮጵያ ተካፍያለው፡፡ በ5ኛው መላው ኢትዮጵያ ጊዜ ከአዲስ አበባ ቡድን ጋር ለዋንጫ ቀርበን ተሸንፈን 2ኛ ሆነን ፈፅመናል፤ ሀርምድን ብሔራዊ ሊግ ያስገባሁት እኔ ነኝ ድሬደዋ ላይ ዋንጫ በልቼ በሊጉ አዲስ አበባ ላይ ብሔራዊ ሊግ አስገብቻለሁ ብዙውን ጊዜ ውጤታማ ነኝ አሁን አሁን ነገሮች እንደዚህ መሆናቸው ገርሞኛል እስካሁን በሰራኋቸው ቡድኖች ረክቻለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ፍሰሃ ምርጡ አሰልጣኝ ነኝ ብሎ ያምናል?
ፍሰሃ፡- አዎ ነኝ ተጠራጥሬም አላውቅም ይሄማ ግልፅ ነው… የወረቀትም ችግር የለብኝም ብዙ ስልጠናዎችን ወስጃለሁ ሞሮኮ ሄደው ከሰለጠኑ እነ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም፣ እነ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ጋር ሄጄ ስልጠና ወስጃለሁ፡፡ 25 አመት ቀላል አይደለም እግር ኳሱ ስሙ ልምድ ነው እኔ ደግሞ የ25 አመት ልምድ አለኝ በእግር ኳስና በጋራዥ ሥራ ልምድ ውድ ነው፤ ከትምህርት ቤት ተመርቀህ ወጥተህ ሞተር መስራት አትችልም ውስጡ መኖር አለብህ፡፡ እግር ኳስን ስጫወት ነው ያደኩት… የምድር ባቡር ተጨዋች ነበርኩ ምድር ባቡር እያለሁ ቅፅል ስሜ /አሞካቺ/ ነበር… ከነ ኬኔዲና ጁንዲ ጋር ተጫውቻለሁ እግሬ ሲሰበር ነው ወደ አሰልጣኝነት የገባሁት…. እነ ሳምሶን፣ ግሩም፣ ስዩም እነርሱ ላይ ነው የሰራሁት እነርሱን የዛሬ 23 አመት በማሰልጠን ነው ስራውን የጀመርኩት፡፡

ሀትሪክ፡- በዘንድሮ ፕሪሚየር ሊግ ላይ ለዲ.ኤስ.ቲቪ ስትናገር ትኩረት ትስባለህ… ምክንያቱ ምን ይሆን?

ፍሰሃ፡-ብዙ ጊዜ የድሬዳዋ ልጅ ባህሪ ይሄ ነው ፊት ለፊት በመናገር እታወቃለሁ እኔ ስሜቴን ፊት ለፊት እገልፃለሁ ያልኩትን ደግሜ ሳየው ግን እደነግጣለሁ እኔ ነኝ እንዲህ ያልኩት ብዬ እገረማለሁ .. ፈልጌ የማደርገው ነገር አይደለም ያለውን ስሜቴን መናገሬ ደስ ይለኛል፡፡ ፊት ለፊት ተናግሬ ጨጓሯዬ ሳይታመም ወደ ቤቴ እሄደለሁ…. አብዛኞቹ የፕሪሚየር ሊጉ አሰልጣኞች ስሜታቸውን አፍነው ተቃጥለው ስለሚሄዱ የጨጓራ በሽተኞች ሆነዋል፡፡ በዚህ በኩል ተንፈስ ብዬ ወደ ቤቴ እሄዳለሁ /ሳቅ/ ይሄ ፊት ለፊት መናገር የድሬደዋ ተወላጅ መገለጫ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የድሬ ህብረተሰብ ስላንተ ምን እያለ ነው? መረጃው አለህ?

ፍሰሃ፡- የድሬደዋ ደጋፊዎች በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች መልካም ነገር እየተመኙልኝ ነው ወደፊት በድሬዳዋ ቡድን ላይ ባይሆንም በሌላ ቡድን ላይ አቅሜን አሳይቼ አስደስታችዋለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-በእርግጥ ከቡድኑ ጋር ተለያይቻለሁ የሚለውን ልብህ ያምነዋል?

ፍሰሃ፡- ስንብቱማ የግድ ነው… ይሄ የተረጋገጠ ነው… ክለቡ የሰጠኝ ነገር ባይኖርም ከዘማርያምጋር ስለተነጋገረ አብሬ መቀጠል አልፈልግም ዘማርያምን ማነጋገራቸውን ሰምቻለሁ፤ ከዚህ ይበልጥ ቅር ያለኝ የማኅበራዊ ድረ ገጾችና ሚዲያዎች እውነተኛ መሆን አለባቸው ቶሎ ቶሎ ብለው የኔን ሁኔታ መዘነገብ ይቀላቸዋል ይሄ ልክ አይደለም ባላንስ የተደረጉ ዜናዎችን መዘገብ ይኖርባቸዋል ባይ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ጨረስኩ.. የመጨረሻ ቃል?

ፍሰሃ፡-ተወልጄ ያደኩበት ድሬደዋ ነው… አሁንም ቢሆን ከቡድኑ ብርቅም በቴሌቪዥን እያየሁ እደግፈዋለሁ ድሬደዋን ሳሰለጠንና ሌላውን ሳሰለጥን ይለያያል ተጫውቼ ያደኩበት ቡድን ነው ቡድኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲኖር እፈልጋለሁ ብዙ ወጣቶችኮ አሉ ፕሮጀክት ላይ ከ1990 ጀምሮ ስለሰራሁ ሙሉ ደጋፊ ነኝ…. እድገታቸውን እመኛለሁ፡፡ በክለብ ደረጃ አምነውብኝ አቅሜን እንዳሳይ ያገዙኝን የክለቡ የቦርድ አባላት፣ ሲያበረታቱኝ የነበሩ ደጋፊዎች፣ ጓደኞቼ ወዳጆቼ በአጠቃላይ መላው የድሬደዋን ህዝብ ማመስገን እፈልጋለሁ… ለአዲሱ አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ በጣም የምወደው ጓደኛዬ ነው ለእሱና ለቡድኑ መልካም ውጤት እንዲያስመዘግቡ ከልቤ እመኛለሁ፡፡

ስለ አባይ

የአባይ ግድብ የመጀመሪያ የውሃ ሙሌትማ በደስታ አስክሮኛል፤ አባይ ግድብ ለሀገሬ ትልቅ ትርጉምና ዋጋ አለው… ኬኔዲ የሚባለው ተጨዋች የዛሬ 20 አመት የነገረኝን አልረሳውም፡፡ ከብሔራዊ ቡድናችን ጋር ለእግር ኳስ ጨዋታ ተመርጦ ግብፅ ሄደና በአባይ ውሃ ታጠበ… ሀገሬ እያለሁ ያላየሁትና ያልነካሁት አባይን በሰው ሀገር ታጠብኩበት ብሎ በስሜት የነገረኝን መቼም አልረሳውም በእውነት ህብረተሰቡ ሊያስብበት ሊረባረብ ከልቡ ሊደግፈው ይገባል ለእኔ የአባይ ግድብ ኩራቴ በመሆኑ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት አስደስቶኛል…ትልቅ ዋጋ ያለውና የሀገራችንን የኢኮኖሚ መሰረት የሚቀይር ታሪክ ነው፡፡

ስለ ኮቪድ 19

ህብረተሰቡ እየተጠነቀቀ ነው ወይ ቢባል አልስማማም… ማክስ ያደረገ ማግኘት ሊናፍቅን እኮ ይችላል ማክስ ማድረግ፣ ርቀት መጠበቅና በሳኒታይዘር መፅዳት የግድ ወሳኝ ተግባር መሆኑን ማመን አለብን ህብረተሰቡ በተለይ ደግሞ ቅርቤ የሆነው ስፖርተኛው አካባቢ ያለው ቸልተኝነት መስተካከል አለበት በሚፈልገው መጠን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን አሁን ያለው ነገር ግን ይህንን አያሳይም፡፡ ሁሉም ለራሴ ብሎ ከተጠነቀቀ ኮቪድ 19ኝን መከላከል ይቻላል፡፡

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየዲሲፕሊን ውሳኔዎችዲሲፕሊን ውሳኔ

የዲሲፕሊን ውሳኔዎች

ገዛኸኝ ደሳለኝ (ሸገር ከተማ) : ክለቡ ከ ኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረገው የ26ኛ...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በዝናባማው ጨዋታ በመቻል ሲረታ የጣናው ሞገድም አሸንፏል

እጅግ በከባድ ዝናብ ታጅቦ በተደረገው ጨዋታ መቻል የሊጉን መሪ ሲዳማ ቡናን 3ለ1...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ሀድያ ሆሳዕና ፣ ፋሲል ከነማ እና ወላይታ ድቻ ወሳኝ ድል አግኝተዋል

በሊጉ የሳምንቱ የሁለተኛ ቀን መርሀግብር ሀዋሳ ከተማ ወደ ሊጉ መሪ የሚጠጋበትን ዕድል...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ፈረሰኞቹ በድል ሲቀጥሉ ንግድ ባንክ እና ድሬዳዋም አሸንፈዋል

ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታታይ ድሉን ወደ ቋቱ ሲከት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከጨዋታ ብልጫ...