“ከምወደውና ታሪክ ከሠራሁበት ክለቤ ጋር በእንዲህ መልኩ በመለያየቴ አዝናለሁ”አስቻለሁ ታመነ /ቅዱስ ጊዮርጊስ/

“ከምወደውና ታሪክ ከሠራሁበት ክለቤ ጋር በእንዲህ መልኩ በመለያየቴ አዝናለሁ”

“ተሳስቻለሁ… ለሠራሁትም ጥፋት የቅዱስ ጊዮርጊስን ቤተሰብ ይቅርታ እጠይቃለሁ”
አስቻለሁ ታመነ /ቅዱስ ጊዮርጊስ/

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከፍተኛ የዲሲፕሊን ጥሰት ፈፅመዋል በሚል አምበሉን ጌታነህ ከበደን ጨምሮ ሙላለም መስፍን (ዴኮ)፣ አስቻለሁ ታመነና ጋዲሳ መብራቴን ከቡድኑ የማገዱ ዜና የሰሞኑ መነጋጋሪያ ርዕስ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በሳምንቱ አጋማሽ ደግሞ የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብነት ገ/መስቀል ከውጪ ሀገር መመለሳቸውን ተከትሎ ቦርዱ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ 4ቱ ተጨዋቾች ላይ የመጨረሻ ነው የተባለውን ውሣኔ አስተላልፏል፡፡ በዚህ መሠረት የአንድ አመት ውል የሚቀረው ጌታነህ ከበደን ጨምሮ ሰኔ 30/2013 ውላቸው የሚያልቀው አስቻለሁ ታመነ፣ ጋዲሳ መብራቴና ሙላለም መስፍንን በነፍስ ወከፍ ሃያ ሃያ ሺህ ብር እንዲከፍሉና እስከ ውላቸው ፍፃሜ ድረስ በማገድ ከዚህ በኋላ የክለቡን ማሊያ እንዳይለብሱ የመጨረሻ ያለውን ውሣኔ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ ይሄን የቦርዱን ውሣኔ ተከትሎ የመሃል ተከላካዩ አስቻለሁ ታመነ ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ በውሣኔው መደናገጡንና በዚህ መልኩ ከክለቡ ጋር እሰናበታለሁ ብሎ እንዳልጠበቀ በመግለፅ ስህተት በመስራቱ ይቅርታ የጠየቀበትን ቃለ ምልልስ እንዲህ አዘጋጅተነዋል፡፡

ሀትሪክ፡- አመሰግናለሁ.. የቅዱስ ጊዮርጊስ ቦርድን ውሣኔ እንዴት አገኘኸው…?

አስቻለው፡- በጣም ተከፍቻለሁ… በፍፁም እንዲህ ይወስናሉ ብዬ አልጠበኩም ያም ሆኖ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቦርድ የወሰነውን ውሣኔ አከብራለሁ እቀበላለሁ.. ኃላፊቱን ለመውሰድም ዝግጁ ነኝ ስህተቱ የኔ በመሆኑ የማቀርበው ቅሬታ የለኝም ነገር ግን ለጊዮርጊስ ካደረኩት አንፃር ውሣኔው ከባድ ሆኖብኛል ቅዱስ ጊዮርጊስ ለኔ ትልቅ ትርጉም ያለው ክለቤ ነው ብዙ ነገር ያገኘሁበት፣ ህይወቴን የለወጥኩበት ለብሔራዊ ቡድን የተመረጥኩበት ክለቡ አምኖኝ አምበል ደረጃ የደረስኩበት ታሪኬ ከጊዮርጊስ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ትልቅ ፍቅርና ክብር አለኝ፡፡ በውሳኔው በጣም ተሰምቶኛል ጥፋተኝነቱ የኔም ቢሆን እንዲህ ይጨክናሉ ብዬ አልጠበኩም ነበር፡፡ ከድሬደዋ ከመጣው በኋላ ከቤት ሁሉ አልወጣውም ውስጤ ተጎድቷል፤ በጣም ፀፀት ተሰምቶኛል ውሳኔው በፈጠረብኝ ሀዘን የበዓል ስሜት እየተሰማኝ አይደለም፡፡ የቦርዱን ውሣኔ አከብራለሁ ብያለሁ መነሻ ጥፋቱ የኔ ነውና ትክክለኛ ውሣኔ ነው የወሰነው ምንም ማለት አልችልም ነገር ግን ጥፋቴን ተረድቼ ይህን ታላቅ ክለብ በከፍተኛ የካሳ ስሜት ለማገልገል እያሰብኩ ሳለ የተሰጠው ውሣኔ ግን አስደንግጦኛል የተሰማኝ ፀፀት ከውሣኔው በኋላ የባሰ ሆኗል እያስተባበልኩ አይደለም ራሴን ወክዬ እንደማውራቴ ሙሉ በሙሉ ጥፋተኛ ነኝ ከምወደውና ታሪክ ከሠራሁበት ክለቤ ጋር በእንዲህ መልኩ በመለያየቴ አዝናለሁ ትልቅ ታሪክ የሰራሁበት በመጣሁበት ሁለት ተከታታይ አመታት ኮከብ ተጨዋች ተብዬ የተመረጥኩበት ክለቤ ነው የሊጉ ሻምፒዮን ሆኜ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ውጤታማ የሆንኩበት ለማልረሳው ምርጥ ታሪክ ያበቃኝ ክለብ ነው በጣም ነው የምወደው በዚህ መልኩ መለያየት ግን በጣም ያማል፡፡

ሀትሪክ፡- የይቅርታ ደብዳቤ አስገብተሃል… ካገባኸው ደብዳቤ አንፃር ይሄ ውሣኔ ይወሰነብኛል ብለህ ጠብቀሃል?

አስቻለው፡- ከድሬደዋ በመጣው በነጋታው የስፖርት ክለቡ ጽ/ቤት ተገኝቼ የይቅርታ ደብዳቤ አስገብቻለሁ ከዚህ አንፃር ውሣኔው እንዲህ ይከብዳል ብዬ አልጠበኩም መቀጣቴ ባይቀርም ግራና ቀኝ አይቶና አመዛዝኖ ይወስናል እንጂ ይህን ያህል ይጨከናል ብዬ አላሰብኩም በሰማሁት ውሣኔም ደንግጫለሁ በዚህ አጋጣሚ በቅዱስ ጊዮርጊስ ማሊያ ለነበረኝ ምርጥ ጊዜያት ከጎኔ ለነበሩ ደጋፊዎች አመራሮች፣ በአጠቃላይ ለስፖርት ቤተሰቡ ይቅርታ እጠይቃለሁ በዚህ መልኩ ስሜ መነሳቱ ጎድቶኛል ይሄን መጥፎ ስሜን የማድስበት ጊዜ እንደሚኖረኝ አምናለሁ ተሳስቻለሁ… ለሠራሁትም ጥፋት የቅዱስ ጊዮርጊስን ቤተሰብ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ክለቤንና የሀገሬን ብሔራዊ ቡድን በጥሩ ብቃት አገለግላለሁ ብዬ አስብ ነበር ለማንኛውም በተፈጠረው ችግር አዝኛለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት 3 አመታት ውጤታማ አልነበረም… ይሄስ ምን ስሜት ይፈጥራል…?

አስቻለው፡- ከባድ ጊዜ ነው ያሳለፍነው… ይሄ ለጊዮርጊሳዊያን አዲስ ነገር ነው ሁሉም የቡድኑ አባላት ልብ ውስጥ ትልቅ ሀዘን ነው ያለው… በተለያየ ምክንያት ነው ዋንጫ ያጣነው… በእግር ኳሳዊ ይሁን እግር ኳሳዊ ባልሆኑ ምክንያቶች ዋንጫ አጥተናል ያም ያበሳጫል ጊዮርጊስ ቤት የሚፈርመው ተጨዋች በሌላ ክለብ ውስጥ ኮከብ የሆነ ቢሆንም እኛጋ ሲመጣ ከቡድኑ ጋር ተዋህዶ ውጤትማ ለመሆን ጊዜ ይፈልጋል ይህም አንዱ ምክንያት ነው ያም ሆኖ ይሄ ውጤታማ ያልሆነ ታሪክ የሚያበቃበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ይሰማኛል… የቦርድ አመራሮቹ ለክለቡ ሟች ቀንና ማታ አሳቢ በመሆናቸው ለዚህ ክለብ ያላደረጉት ነገር የለም በውጤት ማጣቱ እነርሱን መተቸት አይቻልም ምርጥ መሪዎች ያለው ክለብ በመሆኑ ነገም ሌላ የድል ቀን እንደሚመጣ እርግጠኛ ነኝ… ከዚህ በተረፈ ለቡድኑ ተጨዋቾች በሀዋሳ በሚደረገው ቀሪ የፕሪሚየር ሊጉ መርሃ ግብር አብሬያቸው በመንፈስ ከነርሱ ጋር መሆኔን ለመግለፅ እፈልጋለሁ በርትተው ክለባችን ካለበት ደረጃ ከፍ በማድረግ ቢያንስ ሁለተኛ ሆኖ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ተሳታፎ ያበቁታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ምናልባት የቦርዱ ውሣኔ የብሔራዊ ቡድን ቦታዬን ያሳጣኛል ብለህ ትሰጋለህ…?

አስቻለው፡- እሱ አሁን አያሳሰበኝም የሀገሬ ብሔራዊ ቡድንን የማገልገል እድሌን አጣለሁ ብዬም አልሰጋም ገና ረጅም ጊዜያት አሉ ስሜን በመልካም የማስጠራበት ጊዜያቶች ይኖሩኛል ብዬ አምናለሁ ከርሱ ይልቅ የብሔራዊ ቡድን ተጨዋች እንደመሆኔ ትልቅ ተምሣሌት መሆን ሲገባኝ በዚህ መልኩ ስሜ በመነሳቱ አዝናለሁ… በተለይ ሙሉ እምነቱን ለጣለብኝ አሰልጣኝ ውበቱ አባተና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ትልቅ ይቅርታ እጠይቃለው፤ መጪው ጊዜዬ ክለቤንም ሀገሬንም የምክስበት እንደሚሆን ርግጠኛ ነኝ፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport