“ፋሲል ከነማ ጥንካሬውን በሚገባ አሳይቷል፤ የእዚህ ዓመት ዋንጫም ይገባዋልና ሊያነሳ ተቃርቧል”በዛብህ መላዮ /ፋሲል ከነማ/

“ፋሲል ከነማ ጥንካሬውን በሚገባ አሳይቷል፤ የእዚህ ዓመት ዋንጫም ይገባዋልና ሊያነሳ ተቃርቧል”

“ለዋንጫ የሚጫወት ቡድን ጥሩም ሆነ ጥሩ ባልነበረበት ጨዋታ ላይ ግጥሚያን ያሸንፋልና እኛንም እንደዛ አይነት ሁኔታ አልፎ አልፎ አጋጥሞን ያውቃል”

“በሁለቱም የጨዋታ ሚናዎች ላይ ምንም አይነት ችግር የለብኝም፤ ፍላጎቴ ቡድኔን ውጤታማ ያድርግ እንጂ አሰልጣኜ በሚያጫውተኝ የትም ቦታ ላይ መጫወትን እፈልጋለሁ”በዛብህ መላዮ /ፋሲል ከነማ/

የፋሲል ከነማው የአማካይ ስፍራ ተጨዋች በዛብህ መላዮ ቡድናቸው አዳማ ከተማን 2-1 ካሸነፈ በኋላ ስለ ዕለቱ ጨዋታ፣ የድል ጎልን ስለማስቆጠሩ፣ ስለ ቡድናቸው የውድድር ዘመኑ ጉዞ እና ሌሎችንም ጥያቄዎች ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ አንስቶለት የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል።

ለትንሳኤ በዓል እንኳን አደረሰህ?

“እናንተንም እንኳን አደረሳችሁ፤ አመሰግናለሁ”።
በዚህ አጋጣሚ እንኳን አደረሳችሁ ለማለት የምትፈልገው
“ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች፣ በጣም ለምወዳቸው እና ለእኔ ብዙ ነገርን ላደረጉልኝ ቤተሰቦቼ፣ ለፋሲል ከነማ ደጋፊዎች፣ ለክለቡ አጠቃላይ የቡድን አባላትና አመራሮች እንደዚሁም ለአብሮ አደግ ጓደኞቼ እንኳን አደረሳችሁ እያልኩ በዓሉ የሰላም የፍቅር የመተሳሰብ እንዲሆን እመኛለሁ፤ መልካም በዓል ለሁላችሁም ይሁን”።

በቤትኪንጉ አዳማ ከተማን ድል ስላደረጉበት ጨዋታ

“በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታው የሚከብድ እና ሜዳው ደግሞ ኳስ ለመቀባበል ፈፅሞ የማያመች ነበር። በዛ ላይ የምንጫወተው ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ከሚታገል ቡድን ጋር ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ አዳማዎች ይህን አውቀው ዳይሬክት ፉትቦል /ቀጥተኛ ኳስን/ ሲጫወቱ ስናይም ነበር፤ እኛም የእነሱን አይነት አጨዋወት ልንሞክር ስንል እንቅስቃሴው አዋጭ ስላልነበር ከእረፍት በኋላ በምን መልኩ መንቀሳቀስ እንዳለብንና ይህ ውጤት ደግሞ በጣም የሚያስፈልገን መሆኑን በመነጋገርና እኛን በሚገልፅ መልኩም በዚሁ ጊዜ ለመጫወት በመሞከር ከመጀመሪያው አጋማሽ የሚሻለውን ቡድን ይዘን ቀርበን የግጥሚያው አሸናፊ ልንሆን ችልናል”።

የመጀመሪያ ጎላቸውን ለማስቆጠር ስለመዘግየታቸው

“ጎሉን ለማስቆጠር የእውነት ነው ዘግይተናል፤ የሜዳው ለጨዋታ አመቺ አለመሆንም ነው በዋናነት ግቡን እንዳናስቆጥር ያደረገን። በኋላ ላይ ግን የእኛ ቡድን ለዋንጫ የሚጫወት በመሆኑ ዘግይተንም ቢሆን ግቡን አስቆጥረናል። ሌላ ባስቆጠርነው ተጨማሪ ግብም ለማሸነፍ ችለናል”።

ፋሲል ከነማ አልፎ አልፎ ጥሩ ባልነበረበት ግጥሚያዎች ላይም ጨዋታዎችን አሸንፎ ስለሚወጣበት መንገድ

“ይህ በእግር ኳስ ጨዋታ ሊያጋጥም የሚችል አይነት ነው። የሜዳዎች ለምታስበው እንቅስቃሴ ምቹ አለመሆንና አንድ አንዴ ደግሞ ቀንህ ይሆንና ብዙዎች በሚጠብቁቅ መልኩና ራስህም በሚታወቅህ ሁኔታ ጥሩ ላትንቀሳቀስ ትችላለህ። ይህ አይነቱ ሁኔታ እኛን ያጋጠመን ቢሆንም ከውጤት አንፃር ግን የዋንጫ ቡድን ከመሆናችን አኳያ ግጥሚያዎችን አሸንፈን ልንወጣ በቅተናል። ጥሩ ያልነበርንበትን እንቅስቃሴ ደግሞ በቀጣይነት አርመን የምንመጣ ይሆናል”።

አዳማ ከተማን ባሸነፉበት ጨዋታ የድል ግብን ስለማስቆጠሩ እና ከዛ በፊትም በነበሩት የኳስ ህይወቱ ወሳኝ ወሳኝ ግቦችን ስለማግባቱ

“ወሳኝ ግቦችን ለማስቆጠር መቻል ሁሌም ቢሆን ደስታን ይሰጥሃል። እነዛን ግቦች ለማስቆጠር ደግሞ የምትጫወትበት ቦታም ይወስነዋልና ለዛ ነው ግቦችን የማስቆጥረው። ወላይታ ድቻ ሳለው ፕሌይ ሜከር ሆኜ ነበር የምጫወተው ግብ ጋር ቶሎ ቶሎ እደርስ ስለነበርም በኢንተርናሽናል ጨዋታ ላይ ጭምር ግብን ላስቆጥርም ችያለሁ። ለፋሲል ከነማ ስጫወት ስኪመር ሆኜ ነበር ስጫወት የነበርኩት። በሁለት ስኪመርም ነበር ስንጫወት የነበረው። ሱራፌል በ5 ቢጫ ሲያርፍ ደግሞ ፕሌይ ሜከር ሆንኩ። አሰልጣኝ ስዩም ለእኔ የተለየ ሚና እየሰጠኝም ከስኪመር እየተነሳው እንዳጠቃም ያደርገኛል። በእነዚህ የጨዋታ ሚናዎች ሁሉ ነው ግብ ጋር የመድረስ ብቃቱ ስላለኝ ግቦችን ለማስቆጠር የቻልኩት”።

ፕሌይ ሜከር? ወይንስ ስኪመር?
ከሁለቱ ሚናዎች በየቱ ላይ መጫወትን እንደሚመርጥ

“በሁለቱም የጨዋታ ሚናዎች ምንም አይነት ችግር የለብኝም፤ ፍላጎቴ ቡድኔን ውጤታማ ያድርግ እንጂ አሰልጣኜ በሚያጫውተኝ የትም ቦታ ላይ መጫወትን እፈልጋለሁ”።

በሀድያ ሆሳዕና ላይ ጎል ሲያገባ ደስታውን በአክብሮት ስለገለፀበት መንገድ

“ከእነሱ ጋር ስንጫወት ጎል አግብቼ ደስታዬን ለእነሱ ካለኝ ከፍተኛ ፍቅር የተነሳ በአክብሮት ደረጃ ለመግለፅ የቻልኩት ሀድያ ሆሳዕና ተወልጄ ያደግኩበት እና በኋላ ላይም በልጅነት ዕድሜዬ ላይ አባቴ ይሰራበት ወደነበረው መርቲ ጃጁ ከሄድኩ በኋላና ኳስንም ከትምህርት ጋር ጎን ለጎን እያስኬድኩት ወደ 9ኛ ክፍል ካለፍኩ በኋላ ተመልሼ ወደ ሆሳዕና መጥቼ ከኖርኩና ኳስንም ከተጫወትኩ በኋላ ወደ ወላይታ ድቻም እንድገባ የጥርጊያ መንገድን ሊከፍትልኝ የቻለ የምወደው ቡድኔ በመሆኑ ለዛም ነው ያንን የደስታ አገላለፅ ያሳየሁት”።

አዳማን ካሸነፋችሁ በኋላ በመልበሻ ክፍል ውስጥ የገለፃችሁት ደስታ ሻምፒዮናነታችሁን ያረጋገጣችሁ ያህል መሆኑ

“የእውነት ነው ለብዙዎች ይመስላል። እኛ ግን በዚህ መልኩ ደስታችንን የገለፅነው በዛ ጨዋታ ላይ ብቻ ሳይሆን ከባህርዳር ጨዋታ ጀምሮ ነው”።

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫውን ድሬዳዋ ላይ እናረጋግጣለን ብላችሁ ጠብቃችሁ እንደነበር

“አዎን ካለን ጥንካሬ አኳያና ከምርጥ የቡድን መንፈሳችን አንፃር እኛ ብቻ ሳንሆን ብዙዎችም ነበር የጠበቁን። ግን የኳስ ነገር ሆነና ይሄን ሳናሳካ ቀረን። ፈጣሪ ለእኛ ያለው ሐዋሳ ላይ ይሄን ድል ትቀዳጃላችሁ ብሎ ስለሆነ ያን እየጠበቅን ነው”።
የቤትኪንግ ዋንጫው ይገባቸው እንደሆነ
“በሚገባ ነዋ! ፋሲል ከነማ ዘንድሮ ጥንካሬውን አሳይቷል፤ ከልፋቱ አንፃርም የእዚህ ዓመት ዋንጫ ይገባዋል፤ እሱንም ሊያነሳም ተቃርቧል”።

ፋሲል ከነማን የሚለየው

“ብዙ ቡድኖችን እንደተመለከትኩት አቻ መውጣት ሲያስደስታቸው ይታያል። እኛ ፋሲሎች ጋር ስትመጣ ግን ሁሌም ወደ ሜዳ የምንገባው እያንዳንዱን ጨዋታ ለማሸነፍ ነውና ያ ካልተሳካ አለያም ደግሞ ጥሩ ሳንሆን ስንቀር ራሱ የተሸነፍን ያህል ያለመነጋገር ስሜት እና ጥሩ ስንሆን ደግሞ አሪፍ ነው በመባባል ራሳችንን የመውቀስም የማበረታታትም ስሜት አለንና በዚህ መልኩ ነው የምንገለፀው”።

በመጨረሻ

“ፋሲል ከነማ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ እያሳካ ላለው ድንቅ ውጤት ፈጣሪን በቅድሚያ ማመስገን እፈልጋለሁ። ከዛ ውጪ በጣም የሚለፋ አሰልጣኝ አለንና ስዩም ከበደንና ኮቺንግ ስታፉን እንደዚሁም ደግሞ ታሪካዊ ደጋፊም አለንና እነሱ ዘንድሮ በአካል ተገኝተው ባይመለከቱንም ሊመሰገኑ ይገባል። ቤተሰበ

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website