“የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ እንዳናነሳ ያደርገናል ብዬ የምሰጋው አንድም ክለብ አላየሁም” አብዱልከሪም መሐመድ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ቅዱስ ጊዮርጊስ በፋሲል ከነማ ከደረሰበት ሽንፈት በኋላ ከድሬደዋ ከተማና ከሀዋሳ ከተማ ጋር ያደረገውን ጨዋታ በድል ከመወጣቱም በላይ በ2 ጨዋታ 7 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ እየተጠናከረ መምጣቱን ለተጋጣሚዎቹ አሳይቷል ሲል ተከላካዩ አብዱልከሪም መሐመድ /ተርሚኔተር/ ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል፡፡ አብዱልከሪም ስለቡደኑ፣ ስለዋንጫው፣ ላለመውረድ ስለሚደረገው ፉክክር ስለ አዲሱ አሰልጣኝ፣ ውድድሩ በዝግ ስለመካሄዱና ሌሎች ጉዳዮች ምላሹን ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- በፋሲል ከነማ ከደረሰባችሁ ሽንፈት በኋላ በተከታታይ 2 ጨዋታ አሸንፋችኋል… ምክንያቱ ምን ይሆን… ውይይትስ አደረጋችሁ?

አብዱልከሪም፡- ከሽንፈቱ ብቻ ሳይሆን ከጨዋታው በፊትም በነበረን ሃሣብ በልባችን ግጥሚያዎችን በሙሉ የማሸነፍ እቅድ ይዘን ነበር የተነሳነው፡፡ ከፋሲል ጋር በነበረን ጨዋታ ሽንፈት የገጠመን ባለፉት 3 አመታት የመጀመሪያ ጨዋታ ላይ ማሸነፍ ባለመቻላችን ይህን ታሪክ ለመለወጥ የነበረን ጉጉት ያመጣው ሽንፈት ይመስለኛል፡፡ በዚያ ላይ ግቡ የተቆጠረብን የጨዋታው መጨረሻ አካባቢ መሆኑ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ውስጥ ከቶን ስለነበረም ጭምር ነው፤ በዚያ ላይ ከጎሉ በኋላ እነሱ ኳሱን ይዘው መጫወት በመቻላቸው ያሰብነው ሳይሳካ ቀርቷል፤ ከሽንፈቱ በኋላ በነበረን ውይይት ይሄን ሽንፈት አንመልሰውም ለቀጣዮቹ ግን ደካማ ጎኖቻችንን አስተካክለን የታየውን ክፍተት በመዝጋት ማሸነፍ አለብን ብለን በመነጋገር የተሻለ ውጤት ለማምጣትና በርካታ ግቦችን ለማስቆጠር ችለናል፡፡

ሀትሪክ፡- የግብ ጠባቂው ማታሲ ስህተትም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረውኮ… ይሄንንስ ተነጋገራችሁበት…?

አብዱልከሪም፡-ግብ ጠባቂያችን ጥሩ አቅም አለው በፋሲል ጨዋታ ላይ በተፈጠረው ስህተት ከግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ጋር አውርተዋል ብዬ አምናለው እሱም ያሉበትን ደካማ ጎኖች በየጨዋታው እያረመ መጥቷል በዚያ ላይ በዲ.ኤስ.ቲቪ መተላለፉ በድጋሚ ጨዋታዎችን የማየት እድል ስላገኘን ስህተቶችን የማረምና ጥንካሬያችን ላይ የበለጠ ጠንክሮ የመስራት እድል በመመቻቸቱ ብዙ ለውጦች ይታያሉ ብዬ አስባለው፡፡

ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ስብስብ ብቻ ነው ያለው ስብስብ ውጤት አያመጣም የሚሉ ወገኖች አሉ… ምላሽህ ምንድነው?

አብዱልከሪም፡- እውነት ነው ስብስብ ብቻውን ለውጥ አያመጣም ነገር ግን ባለን ስብስብ ላይ የተሻለ ነገር የመስራት አቅሙ ስላለን ለውጥ የሚያመጣ ስብስብ እንደሚሆን ርግጠኛ ነኝ፤ የኛ ስብስብ ከዚህ በፊት እንደሚባለው ወይም ሌሎች ክለቦች ላይ እንደሆነው ለውጥ የማያመጣ ስብስብ ነው ብዬ አላምንም፤ በዚህ አመት የተሻለ ውጤትና ለውጥ የምናመጣበት እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ፡፡ ቡድናችን 2 ጨዋታዎችን አሽንፏል፡፡ የበለጠ እያሸነፍን ስንሄድ የሁሉም በራስ መተማመን ስለሚጨምር በስብስቡ ተጠቃሚ እንሆናለን የሚል ግምት አለኝ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስም ትልቅ ክለብ እንደመሆኑ እየተስተካከለና እየተለወጠ ይመጣል ባይ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- የጀርመናዊው ዋና አሰልጣኝ ከቡድኑ መለየትና ቀድሞ ምክትል የነበሩት አሰልጣኝ የአሁኑ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ መሆናቸው ክፍተት ፈጥሯል? ወይስ..?

አብዱልከሪም፡- በዋና አሰልጣኙ መሄድ የተፈጠረ ክፍተት አለ ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም ዋና አሰልጣኙ እያለም ቢሆን የቡድኑ አባላት ልምምድ ሲሰሩ የነበሩት ከምክትል አሰልጣኙ ጋር በመሆኑ ብዙም ለውጥ ይኖረዋል ብዬ አላምንም ዋናው አሰልጣኝ የልምምድ ፕሮግራሙን ይመራ ነበር እንጂ በደንብ የሰራነው በምክትሉ በመሆኑ ክፍተት ይፈጥራል ብዬ አላስብም፡፡

ሀትሪክ፡- በፕሪሚየር ሊጉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለ4ኛ አመታት ዋንጫ ያለማግኘት ስጋት አለበት?
አብዱልከሪም፡- ዋንጫ የማጣት ስጋት በፍፁም የለብንም ዋንጫውንም አናጣም፡፡

ሀትሪክ፡- አያሰጋንም ማለት ዋንጫው የኛ ነው ከ3 አመት በኃላ በሊጉ ላይ እንነግሳለን እያልክ ነው?

አብዱልከሪም፡- /ሳቅ/ አዎ ከአላህ ጋር የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ የኛ ነው ለዚህ ደግሞ ዝግጁ ነን፡፡

ሀትሪክ፡- የኛ ቀንደኛ ተፎካካሪ ናቸው የምትላቸውስ ክለቦች የሉም?

አብዱልከሪም፡- በያዝነው ስብስብ ጥራት ርግጠኞች ነን፡፡ ከዚህ አንፃር የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ እንዳናነሳ የሚያደርገን አንድም ክለብ አላየሁም፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና ሊጉን እየመራ ነው… ፋሲል ከነማ ጠንካራ ስብስብ አለው፤.. እነኚህስ አያሳስብም /ቃለ ምልልሱ ረቡዕ እለት የተደረገ ነው/

አብዱልከሪም፡- /ሳቅ/ ሊጉን እየመራ ያለውም ክለብ በ2 ጨዋታ ስለመራ ብቻ ሻምፒዮና ይሆናል ብዬ አላስብም ካለን ስኳድ እያሳየን ካለው መሻሻል እኛ አሁንም የተሻልን ነን ብዬ ነው የማስበው፡፡ ለዚህ ነው እኛን ቻሌንጅ የሚያደርግ ክለብ አለ ብዬ የማላምነው፡፡
ሀትሪክ፡- በቦታህ በሁለቱ ጨዋታ እያሳየህ ያለው አቋም ምርጡ ነው?… ወይስ በቀጣይ ጨዋታዎች የተለየውን ከሪም/ ተርሚኔተርን/ እንጠብቅ?

አብዱልከሪም፡- ገና ጅማሮ ላይ ነን ውድድሩ ገና ረጅም ጉዞ አለውና ቀስ በቀስ እየተሻሻልኩ እመጣለሁ በዚያ ላይ አሰልጣኙ አዲስ እንደመሆኑ ከአዲሱ አጨዋወት ጋር በመናበብና በመላመድ የተሻለው ከሪም ከፊት የሚመጣው ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውጪ መሆንህ በአሰልጣኞቹ የፍልስፍና ጉዞ? ወይስ ደካማ አቋም በማሳየትህ?… የቱ ነው ትላለህ?

አብዱልከሪም፡- በቀሪዎቹ አመታት ላይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡደን ውስጥ በደንብ እገባለው ብዬ አምናለሁ፡፡ እስካሁንም የቡድኑ አባል ያልሆንኩት የበፊቱ ከሪምን ማምጣት አልቻለኩም በክለብ የተሻለ አቋም ያላሳየ ደግሞ አይመረጥምና ባለፉት አመታት ከዋሊያዎቹ ውጪ ሆኛለሁ፡፡ ጥሩ አለመሆኔን እቀበላለሁ፡፡ ከ2013 በኋላ ግን አቋሜን አስተካክዬ ወደ ዋሊያዎቹ እመለሳለሁ ብዬ አምናለሁ ለዚህም ጠንክሬ እየሰራሁ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ከኮሮና ጋር ተያይዞ ውድድሮች አልነበሩምና.. ዳሌ ያወጡ በርካታ ተጨዋቾች አሉ ይባላል… አንተስ ከነርሱ አንዱ ነህ ዳሌ አወጣህ…?

አብዱልከሪም፡- /ሳቅ በሳቅ/ ከሪም በፍፁም አላወጣም ከሪም ብቻ ሳይሆን ተጨዋች ስራው በመሆኑ ቀለል ያለ ልምምድ እየሰራ ይጠብቃል እንጂ ዳሌ እስኪያወጣ ድረስ ይወፍራል ብዬ አላምንም፤.. በርካታ ዳሌ ያወጡ የሚያስብልም ዳሌ አልታየም፡፡
ሀትሪክ፡-የወፈረ የለም እያልክ ነው?
አብዱልከሪም፡-/ሳቅ/ የወፈረ ተጨዋች ቢኖርም ዳሌ የማውጣት ያህል የወፈረ ግን የለም አባባሉ የተጋነነ ይመስለኛል /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጎልቶ የሚወጣ ተጨዋች ማን ይመስልሃል?

አብዱልከሪም፡- አሁን ላይ መገመት ይከብዳል ቡድኑ በተሻለ መንገድ እየተሰራ ነው ትልቅ ለውጥ ይኖረዋል አቅሙንም ያሳያል ብዬ አምናለሁ አሁን ግን እንደዚህ ነው ብዬ ለመገመት እቸገራለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ከ13 ክለቦች ሶስት መውረዳቸው አይከብድም? ለዋንጫና ላለመውረድ ከሚደረገው ፉክክር የትኛው ይከብዳል?

 

አብዱልከሪም፡- ከ13ቱ 3 ክለቦች መውረዳቸው በጣም ከባድ ይመስለኛል፤ ከዋንጫው በላይ ላለመውረድ የሚደረገው ፉክክር ከፍተኛ ፍልሚያ ይታይበታል ብዬ አስባለው፤ ወርደው መመለስ ከበድ ስለሚል ትልቅ ፍልሚያ ይኖራል ብዬ እጠብቃለሁ፤ ወገብ ላይ ያሉና ከወገብ በታች ሆነው ለሚጨርሱ ትልቅ ፈተና እንደሚሆን እጠብቃለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ሊጉ በዲ.ኤስ ቲቪ መተላለፉ ለተጨዋቾች የሚፈጥረው እድል ይኖራል ከሚሉ ወገኖች መሀል ነህ? ወይስ?

አብዱልከሪም፡- ትልቅ እድል ነው ከሚሉ ወገኖች መሀል ነኝ እኛም ያለንን አቅም አውጥተን ማሳየት ከቻልን ትልቅ አድቫንቲጅ ይፈጥራል ብዬ አስባለው፡፡

ሀትሪክ፡- በዲ.ኤስ.ቲቪ ጨዋታው መተላለፉ የዳኞችን ደካማ ብቃት ያጋልጣል የሚሉ ወገኖች አሉ… አንተስ?

አብዱልከሪም፡- ዳኞቻችን ጎበዘው ካልተገኙ የሚያጋልጣቸው ይሆናል እያየነው ያለውም ይሄንን ነው ዳኞችም ጨወታቸውን ደግመው አይተው ስህተታቸውን ያርማሉ ብዬ አስባለው፡፡ ሲሳሳቱ አሁንም እያየን ነው በዲ.ኤስ.ቲቪ መተላለፉ አንደኛው አቅም የሌለው ያጋልጣል ሁለተኛው ስህተታቸውን አይተው ይማሩበታል ብዬ አስባለው ስህተት እየቀነሱ መሄድ ወደ ምርጥ አቅም ያመጣል ብዬም አምናለው… ሰው ከሚናገር ያየሁትን ስህተት በራሴ ባረም የተሻለ ይሆናል ዲ.ኤስ.ቲቪ ደግሞ ይህን እድል ፈጥሯል፡፡

ሀትሪክ፡- ደጋፊው የሌለበት ጨዋታ መሆኑ አይከብድም?

አብዱልከሪም፡-ያለ ደጋፊ መጫወት በጣም ከባድ ነው የሆነ የጎደለ ነገር እንዳለ ተሰምቶኛል ለኔ ያለ ደጋፊ መጫወት ይከብዳል፡፡ በኮቪድ 19 ምክንያት ተመልካች ሙሉ አመት ይገባል ብዬ አላስብምና በቀጣይ ግጥሚያዎች በማሸነፍ ባለፉት 2 አመታት የነበረውን ደካማ ታሪክ አስተካክለን በዚህ አመት ሻምፒዮን ሆነን እንክሳቸዋለን ብዬ አስባለው፡፡

ሀትሪክ፡- የፊታችን ሰኞ ከሰበታ ከተማ ጋር በሊጉ 4ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ላይ ትገናኛላችሁ.. ውጤቱ ምን ይሆናል?

አብዱልከሪም፡-ቡደናችን ወደሸናፊነት ተመልሷል ከዚህ በኋላ አሸናፊነታችን እንቀጥላለን፤ ሰበታ ከተማንም እናሸንፈዋለን ተረኛ ተሸናፊ ሰበታ ከተማ ይሆናል፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport