አለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ አካል ፊፋ በ2021 ኢንተርናሽናል ባጅ ያላቸው ናቸው ያላቸውን 21 አርቢትሮች ይፋ አድርጓል፡፡
ፊፋ የላከው ብሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዳስታወቀው በወንዶች በዋና ዳኝነት 7 አርቢትሮች የተመረጡ ሲሆን አርቢትር በአምላክ ተሰማ፣ አርቢትር በላይ ታደሰ፣ አርቢትር ብሩክ የማነ ብርሃን፣ አርቢትር ቴዎድሮስ ምትኩ፣ አርቢትር ለማ ንጉሴ፣ አርቢትር አማኑኤል ኃ/ስላሴና አርቢትር ኃይለየሱስ ባዘዘው ሲሆኑ በሴቶች አርቢትር ሊዲያ ታፈሰ፣ አርቢትር ፀሐይነሽ አበበ፣ አርቢትር አስናቀች ገብሬና አርቢትር መዳብ ወንድሙ መመረጣቸው ታውቋል፡፡
በረዳት ወንድ ዳኞች 6 አርቢትሮች የተመረጡ ሲሆን ረዳት ዳኛ ክንዴ ሙሴ፣ ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው፣ ረዳት ዳኛ ሸዋንግዛው ተባበል፣ ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል፣ ረዳት ዳኛ ፋሲካ ብሩና ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ ሲመረጡ በረዳት ሴት ዳኞች ረዳት ዳኛ ወይንሸት ካሳዬ፣ ረዳት ዳኛ ይልፋሸዋ ካሳሁን፣ ረዳት ዳኛ ብርቱካን ማሞና ረዳት ዳኛ ወጋየሁ ዘውዱ ለ2021 በፊፋ የተመረጡ 21 ኢትዮጵያዊያን አርቢትሮች ሆነዋል፡፡

ከነዚህ ዳኞች መሀል ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በአምላክ ተሰማ በቪዲዮ ዳኝነት የተመረጠ ሲሆን ኢንተርናኛል ረዳት ዳኛ ባጅ ለማግኘት ሞከሮ የነበረው ረዳት ዳኛ መመዘኛውን ባለመሟላላቱ ኢትዮጵያ የነበራት ኮታ በአንድ ዝቅ ብሏል፡፡ ሀትሪክ ከታማኝ ምንጯ ባገኘችው መረጃ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ለመሆን ሞክሮ ያልተሳካለት ዳንኤል ጥበቡ መሆኑን አረጋግጣለች፡፡
ከዚሁ ጎን ኢትዮጵያ የነበራት የኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ኮታ 7 የነበረ ሲሆን ከአምና ጀምሮ ወደ 6 እንዲቀንስ መደረጉ ቅሬታ ፈጥሯል፡፡ በ2020 ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ የነበረው በላቸው ይታየው በእድሜ ከተቀነሰ በኋላ ቦታው በሌላ ረዳት ዳኛ ያልተተካ ሲሆን በ2021 ይሄ ቦታ ሳይተካ ያለፉት 6 ዳኞች ብቻ ተደርጎ መምጣቱ ነገ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ እንሆናለን ብለው ተስፋ ለሚያደርጉ ረዳት ዳኞች ትልቅ የሞራል ጉዳት እንዳይሆን ተሰግቷል፡፡ ፌዴሬሽኑ ኮታውን ለማስጠበቅ ብዙ ርቀት አልተጓዘም ሲሉም ዳኞች ቅሬታቸውን ያቀርባሉ፡፡
በዚህ ቅሬታ ዙሪያ የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በተለይ ለሀትሪክ እንደተናገሩት “ኮታው ለምን ወደ ስድስት ዝቅ እንደተደረገና 7ተኛ አድርገን የላክነውን የረዳት ዳኛ ዳንኤል ጥበቡን ለምን እንዳልተቀበሉት ፊፋን ማብራሪያ ጠይቀን ምላሽ እየጠበቅን ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ የዳኞችን እድሜ በማየት እዚሁ ስማቸው ሳይላክ ለነገ ተተኪ የሚሆኑ የዳኞችን ስም መላከ ላይ ድፍረት ይጎድለዋል የሚሉ ወገኖችም በርካቶች ናቸው፡፡
ከዚህ የፕሪሚየር ሊግ ዳኝነት ሳንወጣ ዲ.ኤስ.ቲቪ ሊጉን እያስተላለፈ መሆኑ የዳኞቻችንን አቅም እያጋለጠው ነው የሚል ቅሬታም እየተሰማ ነው ባለፉት አመታት ይታይ የነበረው የጨዋታ ውጤት መዛባት ደጋፊዎችና የክለብ አመራሮች በሚፈጥሩት ጫና ይሳባብ የነበረ ቢሆንም የዘንድሮ ውድድር በኮቪድ19 ፕሮቶኮል ምክንያት በዝግ በመካሄዱና ጫና አለመኖሩ ዲ.ኤስ.ቲቪ የተደበቀውን የአርቢትሮች ድክመት እያሳየ መሆኑ ተስተውሏል፡፡
የህግ ጥሰቶች፣ የውሳኔ መዘበራረቆች ኦፍ ሣይድ ያልሆኑ ኳሶች በረዳት ዳኞች ሲቆሙ የሚታዩ እውነታዎች መሆናቸውን ተገንዝበው አርቢትሮቹ አቋማቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የስፖርት ቤተሰቡ ጥሪ እያደረገ ነው፡፡ ውድድሮቹ ገና ከመሆናቸው አንፃር አልረፈደም ያሉ ነባር አርቢትር ሁሉም ከህግ መተርጎም እስከ ፊዚካል ፊትነስ ብቃት ድረስ በሚገባ ሊዘጋጁ ይገባል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከዚሁ ጎን አቅማቸውን የሚያሳዩ ጥሩ ብቃት ላይ እንደሚገኙ የሚያስመሰክሩ ዋናና ረዳት ዳኞች መኖራቸው መዘንጋት እንደሌለበትም እኚሁ ነባር አልቢትር ተናግረዋል፡፡ የፌዴሬሽኑ የዳኞች ኮሚቴ ወደ ፕሪሚየር ሊግ አርቢትሮችን ማሳደጉ በመልካም ጎኑ የሚጠቀስ ቢሆንም አቅማቸውን ያላስተካከሉ አርቢትሮችን ወደ ከፍተኛ ሊግ የማውረድ ደፋር ርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም ይመክራሉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደጉ ዋናና ረዳት ዳኞችን አሳውቋል፡፡ ዘንድሮ ፕሪሚየር ሊጉ ላይ እየዳኙ ያሉትን ኤፍሬም ደበበና ከረን እንግዳን ጨምሮ 14 ዋና ዳኞችና 20 ረዳት ዳኞችን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ አሳድጓል፤ ኮሚቴው በተጨማሪ 30 ዳኞችና 40 ረዳት ዳኞችን ከ1ኛ ሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ ማሳደጉ ታውቋል፡፡
አስተያየት ይስጡ