በሴካፋ ከ17 አመት በታች ላይ ጥሩ ጊዜን ያሳለፉ ተጫዋቾች በፕሪምየር ሊጉ ላይ እናያቸዋለን።
ከሰሞኑ ታንዛኒያ ዩጋንዳን በመርታት ባሸነፈችበት የሴካፋ ከ17 አመት በታች ዋንጫ ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሦስተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ በሞሮኮ በህዳር ወር በሚዘጋጀው የአፍሪካ ከ17 አመት በታች ሻምፒዮና ላይ መሳተፋችን ይታወሳል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ካላት ትልቅ ህልም አኳያ ለሮድ 2029 የተሰባሰቡ ወጣቶችን በአሜሪካዊው አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር አማካኝነት እየተመሩ ሀገራችንን ወክለው በመሳተፍ ከሰሞኑ አስደናቂ ገድልን መፈፀማችን ይታወሳል።
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በተደረገው በዚህ የሴካፋ ዞንን ውድድር ላይ ውድድሩን በስምንት ጎሎች ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ በመጨረስ አስደናቂ ብቃቱን ያሳየን አጥቂው ዳዊት ካሳው እና አምበሉ ቢኒያም መሐሪ ለአንድ የፕሪምየር ሊግ ክለብ ፊርማቸውን ማኖራቸው ተሰምቷል።
ሀትሪክ ስፖርት ባገኘችው መረጃ መሠረት ሁለቱ ተጫዋቾች አዲስ አዳጊውን ክለብ ሸገር ከተማን መቀላቀላቸውን ያወቅን ሲሆን በቀጣዮችም ቀናት ሌሎች ዝውውሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ታውቋል።


