ሰበታ ከተማና ተጨዋቾቹ በክፍያ ጋር በተያያዘ እየተወዛገቡ ነው

 

ዛሬ ወደ የፕሪሚየር ሊጉ የመጨረሻ መርሃ ግብር ወደ ሚደረግባት ሀዋሳ ሊያቀኑ ቀጠሮ ቢይዙም ጉዞው ተስተጓጉሏል። “ባህር ዳር ልንሄድ ስንል ተነጋግረን ስትመለሱ ይከፈላል ተባልን ጨርሰን ወደ ሰበታ ስንመለስ ዝም ተባልን እንደገና ወደ ድሬዳዋ ሄድን አሁንም ስንመለስ ዝም ተባልን አሁንም የተከፈለን ነገር የለም” ሲል ውስጥ አዋቂው ጉዞ የተስተጓጎለበት ምክንያት ገልጾ “ሌላው ቢቀር ሌሎቹ ክለቦች የፋሲካ በአልን ምክንያት አድርገው የሚያዚያ ወር ደመወዝን አስቀድመው ቢከፍሉም የኛ ክለብ አመራሮች ግን በዝምታ ማለፋቸው ተጨዋቾቹ ላይ ቅሬታ ፈጥሯል” ሲልም ተናግሯል።
ከ 2-5 ወር ደመወዝ ያልተከፈላቸው፣ ኢንሴንቲቭ ያልተሰጣቸው፣ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ያልወሰዱ ተጨዋቾች መኖር ደግሞ የክለቡን ውጤት አበላሽቶት ወደ ወራጅ ቀጠና እንዳይገቡ ተሰግቷል።

በ19 ጨዋታ 26 ነጥብና 1 የግብ እዳ ይዞ በ8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ሰበታ ያለመውረድ ተልእኮ ላይ ስጋትም ጭሯል። በመጪው ዓርብ ከሲዳማ ቡና ጋር ጨዋታ ያለበት ሰበታ ከተማ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ምላሽ ለማግኘት ወደ ስራ አስኪያጁ አቶ አለማየሁ ምንዳ ስልክ ብንደውልም ስልካቸው ጥሪ ስለማይቀበል ምላሻቸውን ማግኘት አልቻልንም ነገር ግን የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ቶሎሳን ከረጅም ጊዜ ሙከራ በኋላ አግኝተናቸው በሰጡት ምላሽ ደመወዝ አልተከፈላቸውም የሚለውን ዜና አስተባብለዋል።
“እስከ መጋቢት 30/2013 ድረስ ለሁሉም ደመወዝ ከፍለናል የሚያዚያ ወር ደመወዝ ለመክፈል 4 ቀን ገና አለን 6..5…4 ወር አልተከፈላቸውም የሚለው ውሽት ነው ተጨዋቾቹ መጥተው መነጋገር እንችላለን።በርግጥ የ2 ጨዋታ ኢንሴንቲቭ አልከፈልናቸውም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመክፈል እየጣርን ነው ክለባችን ያለበት የገንዘብ ችግርንም ማሰብ አለባቸው እኛኮ የምንደጋገፍ ቤተሰብ ሆነናል” ሲሉ መልሰዋል።

አቶ ቶሎሳ እንዳሉት ” ጥቅማ ጥቅምን በተመለከተ የ6 ወር ከፍለናል ለሚቀረው ደግሞ ጊዜ አለን የፋይናንስ አቅማችንን አደራጅተን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለመክፈል እንጥራለን ከዚያ ውጪ የአውሮፕላን ጉዞ የሚስተጓጉልበት ምክንያት አልነበረም”ሲሉ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህን ቢሉም ከሰበታ ከተማ እግርኳስ ክለብ ሌላው ምንጫችን እንደገለጸው በፌዴሬሽኑ ህግ መሰረት መከፈል የነበረበት የ50 ሺህ ብር ደመወዝ ወደ 9 ለሚጠጉ ተጨዋቾች አልተከፈላቸውም።

የ6 ወር ደመወዝ ያልተከፈለው አብዱልባሲጥ ከማል፣ የአምስት አምስት ወር ደመወዝ ያልተከፈላቸው ቢያድግልኝ ኤሊያስና ሃ/ሚካኤል አደፍርስ፣ የአራት አራት ወር ደመወዝ ያልተሰጣቸው ታደለ መንገሻና አንተነህ ተስፋዬ፣ የሶስት ሶስት ወር ደመወዝ ያልተከፈላቸው አብዱልሃፊዝ ቶፊቅ፣ አለማየሁ ሙለታ፣ ያሬድ ሃሰንና ቃልኪዳን ዘላለም ደመወዝ ካገኙ ወራቶች ማለፋቸውን በመግለጽ ክለቡ ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ገልጿል።
ዛሬ ወደ ሃዋሳ ሊደረግ የነበረው ጉዞ ተስተጓጉሎ ወደ ነገ ቢዞርም የረቡዕ ጉዞ የመሳካቱ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport