በአጀማመር በኩል ሁለቱም ቡድኖች የመጀመሪያውን አጋማሽ ጥሩ በሚባል የጨዋታ ፍሰት የጀመሩ ሲሆን በተለይ በኮልፌ በኩል ኳስን መሰረት ያደረገ የአጨዋወት መንገድን ሲከተሉ የተመለከትን ሲሆን በጅማ አባጅፋር በኩልም በመስመሮች በኩል ለመጫወት የሚደረጉ ጥረቶችን አልፎ አልፎ መታዘብ ችለናል።
ጨዋታው በጥሩ መንፈስ ቀጥሎ በ36ኛዉ ደቂቃ ላይ የጅማ አባጅፋሩ አጥቂ ራሂም ኡስማኑ የግብ ጠባቂዉን አዲሱ ቦቄ መዉጣት ተመልክቶ ከርቀት ግብ በማስቆጠር አባጅፋሮች እንዲመሩ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ኮልፌ ቀራኒዮ ቢይዝም ግብ ማስቆጠር ሳይችል ቀርቶ የመጀመሪያው አጋማሽ በጅማ አባጅፋር መሪነት ተጠናቋል። በዕረፍት ሰዓት ላይም የኮልፌዉ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ጥላሁን አበበ በዕለቱ ዋና ዳኛ ዳንኤል ግርማይ አማካኝነት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
- ማሰታውቂያ -
ከእረፍት መልስም ይበልጥ ተሻሽለው የገቡት ጅማዎች ተደጋጋሚ በሚባል መልኩ በአጥቂው ራሂም ኡስማኑ እና ተመስገን ደረሰ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተመልክተናል። በተለይ በ52ኛዉ ደቂቃ ላይ መላኩ ወልድ በቅጣት ምት የላካት ኳስ አንግሉን ገጭታ ወጥታለች ይሄም በጅማ በኩል የተደረገ ሌላው የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። በ69ኛዉ ደቂቃ ላይ ጅማ አባጅፋር በራሂም አማካኝነት 2ኛ ግብ ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ዉጭ በሚል በዕለቱ ዳኛ ተሽሯል።
ጨዋታው ቀጥሎ በ74ኛ ደቂቃ ላይ በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቅ የነበረዉ ተመስገን ደረሰ ግሩም ግብ አስቆጥሮ መሪነቱን ወደ 2ለ0 ከፍ ማድረግ ችሎ ነበር። ብዙም ሳይቆይ በ80ኛዉ ደቂቃ ላይ ከሳዲቅ ሴቾ ከግራ መስመር በኩል የተሻገረለትን ኳስ ተመስገን ደረሰ በሚገባ በመጠቀም ለራሱ 2ኛዉን ለክለቡ ደግሞ 3ኛ ጎል በማስቆጠር ጅማ አባጅፋር 3ለ0 በሆነ ዉጤት ኮልፌ ቀራኒዮን በማሸነፍ ጨዋታቸዉን አጠናቀዋል።
ጅማ አባጅፋር ነጥቡን ወደ 7 ከፍ በማድረግ ቀጣይ አመት በሊጉ ለመሳተፍ የሚደረገዉን ዉድድር ወልቂጤ ከተማ ማሸነፉ ተከትሎ ሶስተኛ ደረጃን መያዝ ችሏል።
በዉድድሩ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ሲሸጋገር ወደ ሊጉ የሚያድጉትን ሶስት ክለቦች ለመለየትም የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ በጉጉት የሚጠበቅ ይሆናል።