“ሀገርን ያኮራን፣ ስሟን ያስጠራን ሳይሆን አዋርደን የመጣን ይመስል ሹልክ ብለን ወጥተን ሹልክ ብለን ነው የምንገባው… ይሄ በጣም ያማል” ኢንተ.ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ

በይስሐቅ በላይ


አዲስ ታሪክ ያፃፈችው ሊዲያ ታፈሰ
“ለሀገሬም ለራሴም አዲስ ታሪክ አፅፌ ዞር ብሎ ያየኝ የለም”
“ሀገርን ያኮራን፣ ስሟን ያስጠራን ሳይሆን አዋርደን የመጣን ይመስል ሹልክ ብለን ወጥተን ሹልክ ብለን ነው የምንገባው… ይሄ በጣም ያማል”

የሀገርን ስም ከፍ አድርገው ያስጠሩ… ባንዲራዋ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ምክንያት ለሆኑ ሰዎች ተገቢው ክብርና እውቅና የማይሰጠው ለምንድ ነው? እስከ መቼስ ነው የሰውን ውለታ እየበላንስ የምንኖረው? ይሄ ሁሌም የሚያበሳጨኝ ጉዳይ ነው፤ ከእግር ኳሱ የውጤት ካርታ ስሟ የጠፋው የሀገራችንን ስም በዳኝነት ሙያቸው ከፍ አድርገው እያስጠሩ ያሉት ሁለቱ ኢንተርናሽናል ዳኞቻችን በአምላክ ተሰማና ሊዲያ ታፈሰ የዚህ መጥፎ ባህላችን ሠለባ ከሆኑት ውስጥ ይጠቀሳሉ… ለሀገራቸው የሠሩትን፣ ስሟን ያስጠሩትን፣ ባንዲራዋን ከፍ አድርገው ያውለበለቡትን ያህል ከፍ አድርገን ያላከበርናቸው ይሉቁንስ ለስራቸው እውቅና የነፈግናቸው አንጡራ ሃብቶቻችን ናቸው፡፡
በቻን 2020 የወንዶችን እግር ኳስ ውድድር በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በመምራት ለራሷም ለሀገሯም አዲስ ታሪክ ያፃፈችው ኢንተርናሽናል አርቢትር ሊዲያ ታፈሠ ለዚህ ታላቅ ተልዕኮ ወደ ውድድሩ ስፍራ ስትጓዝም ሆነ አዲሱን ታሪኳን በደማቅ ቀለም አፅፋ ወደ ሀገሯ ስትመለስ ተገቢውን ክብርም እውቅናም የሰጣት አንድም የመንግሥት አካልም ሆነ ፌዴሬሽንም የለም.፡፡
አትሌቶች በግልም ሆነ በቡድንም ሲያሸንፉ፣ ቦክሰኞችና ብስክሊተኞች ስኬታማ ሲሆኑ የአበባ ጉንጉንና የገንዘብ ሽልማት ለመስጠት የሚጣደፉ ከፊት ከፊት የሚሉ አካሎች ለኢንተርናሽናል አርቢትሮቻችን ሲሆን ምን ውስጥ ነው የሚደበቁት? በማለት በቁጭት የሚጠይቀው የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ስኬታማዋን፣ ታሪክ ሰሪዋን ግን ደግሞ በሠራችው፣ ባፃፈችው ታሪክ ልክ ሣይሆን በተቃራኒው እውቅናንና ክብርን የነፈግናትን ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሠ ከብዙ ማግባባት በኋላ አነጋግሯታል፡፡.

“አውሮፓውያን ፈረንሣዊት ዳኛ አለችን ብለው እንደሚመፃደቁት ሁሉ እኛም ሊዲያ ታፈሠ አለችልን” በማለት አፍሪካዊያን በኩራት የሚናገሩላት ሊዲያ ታፈሠ በቻን 2020 ባገኘችው ክብርና ባፃፈችው አዲስ ታሪክ ፊቷ በደስታ ቢሞላም “በሀገር ቤት ያለውን ግን አታንሱብኝ እንኳን ክብርና እውቅና ሊሰጠኝ ቀርቶ ዞር ብሎ ያየኝም የለም… ሹልክ ብዬ ወጥቼ ሹልክ ብሎ መግባቱን ለምጄዋለሁ” በማለት ቁጭትን የሚያጋባ ምላሽ ለጋዜጠኛ ይስሀቅ ሰጥታዋለች፤ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም መመኪያ የሆችው ሊዲያ ታፈሠ ከቻን መልስ በተለይ ለሀትሪክ ጋዜጣ የሰጠችው ቃለ-ምልልስ ከዚህ በታች ያለውን ይመስላል፡፡

ሀትሪክ፡- .. ሊዲያ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም የቻን የወንዶች ውድድርን የመራሽ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ በመሆንሽ እንኳን ደስ አለሽ…?…እንኳን ለዚህ ትልቅ ታሪክ በቃሽ…?…

ሊዲያ፡- …እንኳን አብሮ ደስ አለን…ታሪኩ የእኔ ብቻ አይደለም…የሁላችንም ነው…እኔ ምክንያት ሆንኩ እንጂ…አዲሱ ታሪክ እኔን አበረታቶ፣መክሮ፣አስተምሮ ለዚህ ያደረሰኝ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው…ደስታውም፣ኩራቱም የሁላችንም ነው…

ሀትሪክ፡- …በአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን…የወንዶች ሻምፒዮና (የቻን ውድድርን)… እንደምትመሪ የሠማሽው እንዴት ነው…?…

ሊዲያ፡- …የሚገርምህ ምርጫው የተደረገው በ2020 ነበር…ምክንያቱም ውድድሩ በኮቪድ-19 ምክንያት ባይገፋ ኖሮ በ2020 ነበር የሚካሄደው…መጀመሪያ መረጃውን በዋትስአፕ የላካችልኝ አንድ ጓደኞዬ ናት…

ሀትሪክ፡- …እድሉ በታሪክ የመጀመሪያዋ ሰው የሚያደርግሽ ከመሆኑ አንፃር ለዚህ አዲስ ታሪክ የመመረጥሽን ዜና ስትሰሚ ምን አለሽ…?…እንዴትስ አስተናገድሽው…?…

ሊዲያ፡- …እውነት የሆነ ግን አምነህ ለመቀበል የምትቸገርው ነገር የለም…?…ልክ እንደዛ በቃ…ማመን አቃተኝ…በጣም ደነገጥኩ…ከዚህ በፊት የአለም ዋንጫን ጨምሮ ትልልቅ ውድድሮችን የመምራት እድል አግኝቻለሁ…በተመሳሳይ ለማመን የሚከብድ ነገርም በውስጤ ተፈጥሮ ያውቃል…ይሄኛው ግን ከእስከዛሬው ሁሉ የተለየ ነው…አስበኸዋል…?…ተደርጎ የማያውቀውን የወንዶች ውድድር አንዲት ትንሽ ሴት እንድትመራው ስትታጭ…?…ከ19 ወንድ ዳኞች ስም ዝርዝር ውስጥ የሬሴን ስም ማግኘት ይሄ በጣም የሚያስደነግጥ ነበር…የማደርገው ሁሉ ጠፍቶኝ ወዲያውኑ ተንበርክኬ ነው አምላኬን ያመሰገንኩት..በቃ የሆነ የማላውቀው ስሜት ሰውነቴን ሁሉ ወረረው…ከደስታዬ ብዛት…አልቅሺ…አልቅሺ ሁሉ አለኝ…ከጅማ ትንሽዋ ከተማ ለተገኘችው ሊዲያ…በታሪክ የመጀመሪያ የሚያደርጋትን…ሁሌም የእኔንም የሀገሬ ስም የሚጠራበትን ውድድር ያውም የአህጉሪቱን ሁለተኛው ትልቁን ውድድር እንድትመራ ስትመረጥ ያስደነግጣል…ለማመንም ይከብዳል…ግን ከብዙ ማማጥ በኋላ ደስታዬን ዋጥ አድርጌ አንድ ነገር ማሰብ ጀመርኩ…

ሀትሪክ፡- …ምን…?

ሊዲያ፡- …መመረጥ በጣም ትልቁ ነገር ነው…ግን ይሄ ብቻውን ስኬት ስላልሆነ…ብቁ ሆኜ ለመቅረብ ጠንክሬ መስራት አለብኝ ብዬ ከራሴ ጋር አወራሁ ብቻ ሣይሆን ቃልም ገባሁ…ምክንያቱም ውድድሩ የወንዶች የሀገሪቱ ሁለተኛው ትልቁ የአፍሪካ ዋንጫ ከመሆኑ አንፃር ከእኔ ብዙ ይጠበቃል…ለካ ሴቶችም ከወንዶች ምንም አይተናነሱም የሚለውን በማሣየት ለሌሎች እህቶቼ በሩን በደንብ መክፈት እንዳለብኝ አምኜ…ዝግጅቴን ቀድሜ ነበር የተያያዝኩት…እግዚአብሔር ይመስገን ያሰብኩትን አሳክቼያለሁ ብዬም አስባለሁ…

ሀትሪክ፡- …እንዳልሽው የአህጉሪቱ ሁለተኛው ትልቁ ውድድር ነው…ከ19 ወንድ ዳኞች ውስጥ ብቸኛዋ ሴት ዳኛ ሆነሽ መመረጥሽ በዳኞቹ ላይ ምን አይነት ስሜት ፈጠረ…?…

ሊዲያ፡- …ኦው…!…በጣም ልዩ የሆነ ስሜት ነበር የፈጠረው…በጣም የተለየ አቀባበልም ነው ያደረጉልኝ….በመሀከላቸው ብቸኛዋ ሴት ዳኛ እኔ ስለነበርኩ እንደ ብርቅ ነው የተመለከቱኝ… የሚገርምህ ሁሉም ዳኞች የእኔን ታሪክና ስራ እንዲሁም ካፍ ለዚህ ትልቅ ታሪክ ያለ ምክንያት እንደማይመርጠኝ ስለሚያውቁ በሁሉም ፊት ላይ ማለት እችላለሁ “የትችያለሽ” ስሜትን ነው ያነበብኩባቸው…አብዛኞቹ ትከሻዬን መታ መታ እያደረጉ “ጀግና ነሽ…አይዞሽ በርቺ ከጎንሽ ነን…” ምናምን ይሉኝ ነበር…ይሄ የአዕምሮ ስሜትህን ይበልጥ ያጠነከረዋል…ይበልጥም ያበረታሃል…አንተ ምናልባት ይሄ ሊገርምህ ይችላል…ከዚህ በበለጠ በእኔ ላይ ትልቅ እምነት እንዳላቸው የሚያሳይ አንድ ነገር ልንገርህ…?…

ሀትሪክ፡- …በጣም ደስ ይለኛል…ንገሪኝ…?…

ሊዲያ፡- …የካፍ ከፍተኛ የዳኞች አመራሮች፣ትምህርትና ስልጠና የሚሰጡት ሁሉ በእኔ አቅም…በእኔ ሥራ ከመተማመናቸው…ከመኩራታቸው የተነሣ “…አውሮፓዎች ፈረንስያዊት ምርጥ ዳኛ አለችን ብለው እንደሚናገሩት…እኛ ደግሞ ሊዲያ አለችን…”ብለው ሁሉም ዳኞች በተገኙበት በኩራት ስሜት ሲናገሩ ሁሉ ነበር…ይሄ በጣም ደስ የሚልና ትልቅ ጉልብትን የሚጨምር ነገር ነው….በተለይ ሁለት ፊዚካል ኢንስትራክተሮች አሉኝ “…ሊዲያ አንቺ እኮ ልዩ ሴት ነሽ፤የአፍሪካ መኩሪያ ነሽ…” በማለት ያላቸውን አክብሮትና አድናቆት በተደጋጋሚ ነበር የሚገልፁት…በአጠቃላይ በእኔ ላይ የነበረው እምነትና ክብር በቃላት ከምገልፅልህ በላይ ነው…፡፡

ሀትሪክ፡- …ከመመረጥሽ ሌላ በርካታ የዜና አውታሮችን ያጨናነቀው የቻን 2020 የመክፈቻ ውድድርን በመሀል ዳኝነት እንደምትመሪ በስፋት ስናፈስ ነበር…ይሄ ወሬ ከምንም መነሻነት የተወራ ይመስልሻል…?…እንድትመራ ከተመረጥሽ ለምን ሳትመሪ እንደቀረሽ ጨምረሽ ግለጪልኝ…?…

ሊዲያ፡- …(ፈገግ እንደማለት እያለች)…ይሄንን ዜና እኔም አይቸዋለሁ…በተለይ በማህበራዊ ትስስር ገጾችም…የመክፈቻውን ጨዋታ እኔ እንደምመራ በስፋት ሲናፈስ ነበር…እኔም በወቅቱ የተነገረኝ ነገር ስላልነበር…ነገሩ ሲደጋገምና በስፋት ሲናፈስ…እንዴ…!…ይሄ ነገር ምንድነው…?…ብዬ ደንግጬ ሁሉ ነበር ያየሁት…እንግዲህ ይሄ የሆነው ሰዎች ለእኔ ካላቸው Expectation (ከፍተኛ ግምት) የተነሣ ይመስለኛል…ከማህበራዊ ትስስር ገጾች ውጪ የተሰራጩትን የተለያዩ ዜናዎች ስመለከታቸው ደግሞ ከዚህ በፊት የተለያዩ ታላላቅ ውድድሮችን ማለትም የአፍሪካና የአለም የሴቶች ዋንጫዎችን፣የደረጃ ጨዋታዎችን አለም ዋንጫ ላይ የመራሃቸውን አጋጣሚዎችን እንዲሁም የወንዶች ውድድርን እንድመራ የተመረጥኩ ብቸኛ ሴት የመሀል ዳኛ ከመሆኔ የተነሣ ካላትና ብቃትና ታሪክ እሷ ልትመራው ትችላለች ከሚል ግምት የተወራም ይመስለኛል…ወደ ዕውነታው ስንመጣ ግን …ሲጀመር ሻምፒዮናው የወንዶች ውድድር ነው…ከ18 በላይ ወንድ ዳኞች አሉ…ከዚህ አንፃር ትንሽ ያስቸግራል… ግን ለእኔ የነበረው ግምት ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር ይመስለኛል እንደዛ የተናፈሰው…

ሀትሪክ፡- …አንቺን ባለታሪክ ያደረገሽን የናሚቢያና የታንዛኒያ ጨዋታን እንድትመሪ መመደብሽን ስትሰሚ ምን አለሽ…?…

ሊዲያ፡- …የትኛውን ጨዋታ እንደሆነ መገመት ባልችልም አንድ ጨወታ መምራቴ የማይቀር መሆኑን በውስጤ በጣም እርግጠኛ ስለነበርኩ ብዙም አልተገረምኩም…ከካፍ ከፍተኛ ኃላፊዎች መካከል አንደኛው “…የናሚቢያና የታንዛኒያን ጨዋታ ሰጥተንሻል…እንደምትወጪውም እምነታችን ነው…”ሲለኝ… አምናችሁ ሰጥታችሁኛል…አትጠራጠር…I Will Show to You…(አሣይሃለሁ) ነው ያልኩት…ወደ ሜዳ ገብቼም እምነት የጣሉብኝን ላለማሳፈር፣ለሴት እህቶቼም በር ለመክፈት የምችለውን ሁሉ አድርጌ ለመውጣት ሞክሬያለሁ…

ሀትሪክ፡- …ኃላፊነቱ ያልተለመደና አዲስ ታሪክ የሚመዘገብበት ከመሆኑ አንፃር የነበረው ጫናስ…?…

ሊዲያ፡- …እውነት ለመናገር ጫናው በጣም ከባድ ነበር…ለብዙዎች እንግዳና አዲስ ነገር በመሆኑ የሰውን፣የሚዲያውን ትኩረት በጣም የሳበ ነበር…ጋዜጦች፣የቴሌቪሽን መስኮቶች ሁሉ ወሬያቸው “የወንዶችን ውድድር የምትመራ ብቸኛዋ ሴት የመሀል ዳኛ” እያሉ ነበር በየቀኑ የሚዘግቡት… ጋዜጠኞች በተደጋጋሚ በርህን ያንኳኳሉ…በየጊዜው በየሄድክበት ካሜራ ይደቀንብሃል…በተለይ ልምምድ ስንሰራ የብዙዎች አይን ነበር የሚያርፍብን…ይሄ በጣም ያስጨንቅ…ኃላፊነቱን የበለጠ የከበደ እንደሆነ አድርገህ እንዲሰማህ ያደርግ ነበር…ከዚህ አንፃር መጀመሪያ ላይ ጫናው ትንሽ ከፍ ያለ ነበር…በኋላ ላይ ግን እየተላመድኩት መጣሁ…ከዚህ ይልቅ እኔን ሲየስጨንቀኝ የነበረው ሌላ ጉዳይ ነው…

ሀትሪክ፡-…ምንድነው እሱ…?…

ሊዲያ፡- …በቃ ነገሮች ሁሉ “…ሊዲያ ሊዲያ…” ሆኑ…አብረውኝ የተደለደሉት ሴት ረዳት ዳኞችም የታሪኩ ተካፋይ መሆናቸው እየታወቀ እነሱ ተረሱ…የሚዘገበው፣የሚፃፈው ሁሉ ስለ እኔ ብቻ መሆኑ የአነዚህን ረዳቶቼን አዕምሮ ይጎዳው ይሆን እንዴ…?…ብዬ እንዳስብ አደረገኝ…የእነሱ አዕምሮ መጎዳት ደግሞ ጨዋታዬን ሊረብሽው ይችላል ብዬ እስከመስጋት ሁሉ ደረስኩ…በተቻለኝ አቅም ታሪኩም የአነሱም ስለ ሆነ እነሱን ማበረታትና በአዕምሮ ማዘጋጀት ስለነበረብኝ አይዛችኋሁ አልኳቸው…በዚህ መሀል እያለን ከካፍ ከፍተኛ የዳኞች ኃላፊዎች አንደኛው የልብህን ደም የሚሞላ…የሚያበረታታ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለብኝ የሚያስረዳ ምክሩን ሲሰጠኝ…አረ ይሄ ነገር እንዴት ነው አልኩኝ…

ሀትሪክ፡- …ምን አይነት ምክር…?…

ሊዲያ፡- …“…ስሚ ሊዲያ የምወክለው ዳኞችን ብቻ ነው የሚል ግምት እንዳይኖርሽ…ከዳኝነቱ ከፍ ባለ የምትወክይው የአፍሪካን ሴቶች፣እናቶችን፣እህቶችን ነው…፤…እነዚህን ሁሉ ወክለሽ ነው መድረኩ ላይ የምትቆሚው…ስለዚህ ለጨወታው በጣም ዝግጁ መሆን አለብሽ…በሀገርሽ በጣም ትላልቅ የወንዶችን ውድድሮች እንደምትመሪ እናውቃለን…አንቺ የካፍ ሲኒዬር ዳኛ ነሽ…ከአንቺ መማሪያ፣ምሣሌ የሚሆን ነገር እንፈልጋለን…” ስትባል ኃላፊነቱን ድርብ ድርብርብ ያደርግብሃል…ግን ብርታቱን ጥንካሬውን የሚሰጥ አምላክ አብሮህ ካለ የሚሳንህ ነገር የለም…

ሀትሪክ፡- …እስቲ በታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ዳኛ ወደ አደረገሽ ወደ ናሚቢያና ታንዛኒያ ጨዋታ እንመለስ እስቲ…ጨዋታውን እንዴት ነበር…?…እንዴትስ ተወጣሽው…?

ሊዲያ፡- …ሁለቱም ቡድኖች ሁለተኛ ጨዋታቸው ነው…ሁለቱም በመጀመሪያ ጨወታቸው ስለተሸነፉ ከዚህኛው ጨዋታ የሆነ ነጥብ ይዘው የመውጣት እቅድን ይዘው ነው የመጡት…ሁለቱ ቡድኖች መጀመሪያ ሲጫወቱ በደንብ አይቼያቸዋለሁ…ረዥም ኳስ ነው የሚጫወቱት…በቅብብሎሽ የሚሄዱ ቡድኖች አልነበሩም…በረኞቻቸው ይጠልዛሉ…ዲፌንሶቹም እንደዛው…ከዚህ አንፃር ጨዋታው ብዙም አንደማይከብደኝ ቀድሜ ገምቻለሁ…ሜዳ ከገባሁ በኋላ ግን ነገሮች ሁሉ እንደ ግምቴ አልነበሩም… በተለይ ሁለተኛው 45 የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በጣም ከባድ ነበር…ሁለተኛው 45 ጎሎች የተቆጠሩበት፣ ብዙ ውሣኔዎች የተወሰኑበት፣ካርዶችንም መምዘዝ የጀመርኩበት ጨዋታም ነበር…ያም ቢሆን ግን ጨዋታውን ተቆጣጥሬ ለመውጣት ሞክሬያለሁ…

ሀትሪክ፡- …ለዳኝነትሽ ስንት ነጥብ ተሰጠሽ…?…ከጨዋታው በኃላስ ምን አይነት አስተያየት አገኘሽበት…?…

ሊዲያ፡- …ነጥቡን በተመለከተ ምን ሆነ መሰለህ…ጨዋታው እኔም ብዙዎቹም እንደገመቱት አልነበረም…በጣም ፈጣነ…ጨዋታው መቆም አልቻለም…ሁለቱም ውጤት ለማስመዝገብ ስለነበር ትኩረታቸው…ውጤት አስጠብቄ እወጣለሁ የሚል ነገር አልነበረም…በተለይ የመጀመሪያው 45 ፈታኝና አስቸጋሪ ነበር…ያም ቢሆን ግን…ሁሉም በዳኝነቴ አልተከፋም…በጣም ነው የተደሰቱት…ሁለቱም ረዳቶቼ…በዳኝነቱ ከሚገባው በላይ ነው የተደሰቱት…ኮሚሽነሩም…አሰሰሪዬም በጣም ነበር የተደሰተው… ለካርድ አለመቸኮሌን ወደውታል…“…ሪትሙ የማይታወቅ ጨዋታ ሆኖ ተቆጣጥረሽው ወጥተሻል፤ ኮርተንብሻል”…ብለውኛል…ካፍ ጨዋታውን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው አምኖ ለሴቶች የሰጠው.. ነጥቡንና ሌላውን ነገር ተወውና…በወንዶች ውድድር ላይ ሴቶች መዳኘት አይደለም ሜዳ ውስጥ ገብተው መውጣታቸው ብቻ በቂ ነው ይሉን ሁሉ ነበር…እንደውም በካሜሩን ያለውን ሙቀት በተመለከተ ወንዶቹ ዳኞች ጥያቄ ሲያነሱ…ምን መልስ አንደሚሰጣቸው ታውቃለህ…?

ሀትሪክ፡- …ኧረ አላውቅም ሊድዬ…አንቺው ንገሪኝ እንጂ…?…

ሊዲያ፡- …ሙቀት ነው፣ድካም አለብን ምናምን አትበሉ…ሊዲያ ይሄን ሁሉ Fight አድርጋ(ተቋቁማ) ነው የወጣችው…እያሉ ምሣሌ ሁሉ አድርገው ያነሱኛል…ክላስ ላይ የእኔ ነገር ይነሣል…በየጊዜው ማለት እችላለሁ…የሪፌሪ (ዳኞች) ዲፓርትመንት ጋር ያሉ ሰዎች በአስቡት ልክ ስለተሳካላቸው በጣም ተደስተዋል…ይሄንን ነገር ማስቀጠል ነው የሚፈልጉት…እንዳልኩህ ሌሎች ሴቶች ዳኞች ለካ ይችላሉ? ብለው እንዲያስቡ፣በድፍረት የወንዶችን ጨዋታ መምራት እንደሚችሉ የሚያሳይ በሩን ወለል አድርጎ የሚከፍት ነው…

ሀትሪክ፡-…በዚህ ጨዋታ የሀገርሽ ልጅ የሆነው ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በአምላክ ተሰማም የጨዋታው 4ተኛ ዳኛ ሆኖ አብሮሽ ተመድቦ ነበር…ከእሱ ጋርስ የነበረው ግንኙነት…?…ስለጨወታሽስ ምን አይነት አስተያየት ሰጠሽ…?…

ሊዲያ፡- …በአምላክም በጣም ደስተኛ ነበር…“…አንቺ የሀገሬ ልጅ፣ጓደኛዬ፣እህቴ ነሽ…ይሄንን ትልቅ ታሪክ እንድካፈል አብሬሽ መመደቤ በራሱ እኔንም እድለኛ ያደርገኛል…”…ሁሉ ብሎኛል…በአምላክ አብሮኝ በመኖሩ…እኔም በጣም እድለኛም፣ደስተኛም ነበርኩ…በአምላክ በጣም ነበር የረዳኝ…ከጨዋታው እንቅስቃሴ የራኩ ያህል ሲሰማኝ…በአምላክ እራኩ እንዴ…?…ስለው “…ኖ….ኖ…በፍፁም…”…እያለ ያበረታታኝ ያግዘኝ ሁሉ ነበር…በጣም የሚገርምህ ከበአምላክ ጋር የነበረን መከባበር፣መደማመጥ በጣም የሚያስቀና ነበር…ምግብ ስንበላ፣ትምህርት ሲሰጥ፣ክላስ ውስጥ የምናወራቸው ነገሮች ሁሉ የተለዩ ነበሩ…በአምላክ ባጁን ሲለጥፉልኝ የተመለከቱ ሁሉ…በመከባበራችን፣በመረዳዳታችን በጣም ነው እስከመገረም የደረሱት..በአምላክ ወንድሜ ስለሆነ ይሄንን በማድረጉ እኔ ብዙም ላልገረም እችላለሁ… እዛ የነበሩት ሁሉ ግን ከሚገባው በላይ በጣም ተደንቀዋል…

 

ሀትሪክ፡- …18ቱ ወንዶች ዳኞችስ ወይም ከሀገር ቤትስ ከጨወታው በኋላ የሰጡሽ አስተያየት አለ…?

ሊዲያ፡- …በጣም የሚገርምህ ሁሉም ዳኞች የኔን ጨወታ ተከታትለውታል…ብዙዎቹ በጣም ደስ የሚልና ጉልበት የሚሆን አስተያየት ነው የሰጡኝ….አንዳንዶቹ “…ልቤ በጣም ይመታ ነበር…” ብለውኛል…ሌሎች ደግሞ “…ለደቂቃ እንኳን አይናችንን ከቴሌቭዥን መስኮት ሳንነቅል ነው ጨወታውን የጨረስነው…ውሣኔሽ፣በራስ የመተማመን ስሜትሽ ደስ የሚል ነው…“…Well Done…”…ብለውኛል… ከሀገር ቤት እንኳን ከሰዓታችን ልዩነት አንፃር ብዙም ሰው ጨዋታውን ላይከታተለው ይቻላል… የተከታተሉ ሰዎች ግን በተለይ የእኔ የቅርብ የሆኑ የሙያ ጓደኞቼ ጭምር በጣም ገንቢ አስተያየት ሰጥተውኛል…ከእግር ኳስ አሰልጣኞችም እንዲሁ አስተያየታቸውን የሰጡኝ አሉ…ሁሉም ጥሩ ነገር ነው የሰጡኝ…ይሄን ይሄን ስታይ ደስ ይላል…ይበልጥም ትኮራበታለህ…ሌላው አንቶኒዮ ባፉ ድንገት ጉብኝት አድርጎ ነበር…“…አፍሪካ በአንቺ ኮርታለች…እርግጠኛ ነኝ ኢትዮጵያ ደግሞ በአንቺ የበለጠ ትኮራለች…ሴቶቹን ለመጨበጥ ነው የመጣሁት ሲለኝ…”…እንባ ሁሉ ነው የተናነቀኝ…የፌዴሬሽናችን ፕሬዚዳንት ኢሣያስ ጅራ ያውንዴ ነበር የነበረው…“…በጣም በጭንቀት ነው ያየሁት…ብዙ ሰዎች ኮርተዋል…በጣም ጥሩ ጥሩ ዳኞች ነው ያላችሁ…”…ብለውኛል…ብሎ እሱም ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥቶናል…

ሀትሪክ፡- …ግን..እኮ ሊዲያ ይሄ ሁሉ ሙገሣና አድናቆቶች ቀርበውልሽ…ከአንድ ጨዋታ በላይ ሳትመሪ መመለሽስ…ብዙዎች ላይ ጥያቄ የፈጠረ ነገር ሆኖ ተገኝቷል…ከዚህ ንፃር ምን ትያለሽ…?

ሊዲያ፡- …የሚገርምህ ከናምቢያና ከታንዛኒያ ጨዋታ የመሀል ዳኝነቴ ውጪ ሌላ አንድ ጨወታም በአራተኛ ዳኝነት መርቻለሁ…ብዙዎችም አንተ በጥያቄ ያነሳኸው አይነት የተደበላለቀ ስሜት ተፈጥሮባቸዋል…ሌላ ጨዋታ፣ግማሽ ወይም ሩብ ፍፃሜ ላይ ትመደባለች ብለው ሲጠብቁ…በአንድ ጨዋታ ብቻ መገደቤ ምንድነው ነገሩ…?…ብለው እንዲጠይቁም አድርጓቸዋል…ፕሬዚዳንታችን ኢሳያስም ተመሳሳይ ነገር ብሎኛል…“…የደረጃ ጨዋታ አካባቢ ስትመሪ…አሊያም አራተኛ ዳኛ መሆን ነበረብሽ…”ሁሉ ብሎኛል…አልዋሽህም ወደ ሀገራችሁ ተመለሱ ሲባል እኔም ራሴ ተመሳሳይ ስሜት ነው የተሰማኝ…እንዳልኩህ የብዙዎች ግምት በጣም ከፍ ያለ ነበር…በቃችሁ ስንባል…“…እንዴት ነው ነገሩ…ጥሩ አልዳኘሁም እንዴ…?…ብዬ ራሴን ተጠራጥሬ እስከመጠየቅ ሁሉ ደርሻለሁ…(ሳቅ)…

ሀትሪክ፡- …ግን ምክንያቱን ምንድነው ማለት…እንላለን…?

ሊዲያ፡- …ምንም የተለየ ምክንያት የለውም…አንዳ ረዳቴ እንደውም ችግር ኖርብን ወይም ደክመት ታይቶብን እንድንመለስ የተደረግን መስላት ስትጠይቅ…“…ኖ…ኖ…እንደዚህ እንዳታስቡ ይሄ እንደ ፕሮጀክት ነው…ሴቶች የወንዶችን ውድድርን በብቃት መምራት ይችላሉ…?…የሚል ነው…ዋናው ፕሮጀክታችንን ማሳካቱና ማስቀጠሉ ነው” ብለዋታል…፡፡…

ሀትሪክ፡- …አንቺስ በግልሽ በአንድ ጨዋታ በመመለስሽ ተቆጭተሻል…ፀፅትስ ተሰምቶሻል…?

ሊዲያ፡- …በፍፁም…!…ምንም አይነት የፀፀትም፣የቁጭትም ስሜት አልተሰማኝም…በጣም ደስተኛ ነኝ…በጣምም እድለኛ ነኝ…ለዚህ ያበቃኝን እግዚብሔርንም በጣም ነው የማመስግነው…እኔስ አንድ ጨዋታ መርቼ ለራሴም፣ለሀገሬም፣ለአህጉሬም አዲስ ታሪክ አፅፌ ነው የተመለስኩት…ይሄንን እድል ያላገኙ እኮ አሉ…በኮቪድ ተይዘው…ተመርምረው በኋላ ነፃ ቢሆኑም ግን የማጫወት እድል ሳያገኙ የተመለሱ አሉ…ከዚህ አንፃር እኔ በጣም እድለኛ ነኝ…እግዚብሔርንም በጣም ነው የማመሰግነው…ሴት ልጅ ሜዳ ገብታ የወንዶችን ውድድር ከወንዶች እኩል አጫውታ ማንም ሰው ቅር ሣይለውም ያለቀ ጨዋታ ነው…ያ ነው ትልቁ ነገር…

ሀትሪክ፡- …ብቸኛ ሴት የመሀል ዳኛ ከመሆንሽ አንፃር በካሜሩን የነበረውን አቀባበልስ እንዴት ነው የምትገልጬ?

ሊዲያ፡- …በጣምልዩ አቀባበል ነው የነበረው…በነገራችን ላይ ሴት ዋና ዳኛ እኔ ብቻ ብሆንም ሶስት ረዳት ሴቶች አብረውኝ ነበሩ…በካፍ ለውድድሩ የሚመደበው ሁለት ረዳት ዳኛ ብቻ ነበር…ነገር ግን ካሜሩን በአዘጋጅ ሀገርነትዋ ተጠቃሚ እንድትሆን አንድ ረዳት ዳኛ ተጨምሮላታል… ሁሉም ረዳቶቼ በጣም ብቁ፣ለውድድሩም የሚመጥኑ ናቸው…ወደ አቀባበሉ ስንመለስ…ለዳኞች በተለይ ለእኛ የተሰጠን ክብር በጣም የተለየ ነበር…በጣም የሚገርምህ…ብዙዎቹ በአዲስ አበባ በኩል ትራንዚት አድርገው ስለሚሄዱ እንክብካቤው የጀመረው ከኤርፓርት ጀምሮ ነው…ሻንጣዬን የመያዝ ቅድሚያ የመስጠት ነገር ነበር…ይሄን ያደረጉት በሴትነቴ ብቻ ሣይሆን የመጀመሪያና ሲኒዬር ከመሆኔም ክብር በመስጠት ነው… እዛ እንደደረስንም ከኤርፖርት ጀምሮ የነበረው አቀባበል ልዩ ነበር…መንገደኞች በሚጓዙበት ሣይሆን በልዩ ክብር (VIP) በተባለ ቦታ ነው እንድንሄድ የተደረገው…ሻንጣችን መኪና ድረስ ነው የመጣው..ወደ ሆቴል…ለጨወታ ሣይቀር የምንሄደው በሁለትና በሶስት ሞተረኞች ታጅበን ነው…በአጠቃላይ የጀግና ክብር ነው የተሰጠን…ልዩ አቀባበልም ነው የተደረገልን…በጣም የተለየና የማይዘነጋ የኩራት ስሜት እንደሰማኝም አድርጓል…፡፡

ሀትሪክ፡- …በሀገር ቤት ግን ነገሮች ሁሉ ከዚህ በተቃራኒ እንዳሉ መረዳት የሚከብድ አይመሰለኝም… የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ ብቻ ሣይሆን አፍሪካዊ ዳኛ የሆንሽበትን አዲስ ታሪክ አፅፈሽ…አሸኛኘትና አቀባበል ሳይደረግልሽ ሹልክ ብለሽ ወጥተሽ…ሹልክ ብለሽ ነው የገባሽው…?

ሊዲያ፡- …(…ድንገት አቋረጠችኝና…)…አይ ይሳቅዬ…ይሄንን ነገር ባታነሣው እመርጣለሁ… (እንደመማፀን እያለች)…እባክህ ይሄን ጥያቄ እለፈው…

ሀትሪክ፡- …ለምን አልፈዋለሁ…?…ይሄማ መነሣት አለበት…አንቺም በአምላክም የሀገር አምባሳደር ሆናችሁ…የሀገርን ስም እያስጠራችሁ…ታሪክ እያሰራችሁ…አንድም ቀን መንግሥት ክብርም እውቅናም የሰጠበትን አጋጣሚ አላስተዋልኩም…አትሌቶች ሪከርድ ሰበሩ ተብሎ…ብ/ቡድኑ አሸነፈ ሳይሆን በጠባብ ውጤት ተሸንፈ ተብሎ በአደባባይ ሲሾሙ ሲሽለሙ…አናንተ ይሄንን ሁሉ ታሪክ እየሰራችሁ ተገቢውን ክብር አለማግኘታችሁ ያስቆጫል…የአንቺ ስሜት በዚህ ላይ ምንድነው…?…

ሊዲያ፡- …ይሄንን ነገር ከዚህ በፊት አንተም ሌሎችም እኔንም በአምላክንም ጠይቃችሁን መልስ ሰጥተንበታል…በቃ በዚህ ጉዳይ ባታናግረኝ ደስ ይለኛል…በእኛ ሀገር ለዳኛ የተሰጠው ቦታ በጣም የወረደ ነው…ኢትዮጵያዊ ውስጥ ዳኛ ማለት ምንም አይነት ቦታ የሌለው ሙያ ማለት ነው…በቃ ኢትዮጵያዊ ውስጥ የወረደ ነገር ቢኖር ዳኝነት ነው…በሌላ ሀገር እንደኛ የሀገራቸውን ስም ያስጠሩ አዲስ ታሪክ የፃፉ ሰዎች ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የሚደረግላውን የጀግና አቀበበል ሰምተናል… በአምላክም ደጋግሞ ተናግሮታል…እኛ ሀገር ግን የዚህ ተቃራኒ ነው ያለው…እኔ በቻን ውድድር አዲስ ታሪክ ነው የፃፍኩት…የመጀመሪያዋ ሴትም ነኝ…ለሀገሬም፣ለራሴም አዲስ ታሪክ አፅፌ ስሄድም ሹልክ ብዬ ስመለስም ሹልክ ብዬ ነው የገባሁት…ሹልክ ብሎ ወጥቶ ሹልክ ብሎ መግባትን የለመድነው ነገር ነው…አዲስ ወይም ብርቅ ነገር አይደለም…ለምን ታሪካችንና ስራችን ዋጋና ክብር የሚሰጠው እንዳጣ አይገባኝም…በነገራችን ላይ ይሄ ጥያቄ የብዙ ጋዜጠኞች ጥያቄ ነው…..በየጊዜው ነው የሚነሣው… ሀገርን ያኮራን ስሟን ያሰጠራን ሣይሆን አዋርደን የመጣን ይመስል ሹልክ ብለን ወጥተን ሹልክ ብለን ነው የምንገባው…ይሄ በጣም ያማል…

ሀትሪክ፡- …ይሄ ነገር በጣም ያበሳጭሻል…?…

ሊዲያ፡- …እኔም…በአምላክም ተገቢው ክብርና እውቅና ሳይሰጠን የዳኝነት ዘመናችንን እያገባደድን ነው…እኛ የምንናገረው የምናዝነውም ለእኛ አይደለም…በእኛ እግር ተተክተው የሀገራቸውን ስም ለማስጠራት ለሚደክሙ ዳኞች ነው…እኛማ ለመድነው እኮ….ግን የሀገርን ስም ማስጠራት፣ባንዲራዋን ማውለብለብ ትርጉም ሲያጣ እንደ ሰው ያምሃል…ይሄ ነገር ነገ ለሚመጡት የሚያስተላለፈውን መልዕክት ሳስብ ነው የሚያመኝ…ሁሌም የምትሟገቱት ጋዜጠኞች ናችሁ… በፌዴሬሽንም በመንግሥትም የተለየ ቦታ ተሰጥቶት…ምንም የተደረገልን የተሰጠንም ክብር የለም…በየስብሰባው የፕሮግራሙ ማጣበቂያ ከመሆናችን ውጩ…ደጋፊዎች እንኳን ሥራቸው ዋጋ ተሰጥቶት ሲከበሩ፣ እውቅና ሲሰጣቸው፣ብዙ ነገር ሲያገኙ እኔና በአምላክ ግን ያገኘነውን ተወውና “ጎሽ አበጃችሁ፣ ጀግኖቻችን ናችሁ” ብሎ ያነጋገረን አንድም አካል የለም…ይሄ እንዳልኩህ ነው…በጣም ያማል… መልዕክቱም ከባድ ነው…፡፡

ሀትሪክ፡- …እሺ ይሄ ነገርስ ተስፋ እንድትቆርጪ ለሀገርሽ የበለጠ እንዳትሠሪ ያደረግሻል…?

ሊዲያ፡- …ለመድነው እኮ….ክብር አልተሰጠንም የተደረገልን ነገር የለም ብለን ስሜታችን አይጎዳም… ምክንያቱም ተደርጎልን ያየነው ነገር የለማ…?…ከአመት አመት አዲስ ታሪክ እያስመዘገብን…ሀገርን እያስጠራን ነው የተጓዝነው…ስለለመድነውና ስሜታችን ስለማይጎዳ ነው…፡፡

ሀትሪክ፡- …የአፍሪካና የአለም የሴቶችም ዋንጫን፣የU-20 የሴቶች አለም ዋንጫን የመክፈቻ ጨዋታ እንዲሁም የደረጃ ጨዋታን በማጫወት የሜዳልያ ባለቤት፤አሁን ደግሞ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የቻን 2020ን የወንዶች ውድድርን የመራሽ የመጀመሪያ ሴት ሆነሻል…ከዚህ ሁሉ ታሪክ በኋላ የሚቀርሽ ነገር አለ…?

ሊዲያ፡- … ህልሜ አላለቀም…ገና ያልጨረስኩት የቤት ሥራም አለኝ…ብዙ ስኬቶችን አግኝቻለሁ… ቢሆን ባሳካው ብዬ የምመኘው ነገር አለ…ኦሎምፒክ…!ኦሎምፒክ ማጫወት ትልቁ ግቤ ነው…ዘንድሮ አሳካዋለሁ ብዬ ነበር..ኮቪድ-19 መጥቶ ተላለፈ…እንግዲህ በቀጣይ ይካሄድ…? …አይካሄድ…?… ባላውቅም ኦሎምፒክ ላይ መዳኘት ትልቁ ግቤ ነው…ሌላው ራሴን በደንብ አዘጋጅቼ ሠርቼ የወንዶች ዋናውን የአፍሪካ ዋንጫ የመዳኘት ትልቅ ህልሙ አለኝ…፡፡

ሀትሪክ፡- …በካሜሩን ከካፍ ጋር የተፈራረምሽው ነገር እንዳለ ሰማሁ…እስቲ ስለ እሱ ደግሞ አውሪኝ… ?

ሊዲያ፡-ትክክል ነህ ፕሮፌሽናል ዳኛ ሆኜያለሁ…ለ2 አመትም ፈርሜያለሁ…ካፍ 20 ዳኞችን ይዟል… 18 ወንዶችን 2 ሴቶችን…በካፍ ትሬይኒንጎችን ትሠራለህ…ሪፖርቶች በኦን ላይን የምታቀርቧቸው አሉ…ስለዚህ ካፍ በፈለገ ሰዓት ነው የሚጠራህ…እንደ ፕሮፌሽናል…እንደ ሥራ ነው የምትይዘው… አሁን ከU-20 በኃላ በደንብ ጉዳዩን ያስቀጥሉታል…እኔ ደግሞ በፊፋ የ2023 እጩ ስለሆንኩኝ ትሬይኒንጌን በዛ ውስጥ እየሠራሁ ስለሆነ የመከታተል ነገር ላይኖራቸው ይችላል…ፕሮፌሽናል ዳኞቻቸውን ነው ለአፍሪካ ዋንጫ የሚጠቀሙት ብዬ አስባለሁ…እዛ ውስጥ የመግባት አላማ እለኝ… ኮርስ ይኖራል ከአፍሪካ ዋንጫ በፊት…እዛ ኮርስ ላይ የመሳተፍ እድሉን ካገኘሁኝ ብቃቴን አሣይቼ ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፍ ሌላ ታሪክ መስራት ነው የእኔ አላማ…?…

ሀትሪክ፡- …ባለፈው ከሀትሪክ ጋር በነበረሽ ቆይታ “ከፈረንሣዩ የአለም ዋንጫ በኋላ ዳኝነት በቃኝ፤ ፊሽካዬን እሰቅላለሁ”…ብለሽኝ ነበር…እስከአሁን ማጫወትሽ የተመለከቱ ዘገባውን ሀስተኛ አድርገው የወሰዱም አሉ…የቀጠልሽው የአቋም ለውጥ አድርገኸ ነው…?…

ሊዲያ፡- …ያኔ በወቅቱ ለአንተ መግለጫውን በሰጠሁበት ወቅት በሀገራችን በነበረው የዳኝነት ሁኔታ በጣም ተበሳጭቼ ነበር…የዳኝነት ውሳኔ በፖለቲካ መነፅር ነበር የሚታየው…ዳኞች ይደበደባሉ…ሁለት ዳኞች ተደብድበዋል…አንደኛው ኮማ ውስጥ እስከመግባት ደርሷል…በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ ሀገር ውስጥ ለማጫወት ከባድ የሆነበት ሁኔታ ነበር…ፊፋ ደግሞ ምን ያህል የወንድ ጨዋታ አጫውታለች? ቶፕ ሌቭል ነው? ወይም ሁለተኛ ደረጃ ያለን ውድድር ነው የምታጫውተው? ብሎ ይጠይቃል…ሌላውን ተወውና የሴቶች እንኳን ቢሆን የተመረጠ ይላል…ፖለቲካው በተጨማለቀበት ሰዓት ሂደህ ማጫወት ህይወትህን ነው መስዋዕት የምታደርገው…በሌሎች ሰዎችም ለዳኘነት የሚሰጠው ክብር በጣም የወረደ ነበር…ለተደበደቡ ዳኞች ከማዘን ከመቆርቆር ይልቅ መደብደባቸው፣መሰደባቸው ትክክል ነው እስከማለት ተደርሷል…አንዳንድ ሚዲያዎችም ዳኝነት በጣም እየወረደ ነው፣አሣፋሪ ደረጃ ላይ ነው እየተባለ አስተያየት ይሰጥ ነበር…በእነዚህ ነገሮች በጣም ንዴት ነበረብኝ…እየተሰደብን፣ እየተዋረድን፣እየተደበደብን የምናጫወተው ለምንድነው?የሚል ነገር ነበር በውስጤ የመጣብኝ…በዚህ ሁኔታ እዚህ ሀገር ማጫወት አይቻልም ብዬ…ከዚህ በኋላ ቢበቃኝስ…?…ብዬ በብስጭት የወሰንኩት ነገር ነበር…

ሀትሪክ፡- …ክርስቲያኖ ሮናልዶ እስከ 40 አመቴ በቶፕ ክለብ ደረጃ በብቃት እጫወታለሁ ብሏል… ሊዲያስ ከዚህ በኋላ ስንት አመት የማጫወት ሃሣቡ አላት…?…ፊሽካሽን መቼ የመስቀል ሃሣቡ አለሽ…?

ሊዲያ፡- …እንደዚህ አደርጋለሁ የምለው ነገር አይደለም…እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ነው የምቀጥለው…ይሄ ፊሽካ መስቀልን በተመለከተ…አንዴ ለአንተ እንዳልኩህ…ከዚህ በኋላ ዳኝነት በቃኝ… ማለቴን ዶክተር አያሌው ጥላሁን አይቶ…“…ሁለተኛ እንደዚህ አንዳትይ…ራስሽን እዚህ ጋ አቆማለሁ ብለሽ እንዳታወሪው…አንቺ በጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያለሽው አቆማለሁ የሚል ነገር ከአንቺ መስማት የለብንም…ሰውነትሽ በቃሽ ብሎ ሊያስቆምሽ ይገባል እንጂ ቀድመሽ በቃኝ ማለት የለብሽም…የተለያዩ ታሪኮችን…እየሠራሽ ነው ያለሽው…ሌላ ታሪክ ነው ከአንቺ የምንጠብቀው” ብሎኛል አባባሉ ትክክል ነው…እንግዲህ መቼ እንደማቆም እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው…ከፊቴም ብዙ ትልልቅ ውድድሮች አሉ….ኦሎምፒክ አለ፣2022 ሞሮኮ ላይ የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ አለ…ፋይናሉን የማጫወት ህልሙ አለኝ…ቀጣይ የወንዶች አፍሪካ ዋንጫ አለ…እዛ ውስጥም የመግባት እቅድም ህልምም አለኝ…የ2023 እጩ ውስጥም አለሁበት…መስመር ውስጥ ስለሆንኩኝ እግዚብሔር እሰኪፈቅድ መቀጠልን እንጂ በዚህ ቀን አቆማለሁ ብዬ የምሰጠው ቀጠሮ የለም…

ሀትሪክ፡- ..ሊዲዬ ለጊዜሽ በጣም አመሰግናለሁ…ያልተነሣ…የቀረ አለ የምትይው ነገር ካለ በይኝና እንለያይ…?…

ሊዲያ፡- …ለቻን ውድድር ከመሄድ በፊት…የዳኞች ኮሚቴ ሊዲያ ቻን ስለምትጓዝ፣ሀገር ስለምትወክል ብለው የመጀመሪያ ምርጫ ውስጥ አካተውኛል…በጣም ጥሩ የተመረጡ ጨዋታዎችን ሰጥተውኛልና እነሱን ማመስገን እፈልጋለሁ…ፌዴሬሽኑም እያንዳንዱን ነገር ይተባበረኝ ነበር…ወረቀት ሳላስገባ ሆቴል ሆኜ ደብዳቤ ይፃፍልኝ ስል እያንደንዱ ነገር ይፈፅምልኝ ነበር…መዝገብ ቤት ብትሄድ…የጽ/ቤት ኃላፊው ባህሩ ጋ ስሄድ ትልቅ ትብብር ነበር ለእኔም ለበአምላክም ሲደረገልን የነበረው…ስለዚህ እነሱን በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ…ከዚህ በተጨማሪ እዚህ ደረጃ እስክደርስ የረዱኝን፣የደስታዬ ተካፋይ የሆኑ ብዙ ሰዎች ናቸውና በተለይ ትልቅ ድጋፍ የሰጡኝን ሚዲያዎችን ጨምሮ…ለእኔ አቅም የሆኑትን ሰዎች ማመስገን እፈልጋለሁ…ለዚህ ላበቁኝ ሰዎችም ክብር አለኝ…አሁንም ከጎኔ እንደሚሆኑ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ…ሌላው ሀገራችን ሠላም እንደትሆን ነው ምኞቴ…ሀገር ወክለህ እየሄድክ ሀገር ሰላም ካጣች ያሳስብሃል…ሠላም ካልሆንን የትም መድረስ አንችልም…እግዚብሔር ይጠብቀን እላለሁ…ሌላው ትልቁ ህልሜ እኔ አዚህ እንደደረስኩኝ…ሌሎችም እኔ የደረስኩበት ደረጃ እንዲደርሱ የማበቃ ሰው አምላክ ያድርገኝ ነው መዝጊያዬ፡፡

 

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.