“ቅ/ጊዮርጊስን በሚያክል ትልቅ ቡድን ላይ የድል ግብን ላስቆጥር እንጂ ገና ብዙ የሚቀረኝ ተጨዋች ነኝ” ስንታየሁ መንግስቱ /ወላይታ ድቻ/

ወላይታ ድቻ ቅ/ጊዮርጊስን በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ስንታየሁ መንግስቱ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች 2-1 በማሸነፍ ደረጃውን ከ ወደ በማምጣት ያሻሻለ ሲሆን ለቡድኑ የአጥቂ ስፍራ ተጨዋችም ስንታየሁ ግቡ 9ኛ ሆኖም ተመዝግቦለታል።

ለወላይታ ድቻ ውጤት ማማር ዘንድሮ ጥሩ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው ይኸው ተጨዋች ቡድኑ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከረታ በኋላም ግብ ማስቆጠሩን ተከትሎም “ቅ/ጊዮርጊስን በሚያክል ትልቅ ቡድን ላይ የድል ግብን ላስቆጥር እንጂ በችሎታዬ ገና ብዙ የሚቀረኝ ተጨዋች ነኝ” ሲልም የሀትሪክ ስፖርት ጋዜጠኛው መሸሻ ወልዴ ባደረገለት ቃለ-ምልልስም አስተያየቱን ሰጥቷል።

ሀትሪክ ስፖርት በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ላይ ለወላይታ ድቻ በመጫወት ግቦችን እያስቆጠረ ካለውና ጥሩም በመንቀሳቀስ ላይ ከሚገኘው ስንታየሁ መንግስቱ ጋር በኳስ ህይወቱ እንደዚሁም ደግሞ በወላይታ ድቻ ውስጥ እያደረገ ስላለው ተሳትፎና ሌሎችን ጥያቄዎች አንስተንለት የሰጠን ምላሽ በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፤ ተከታተሉት።

ስለ ትውልድ ሀገሩና ስለ ቤተሰቡ

“የተወለድኩትና ያደግኩት በወላይታ ሶዶ ከተማ ውስጥ ነው፤ ቤተሰባችን ውስጥም 3 እህቶች እና 2 ወንድሞችም አሉኝ። ከእነዛ ውስጥም እኔ የመጨረሻው ልጅም ነኝ”።

ስለ እግር ኳስ ጅማሬው እና በቤተሰቡ ውስጥ እሱ ብቻ ስፖርተኛ እንደሆነ

“የእግር ኳስን መጫወት የጀመርኩት ገና ልጅ በነበርኩበት ሰዓት ዋይዛፕ ለሚባል የፕሮጀክት ቡድን ነው። ያኔም ከ15 ዓመት በታች ላለው ቡድንም መጫወት ጀመርኩ ትንሽ ከፍ ስልም ወላይታ ድቻን በወጣትነት ዕድሜዬ ተቀላቀልኩ። ከእኛ ቤተሰብ ውስጥ ብቸኛው ስፖርተኛ ደግሞ እኔው ነኝ። ሌሎቹ ወንድሞቼና እህቶቼ ደግሞ በንግድ ሙያ ላይ የተሰማሩና የመንግስት ሰራተኞችም ናቸው”።

የእግር ኳስን መጫወት ሲጀምር አድንቆት ስላደገው ተጨዋች

“በኳሱ ልጅ ሆኜ ያኔ ስጫወት ያደነቅኩት ተጨዋች ሽመክት ጉግሳን ነበር። ከውጪ ተጨዋቾች ደግሞ የዝላታን ኢብራይሞቪች አድናቂ ነበርኩ”።

ከዋናው ውጪ ስለሚጠራበት ቅፅል ስሙ

“በሶዶ እያለው አሁንም ድረስ አቡሽ ተብዬ ስጠራ በአርባምንጭ ደግሞ ዝላታን ኢብራሂሞቪች በሚል ነው የሚጠሩኝና እነዚህ ቅፅል ስሞቼ ሆነው ዘልቀዋል”።
ተጫውቶ ያሳለፈባቸው ክለቦችና ስለነበረው ቆይታ
“የመጀመሪያ ክለቤ ወላይታ ድቻ ነው፤ ከዛ በመቀጠል ደግሞ ለአርባምንጭ ከተማ ነው የተጫወትኩት ይኸው ቡድን ለሀላባ ከተማ በውሰት ሰጥቶኝም ከተጫወትኩ በኋላም ተመልሼ ወደ ቡድኑ መጣውና በመሀል ዓምና በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ወደሚሰለጥነው ባህርዳር ከተማ ከገባው በኋላ በአሁን ሰዓት ላይ ደግሞ ወላይታ ድቻን ተቀላቅዬ እየተጫወትኩ እገኛለሁ። በነበሩኝ የእስካሁን ቆይታዎቼም በተለይ ደግሞ ለአርባምንጭ ከተማና ለወላይታ ድቻ ስጫወት ለየቡድኖቹ 16 እና አሁን ደግሞ 9 ግቦችንም በማስቆጠር ቡድኖቹን ልጠቅም እና በቆይታዎቼም ደስተኛ ሆኜ ላሳለፍም ችያለሁ”።

የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታውን በተመለከተ

“ያ ጨዋታ በ2008 ሶዶ ላይ ለወላይታ ድቻ ገና ከu-17 እንዳደግኩኝ ተቀይሬ በመግባት ያደረግኩት ነበር። በወቅቱም ተስፋ ሰጪ ነገርን በራሴ ላይ ልመለከት ችያለሁ”።
በእግር ኳስ መጫወቱ ላይ ስላለው የቤተሰብ አመለካከት
“እነሱ ሁሌም ከጎኔ ናቸው። በተለይ እህቶቼ ያኔ ስለ ኳስ የሚያውቁት ነገር ባይኖርም እኔ ከምነግራቸው ነገር በመነሳት በብዙ ነገሮች ይደግፉኝ ነበር። አሁንም ድረስ ለእኔ ጥሩ ነገር አላቸው”።

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ቡድናቸው እያደረገ ስላለው የውድድር ተሳትፎው እና 9 የሚደርሱ ግቦችን እስካሁን ስለማስቆጠሩ

“የወላይታ ድቻ የእዚህ ዓመት ጉዞ ውድድሩ ሲጀመር ባሰብነው መልኩ ባይሄድልንም አሁን ላይ ግን ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ስናመራ ከፍተኛ መሻሻልን እያሳየን ነው። መጀመሪያ ላይ ቡድናችን በእንቅስቃሴ ደረጃ ጥሩ የነበረ ቢሆንም ከተጨዋቾች የልምድ እጦት ማነስ እና በጥቃቅን ስህተቶች ውጤትን እያጣን ነበር። ከዛም ያለብንን ችግሮች በአዲሱ አሰልጣኛችን ከቀረፍን በኋላ አሁን ላይ ወደ ውጤታማነቱም እያመራን ይገኛል። ይሄ የመጣው ለውጥም ቡድናችንን እያስደሰተው ይገኛል። ከጎል ማስቆጠሬ ጋር በተያያዘ ዘንድሮ በ20 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፌ 9 ግቦችን ላስቆጥርና 3 የግብ ኳሶችን ደግሞ አሲስት /ላቀብል/ ላደርግ የቻልኩት በልምምድ ሜዳ ላይ ሁሌም ጠንክሬ መስራት ስለቻልኩና ጎል ጋርም የማልጠፋም ተጨዋች ስለሆንኩ ነው። ከዛ በተጨማሪም ቀደም ሲል እኛን ያሰለጥነን የነበረው የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ፣ ደለለኝ ዲቻሳና የአሁኑ አሰልጣኛችን ዘላለም ሽፈራው የሚሰጡኝን የጨዋታ ታክቲክና ምክርንም የምተገብር እና ሁሌሞ በአግባቡም የማዳምጥ ተጨዋች መሆኔም ለእዚሁ ግብ አግቢነቴ በጣሙን ሊረዳኝ ችሏል”።

ወላይታ ድቻ በቤትኪንጉ የት ድረስ ይጓዝ እንደሆነ

“ውድድሩን ስንጀምር ከውጤት ማጣት ጋር በተያያዘ የእኛ ዋንኛ ዓላማ የነበረው በሊጉ ላይ ጥሩ ተፎካካሪ በመሆን እዛው ለመቅረት እና ለመትረፍ ነበር፤ በኋላ ላይ ግን የውጤት መሻሻሎች ሲመጡና አሁን ላይ ደግሞ ከፍተኛ መሻሻሎች ሲኖሩ ውድድሩን እስከ ደረጃ ተፎካካሪነት በሚያስፈፅም ሁኔታ ላይ የመጨረስ ዕድሉ ስላለን ያን ለማስፈፀም በእያንዳንዱ ቀሪ ጨዋታዎቻችን ላይ ተግተን እንሰራለን”።

ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ስላደረጉት ጨዋታና ስለተጎናፀፉት ድል

“በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሚያክል ጠንካራ ቡድን ጋር ተጫውተህ ግጥሚያን ማሸነፍ መቻል በጣም ያስደስታል። በኳሱ ላይ ከፍተኛ ተነሳሽነትንም ይፈጥርልሃል። ከእነሱ ጋር ባደረግነው የረቡዕ ጨዋታ ሜዳው በጣም ጨቅይቶ ነበር፤ ለምታደርገው እንቅስቃሴም ሜዳው ምቾትንም አይሰጥምም ነበርና በዛ መልኩ ተጫውተን ነው ግጥሚያውን ለማሸነፍ የቻልነውና ያ የእኛን ቁርጠኛ መሆንን ያሳያል፤ ያገኘነው ድልም ይገባናል”።

በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የድል ግብን ስለማስቆጠሩ እና ዘንድሮ ግቦችን ካስቆጠረ በኋላ እያሳየ ስላለው የደስታ አገላለፁ

“በቅ/ጊዮርጊስ ላይ ቡድናችንን ለአሸናፊነት ያበቁትን ግቦች ለማስቆጠር በመቻሌ በጣም ነው ደስ ያለኝ ከእነሱ ጋር በተደረገ የሊግ ግጥሚያ ላይም ያ ጨዋታ ለእኔ የመጀመሪያዬ ስለሆነና ግብ ስላስቆጠርኩበትም ነው ልደሰት የቻልኩት። ግብን ካስቆጠርኩ በኋላ የማሳያቸው የደስታ አገላለፆች ማንም ቡድን ላይ ጎል አገባው የተለየ የሚባልም አይደለም ። እነዚህን ግቦች ሳስቆጥርም ሁሌም ከጎኔ ናቸውና እህቶቼንም ነው የማስባቸውም”።

በቅ/ጊዮርጊስ ላይ ግብ ማስቆጠሩን ተከትሎ እና አሁን ላይ ካለው ብቃት አንፃር ራሱን የተለየ ተጨዋች አድርጎ ያስብ እንደሆነ

“በፍፁም፤ እኔ ቅ/ጊዮርጊስን በሚያክል ትልቅ ቡድን ላይ የድል ጎልን ላስቆጥር እንጂ በችሎታዬ ገና ብዙ የሚቀረኝ ተጨዋች ነኝ። አሁን ላይ የምገኝበትን ደረጃም በደንብ እያወቅኩትም እገኛለሁ እና ቀጣዩን ጊዜ እያሰብኩ ነው ለትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ ከወዲሁ እየተጋው የሚገኘው”።

ስለ ወደፊት እልሙ

“ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከዛ በፊት ደግሞ ለተተኪው ቡድን ተመርጬ ብጫወት ደስ ይለኛል። እነዚህ ዋንኛ እልሞቼ ናቸው። ሌሎቹ እልሞቼና ምኞቶቼ ደግሞ እንደ እነ ጌታነህ ከበደ፣ ሽመልስ በቀለ እና ሌሎችም ተጨዋቾች ወደ ውጪ በመውጣት በፕሮፌሽናል ደረጃ እንደተጫወቱት ሁሉ እኔም ይህንን ማሳካት እፈልጋለሁ”።

በእግር ኳስ ተጨዋችነቱ ማሻሻል ያለበት

“በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ላይ ቸርነት ጉግሳ አቀብሎኝ ያገኘዋትን ኳስ ወደ ግብነት እንደቀየርኳት ሁሉ አሁንም ከአንድ አንድ የማገኛቸውን ግቦች ማስቆጠሩ ላይ በሚገባ ትኩረት በማድረግ መስራት አለብኝ። ሌላኛው ደግሞ ከግል እንቅስቃሴ ይልቅ የቡድን ስራም ላይ በደንብ መሳተፍም ይኖርብኛልና እነዚህን ነው ማሻሻል የምፈልገው”።

የፋሲካን በዓል አስመልክቶ

“በቅድሚያ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለእዚህ በዓል አደረሳችሁ ለማለት እፈልጋለሁ። በዓሉም የሰላም የፍቅርና የመተሳሰብ እንዲሆንላችሁም እመኛለሁ”።

ፋሲካን ከዚህ ቀደም በምን መልኩ ሲያሳልፍ እንደነበርና ዘንድሮስ

“ይህን በዓል ከዚህ በፊት ያከበርኩት ከቤተሰቦቼ ጋር ሆኜ ነበር። አሁን ግን ሐዋሳ ላይ ረቡዕ ጨዋታ ስላለን ወደዛ በመጓዝ የነገውን በዓል ከቡድን ጓደኞቼ ጋር እዛው አሳልፋለሁ”።

ከኢትዮጵያ ቡና ስላላቸው ቀጣይ ጨዋታ

“ጥሩ ጨዋታን ለእንቅስቃሴ አመቺ በሆነው የሐዋሳ ሜዳ ላይ ሁለታችንም እናሳያለን። በ90 ደቂቃው የጨዋታው ሰዓት ደግሞ የተሻለው ቡድን አሸናፊ ሆኖ የሚወጣ ይሆናል”።

በመጨረሻ

“በእግር ኳሱ ዛሬ ላይ ለደረስኩበት ደረጃ የእኔ ጥረት ብቻ እዚህ ቦታ ላይ አላስቀመጠኝም። ስለዚህም በብዙ ነገሮች የረዱኝን ቅድሚያ ምስጋናን የማስቀምጥለት ፈጣሪዬ ነውና እሱን ላመስግን። ከዛ ቤተሰቦቼን፣ የቡድን ጓደኞቼን፣ ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች፣ የወላይታ ሶዶ ህዝብና አብሮ አደጎቼን ላመሰግናቸው እወዳለሁ”።

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website